Monday, 08 December 2014 14:18

የህንድ የአይን ህክምና ማዕከል (OIA) በታካሚዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ተገለፀ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

* “ብዙ ብር ከፍለን የዓይን ብርሃናችንን አጥተን ተመልሰናል”  -ታካሚዎች
* ከመነሻው የማዕከሉ አደረጃጀት አዋጁን የሚቃረን ነው - - የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ
* ማዕከሉ በየዓመቱ የሚታደስ የህክምና አገልግሎት ፈቃድ አልተሰጠውም

             ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት የተሻለ የአይን ህክምና ለመስጠት፣ ለኢትዮጵያውያን ሀኪሞች የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርግና በዘርፉ ምርምርና ጥናት እንዲያካሂድ ታስቦ በዘውዲቱ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ የተገነባው የህንድ የአይን ህክምና ማዕከል በታካሚዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ተገለፀ፡፡
ጉዳት የደረሰባቸው ታካሚዎች እንደተናገሩት በማዕከሉ በተሰጣቸው ህክምና ሳቢያ የዓይን ብርሃናቸውን አጥተዋል፡፡ በማዕከሉ የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት የተሟላ የህክምና ቁሳቁስ፣ በዘርፉ በቂ እውቀት ያላቸው ባለሙያዎችና ደረጃውን የጠበቀ ግንባታ ሳያሟላ የሚሰጠው ጥራቱን ያልጠበቀ አገልግሎት ዜጎችን ለአይነ ስውርነት፣ ለተጋነነ ወጪና ለእንግልት እየዳረገ ነው፡፡
ማዕከሉ ለኢትዮጵያውያን ሃኪሞች የቴክኖሎጂ ሽግግር ያደርጋል ቢባልም ሁሉም የህክምና ቁልፍ ቦታዎች በህንዳዊያን በመያዛቸው እቅዱ እንዳልተሳካና ከስምምነት ውጪ በተጋነነ የደሞዝ ክፍያ ምዝበራ እንደሚፈፀም ተገልጿል፡፡
የአይን ህክምና ማዕከሉ ከተለያዩ ተቋማት ገምጋሚ ተመድቦለት የአንድ ዓመት ተኩል የስራ አፈፃፀሙ በተገመገመበት ወቅት ከግንባታው ጀምሮ ችግር እንዳለበት በመግለፅ ችግሩ ሳይቀረፍ የትኛውም የመንግስት አካል ለማዕከሉ ድጋፍ እንዳያደርግ ገምጋሚዎቹ ቢያስጠነቅቁም ፈቃድ አግኝቶ ደረጃ ሳይወጣለት፣ ጥራቱን ሳይጠብቅና ባለሙያና መሳሪያ ሳያሟላ ወደ ስራመግባቱ ተገቢ አልነበረም ተብሏል፡፡ መንግስት በተቋሙ ላይ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ እንዳለበትም ገምጋሚዎችና የማዕከሉ ሰራተኞች አሳስበዋል፡፡
