Monday, 05 January 2015 08:38

የአማርኛ ፊደል ይሻሻል…ጥያቄ አግባብ ነውን?

Written by  ጌታቸው አበበ አየለ
Rate this item
(9 votes)

ክፍል ፫
የክፍል ፪ ጽሑፍን ያቆምነው የአማርኛ ፊደል ያሉት 7 ድምፅ ወካይ ሆሄያት ብቻ ሆኖ ሳለ የአማርኛ ፊደል መሻሻል ወይም በዝተዋልና ይቀነሱ ጥያቄዎች መነሣት ይገባቸዋልን የሚለውን በቀጣይ እናየዋለን በማለት ነበር፡፡ ቀደም ብሎ በክፍል ፩ ጽሑፌ የአማርኛ ፊደል ይሻሻል በሚል ሰበብ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የቀረቡትን ነጥቦች ከብዙዎቹ መካከል ጥቂቶቹን ብቻ እንደ ምሳሌ መጥቀሴ ይታወሳል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ የጥያቄዎቹ መነሣት አግባብነት አለውን? በሚለው ዐቢይ ጉዳዩ ላይ አተኩራለሁ፡፡
በታሪክ አጋጣሚ ግዕዝ ቦታውን ለቅቆ ለአማርኛ ያስረክብ እንጂ አማርኛ የሚጠቀምበት ፊደል ባለቤት ግን ግዕዝ መኾኑ ያከራክራል አልልም፡፡ ይልቁንም አማርኛ የግዕዝ ተወካይ ሆኖ እንዲያገለግል ተደርጓል ማለቱ ይቀላል፡፡ ይሁን እንጂ የአማርኛ ፊደል እንዲሻሻል ወይም ሆሄያቱ እንዲቀነሱ ደፋ ቀና የሚሉ ክፍሎች ብዙ ጊዜ ጥያቄአቸው የግዕዝ ፊደልን እንደማይመለከት ሲወተውቱ ይደመጣሉ፡፡ “አህያን ተከልሎ ጅብን ይወጉ” እንደሚባለው ዓይነት መኾኑ ነው፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ግዕዝና አማርኛ በስም ይለያዩ እንጂ ሁለቱም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ አንደኛውን ነጥሎ ማቁሰል ያስቸግራል፡፡ ይልቁንም እነዚህ የፊደል ቅነሳ ተሟጋቾች፤ ይህንን ጥቅም የለሽ ሙግታቸውን ትተው፣ ፊደሉ ግዕዝና አማርኛ እየተባለ መጠራቱ ቀርቶ የኢትዮጵያ ፊደል የሚል ስያሜ ይሰጠው ቢሉ የተሻለ ነበር፡፡ የእነሱ ዓላማ ግን ያተኮረው አንድም የግል ዕውቅናን (ዝናን) ለማግኘት ከመሻት፤ አንድም ፊደሉን ፍጹም ካለመፈለግ ስሜቶች የመነጨ በመኾኑ፣ ፊደሉን ከአገራዊ ፋይዳው ጋር አመዛዝኖ ማየት ተሳናቸው፡፡
ለማንኛውም የአማርኛው ፊደል ጉድለቶች ናቸው በማለት የሚያቀርቧቸውን ምክንያቶች ምንነት ለመመልከት እንሞክር፡፡ ምክንያቶቻቸው በጥቅል ሲታዩ በሦስት ክፍሎች ይመደባሉ፡፡
፩ኛ - ፊደሉ ለሥራ ምቹ አይደለም፡፡
፪ኛ - ቋንቋው ካለው ድምፅ ጋር ሲመዛዘን ትርፍ ሆሄያት አሉት፡፡
፫ኛ - ወደ አማርኛ ለሚገቡ ቃላት በቂ ሆሄያት የሉትም፡፡ የሚሉ እርስበርስ የሚጣረሱ ምክንያቶች ናቸው፡፡ በዝርዝር ሲቀመጡም የሚከተሉትን ይመስላሉ፡፡
፩ኛ - ፊደሉ ለሥራ ምቹ አይደለም
አሁን ያለው የፊደል ገበታ ለሥራ ምቹ አይደለም በማለት ከዚህ በታች ያሉትን ምክንያቶቻቸውን ይደረድራሉ፡፡
