Monday, 05 January 2015 08:00

ጌድዮን ዘላለም አሜሪካዊ ሆነ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)

ከ3 ወራት በኋላ በአሜሪካ ማልያ ሊጫወት ይችላል

    የ17 ዓመቱ የአርሰናል ተስፋ ቡድን ተጨዋች ጌድዮን ዘላለም ለአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን ሊጫወት ነው፡፡ ዋሽንግተን ፖስት ባለፈው ማክሰኞ  ባቀረበው ዘገባ ጌድዮን አሜሪካዊ ዜግነቱን እንዳረጋገጠና በፊፋ ህጋዊ እውቅና ከተሰጠው በኋላ ፓስፖርቱን እንደሚያገኝ አስታውቋል፡፡ ከዚሁ የዋሽንግተን ፖስት ዘገባ በኋላ በማግስቱ የአሜሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት  በትዊተር ማስታወሻቸው የመረጃውን እውነተኛነት ሲያረጋግጡ፤ ፌዴሬሽናቸው  በጉዳዩ ላይ ለፊፋ ማመልከቻ በማስገባት ህጋዊ ፍቃዱን ለማግኘት እየሠራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ በሌላ በኩል የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጀርመናዊው የርገን ክሊንስማን በበኩሉ ጌዲዮን ዘላለም አሜሪካዊ ዜግነት ማግኘቱን “ታላቅ የምስራች” ብሎታል፡፡ እጅግ ተስፋ የጣለበት ተጨዋች መሆኑንም በመግለፅም የአሜሪካ ብሄራዊ ቡድንን የሚቀላቀልበትን ወቅት በጉጉት እንደሚጠባበቅ አስታውቋል፡፡
ጌድዮን ዘላለም ትውልዱ በጀርመን፣ ዕድገቱ በአሜሪካ ነው፡፡ የቤተሰቡ አገር ደግሞ ኢትዮጵያ ነበረች በ2014 እ.ኤ.አ ለሦስቱ አገራት የመጫወት ዕድል ነበረው፡፡ ከሦስቱ አገራት በተለይ ጀርመንና አሜሪካ የተጨዋቹን ዜግነት ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ግን ጥረቱ ያነሰ ነበር፡፡ አባቱ አቶ ዘላለም በጉዳዩ ላይ ሰሞኑን በሰጡት አስተያየት አሜሪካዊነት እንደሚስማማው አስረድተው፤ ብዙ ጓደኞቹም አሜሪካዊ እንደሆኑ በመጥቀስ ውሳኔው ተገቢ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ጌዲዮን ዘላለም ገና በአርሰናል ክለብ ወጣት ቡድን ተሰላፊ ነው፡፡ በታዳጊነቱ በእንግሊዝ እግር ኳስ ያካበተው ልምድ ግን ከፍተኛ መነጋገሪያ አድርጐታል፡፡ በለንደን ከተማ ኮሊኒ ውስጥ በሚገኘው የአርሰናል አካዳሚ ስልጠና ከወሰዱ ታዳጊዎች ጎልቶ መውጣት የቻለ ሲሆን፤ አዲሱ ሴስክ ፋብሪጋዝ ተብሎም ተሞካሽቷል፡፡ በአርሰናል ዋና ቡድን ማልያ የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታ እስካሁን ባያደርግም በአሰልጣኝ አርሰን ቬንገር ትኩረት ተሰጥቶታል ስለሆነም፤ በቋሚ ቡድኑ የተጨዋቾች ዝርዝር በ2014 የውድድር ዘመን ሶስቴ በመካተት የጨዋታ ልምዶችን ማግኘት ችሏል፡፡ ባለፈው ዓመት በአርሰናል ክለብ ዋና ቡድን ተሰልፎ በኤፍካፕ ተጫውቷል፡፡ ከወር በፊት ደግሞ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ አርሰናል ከቱርኩ ክለብ ጋላተሰራይ ባደረገው ጨዋታ ሙሉውን ሁለተኛ ግማሽ ተቀይሮ በመግባት ለመጫወት ችሎ ነበር፡፡
ጌድዮን ዘላለም አሜሪካዊ እንደሚሆን ከተገለፀ በኋላ  የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድንን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚለውጥ እየተነገረለት ነው፡፡ የአርሰናሉ አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር ስለ ጌድዮን ዘላለም ሲናገሩ የአሜሪካ ቡድን በዓለም ዋንጫ የሚያስፈልገው ምርጥ ተጨዋች ብለው መስክረዋል ይህን አረጋግጠውታል፡፡ የኳስ ቁጥጥሩ እና የማቀበል ችሎታው ለአሜሪካ ብሄራዊ ቡድን ከፍተኛ ለውጥ ሊፈጥር እንደሚችልም በተለያዩ ዘገባዎች ተንትኗል፡፡ የአሜሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽን ለፊፋ ያስገባው የተጨዋች ተገቢነት ማመልከቻ ህጋዊ ሆኖ ሲፀድቅለት ጌድዮን ዘላለም የአሜሪካ ፓስፖርትን ያገኛል፡፡ ከ2 ወራት በኋላ የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድንን ሊቀላቀል ይችላል፡፡ ከ3 ወራት በኋላ ደግሞ የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን ከዴንማርክ እና ከስዊዘርላንድ ጋር በሚያደርጋቸወ የወዳጅነት ጨዋታዎች ሊሰለፍ ይችላል፡፡

Read 6102 times