Saturday, 22 November 2014 12:27

ልብወለዱና ገሃዱ ዓለም በኮከብ ትንተና

Written by  አደዳ ኃይለሥላሴ adedahaile@yahoo.com
Rate this item
(56 votes)

*የ‘ፍቅር እስከመቃብር’ ጉዱ ካሣ ኮከቡ ምንድነው?
*የኔልሰን ማንዴላና የመለስ ዜናዊስ?

ቀዳሚ ቃል
የኢትዮጵያ ኮከብ ቁጥር 2 የሆነው ፍካሬ ኢትዮጵያ፣ የአብነት ሁለተኛ የታተመ ሥራው ነው። ከመጀመሪያው ጋር የሚያገናኘው ነገር ቢኖር ሁለቱም የአስትሮሎጂ መጻሕፍት መሆናቸው ብቻ ነው። ከዚያ በዘለለ፣ የተደገመ ሀሳብም ሆነ ይዘት የለም-ከስመጥሮች ዝርዝር ውጪ። በየኢትዮጵያ ኮከብ ቁጥር 1 ውስጥ የተካተቱት ስመጥሮች 500 ያህል ነበሩ፣ አሁን በፍካሬ ኢትዮጵያ ሌሎች ተጨማሪ 700 ስመጥሮች ተካተው፣ የስመጥሮች ዝርዝር ወደ 1,200 ከፍ እንዲል ተደርጓል። የኢትዮጵያ ኮከብ ቁጥር 1ን ማርታ በፍቃዱ የተባለች አንባቢ፣ በሰንደቅ ጋዜጣ ላይ “የአስትሮሎጂ መሰረታዊያን (Introduction to Astrology) ሊባል ይችላል” ያለችውን ገለጻ እኔም ብጠቀመው እወዳለሁ። ፍካሬ ኢትዮጵያን የበለጠ ለማጣጣምና ለመረዳት የኢትዮጵያ ኮከብ እንደ አብሪ ጥይት መንገድ ጠራጊ ሆኖ የሚያገልግል መጽሐፍ ነው።
በፍካሬ ኢትዮጵያ፣ አርኪ በሆነ መልኩ የባዮግራፊ ኮክቴል ታገኛላችሁ። እነዚህን ከመቶ ሃምሳ በላይ የባዮግራፊ ክምችቶች ስታነቡ፣ ነፍሳችሁ እጅግ ሀሴት እንደምታደርግ አልጠራጠርም። ስለ ሀዲስ ዓለማየሁ፣ ስለ እማሆይ ጽጌ ማርያም፣ ስለ መኮንን ሐብተወልድ፣ ስለ አዳም እና ሔዋን፣ ስለ መንግሥቱ ለማ፣ ስለ አጼ ምኒልክና ስለ ጣይቱ፣ ስለ አጼ ሐይለሥላሴና ስለ ኢያሱ፣ ስለ እነ አክሊሉ ሀብተወልድ እና ……. ስለ ሌሎች ኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ስመጥር ሰዎች የሕይወት ታሪክ በጣፋጭ ቋንቋ ተሰናድቷል።
መጽሐፉ አራት ዐብይ ክፍሎችና እና 18 ምእራፎች ሲኖሩት፣ ከፊቱ አበርክቶ፣ ማውጫና፣ መቅድም አለው፣ ከኋላው ደግሞ ድኅረ ቃል፣ ዋቢ መጻሕፍት እና ምስጋናን ይዟል። እነዚህን አለፍ አለፍ እያልኩ አስተዋውቃለሁ።
ክፍል አንድ፡ የአሥራ ሁለቱ ነገደ ከዋክብት ፍካሬ
በክፍል አንድ የአሥራ ሁለቱ ዋና ዋና ኮከቦች ሰፋ ያለ ሐተታ በሁለት፣ በሁለት ክፍል ተዋቅሮ ቀርቧል። በመጀመሪያው ክፍል የየኮከቡ ንድፈ ሐሳባዊ ገለጻ በስፋትና በብቃት ተብራርቷል፤ በለጣቂው ክፍል ደግሞ ተጨማሪ ንድፈ ሐሳባዊ ማብራሪያዎች በምሳሌዎች ዳብረው ቀርበዋል።
