Saturday, 20 December 2014 12:55

“የድሃ እናት ተስፋ” ሂሳዊ ንባብን ሲያደናግዝ

Written by  አብደላ ዕዝራ
Rate this item
(1 Vote)

[የካሜራዋ ሰምና ወርቅ “የሜሊ ታደሰ” የእናትና ልጅ ዉብ መሳጭ ፎቶ ግጥሙን ይመጥነዋል።]
ካዛንቺስ የአራት ትዉልድ እትብትና ትዝታ ብቻ ሳይሆን የገደል ማሚቶም የተከማቸበት መንደር ነዉ። ይህ ስፍራ -ከመናኸሪያ ከፍ ብሎ- ለደምሰዉ መርሻ የኅላዌና የብዕር ትርታ ቤተመቅደሱ ነዉ። እኛ ከሚዳሰሰዉ እየታከክን ተላምደነዉ ልብ የማንለዉ ይበዛል፤ ደምሰዉ ግን እያደባ “ሽንቁር” እያበጀ በግጥም ይደመማል። በዕዉቀቱ ስዩም “ያጮለቀ ብቻ” ብሎ የተቀኘዉ ለራሱና ለደምሰዉ መርሻ ይመስለኛል።
ጠቢብ ቤት ሳይኖረዉ፥ መስኮት ይከራያል
ግድግዳ ሳያቆም፥ ሽንቁር ይከራያል
ያጮለቀ ብቻ ሁሉን ነገር ያያል። -----
[ስብስብ ግጥሞች፥ ገፅ 102]
ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ “መንገድ ላይ የሚያብረቀርቅ ስንኝ እያፈተለከበት በሰመመን የሚሰፍ አንድ ባለቅኔ ላስተዋዉቅህ” ብሎ ከደምስ ጋር አገጣጠመኝ። ዕዉነትም በወረቀት ያልተፃፈ በቃሉ የጠቀለለዉን ሁለት-ሶስት ግጥም ሲያሰማኝ፥ ለፈንጠዝያ ሣይሆን ዉስጡን ለመዘመዘዉ ትዕይንት ሆነ ግለሰብ ሲጠወልግና ሲፈካ አገኘሁት። አነጋገሩ፥ አተካከዙ፥ ድንገት መጨነቁ፥ ሳትጠብቁት መሳቁ ... እንጀራ በመጠኑ፥ በብዛት ግን ግጥም እየቆረጣጠመ መጐምራቱ ያስታዉቃል። ያኔ፥ የዛሬ ሁለት አመት ገደማ ማስታወሻ ደብተሬ ላይ ያስቀረሁት አጭር ግጥም ዛሬም ያባንነኛል። ከወራት በፊት ማርታ ሃይለየሱስ የደምስን ሶስት ግጥሞች facebook ላይ ስታንሳፍፍ መንፈሴ ተረበሸ። ግጥሙን “የድሃ እናት ተስፋ”ን አብረን እናንብብለት።
“ካንዲት ምስኪን ድሃ
ይወለዳል ንጉሥ፥ ይወለዳል ጀግና”
መባሉን ሰምቼ፤
አምና ጀግና ወለድኩ
እራብ እየላሰኝ፥ ችጋር ላይ ተኝቼ፤
ይኸዉ ዘንድሮም አረገዝኩ
ያለመጠራጠር ንጉሥ እንደሚሆን
በምነቴ ፀንቼ።
እናት ድህነቷን ለመቋቋም የተስፋን ዱካ ተከትላ ታዘግማለች መባሉ የተለመደ እሳቦት ስለሆነ በግጥም አይነቃቃም። ግን የተካነ ባለቅኔ ይህን ፍዝነት በመግፈፍ በለጋነት እንዲነዝር ያበቀዋል። እንዴት? ደምሰዉ ሥነተረት በመሰለ ትንቢት ጀመረ። “ሥነተረት -mythology- ... ለተፈጥሮና ለኅብረተሰብ ኃይሎች ዲበ ተፈጥሮአዊ መልክና ፍች በመስጠት በሰዎች ዘንድ ሃይለኛ ስሜቶችን ... የሚቀሰቅስ ነዉ። ... የሃይማኖትን ጥንተ ነገሮች ያቀፈ ቢሆንም ሥነዉበታዊ ፍችም አለዉ። ከሚቀሰቅሳቸዉ ሥነዉበታዊ ስሜቶችና ከሚጠቀምበት ምናባዊ ፈጠራ አንፃር ሥነተረት ንቁ ያልሆነ የእዉነታ የሥነ ጥበባዊ አመለካከት ነዉ” [ማሌመዝገበ ቃላት፥ ገፅ 117] “ካንዲት ምስኪን ድሃ/ ይወለዳል ንጉሥ፥ ይወለዳል ጀግና” ሥነዉበታዊ አቅሙ በምናብ የሆነ ታሪክ፥ የተለየ ድርጊት ለማጥለል ማመቸቱ ነዉ። የሙሴን፥ የኦዲፐስ፥ የሼህ ሁሴን ጅብሪል ... ትንቢትም ይቀሰቅሳል። ለእናት ብቻ ሳይሆን ለሀገር ዕጣና ጦስ የመብቃት ጉልበት። እናት ለዚህ ትንቢት እንደ እመቤታችን የታጨች ይመስል ተንገላታለች። ግጥሙ ወሬ-ዘገባ ሳይሆን የአለመሸነፍን እልህ ለመቀኘት ሣይንዛዛ ቅዠት የመሰለ ትንቢትን በድርጊት ያላትማል።
እጦት ሶስት አይነት ሰዉ ይመለምላል። ኑሮ ገፈታትሮ ጥግ ሲያስገባዉ ተስፋ የሚቆርጥ፤ እጅጉን እየታከተ እየተላተመ መንፈሳዊ ተገን ሳይለማመጥ ለብሩህ ቀን የሚበቃ፤ ያጣ የነጣ፥ የአንድ ቀን ምግብና አዳር ፈተና የሆነበት፥ አንዳች ታዕምር ጨምድዶ የማይለቅ - ናቸዉ። ደምስ የቀረፃት እናት ሶስተኛዋ አይነት ናት፤ በትንቢት አምና ትንቢቱን ለመኖር እየተላጠች፣ ተስፋን እንደ ጥጥ ከምንም ከባዶ የምትከምር ያልጐበጠች እናት። ምኞት አልያም ተስፋ እዉስጧ አድፍጦ፣ ልጇን ወንዝ ልታሻግር ያለ እረፍት ዳክራ፣ ትንሽ ሲቀራት ሞት የሚወስዳት እናት ታስተክዛለች። ሀዲስ -የበዐሉ ግርማ ገፀባህሪ- ለወግ ለማዕረግ ሊበቃ ሲቃረብ እናቱ አሸልበዉ ያልፋሉ።
“እርጅና ከቀን ቀን እየተጫናቸዉ የሚሄዱት ድሃ እናቱ ብቻቸዉን ናቸዉ። ከእሱ ሌላ ምርኩዝና ተስፋ የላቸዉም... ቅጠል ለቅመዉ በመሸጥ ... እህል ቀምሰዉ ማደር ተስኖአቸዋል ... የተለበለበ እንጨት የሚመስለዉ ክንዳቸዉ ተዘርግቶ ጭራሮ መስበር አቅቶታል ... ፀሐይ ወጥታ እስከምትጠልቅበት ጊዜ ደከመኝን የማያዉቁ ሴት፥ እየበረደ ከሚሄደዉ ምድጃቸዉ ዳር ከቤት መዋል ጀምረዋል። ... ለመኖር የነበራቸዉ እልክ ያለቀ ይመስላል።... የድሃ ህይወት -ረጅም የግዞ ፍታት... እናቱ “ድሀም አገር አለኝ ይላል? መቃብርም የለዉ እቴ። በህይወት የተፋችዉ መሬት ሲሞት ምን መቃብር ትሆነዋለች? ... ካፌ እየነጠኩ የእድር መዋጮዬን ስከፍል የኖርኩት ለምን መሰለህ? ቀባሪ እንዳላጣ ነዉ። ... አይዞህ ድህነትን እንጂ መጥፎ ስምና እዳ አላወርስህም።” [“ሀዲስ” ልቦለድ]