ሀ. “በተቀላጠፈ መንገድ አማርኛ መዝገበ ቃላትን ለመጻፍ አይቻልም” ይላሉ፡፡ ግን ይህንን ለማለት ያስቻላቸው በቂ ማስረጃ የላቸውም፡፡ መቼም መዝገበ ቃላት የሚዘጋጀው በፊደል ተራ (Alphabetical order) መኾኑን የማያውቅ ሰው አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ማንበብና መረዳት የቻለ ሁሉ አይጠፋውም፡፡ እናም የላቲኑ (A,B,C,D…) እንደሚለው፣ አማርኛውም (ሀ፣ለ፣ ሐ፣ መ…) ፊደል ተራ ይጠቀማል፡፡ በተረፈ የመዝገበ ቃላት አዘገጃጀት የአዘጋጂውን ልዩ ችሎታ የሚጠይቅ እንጂ የፊደል ገበታው እንቅፋት ይሆናል ማለት ከንቱ ምክንያት ነው፡፡
ለ. “በፊደሉ ውስጥ ያሉት ምልክቶች በመብዛታቸው ለጽሕፈት መኪና ምቹ አይደሉም፡፡” የሚለው ሌላው ምክንያታቸው ነው፡፡ ይህ ጥያቄ ቀደም ሲልም የጽሕፈት መኪና (ታይፕ ራይተር) በነበረበት ጊዜ ሁሉ ሲለፈፍ ቆይቷል፡፡ የሚገርመው ታድያ! ይህ ጥያቄ አሁን ድረስ እየተነሣ መገኘቱ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ዛሬ ቴክኖሎጂው አድጎ ኮምፒዩተር በተስፋፋበት ዘመን ይቅርና በወትሮውም መጻፊያ መኪና (ታይፕ ራይተር) በአማርኛ ፊደል ሲጻፍ ነበር፡፡ እንደ እውነቱ ችግር ቢኖር እንኳን ፊደሉን ለመቅረጽ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ይፈጠራል እንጂ ለቴክኖሎጂው ተብሎ ታሪካዊ ቅርስ አይለወጥም፡፡
እዚህ ላይ ባለፈው ክፍል ፩ ጽሑፌ ላይ አንባብያን የተቸገራችሁበትን ጉዳይ አሁንም ልጠቅሰው ፈለግሁ፡፡ ይህም ጋዜጣው እኔ የሰጠሁትን በዶ/ር ፍቅሬ ዮሴፍ አዲስ የፊደል ገበታ መሠረት የተጻፈ ዓረፍተ ነገር ፊደሎቹን በኮምፒዩተር መጻፍ ስላልተቻለ የተፈጠረ ችግር ነው፡፡ አሁንም ያንን ለመግለጽ ስለማይቻል “ብቸኛው አፍሪካዊ ፊደል” (The Sole African Alphabet) መጽሐፋቸው ገጽ 68 እና 69 ላይ እንድታዩት እመክራለሁ፡፡ ታድያ! የአማርኛ ፊደል በዝቷል፣ ለጽሕፈት መኪና ያስቸግራል እያሉ በሌላ በኩል ደግሞ የዘመኑ ቴክኖሎጂ እንኳን በማያውቀው አዲስ ፊደል ይተካ ማለት ምን ዓይነት አመለካከት ይሆን? ያሰኛል፡፡
ሐ. “ተናባቢው ተለይቶ ባለመጻፉ በአማርኛ የሥነ ልሳን ላይ ጥናትን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለማካሄድ አይቻልም፡፡” የሚል እሮሮም ያሰማሉ፡፡
ኧረ! መቼ ይሆን የአገራችን ምሁራን ከፈረንጅ ባህልና ፍልስፍና ጥገኝነት ተላቅቀው በራሳቸው እግር የሚቆሙት ያስብላል፡፡ ለመኾኑ ሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር በማድረግ አዲስ ግኝት የሚፈጥረው ፈረንጅ ብቻ ነው የሚል ሕግ ተደንግጓልን? ጥያቄው ስለ ፊደሉ ደኅንነት የቆሙትን አይመለከትም፡፡
ዛሬ በተፈጠረ የፈረንጅ ሳይንስ አመካኝቶ ለሺዎች ዓመታት የቆየውን ታሪካዊ ፊደል ማጣጣል ያሳፍራል እንጂ አያስከብርም፡፡ እናም የአማርኛ ፊደል በዝቷልና ይቀነስ፣ በማለት ተናባቢው ተይቶ ባለመጻፉ ሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር ማድረግ አይቻልም የሚል “የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ” ዓይነት ምክንያት መደርደሩ አጥጋቢ አይደለም፡፡