ለምሳሌ ያህል፣ እስኪ ቶረስን እንይ። በመጀመሪያዎቹ አምሥት ገጾች፣ ስለ ቶረስ ባህርያት ከተብራራ በኋላ፣ በቀጣዮቹ 14 ገጾች ከላይ ለተጠቀሰው እንደ ማጠናከሪያና ማስፋፊያ፣ የህይወት ታሪክ አጻጻፍ ስልትን በተከተለ መልኩ የቶረስ ኮከብ ያላቸው ስመጥር ሰዎችና የቶረስ ኮከብ ባለቤት ከመሆናቸው የተነሳ ያሳዩት ባሕሪና የከወኗቸው ድርጊቶች ተተርከዋል። ከነዚህም ውስጥ የአጼ ኃይለሥላሴ አባት ራስ መኮንን፣ ካርል ማርክስ፣ ሌኒን፣ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር፣ የኡራጋዩ ፕሬዚደንት ጆሴ ሙጂካ፣ የኤደን ገነት፣ ሶቅራጥስ፣ ናርሲሰስ፣ አዶኒስ፣ ሼክስፒር፣ ማኪያቬሊ፣ ፍሮይድ፣ ፒኬቲ እና ሌሎችም በርካታ ቶረሶች  የከወኗቸው አስደናቂ ተግባራት በሚጣፍጥ ቋንቋ በበቂ ሁኔታ ቀርቦላችኋል።  
ስለነዚህ ሰዎች ስታነቡ፣ ራሳችሁ ቶረስ የሆናችሁ እንደሆነ የራሳችሁን ገጽታ በሌላ ሰው ስብእና ውስጥ ታገኙታላችሁ፤ አልሆናችሁ እንደሆነ ደግሞ የምታውቋቸውን ሰዎች እያሰባችሁ አንድን ነገር ለምን እንዳደረጉት ትረዱዋቸዋላችሁ። ከዚህ ከቶረስ ክፍል፣ የአንዲት አንቀጽ ክፋይ ላቅምሳችሁ (ገጽ 49)፡-
ከሚያዚያ 27፣ 1928 እስከ 2004 የኖረው ስብሐት ገብረእግዚአብሔርም ከስመጥር ፈላስፋዎች ጐን የሚመደብ ነው። ስብሐት ለሲግመንድ ፍሮይድ፣ ለካርል ማርክስና ለሼክስፒር ልዩ ፍቅር እንዳለው እየደጋገመ ይናገር ነበር። የሦስቱም ኮከብ ቶረስ ነው። ዶስቶቭስኪና ካሙ ለተባሉት ደራሲያንና ደጎል ለተባለው መሪ ደግሞ ልዩ አድናቆት ነበረው። ሦስቱም ስኮርፒዮ ናቸው። ስኮርፒዮ የቶረስ ዋልታዊ ተቃርኖ ኮከብ ነው፤ ሁሉም ኮከቦች በተቃራኒ ኮከባቸው ባህሪና ተፈጥሮ ይደመማሉ።
የ12ቱ ኮከብ ሐተታ፤ ወጥ አካሔድ መከተሉ፣ መጽሐፉን ለአንባቢ በጣም ምቹና ቀላል ያደርገዋል። ሐተታው በአጠቃላይ 260 ገጾችን የያዘ ሲሆን እያንዳንዱ በአማካይ በ21 ገጾች ተብራርቷል ማለት ነው። እያንዳንዱ ክፍል በፈረንጅና በአበሻ ኦቆጣጠር ከመቼ እስከ መቼ ነው የሚውለው በሚል ይጀምራል፤ ለምሳሌ ሳጁታሪየስ (ከ23 ኖቬምበር - 21 ዲሴምበር ወይም ከህዳር 14 - ታህሳስ 12) እንደ ማለት ነው። እያንዳንዱን ኮከብ ይገልጻሉ ተብለው የታሰቡ ጥቅሶች ተመርጠው ቀርበዋል። ለምሳሌ ያህል ስለ ጂኦሎጂ ብቻ ብዙ ነገር ከማውቅ፣ ስለ ስነ ጽሁፍም፣ ስለ ፖለቲካም፣ ስለ ባህልም፣ ስለ ፊዚክስም፣ ስለ ሀይማኖትም፣ ስለ ስነ ፍጥረትም … ትንሽ ትንሽ ባውቅ የተሻለ ነው ብለው የሚያስቡትን ጄሚናዮች ይወክላል የተባለው ጥቅስ የሚከተለው ነው (ገጽ 55)፡ “ስለ አንድ ጉዳይ ሁሉን ከማወቅ፣ ስለ ሁሉም ጉዳዮች አንድ ነገር ማወቅ ይበልጣል።