ድህነትን መዉረስ ይጐመዝዛል። ሀዲስ፥ ነብይ መኰንን “ጉስቁልቁል ያለ ሰዉዬ፥ ኑሮ እንደሸሚዝ ያለቀበት” የሚለዉ አይነት ቢሆንም ተስፋዉ አልነጠፈም። ማርክስ “የህዝብ ዕፀፋርስ ሃይማኖት ነዉ” ቢልም፥ ሰዉ እንዳያምፅ መንፈሳዊ ቅዠቱ እግር ተወርች ያስረዋል ቢልም ተደፈጥጦ ከመቅረት የሆነ የተስፋ ጭላንጭል እያደባ  መከተል ይበጃል። ደምሰዉ በግጥሙ ከእናት ሽንፈት ይልቅ በተስፋ የማንሰራራት እልህ ነዉ የተፈታተነዉ። “ልጄ አንድ ቀን ሰዉ ሆኖ ያልፍልኛል” -ወይ ጀግና ወይ ንጉሥ- በየዳሳሳ ጐጆ ሚካኤልን፥ ማርያምን ... የሚማጠኑበት ተስፋ ነዉ። ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ይህን ከመሰለ ተስፋ አንዲት እናት ታዕምር ስታባብል ተቀኝቷል። ሀሩሩ በሚወብቅበት ወር የከሰል ክምር የምትነግድ “ጉሊት የዋለች ነፍስ” ጦሟን ላለማደር ለመንፈሳዊ እርዳታ ታጐበድዳለች።
በወርሀ ግንቦት፥
ገዢ የሌለዉ ከሰል፥
አሁንም አሁንም እየሰፋፈረች፤
እሷ ታስባለች።
አንጋጣ ወደ ሰማይ
(ደመናም ባይታይ)
እግዜር ምን ተስኖት፥
ከጠራዉ ሰማይ ስር፥ ዝናቡን አዉርዶት፤
ሰዉ ሁሉ በርዶት፤
መደቧን ሲከበዉ።
እሷ ትገርማለች፤
በደረቀ ግንቦት፥
ከፈረሰ መደብ፤
ከደቃቅ ከሰል ስር፤ ተስፋ ትምሳለች::----[“እዉነት ማለት” ...፥ ገፅ 20]
ቴዎድሮስ ከምንም አንሰራርቶ ጀግናም ንጉስም ሆነ። የደምሰዉ ድሃ ሴት እሱን ዳግም ለመዉለድ -ያለ ዘመኑና አዉዱ- ትንቢቱን እንደ ትኩስ ቃል ወርሳ ይሆን? በአባቷ ሽንፈት ተማራ ምንትዋብ አንድ ለናቱን ልትሳለቅበት ሞከረች።  
ሺህ ፈረስ ከኋላዉ፥ ሺህ ፈረስ ከፊቱ
ሺህ ብረት ከኋላዉ፥ ሺህ ብረት ከፊቱ
ይህን ሳታይ ሞተች ኮሶ ሻጭ እናቱ።
ደምሰዉ የሴቷን ህልም እንደራሰ ዉስጥ ልብስ፥ እንደ ገመና በየስንኙ ላይ አሰጣዉ እንጂ እናትየዉን አበጅታለች ወይም ተሳስታለች አላለም። ተስፋ ወንዝ ባያሻግራትም እዉስጡ ከመስመጥ ለጊዜዉ ያንሳፍፋት ይሆናል። ግን አንዳንዴ ሰዉ ለመትረፍ ወደ ብርሃን የገሰገሰ እየመሰለዉ የግልብጥ ከጨለማ አዘቅት ይወድቃል። የተሸሸገ ታሪክ አላት። የወለደችዉ ለምትወደዉ መከታ ለሚሆናት ተባዕት ሳለ ከከዳትስ? “አምና ጀግና ወለድኩ/ እራብ እየላሰኝ፥ ችጋር ላይ ተኝቼ፤”ስትል እመጫት እንጀራ በወጥ ማጣቀስ እንዳማራት ለረሃብ ስትዳረግ ይሰቅቃል። አሁን ደግሞ በሌላ አዳም ተመክታ ቁስሏ ሳይጠግ እንደገና ፀነሰች። እንደ ሙሴ ፅላት የምታምነዉ ወንድ ቢያስፈልጋትም መች ሰመረ? ለምን ልቧ ለወንድ ትርክክ አለ? እንዴትስ ተዘናጋች? እነዚህ መልስ ልታገኝባቸዉ ከፊት ለፊቷ የሚርመሰመሱ ጥያቄዎች አይደሉም፤ አንባቢን ነዉ የሚያሳስቡት። እንደ ታማኝ ዉሻ ዝም ብሎ የሆነ ትንቢት ተከትሎ መኖር ተስፋም ነዉ።ዶ/ር አብረሃም ፈለቀ “ባይጣፍጥ ህልማችን” እንዳለዉ ነዉ።
ከሜዳ ላይ ሲቀር - ድካም ልፋታችን
በዉሃ ሲበረዝ - ወዛችን ላባችን ?