በተረፈ ግን የቀድሞዎቹ ሊቃውንት እንደ ዛሬዎቹ ምሁራን ሳይንሳዊ ምንትሳዊ አይበሉ እንጂ ሆሄያቱን በዘፈቀደ አላስቀመጧቸውም፡፡ ከዚህም የተነሣ አናባቢዎችና ተነባቢዎች ለየብቻ ሲሆኑ ከአላቸው ጠቀሜታ ይልቅ ሆሄያቱ በራሳቸው እንዲናበቡ ቢደረግ የተሻለ መኾኑን አጥንተው ያደረጉት ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል በአማርኛው “በላቸው” ተብሎ” የተጻፈውን በላቲኑ እንጻፈው ብንል Belachew ይሆናል፡፡ ብዙ ሆሄያትን የተጠቀመው የትኛው ነው? የአማርኛው ፊደል ሆሄያቱ ራሳቸው በራሳቸው የሚናበቡ በመኾናቸው አራት ሆሄያትን ብቻ ተጠቅሟል፡፡ በላቲኑ ግን ይህንኑ ተመሳሳይ ስም ለመጻፍ ስምንት ሆሄያት አስፈለጉ፡፡ ታድያ ከዚህ የበለጠ ሳይንሳዊ አሠራር አለን?
ይሁን እንጂ የኛዎቹ “ፈረንጅ አምላኪዎች”ና የራሳቸውን ወርቅ ንቀው የሌላውን መዳብ ፈላጊ ምሁራን፣ እንደ ላቲኑ ተነባቢና አናባቢዎች (Consonants and Vowels) ተለይተው ካልተቀመጡልን ይላሉ፡፡ ስለዚህ ለተውሶ ሳይንስ ተብሎ ጥንታውያን ምሁራን አባቶች ያቆዩአቸውን የኪነጥበብ፣ የፍልስፍና፣ የታሪክና የመሳሰሉት ቅርሶች ሲመዘገቡበት የኖረውን ፊደል እንዲጠፋ መታገል ተገቢ አይደለም፡፡
መ. “በእጅ ለመጻፍ አይመችም፣ አያፈጥንም፡፡” ይህ ደግሞ ሌላው አስቂኝ ምክንያታቸው ነው፡፡ የግል ችሎታን ከፊደል ጋር ምን አገናኘው? ነው ወይስ እንደ ላቲኑ ትልቅ (Capital)፣ ትንሽ (Small) ቅጥልጥል (Cursive) በሚል አስጨናቂ አጻጻፍ እንዲሆንላቸው ፈልገው ይሆን? የአማርኛው ፊደል ከፍ ዝቅ፣ ወፍራም ቀጭን፤ ጠማማ ቁልፍልፍ የሌለው አንድን መሥመር ተከትሎ የሚሔድ ቀና ሆሄያት ያሉት በመሆኑ ሊኮሩበት በተገባ ነበር፡፡
፪ኛ. “ቋንቋው ካለው ድምፅ ጋር ሲመዛዘን ትርፍ ሆሄያት አሉት”
ለምሳሌ ሀ-ሐ-ኅ፣ ሠ-ሰ፣ አ-ዐ፣ ጸ-ፀ የመሳሰሉት፡፡” የሚለው ዐቢይ ምክንያታቸው ነው፡፡ ልብ ብለን ማጤን የሚገባንም ይኸኛውን መሆን እንዳለበት እናምናለን፡፡ ሌሎቹን ትርኪምርኪ የሆኑ ሰበቦቻቸውን የሚደረድሯቸውም ለዚሁ ፊደሉን ለመቀናነስ ዓላማቸው እንዲያግዟቸው ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ እነሱ እንደሚሉት፤ ተመሳሳይ የሆነ ድምፅ የሚሰጡ ተደራራቢ ሆሄዎች መኖራቸው አይካድም፡፡ ይህም “አንድ ምልክት ለአንድ ድምፅ” በሚለው ሳይንሳዊ የቋንቋ ሕጋቸው መሠረት አባባላቸው እውነትነት አለው፡፡ በእርግጥም አንድ ምልክት አንድን ድምፅ ወይም ክፍለ ቃል፣ አንድ ክፍለ ቃልም በአንድ ምልክት መወከል አለበት፡፡