-ፓስካል”። የሚገርመው ነገር ፓስካል ራሱ ጄሚናይ መሆኑ ነው። ጄሚናዮች ይህ ይወክላችኋል? እኔን በደንብ ወክሎኛል። ከዚህ በመቀጠል ደግሞ፣ አሁንም ለእያንዳንዱ ሐተታ ኮከብ መግቢያ፣ ምንጫቸው ህዝባዊ የሆነ ሀገር በቀል ባለ ሁለት ስንኝ መንቶ ቃላዊ ግጥሞች ይገኛሉ። እነዚህም፣ እያንዳንዱን ኮከብ የበለጠ ለመግለጽ የዋሉ ናቸው። ለምሳሌ፣ ወግ አጥባቂዎቹን ካፕሪኮርኖች ለመግለጽ፣ጸሃፊው፣ “እንደምነህ ብለው - እንደምነሽ አለኝ፤ የግዚሀር ሰላምታ - ሊቀር ነው መሰለኝ።” የሚለውን ስነቃል ተጠቅሟል። ካፔዎች ምን ትላላችሁ?

ከእያንዳንዱ ሐተታ ኮከብ የገለፃዎቹ ማብቂያ ላይ ደግሞ፣ እንደ መውጫ፣ በፊደል ቅደም ተከተል ተራ  ከአንድ ሺ ሁለት መቶ በላይ የስመጥሮች ዝርዝር ቀርቧል። በዝርዝሩ ውስጥ በዋናነት የኢትዮጵያውያንና የውጭ ሀገር ስመጥሮች፣ የአገሮች፣ የከተሞችና የገፀባህርያት ስሞች ተካተዋል።  አሕጽሮተ ቃላት፤ መቅ= መጽሐፍ ቅዱስ፤ ልፊ= በልቦለድ እና በፊልም ውስጥ የሚታወቁ ገፀባህርያት፤ ፍእመ= ፍቅር እስከ መቃብር፤ ግአ= ግሪክ አፈታሪክ፤ ተ=በተረት ውስጥ የሚታወቁ ገፀባህርያት በማለትም ገለጻቸው ተካቷል። ለምሳሌ፣ ራሱ ስኮርፒዮ በሆነው ተቋም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በአንድ ወቅት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶክተር ዐቢይ ክፍሌና፣ ፕሮፌሰር አንድርያስ እሽቴ ሦስቱም በስመ ጥር ስኮርፒዮዎች ምድብ ውስጥ ቀርበዋል። የፍልስፍና መምህሩ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ፣ ትንቢት ተናጋሪው የወሎው ሼክ ሁሴን ጅብሪልና የሐረር ከተማ - ሦስቱም ከስመጥር ሳጁታሪየሶች ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል። አንዳች መመሳል ይታያችኋል? እንዲህ እንዲህ እያላችሁ ከግለሰቦች አልፎ፣ ሀገራትና ተቋማት፣ ገጸባህርያትና ጋዜጦች መጽሔቶች ሁሉ ኮከብ እንዳላቸውና ኮከባቸው ምን እንደሆነ፣ በዚያም የተነሳ ምን ምን ባህሪ እንደሚያሳዩ በመጽሀፉ ውስጥ ተብራርቷል።
ክፍል ሁለት፡ የዐውደ ነገሥት፣ የባሕረ ሐሳብ እና የፍቅር እስከ መቃብር ፍካሬ