ከመነሻው የኢትዮጵያ ነዋሪዎች በጎ አድራጎት ድርጅት መሆኑ እየታወቀ የጤና ማዕከሉ፣ ሜዲካል ዳይሬክተር፣ ስራ አስኪያጁ፣ የሃብት ማፈላለጉና ሌሎች ከፍተኛ ኃላፊነቶች በውጭ ዜጎች መያዛቸው የፌደራል በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ አዋጅን ፍፁም የሚቃረን ነው ያሉት በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የጤና ፕሮጀክት ክትትል እና ድጋፍ ባለሙያ አቶ ጥላሁን አለሙ፤ ማዕከሉ በርካታ  ዘርፈ ብዙ ችግሮች ያሉበት መሆኑንና የተጠቃሚን አቅም ያላገናዘበ፣ ባለሙያ ያልተሳተፈበትና በከተማ አስተዳደሩ ስልጣን በተሰጠው አካል ያልፀደቀ የክፍያ ተመን በማውጣት የተጋነነ ክፍያ የሚያስከፍል፣ በጤና ንግድ ስራ ላይ የተሰማራ ድርጅት ነው ብለዋል፡፡
የጤና ማዕከሉ ካሉበት ችግሮች ውስጥ የማዕከሉ የውጭ ሞያተኞች የጤና የስራ ፈቃድ ከመውሰዳቸው በፊት ከኦፕሬሽን ጀምሮ ሌሎች የህክምና አገልግሎቶችን እየሰጡ እንደሆኑ የገምጋሚዎቹ ሪፖርት ያመለክታል፡፡ በተጨማሪም ማዕከሉ በየዓመቱ የሚታደስ የህክምና አገልግሎት ፈቃድ ያልተሰጠው ህገ-ወጥ ተቋም ነው ሲልም ሪፖርቱ ገልጿል፡፡
አቶ ወ/ፃዲቅ ማናዬ ይባላሉ፤ የ62 ዓመት አዛውንት ናቸው፡፡
አዲስ አበባ ቂርቆስ ክ/ከተማ ኦሎምፒያ አካባቢ ይኖራሉ፡፡ “አምና መጋቢት ወር ላይ ዓይኔን ታምሜ ወደ OIA የሄድኩት ህንዶቹ ጥሩ ህክምና ይሰጣሉ ተብዬ ነው ያሉት አዛውንቱ፤ በመጀመሪያ የሞራ ግርዶሽ ነው ተብለው 4250 ብር ከፍለው የቀዶ ህክምና ማድረጋቸውን ይናገራሉ፡፡ “በመጨረሻ እራሳቸው በፈጠሩት ስህተት ከአንድም ሶስት ጊዜ ኦፕራሲዮን ተደርጌ ሬቲናዬን አበላሹት” የሚሉት አዛውንቱ፤ ከዚያም በኋላ ያለ ምንም መድሃኒትና እርዳታ ዝም ብለው እንዲጠብቁ በመደረጋቸው ቀኝ አይናቸው ሙሉ ለሙሉ ከጥቅም ውጭ ሆኖ ማየት እንደተሳናቸው በምሬት ገልፀዋል፡፡
ያለ ምንም መድሃኒት ለሁለት ወር ቀጠሮ ሰጥተውኝ ስመለስ “ያንተ የሬቲና ችግር ነው አሉኝ” የሚሉት አቶ ወ/ፃዲቅ፤ “የሬቲና ችግር ከሆነ ለምን ሶስት ጊዜ አደንዝዛችሁ ሞራ ነው በማለት ኦፕሬሽን አደረጋችሁኝ” በማለት ህንዳዊ ሀኪሞቹን መጠየቃቸውን፤ ነገር ግን ከማመናጨቅ ውጭ ቀና ምላሽ ማጣታቸውን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ “ወደ ሌላ ህክምና ለመሄድ ሪፈር ፃፉልኝ፤ አለበለዚያም እናንተ ጋር ያደረግሁትን አጠቃላይ የህክምና መረጃ ስጡኝ” ብለው መጠየቃቸውን የሚናገሩት አዛውንቱ፤ የምናውቀው ነገር የለም የፈለጋችሁበት ሄዳችሁ ክሰሱን፤ ምላሽ እንሰጣለን” በማለት አመናጭቀው እንደሸኟቸውና እይታቸውን አጥተው ቤት ውስጥ ከተቀመጡ 10 ወር እንዳለፋቸው ገልፀው፤ ማንበብና መፃፍ ሁሉ እንደተሳናቸው ተናግረዋል፡፡