በዳዋ ሲወረር - ቡቃያዉ ምርታችን
ምን ይዉጠን ነበር ?
ባይጣፍጥ ህልማችን
ባይጥም ቅዠታችን :: ----
[ቢላዋና ብዕር፥ ገፅ 7]  
ደምሰዉ እንግልቷን ስለአደመቀዉ ባይናገረዉም ከድህነት ለመገላገል ልጅ መገላገል መፍትሔ እንዳልሆነ ይጦቅማል። ከባዶነት፥ ዉስጧ እየተፍገመገመ የሚሰማት እንደ ተስፋ የሚሰፍ የሃሳብ ላባም ቢሆን መከተል መርጣለች። ታገል ሠይፉ “ፈልግ ይታየሃል” በሚል ግጥሙ ከጨለማ እምብርት ብርሃን ቦግ ሲል ሰዉ አስተዉሎ አፈፍ ካላደረገዉ አይነጋለትም ባይ ነዉ።
መብራት ታጠፋና
ቤት ታጨልምና
በጨለማዉ መሐል
ፈልግ ይታይሃል
ከዉስጥ የቆምክበት -የዉስጥ ዓለም ጮራ
አንተ ካንቀላፋህ - ያ መብራት ሲበራ
የለም ሌላ ፀሐይ፥ የለም ሌላ ብርሃን፥                አንተን የሚመራ። ---
[“የሰዶም ፍፃሜ”፥ ገፅ 51]
ጀግና እና ንጉሥ ለምትወልድ ሴት የታያት ተስፋ፥ ከትንቢት የተፈለፈለ እንጂ እንደ መብራትስ የሚመራት አይደለም፤ ድህነት ይበልጥ ዶቀሳት። ዕጣዋ ምን ይቀፈቅፍላታል? ወገግታ ሳይሆን እንደ ሙዝ ልጣጭ የሚያንሸራትታት የማይጠቅም ትንቢት ደምበሾነቱ ያደናግራል። ልጆቿ ለመመገብ፥ ለመልበስ ... ሲደርሱ “እንደ ሰዉ” ለመኖር ታባቃቸዉ ይሆን? ሰዉ ሌጣዉን ቢሆንም እጅ ካጠረዉ ተራ በመሰለ ጥቃቅን ምኞት ዉስጡ ይሸበራል፤ ሥነልቦናዊ እንግልቱ ይደፈርሳል። ደምሰዉ በሌላ “ግማሽ ገደል” ድንቅ ግጥሙ ይህን አስተዉሏል። በዚያ የቀን ግማሽ ጨረቃን እንዳጨ፥ ተጀንኜ ማልፈዉ እንደሰዉ እንደሰዉ እንደሰዉ አለ አይደል አንዳንዴ እንደሰዉ የምታይ እየመሰለኝ ነዉ በዚያች ትንሽ ነፍሴ የምጨማለቀዉ አጨብጭቦ ማዘዝ እየናፈቀኝ ነዉ፡፡ሊገለጥ የሚያዳግት፥ የዕለት ጋጋታና እንቅስቃሴ ዉስጥ፥ ልብ የማይሉት ምኞት... ሳይፈረካከስ ሳይበተን ደምስ በግጥም እሳት ጭሮበት ቦግ ሲያደርገዉ ያጥበረብራል። የድህነት ክፋትና መዘዝ ለፊልምና ለአብይ ልቦለድ የሚትረፈረፍ ጭብጥ ነዉ።
ተስፋን ከነተበ መቀነት ዉስጥ ተሸሽጐ እንደ ሆነ የምር ማበጠር ያባብሰዋል። ይህንን ነዉ ደምሰዉ በእምቅ አጭር ግጥም ሸብሽቦ ማወራጨት የደፈረዉ። ሁሉም ነገር የተሰወረ ስንጥቅ አለዉ፤ ለዚህም ነዉ ብርሃን ሾልኮ የሚያስደምመን ይላል ካናዳዊ ሙዚቀኛ Leonard Cohen “There is a crack in everything. That is how the light gets in”። ትንቢት ደግሞ ዉሸትም ዕዉነትም ነዉ።

Read 2715 times