Saturday, 20 December 2014 13:23

ትሬፓታ-ዕድል ያላገኘው የስልጠና ፍልስፍና

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

በኤሮቢክስ አሰልጣኝነት ከ10 ዓመታት በላይ የሰራው አቤኔዘር ይብዛ በእግር ኳስ አሰልጣኝነት ሙያው የሚያስፈልገውን ትምህርት የቀሰመ ቢሆንም የመስራት እድል አላገኘም፡፡ ከ3 ዓመት በፊት ትሬፓታ የተባለውን የእግር ኳስ አሰለጣጠን ፍልስፍና መቅረፅ ችሏል፡፡ ግን የሙከራ እድል ማግኘት አልቻለም፡፡ የስፖርት ባለሙያው አቤኔዘር ይብዛ ባለፈው ሳምንት ከስፖርት አድማስ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ በተጨዋችነት ስላሳለፈው ጊዜ፤ ከዚያም በኢትዮጵያ እግር ኳስ  ያስተዋላቸውን ሁኔታዎች፤ በስፖርቱ ዙርያ ያሉትን መሰረታዊ ችግሮችን ከዓለም አኳያ በንፅፅር በማየት ማብራርያ ሰጥቷል፡፡ የቃለምልልሱ ሁለተኛ ክፍል ከዚህ በታች እንደቀረበው ነው፡፡

ትሬፓታ እንዴት ተፈጠረ?
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ስልጠና ችግር ላይ መሆኑን ሁሌም እየተነጋገርን ግን ምንም አለመሰራቱ ያሳስበኛል የሚለው አቤነዘር፤ መፍትሄ መፈለጉን ስላመነበት የግሉን ጥረት አድርጓል፡፡ ኢትዮጵያ  በእግር ኳሷ አንድ የተለየ እና ከዓለም ጋር ተፎካካሪ የሚያደርግ የስልጠና ስርዓት ያስፈልጋታል ብሎ መፍትሄ ለማፈላለግ ሲመራመር ቆይቷል፡፡ ምሳሌ አድርጎ የተነሳው ደግሞ በባርሴሎናው አካዳሚ ላሜሲያ ያስተዋለውን የስልጠና መዋቅርን ነው፡፡ የቀድሞው የሆላንድ ምርጥ ተጨዋች እና አሰልጣኝ ዮሃን ክሮይፍ፤ ቶታል ፉትቦልን እንዴት ይዞት ስፔን እንደገባ አጥንቷል፡፡ ይህንኑ ሲያስረዳም  የሆላንድ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩት ሩኒስ ሚሸልስ በአያክስ ክለብ የሚሰሩበትን ስልጠና ወደ ስፔን በማሻገር ዮሃን ክሮይፍ እንዴት ስኬታማ እንደሆነ በማብራራት  ነበር፡፡ ክሮይፍ በዚህ የጨዋታ ታክቲክ በሱ ዘመን የሚፈለግበት ደረጃ ባይደርስም ይሁንና በላሜሲያ አካዳሚ ከስር መሰረቱ እንዲሰራበት አደረገ፡፡ በአንድ ወቅት አድጎ ከፍተኛ ለውጥ በማምጣት በዓለም አቀፍ ደረጃ ገንኖ ይወጣል በሚል እምነት ነበር፡፡ ይሄው የስልጠና ስርዓት በቅብብሎሽ አካዳሚው ውስጥ ሲሰራበት ቆይቶ ከቫን ሀል ወደ ፍራንክ ሪያካርድ በመጨረሻ በባርሴሎና ፔፔ ጋርድዮላ የአሰልጣኝነት ዘመን ክለብ ተግባራዊ ሆኖ ውጤቱን ለማየት ተችሏል፡፡ በዚህ አይነት መንገድ የሚሰራበት የአሰለጣጠን