 በዘመኑ ሳይንስ ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ፊደሉ ሲፈለሰፍ የዘመኑ ሳይንስ አልነበረም፡፡ ያም ሆኖ ሆሄያቱ የአጠቃቀም ሥርዓት አልነበራቸውም ማለት አይደለም፡፡ የየራሳቸውን አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርገው የተሠሩ ስለመሆናቸው በርካታ የቋንቋው ቃላት ከተጻፉበት ሥርዓት መረዳት ይቻላል፡፡ ለዚህም የሚከተሉትን የሦስት ዓይነት የቃላት አጻጻፍ ሥርዓቶችን እንደምሳሌ እንመልከት፡፡
1ኛ. በሆሄያት አደራደር ተመሳሳይ ሆነው በሞክሸ ሆሄያት ልዩነት ትርጉማቸው የሚለያዩ ከሆኑት (ድኅነት - ድኽነት፣ ምሑር - ምሁር፣…)
ድኅነት፡- በዚህ መልኩ ተጽፎ ብናገኘው ያለምንም ጥርጥር መዳን፣ ምሕረት ማግኘት የሚል ትርጉም እንደያዘ እንረዳለን፡፡
ድኽነት፡- ቃሉ በዚህ መልኩ ከተጻፈ ደግሞ መደኽየት፤ የሚለበስ፣ የሚበላ ነገር ማጣት፣ መቸገር ማለት እንደኾነ እናረጋግጣለን፡፡ በተጨማሪም “ድህነት” ተብሎ እንኳን አልተጻፈም፡፡ ለምን ቢባል ሥርወ ቃሉ (ግሡ) ደኸየ ስለሆነ ነው፡፡
ምሑር፡- የሚለው ቃል የ “ሐ”ን ዘር ይዞ በመጻፉ ብቻውን እንኳን ተጽፎ ብናገኘው ምሕረት ያገኘ፣ ይቅር የተባለ ትርጉም እንዳለው በቀላሉ እንረዳለን፡፡
ምሁር፡- በዚህ መልኩ የ “ሀ”ን ዘር ሆሄ በመጠቀም ተጽፎ ከተገኘ ደግሞ የተማረ፣ የተመራመረ፣ ዕውቀት ያለው ማለት መኾኑን እንገነዘባለን፡፡
2ኛ/ ሞክሼ ሆሄያት ያለ አግባብ ጥቅም ላይ ከዋሉ ትርጉም ይለውጣሉ፡፡ ለምሳሌ ፡- በግል መጠሪያ በኩል “ኃ” እና “ሀ” የተለያየ ትርጉም አላቸው፡፡ ሀ/ሚካኤል፣ ተብሎ ቢጻፍ አንድሮተ ቃል ሆና የገባችው “ሀ” ሀብተሚካኤል መሆንን ስታመለከት፣ ኃ/ሚካኤል ቢባል ደግሞ በአኃጽሮተ ቃልነት ጥቅም ላይ የዋለችው “ኃ” ኃይለ ሚካኤል መሆኑን ታሳውቀናለች፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች በርካታ የሆኑ ቃላት አማርኛ ከግዕዝ ወርሶ እየተጠቀመባቸው ከመኾኑም በላይ ብዙዎቹን የኢትዮጵያ ጽሑፋዊ ቅርሶችን በዚሁ መልክ አሰባስቦባቸዋል፡፡ ይህም ማለት ግዕዙ ባስቀመጣቸው ሥርዓተ ሆሄያት እየተጠቀመ ጽፏቸዋል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ “ጻፈ” የሚለውን ቃል ጸሐፊ ከሚለው በመውሰዱ ከዚህ ግሥ የሚመሠረቱትን ውልድ ቃላት በሙሉ (ጸሐፊ፣ ጽሕፈት፣…) ብሎ ሲጠቀምባቸው ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ እንደእነዚህ ያሉትን የሆሄያት አጠቃቀም ሥርዓት ስንመለከት ዘመቻ እየተካሄደበት ያለው ፊደል ቀድሞውንም ቢሆን ሳይንሳዊ አሠራር ነበረው ያሰኛል፡፡ ለዚህም ነው ከላይ እንደተጠቀሰው ፊደል ይቀነስ ባይ ምሁራን እውነት የጐደለ ካለ ሆሄያቱ ባሉበት የአጠቃቀም ሥርዓት ያብጁላቸው የተባለው፡፡
