Saturday, 29 November 2014 10:42

የዲጂታል ቴሌቪዥን መሣሪያዎች ግዥና የግንባታ ጨረታ ሊወጣ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

         የቴሌቪዥን አገልግሎትን ከአናሎግ ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማሸጋገር በቅርቡ የዲጂታል ቴሌቪዥን መሳሪያዎች ግዥና የግንባታ ጨረታ እንደሚወጣ ተጠቆመ፡፡
ለዲጂታል ቴክኖሎጂው አገልግሎት አስፈላጊ የሆኑ ትራንስሚተሮችና ልዩ ልዩ መሳሪያዎች ግዥ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በኩል እንዲካሄድ፣ አጠቃላይ የፕሮጀክት አስተዳደሩንና የቴክኖሎጂ ሽግግሩን ደግሞ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እንዲከታተለው ተወስኗል፡፡ በቅርቡ ጨረታውን ለማውጣት ቅድመ ዝግጅቱ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ የመሳሪያዎቹ ግዥ፣ ተከላና ግንባታም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የዲጂታል ቴሌቪዥን ስርጭት አገልግሎትን ለማግኘት የዲጂታል መቀበያ መሳሪያዎች (ሴት-ቶፕ ቦክስ) ዲጂታል ኢንተግሬትድ ቴሌቭዥን (IDTV) እና አንቴና በዋንኛነት የሚያስፈልጉ ሲሆን መሳሪያዎቹ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ እንደሆኑ ታውቋል፡፡ መንግስት መሳሪያዎቹ ከቀረጥ ነጻ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡበትን ሁኔታ በማመቻቸት በድጎማና በረጅም ጊዜ ክፍያ ተገልጋዩ እንዲገዛቸው ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባውም መረጃው አመልክቷል፡፡
ደረጃውን ያልጠበቀ መሳሪያ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ እንደሚገባ የተገለፀ ሲሆን፤ የአናሎግ ቴሌቪዥኖች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡና በአገር ውስጥ እንዳይመረቱ ለማድረግ የሚቻልበትን ጊዜ ለመወሰን የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ እንደሆነም ታውቋል፡፡

Read 1965 times