ክፍል ሁለት፣ ሦስት ፍካሬዎችን አካቷል፡ የዐውደ ነገሥት ፍካሬ የሚለው የመጀመሪያው ንዑስ ክፍል ሲሆን በ13 ገጾች ተብራርቷል። በውስጡም፣ በዐውደ ነገሥት አሰራር የአንድ ሰው ኮከብ እንዴት እንደሚወሰንና የሞክሼ ፊደላት ጉዳይ በስሌቱ ላይ ያላቸው ተጽእኖ፣ የፊደልና የልደት ቀን ኮከብ ይመሳሰላል ወይስ አይመሳሰልም? ወደ የትኛው ማድላት ይሻላል? የሚለው፣ ዐውደ ነገሥት 12ቱን ኮከቦች የገለፀባቸው አግባብነት፣ እንዲሁም ስለ ዐውደ ነገሥትና ሆራሪ አስትሮሎጂ እና ሌሎች መሰል ርእሰ ጉዳዮችን የያዙ ሀሳቦች ተብራርተዋል።
እንዲሁም፣ የባሕረ ሐሳብ ፍካሬም ለውይይት ቀርቧል። ባሕረ ሐሳብ ወይም የኢትዮጵያ የዘመን ቆጠራ ጥበብ፣ አለቃ ያሬድ ፈንታና ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በየመጸሕፍቶቻቸው ያነሱት ሀሳብ ተፍታቶ ቀርቧል። በገጽ 287 ላይ፣ “ባሕረ ሐሳብ ድንቅ የዕውቀትና የጥበብ መስክ ነው፡፡ ተድበስብሶና ተዝረክርኮ የቀረ የሚመስለውን አገር በቀሉን የፍካሬ ከዋክብት ዕውቀታችንን ለማሰባሰብም ባሕረ ሐሳብ አንዱና ዋነኛው መንገድ ሊሆን ይችላል፡፡” ይላል ደራሲው።
የፍቅር እስከ መቃብር ፍካሬ በ52 ገጾች ተብራርቷል። ይህ ገጸ ባህርያትን በአስትሮሎጂ ማእቀፍ ውስጥ ማየት በስነጽሁፉ ዘርፍ ፈር ቀዳጅና ልዩ የሆነ አካሔድ ነው። ጸሃፊው በፍቅር አስከ መቃብር ውስጥ ካሉት ዋና ዋና ገጸ ባህርያት አንዱ የሆነውን የጉዱ ካሳን ዓመልና ባሕሪ በማጥናት ኮከቡ አኳሪየስ መሆኑን፣ በ2001 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋዎች ጥናት ተቋም ባዘጋጀው 21ኛው የቋንቋዎች ጥናት ኮንፍረንስ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ማቅረቡን አውቃለሁ። ርእሱም፡-‘የዘመን፣ የአገር እና የገፀ ባሕሪ ትንተና በአስትሮሎጂ ማእቀፍ ውስጥʼ የሚል ነበር። የጉዱ ካሳ ኮከብ አኳሪየስ ለመሆኑ ከመጽሐፉ ውስጥ ዐበይት የሆኑትን የካሳ ዳምጤን ባሕርያት በማውጣት አሳይቷል፡፡ በወቅቱም የቋንቋ ምሁራኑ፣ ፈር ቀዳጅና አዲስ አቀራረብ ነው በማለት አድንቀውታል። ይህንን ምእራፍ ሳነብ፣ ምነው ሀዲስ ዓለማየሁ በኖሩና፣ የሚሉትን በሰማሁ ብዬ መመኘቴ አልቀረም። ጉዱ ካሳ አኳሪየስ ነው፣ በዛብህ ፓይሰስ ነው፣ ሰብለወንጌል ስኮርፒዮ ናት ወይም ካሳ ዳምጤ፣ ደለዊ ንፋስ፣ በዛብህ ሁት ውሃ፣ ሰብለወንጌል ደግሞ ዐቅራብ ውሃ ናቸው ሲባሉ፣ምን ይሉ ነበር?