 እንከን ከሌለው ግን መነካካቱ የሚበጅ አይደለም፡፡ ከዚህም ሌላ በተለይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ፲፱፻፺፫ ዓ.ም ባወጣው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ሆሄያትን መቀነስ ብቻ ሳይሆን ማሻሻዮችም በማድረጉ ይህንንም ማየት ግድ ይላል፡፡ በእርግጥ በክፍል ፩ ጽሑፍ መጠቀሱ ይታወሳል፡፡ ሆኖም በድጋሚ እንዲነሣ ያስደረገን ጉዳይ በመኖሩ እንደገና ብቅ ሊል ችሏል፡፡ የአማርኛ ቋንቋ ከግዕዝ በወረሳቸው ሆሄያት በተጨማሪ ለቋንቋው የሚስማሙ ሰባት ሆሄያትን መጨመሩም ቀደም ሲል ተገልጿል፡፡ ከሰባቱ ውስጥም አንዱ “ኸ” የተባለው ድምፅ ወካይ ነው፡፡ ለምን ይኸን ድምፅ ወካይ ጨመረ ቢባል መልሱ ቀላል ይመስለኛል፡፡ የ “ከ” ሆሄ በአማርኛውም በግዕዙም ውስጥ ድምፁ አለ፡፡ ይሁን እንጂ የ “ኸ” ድምፅ በአማርኛው እንጂ በግዕዙ ቋንቋ አይገኝም፡፡ ስለዚህ “በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” እንዲሉ በአንድ በኩል ከግዕዝ የወረሳቸው ቃላት የአጠቃቀም ሥርዓት እንዳይፋለስ በማሰብ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ የሚገኘውን ድምፅ እንዲወክል ለማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ በግዕዙ “ኩሉ” የሚለውን ኹሉ፣ “ኮነ” የሚለውን ኾነ በማለት ሲጽፍ፣ በሌላ በኩል በአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ዘንድ በ “ከ” ምትክ የ “ኸ”ን ድምፅ የሚጠቀሙ (“ኸዚህ፣ ኸዚያ፣ ኸምኑ…በማለት) በመኖራቸው ይህንን ለማሟላት የፈጠረው ነው፡፡ ስለሆነም “ኸ” የሚለው ወካይ ድምጽ የሚወገድበትና በ “ሀ” ሊተካ የሚችልበት ምንም ምክንያት የለውም፡፡ በአጠቃላይ የአማርኛ ፊደል ተብለው ከግዕዝ የተወረሱት ሆሄያት በሙሉ እንዲቀነሱ በቋንቋ ምሁራን የተፈረደባቸውን ጨምሮ ለየራሳቸው ትርጉም ያላቸው፣ የፍልስፍና ጥበብ የተሠራባቸው፣ ታሪክ የተዘገበባቸው የአገሪቱ መኩሪያና መመኪያ በመሆናቸው የፊደሉን ቁጥር አብዝተውታል በሚል ሰበብ መነካካት ተገቢ አይደለም፡፡ ፫ኛ. “ወደ አማርኛ ቋንቋ ለሚገቡ ቃላት በቂ ሆሄያት የሉትም፡፡” ይህ ደግሞ ሌላው አስገራሚ ምክንያታቸው ነው፡፡ እንደ ምሳሌም አድርገው “በዳኔ”፣ “በዳሳ”…የመሳሰሉትን የኦሮምኛ ስሞችና ቃላትን  በማለት ይጠቅሳሉ፡፡ በእርግጥ እንዲህ ዓይነት ችግር በየትኛውም አገር ፊደላት ውስጥ ሊኖር የመቻሉን ያህል በአማርኛ አይከሰትም ማለት አይቻልም፡፡ ይሁን እንጂ የአማርኛው ፊደል የያዛቸው ሆሄያት በዝተዋልና ይቀነሱ በማለት እየለፈለፉ መልሰው ደግሞ “በቂ ሆሄያት የሉትም” ሲሉ አያስገርምም ትላላችሁ?
በመጨረሻም በየጊዜው የፊደል ሆሄያት እንዲቀነሱ በማለት የሚነሱ ጥያቄዎች ሁሉም አግባብነት የሌላቸው መኾኑን በዐጭሩ ለመግለጽ ተሞክሯል፡፡ በቀጣይ የአማርኛ ፊደል አጠቃቀም ዙሪያ ስለተፈጠሩ ችግሮችና የችግሩን መነሻዎች ለማየት እንሞክራለን፡፡ ቸር እንሰንብት፡፡     

Read 4096 times