ስርዓት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ በጣም ያስፈልገዋል ብሎ ያመነው አቤኔዘር ተመሳሳይ የአሰለጣጠን ለውጥ  በኢትዮጵያ ውስጥ ለመተግበር ለረጅም ጊዜ እራሱን በማዘጋጀት እና ምርምሩን በማሳደግ ቆይቷል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከላይ በዝርዝር የሰፈሩት የስልጠና መሰረታዊ ግብዓቶች ላይ ሰፊ ተግባራት አለመከናወናቸው በመገንዘብ ይጀመራል፡፡ በስልጠና ፍልስፍና እና የአጨዋወት ታክቲክ ባለመኖሩ በስፖርቱ እድገት እና ለውጥ ለማሳየት አልተቻለም፡፡ አሁን ያሉን ቡድኖች በክለብ እና በብሄራዊ ቡድን ደረጃ በኢንተርናሽናል ውድድር የማለፍ እድል የምናገኘው በጥሎ ማለፍ ነው፡፡  በራሳችን መንገድ ሰርተን ስለማናውቅ ሁሌም ተከታይ ነን፡፡ ስለዚህም የራሳችን መንገድ ያስፈልገናል በማለት አቤኔዜር ይብዛ ትሬፓታን ለመፍጠር እንደተነሳሳ ያስረዳል፡፡  የተሻለ ውጤት ሊመጣ የሚችለው ከላይ የተዘረዘሩት መሰረታዊ ብቃቶች በክህሎት ዳብረው ሲሄዱ ብቻ ነው በማለትም በልበሙሉነት ይናገራል፡፡ የጨዋታ ፍልስፍናውን በቅርቡ ውጤቱን ለማየት እንዲቻል ተብሎ የተጠነሰሰ ነው፡፡ አቤኔዘር ትሬፓታ የጨዋታ ፍልስፍናን የፈጠርኩት ከቲኪታካ የባርሴሎና  አጨዋወት ተነስቼ ነው ይላል፡፡ በመጀመርያ የተጨዋቾቻችን ኪሎ ክብደት አነስተኛነት ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ጋር ሲነፃፀር እንዳነስን በማየት በራሳችን ፍልስፍና ጨዋታ ተሻሽለን የምንገኝበት ስልት ነው፡፡ በትንፋሽ ብልጫ ስላለን በምንሸፍነው ኪሎ ሜትር ከሌላው ዓለም ብልጫ ለመውሰድ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ተጨዋቾች በተፈጥሯቸው አጫጭር ኳስ መጫወት ይወዳሉ፡፡ ተሰጥኦም አላቸው፡፡ ትሬፓታ ይህን ኳስ ይዞ የመጫወት ክህሎትን ዓላማ እንዲኖረው ውጤት እንዲያስገኝ የምናዳብርበት ይሆናል፡፡ በሂደት ማሸነፍ የምንችልበት ነው፡፡
እኔ የፈጠርኩት የጨዋታ ፍልስፍና በይበልጥ ተፎካካሪ እንደሚያደርገን እና ዓለምን እንድንቋቋም እንደሚያስችለን በይበልጥ ማሳየት ፍላጎቱ አለኝ፡፡  ይህን የጨዋታ ፍልስፍናዬን ትሬፓታ ብየዋለሁ፡፡ ትሬፓታ የሚለውን ስያሜ የፈጠርኩት ከጣሊያንና እንግሊዘኛ ቃላቶች ውህደት ነው፡፡ በአማርኛ ቋንቋ ለጨዋታው ፍልስፍና ሙሉ ስያሜ ስላጣሁ ነው ብሏል፡፡ ትሬፓታ በዓለም የስልጠና ፍልስፍና ውስጥ አንድ ስልት ሆኖ የሚገባበት አቅም እንዳለው የሚያምነው አቤኔዜር፤   በጣሊያንኛ ትሬ ማለት ሶስት ሲሆን ፓ ማለት ማቀበል ታ ደግሞ ታክቲክ ነው፡፡ በአጠቃላይ የሶስትዮሽ የጨዋታ ፍልስፍና ማለት ነው፡፡ በሌላ አቅጣጫ ትርጓሜ ሊኖረውም ይችላል፡፡ ታ ለሶስት ማዕዘን፤ ፒ ለፒራሚድ እንዲሁም ቲ ለታክቲክ አድርገን ሶስት ማዕዘናዊ ፒራሚዳዊ ታክቲክ እንደማለት ነው፡፡ ዓለም በብዛት የሚያውቀው 4321 የጨዋታ ታክቲክ ይህን አሻሽሎ የመጣ ነው፡፡ በጣም ተጠጋግተን ተጋጣሚን አድክመን ለመጫወት የሚያስችለን ነው፡፡ ምናልባትም 33 ለ11 ብልጫ ኖሮን ልንጫወትበት የምንችለው ታክቲክ ይሆናል፡፡ ሁል ጊዜ በትሬፓታ 3ለ1 ሆነን ነው ተቃራኒ ቡድንን የምንገጥመው፡፡ በየትኛውም አቅጣጫ የሚንቀሳቀስን የተቃራኒ ቡድን ተጨዋች ለሶስት መካከላከል፤ አንድ ተጨዋች ብዙ በመንቀሳቀስ ይሰራል፡፡ እድሜያቸው ከ13 ጀምሮ የሆኑ ታዳጊዎች ላይ የስልጠና መዋቅሩን ተግባራዊ አድርጎ በመስራት በ17 አመታቸው ለክለብ እና ለብሄራዊ ቡድን የሚበቁ ምርጥ ተጨዋቾችን አሰልጥኖ ማውጣት ይቻላል፡፡ የእድሜ ማጭበርበር ለዚህ አሰራር የሚያዋጣ አይደለም፡፡ በትክክለኛ እድሜ ከሌላው አለም በተለይ ከሰሜን እና ምእራብ አፍሪካ ቡድኖች ጋር ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ የሚያግዝ ስልጠና ያስፈልጋል፡፡በትሬፓታ አንድ ተጨዋች ለሙሉ ብቃት የሚበቃው በኢትዮጵያ ደረጃ  ከአስራ ሶስት አመት ተነስቶ በአስራ ሰባት አመቱ ነው፡፡ ሂደቱ እንዳይነጥፍ ከስር ከስር በመተካት ይሰራበታል፡፡ በሃያ ዓመቱ ለብሄራዊ ቡድን ብቻ ሳይሆን በፕሮፌሽናል ደረጃ ብቁ የሆኑና ለብዙ አመት ቢያንስም እስከ ሰላሳ ዓመታቸው በብቃት የሚጫወቱትን በቀላሉ በትሬፓታ ማፍራት እንደሚቻልም በልበ ሙሉነት ይናገራል፡፡
ከገነነ  ተጠጋግቶ መጫወት አንፃር  ሲታይ
የትሬፓታ ስልጠና በእርግጥ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከተሞከሩ የስልጠና ዘዴዎች እና የጨዋታ ፍልስፍናዎች በብዙ መልኩ ልዩነት አለው፡፡ ከዚህ ቀደም የገነነ መኩርያን ተረዳድቶ ወይንም ተጠጋግቶ መጫወት የተባለውን ፍልስፍና በንፅፅር መገምገሙን አቤኔዘር ያስረዳል፡፡ ገነነ ፈጥሮታል በተባለው የጨዋታ ፍልስፍና ተጨዋቾች ምን ድረስ ተጠጋግተው እንደሚጫወቱ ምክንያታቸው እና ውጤቱ የተብራራ አይመስለኝም የሚለው አቤኔዜር፤ በገነነ የጨዋታ ፍልስፍና ተጋጣሚን ከራስ ሜዳ ጠራርጎ ማውጣት ቢባልም በትሬፓታ ጨዋታ ደግሞ ተጋጣሚን እየቀነሰ ሜዳን አጥቅቶ መጫወት የሚል ዘዴ መኖሩን በማስረዳት ነው፡፡ በትሬፓታ ሜዳን ማጥቃት ምንድነው፤ የባላጋራ ቡድን ተጨዋች በእኔ ቡድን ሜዳ ውስጥ ቢቀር እሱን መጠበቅ የለብኝም፤ ሜዳውን አጠቃላው ተጨዋች እቀንሳለሁ ሜዳን አጠባለሁ፡፡ ወደ ግብ ክልል እደርሳለሁ ጎል ፈጥሬ አገባለሁ፡፡ ድንገት ኳሱ ቢነጠቅ በመልሶ ማጥቃት ቡድኑን አደጋ ላይ የሚጥል አጨዋወት አይሆንም ተብሎ ቢጠየቅም ትሬፓታ ለዚህም መልስ አለው፡፡ አይገባም፡፡ ምክንያቱም በትሬፓታ ሁል ጊዜ ስንጫወት 3ለ1 ሆኖ ክፍተት በሌለበት ሁኔታ መጫወት ኳስ ወደ አደገኛ ክልል እንዳትገባ ስለሚያደርግ ነው፡፡ በገነነ ፍልስፍና 21 ሰው በተቃራኒ ቡድን ሜዳ መሰብሰቡን ያመጣል፡፡ በመጀመርያ በዚህ ጨዋታ ቦታ ለመፍጠር እና ለማግኘት ይቸግራል፡፡ ምክንያቱም 22 ሰው በግማሽ ሜዳ ሲገኝ ምን ያህል ሜዳው  እነደሚጠብ ማሰብ ነው፡፡ ሁለተኛ በጠበበ የጨዋታ ሜዳ ላይ ኳስ የአካል ንክኪ ስላለው ኢትዮጵያን ተጨዋቾች ደግሞ በአካል ብቃት ስለምንደክም ኳስን በቀላሉ በመቀማት አደጋ መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ለምን ጥንካሬ በብዛት አንሰራም ይላል ኳስ ጨዋታ ምንግዜም የሚያደክም ነገር አለው ይህን ሰርቶ ማዳበር ይጠይቃል፡፡ የገነነ ፍልስፍና መፅሃፉ ላይ እንዳየሁት ምንም አይነት ፎርሜሽን የሚያነሳው ነገር የለም፡፡ ያለን ነገር ተብሎ የተፈጠረ ቋንቋ ቢኖርም በገነነ የጨዋታ ፍልስፍና ስላለው ነገር ምንም በግልፅ የተቀመጠ ማብራርያ የለም፡፡ በትሬፓታ የጨዋታ ፍልስፍና ብዙ ልዩ ነገሮች አሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ተጨዋቾች ትንፋሽ አላቸው ባላጋራዎች ፈጣን ጡንቻ አላቸው፡፡ በሳንባችን ፈጣን ጡንቻዎን ማሸነፍ እንችላለን የሚል መሰረታዊ ስራ በትሬፓታ አጨዋወት መተግበሩ ውጤት ያመጣል፡፡
የሙከራ እድል ለምን አጣ?
ትሬፓታ የፈጠርኩት ከሶስት ዓመት በፊት ነው የሚለው አሰልጣኝ አቤኔዘር የጨዋታ ፍልስፍናውን በክለብ ደረጃ በተለይ በሲ ቡድኖች ለመተግበር ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ከድካም በስተቀር ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ወደ አዲስ አበባ ትልልቅ ክለቦች በመሄድ የተሻለ ነገር አለኝ በማለት ሊያሳምን ሞክሮ ምንም ምላሽ ማግኘት አልቻለም፡፡ በታዳጊዎች ላይ ልስራና ስፖርቱን እናሳድግ ብዬ  ብዙ ደክሜያለሁ፡፡ አንዳንዶች ሃሳቤ በመስማት ጥሩ ነው ብለው ቢደግፉም ትንሽ ጊዜ ስጠን ይሉና ተግባራዊ ለማድረግ ግን ይሳናቸዋል፡፡ ወደ ክለቦች ለመቅረብ ብዬ ሌላ ሙከራም አድርጌ ነበር፡፡ በአካል ብቃት አሰልጣኝነት ተቀጥሬ በመግባት የጨዋታ ፍልስፍናዬን ለማስፋፋት ያደረግኩት ሙከራ ነው፡፡ ይሁንና በዚህ መንገድም መሞከርያ እድሉን አላገኘሁም፡፡ በእርግጥ ክለቦች በትሬፓታ የጨዋታ ፍልስፍና ታዳጊዎቻቸውን ለማሰራት ብዙ በጀት ስለሚጠይቃቸው  ፈቃደኛ ያልሆኑ ይመስለኛል፡፡ በየክለቦቹ በቂ የልምምድ ሜዳ፤ የስልጠና መሳርያዎች እና ቁሳቁሶች እንዲሁም የላብ መተኪያ እና የምግብ አቅርቦቶች አለመሟላታቸው እንቅፋቶች ይሆናሉ፡፡ በቂ የህክምና አገልግሎትም ይጠይቃል፡፡ ለትሬፓታ የጨዋታ ፍልስፍና በቂ የስልጠና መዋቅር ለመዘርጋት ደግሞ የተዘረዘሩት ነገሮች በጣም ያስፈልጋሉ፡፡ በጨዋታው ፍልስፍና ለመስራት ከባለሙያዎች ጋር ለመምከር ባደረግኩት ሙከራም በቅርብ ከማውቃቸው ሰዎች እንኳን ድጋፍ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ገና የፍልስፍናውን ስያሜ ስናገር የሳቁብኝ ብዙዎች ናቸው፡፡ ማንም ለመቀበል ቸግሮታል፡፡ ወደ መንግስት እና የግል አካዳሚዎች ሃሳቡን ለማቅረብ የተወሰኑ ጥረቶች አድርጌም ነበር፡፡ በዚያ ግን ለስልጠና ሙያ ዲግሪ እና ከዚያም በላይ የትምህርት ደረጃ በመጠየቁ እንዳማይሳካልኝ ተረድቺያለሁ፡፡ በሌላ በኩል በኢትዮጵያ እግር ኳስ የአሰልጣኞች ቅጥር ያለው አሰራር እንቅፋት የሆነብኝ ይመስለኛል፡፡ ለአዲስ አሰልጣኝ እና የጨዋታ ፍልስፍና በቂ የስራ እድል የለም፡፡ ለነባር አሰልጣኞች ብቻ ነው እድል ያለው የሚጠየቀው ልምድ ብዙ ነው አዲስ ሃሳብ ያለው የመቀጠር እድል የለውም፡፡ ቢያንስ ለዋናው ቡድን ልምድ ያለው አሰልጣኝ እንደመስፈርት ቢቀመጥ መልካም ነው ለቢ እና ለሲ ቡድኖች በተለምዶ የስራ ልምድ መጠየቁ ለአዳዲስ የስልጠና ባለሙያዎች እና ፍልስፍናቸው የመቀጠር እድል መንፈጉ እኔንም ተፈታትኖኛል፡፡፡
በአጠቃላይ በትሬፓታ የጨዋታ ፍልስፍናዬ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ትንሽ ጣሳ ውሃ ይዜ መጥቻለሁ፤ ይህን የጣሳ ውሃ በተቃጠለው የኢትዮጵያ ህዝብ አንጀት እረጨዋለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ጠቃሚነቱን አስቦ የሚሰራበት ባለባልዲ ይመጣል ብዬ ተስፋ አድርጊያለሁ፡፡ ባለባልዲው ባለበርሜሉን ይፈጥራል፤ ባለበርሜሉ ደግሞ በቧንቧ ያመጣው ይሆናል፡፡ ከዚያም በኢትዮጵያ እግር ኳስ የጨዋታ ፍልስፍናው በእድሜዬ ተግባራዊ ባይሆን አሁን ተጀምሮ ሂደቱን ጠብቆ ከሄደ ለሌሎች የእድገት እንቅስቃሴዎች መነሳሻ የሚሆን አቅም ይፈጥራል ብዬ አምናለሁ፡፡
የጨዋታ ፍልስፍናዬን ለመተግበር በጉጉት እጠባበቃለሁ፡፡ ወደ ሚዲያ የመጣሁትም ይህን ትኩረት ለመፍጠር ነው፡፡ ለህዝብ  ያስተዋውቀኛል በሚል ነው፡፡ እያደገ የሚሄድበት መንገድ ይሄው ነው፡፡

Read 3214 times