አንባቢዎች፤ ይህንን የፍቅር እስከ መቃብርን ፍካሬ ካነበባችሁ በኋላ፣ ፍቅር እስከ መቃብርን እንደገና ማንበባችሁ አይቀሬ ነው። ምክንያቱም፣ የመጽሐፉ መግለጫ እነሆ በስነ ከዋክብት ሳይንስ ተሰናስሏልና ነው። ጸሃፊው፣ አልፎ ተርፎም ፍቅር እስከ መቃብርን ከታሪክ ጋር አመሳክሮ ተንትኖ፣ መጽሐፉ ፈጽሞ ልቦለድ አይደለም፣ እውነተኛ ታሪክ ነው ሊለን ይሞክራል። እስኪ አንብቡና ፍረዱ፡፡
በገጽ 293፣ “የፍቅር እስከ መቃብር ታሪክ ከዐፄ ቴዎድሮስ ዘመን አንስቶ እስከ ዐፄ ኃይለሥላሴ የመጨረሻዎቹ ዓመታት ድረስ የሚዘልቅ ነው የሚመስለው። ይኸ አተያይ ደራሲው ራሳቸው ካመላከቱት ዘመን ብዙም የሚዛነፍና የሚጣረስ አይመስለኝም።” በማለት እመት ውድነሽ የ19ኛው  ክፍለ  ዘመን  ኢትዮጵያን  ይወክላሉ ይለናል - ጸሃፊው።
የፍቅር እስከ መቃብር ታሪክ ቢጋር፣ የቦጋለ እና የውድነሽ ኮከብ፣ የቦጋለ እና የውድነሽ ገጸ ባህሪ ውክልና፣ የበዛብህ ኮከብ ትንታኔና በመጽሐፉ ውስጥ ያለው ውክልና፣ የሰብለወንጌል ኮከብ ትንታኔና በመጽሐፉ ውስጥ ያላት ውክልና፣ የሰብለወንጌልና የጉዱ ካሳ ኮከብ የስምምነት ደረጃ፣ የሰብለና የበዛብህ ኮከብ የስምምነት ደረጃ፣ የፊታውራሪ መሸሻ እና የአጼ ኃይለሥላሴ (ሁለቱም ሊዮዎች ናቸው) ተመሳስሎ፣ በተለምዶ የታህሳሱ ግርግር የሚባለው የ1953ቱ መፈንቅለ መንግሥትና በፍቅር እስከ መቃብር የተተረከው የባላገሮች ዓመጽ፣ ጉዱ ካሳ አቤቶ ኢያሱን ይወክላል የሚለው አመክንዮ (ሁለቱም አኳሪየስ ናቸው) እና ሌሎች በጣም አስደናቂ የሆኑ አስትሮሎጂካዊና ታሪካዊ ትንታኔዎች መጽሐፉን እንደገና እንድናነበው ያስገድደናል።
ክፍል ሦስት፡ የማንዴላ ኮከብ ፍካሬ እና የመለስ ኮከብ ፍካሬ
ይህ ክፍል አስትሮሎጂን በተግባር የምናይበት ነው። የኔልሰን ማንዴላን የሕይወት ታሪክ በሙሉም፣ በከፊልም፣ በጥቂቱም እንደሁኔታው የማናውቅ አንኖርም። ኔልሰን ማንዴላ ማነው ቢባል-ደቡብ አፍሪካዊ የነጻት ታጋይ ነው የማይል የለም። ስለዚህ፣ ማንዴላ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ እ.ኤ.አ ጁላይ 18 ቀን 1918 ዓ.ም ከቀኑ 8 ሰዓት ከ54 ደቂቃ  ላይ መወለዱ ምን ተጽእኖ አሳድሮበታል? እንዲሁም፣ ሚያዝያ 30 ቀን 1947 ዓ.ም ዓድዋ ላይ የተወለዱት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በዚህ ቀንና ዓመተ ምህረት መወለዳቸው ለስብእናቸው ምን አስተዋጽኦ ነበረው? እነዚህ የሁለቱ ታላላቅ ሰዎች ትንታኔ ኮከብ፣ በስፋትና በጥልቀት ታይቷል።