በዚሁ የአይን ህክምና ማዕከል የህክምና ስህተት ተፈጽሞብኛል ያሉት የ65 ዓመቱ አዛውንት አቶ ኮሬ ወ/ማርያም፤ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ለህክምና ሲሄዱ የሞራ ግርዶሽ ነው ተብለው አምስት ሺህ ብር ከፍለው ኦፕሬሽን መደረጋቸውን አስታውሰው፣ በ15ኛው ቀን አይናቸው ሙሉ በሙሉ ጠፍቶ ወደ ማዕከሉ ተመልሰው መሄዳቸውን ይናገራሉ፡፡
“አይኔ መጥፋቱን እያወቁ አንድም ጠብታ ሳያዙልኝ ወደ ምኒልክ ሆስፒታል እንድሄድ ነገሩኝ” የሚሉት አዛውንቱ፤ ምኒልክ ሆስፒታል ሁለት ሶስት ጊዜ ቢመላለሱም ምንም እርዳታ ሳያገኙ ሲኤምሲ አትሌቲክስ ህንፃ ላይ በሚገኘው “ብሩህ ቪዥን” ክሊኒክ እንዲታከሙ እንደተነገራቸው ገልፀዋል፡፡
“ብሩህ ቪዥን አንዴ በመርፌ፣ ሌላ ጊዜ በመሳሪያ ይታይ እያሉ ለተጨማሪ 7ሺህ ብር ወጪ ተዳርጌያለሁ” ያሉት እኚህ ታካሚ፤ አራት ወር እንደሆናቸውና አይናቸውንም አጥተው፣ 12 ሺህ ብራቸውን በማፍሰስ ለተጨማሪ ችግር በመዳረጋቸው ተጨማሪ ወጪ እንደሚጠብቃቸው ተናግረዋል፡፡
“የተሟላ መሳሪያ ሳይኖር፣ በዘርፉ የሰለጠነ በቂ ሀኪም በሌለበት የህክምና ማዕከሉ እንዴት ፈቃድ ተሰጠው?” ሲሉ የሚጠይቁት አቶ ኮሬ፤ “መንግስት ለዜጎቹ የሚጨነቅ ከሆነ እንዲህ አይነቶቹን ተቋማትና ሰራተኞች ለፍርድ ማቅረብና ኢንሹራንስ ለተጎጂዎች እንዲከፍሉ፣ ከዚያም በአስቸኳይ ማዕከሉን ዘግቶ ከጥፋታቸው ማስቆም ያስፈልጋል” በማለት ብለዋል፡፡
ወደ ህክምና ማዕከሉ ከመሄዳቸው አስቀድሞ መኪና መንዳት ይችሉ እንደነበር የተናገሩት  የ66 ዓመቱ አዛውንት፤ ከአንድ ዓመት በፊት ህክምና መጀመራቸውን ይናገራሉ፡፡ “ችግሩ የሞራ ግርዶሽ ነው፤ ይህን በቀላሉ እንገፍልሃለን ብለው ኦፕሬሽን ካደረጉኝ በኋላ ጭራሽ አይኔ ማየት አቁሞ ቤት ተቀምጫለሁ” ሲሉ በምሬት የገጠማቸውን ችግር ገልፀዋል፡፡
“ከዚያ በኋላ አይኔ ጠፋ ብዬ በተከታታይ ብመላለስም ምንም መፍትሄ ሳላገኝ እስካሁን አለሁ” ያሉት አዛውንቱ፤ “እርግጥ እኔ የካርድ 40 ብር ከመክፈል በስተቀር ያወጣሁት ወጪ የለም፤ ምክንያቱም የነፃ ህክምና ወረቀት አፅፌ ነበር የሄድኩት” ብለዋል፡፡ እሳቸው ደግሞ የጨረር ህክምና ተደርጐላቸውም መሻሻል እንዳላሳየ ገልፀው ወደ ምኒልክ ሆስፒታል ሪፈር እንደተፃፈላቸው ይናገራሉ፡፡ “ሚኒልክ ሆስፒታል ሄጄ ስመረመር አይንህ ተበላሽቷል፤ የማየትም ተስፋ የለውም ብለው መለሱኝ” የሚሉት ተጎጂው፤ ተስፋ ቆርጠውና እይታቸውን ተነጥቀው ቤት መቀመጣቸውን ጠቅሰው ወዴት አቤት እንደሚባል ግራ እንደገባቸው፤ ይህን ላድርግ ቢሉም አቅምና የእይታ ችግር እንደማይፈቅድላቸው ተናግረዋል - “እግዜር ይክሰሳቸው” ሲሉም በምሬት ተናግረዋል፡፡
በአንድ የመንግስት የሚዲያ ተቋም ውስጥ የሚሰራ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ለህክምና ወደ ማዕከሉ መሄዱንና መቶ ብር ከፍሎ ካርድ ማውጣቱን ይናገራል፡፡ እንደ ሌሎቹ የሞራ ግርዶሽ ችግር ሳይሆን ረጅም ርቀት እይታ ችግር እንዳለበት ተነግሮት፤ ለህክምናው መዘጋጀቱን ነገር ግን በመሃል ወረፋ ሲጠብቅ ስለ ማዕከሉ መጥፎ መጥፎ ነገሮች ሲነገሩ በመስማቱ ህክምናውን እንዳቋረጠ ይናገራል፡፡ “ችግሬን ከድጡ ወደ ማጡ አላደርግም ብዬ ህክምናውን አቁሜ ይልቁንም ክሊኒኩ ውስጥ አለ የተባለውን አሻጥር እየመረመርኩ ነው” ያለው ጋዜጠኛው፤ በማዕከሉ ከሚሰሩ ኢትዮጵያውያን የህክምና ባለሙያዎች የሰማው እጅግ የሚዘገንን ህገ-ወጥ አሰራር አይነ ስውር ከመሆን ያተረፈውን አምላኩን እንዲያመሰግን እንዳደረገው አጫውቶኛል፡፡
ማዕከሉ ከዚህ በተጨማሪም በብልሹ አሰራሮች መተብተቡን የግምገማ ሪፖርቶቹ ይጠቁማሉ፡፡ በሪፖርቱ ከተጠቀሱት ችግሮች መካከል የፋይናንስ፣ የግዢና የሰው ሃብት አስተዳደር ማኑዋሎች የሌሉትና ለምዝበራ የተመቻቸ መሆኑ፣ ማዕከሉ በአዋጅ ኃላፊነትና ስልጣን በተሰጠው ደረጃ መዳቢ አካል ደረጃ ያልወጣለት መሆኑና በምስራቅ አፍሪካ አንደኛ የተባለው ማዕከል ምንም አይነት የላብራቶሪ፣ የጠቅላላ ሰመመን፣ የድንገተኛና መሰል የአገልግሎት ክፍሎች ያልተሟሉለት መሆኑ ይገኙበታል፡፡
በሃገር ውስጥ ሊሟሉ የሚችሉ የቢሮ ቁሳቁሶች በከፍተኛና ወጪ ከውጭ ከመግባታቸው በተጨማሪ ተፈራራሚ አካላት ቢያንስ በፅሁፍ እንዲያውቁት አለመደረጉ የተጠቆመ ሲሆን የፕሮጀክት ክለሳ ሳይደረግ ከእቅድ ውጭ ለሆነ ግንባታ 634ሺ 986 ዶላር እንዲሁም ለህክምና መሳሪያና ለቢሮ ቁሳቁስ 315ሺ 171 ከ37 ሳንቲም በድምሩ 950ሺ 157 ከ37 ዶላር ያለ አግባብ ወጪ መደረጉን የገምጋሚው ኤክስፐርት ሪፖርት አመልክቷል፡
ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ማዕከሉ ሄደን የተለያዩ ህንዳዊያን ሃኪሞችን ለማነጋገር የሞከርን ሲሆን የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ወደ ህንድ በመሄዳቸው መረጃ ማግኘት የምንችለው እሳቸው ሲመለሱ ብቻ እንደሆነ ተገልፆልን ተመልሰናል፡፡

Read 6641 times