ክፍል አራት፡ የዘፈን ምርጫ ለኮከቦች እና የኮከቦች ዝማሬ
እስኪ፣ ለእያንዳንዱ ኮከብ ከተመረጡት ዜማዎች መካከል፣ ለናሙና ያህል የተወሰኑትን እንይ፤
ለኤሪስ- የፍቅር ጦርነት አለ ብትሉኝ፤ የመጀመሪያዋ ዘማች እኔ ነኝ (ብዙነሽ በቀለ)፣ ለቶረስ- ያዋከቡት ነገር (ጥላሁን ገሠሠ፣ ለጄሚናይ- ድንገት ሳላስበው (ብዙነሽ በቀለ)።
ከኮከቦች ብልጭታ ናሙና፡ ካፔ ለእርጋታ፣ አኳሪየስ  ላፈርሳታ፣ ፓይሰስ  ለይሉኝታ።
ከኮከቦችና መርሀቸው ናሙና፡ ሊዮ አደርገዋለሁ  I will፣  ቪርጐ  እተነትናለሁ  I analyze፣ ሊብራ   አመዛዝናለሁ  I balance
ኮከቦችና ሚንስቴር መስሪያቤቶች፣ የኮከቦች ገደኛ ቁጥር፣ ኮከቦችና የህክምና ዘርፎች እንዲሁም፣ ኮከቦቹን ሊወክል የሚችል አንድ አንድ ቃል፣ በዜማዊ ቃና ተመርጦ ቀርቧል።
በድኅረ ቃል
አልበርት ፓይክ MORALS and DOGMA በተባለው መጽሐፉ ከዘገበውና ጆን ጃክሰን ደግሞ Ethiopia and the Origin of Civilization በሚለው ጽሑፉ ስለ ኢትዮጵያ የአስትሮሎጂ ጥበብ ጀማሪነት ያቀረቡት ማስረጃ፣ በጣም አስደናቂና ለካንስ እኛ የብዙ ነገር ጀማሪዎች ነን የምንባለው ያለ ነገር አይደለም ያስብላል።
በዚያው ያልገፋንበትና ዛሬ ከእኛ እኩል ከነበሩት ከነ ቻይና፣ ኮሪያ እና ጃፓን አንሰን ያለነው ለምንድነው? የአስትሮሎጂ እውቀት ጀማሪ መሆናችንና አሁን ደግሞ ስለ አስትሮሎጂ ከፈረንጆቹ ለማወቅ የምንተጋው ለምንድነው? ሀገር በቀል የሆነው እውቀት እንዴት ባህር ተሻግሮ ሊሄድ ቻለ? በአስትሮሎጂ ሳይንስ እውቀት ያደጉት አገሮች ተጠቅመዋል ወይ? እኛስ ምን ቀረብን ? እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ያጭርብናል።
አስትሮሎጂካዊ የምስጋና አጻጻፍ ዘዴ
ከአሁን በፊት ለተለያየ አላማ ባነበብኳቸው የአማርኛም ሆነ የእንግሊዝኛ መጻሕፍት ውስጥ፣ ምስጋና በተለያየ መልክ ሲጻፍ አይቻለሁ። ሆኖም የፍካሬ ኢትዮጵያን ምስጋና የመሰለ እስካሆን አላየሁም። አንድ ዘና የሚያደርግ አንቀጽ ላሳያችሁ -ገጽ 402፡ለመጽሐፉ  ምርቃት  አክብረውኝ  የተገኙልኝን  ሁሉ ከልብ ማመስገን እወዳለሁ፡፡ በፍጥነት ለማስታወስ የቻልኳውን ስሞች ብቻ እጠቅሳለሁ፡፡
ፕሮፌሰር ባየ ይማም (ካፕሪኮርን)፣ ዶክተር ፈቃደ አዘዘ (ካንሰር)፣ ዶክተር ታከለ ታደሰ (ስኮርፒዮ)፣ አቶ ተስፋየ ገብረ ማርያም (ጄሚናይ)፣ ዶክተር ሙሉጌታ ሥዩም፣ እሸቱ ጥሩነህ (ፓይሰስ) ፣ አበረ አዳሙ (ስኮርፒዮ)፣ ታደለ ገድሌ (ቶረስ)፣ ሊቀ ሕሩያን ተግባሩ አዳነ (ካፕሪኮርን)፣ ጥበቡ በለጠ (ኤሪስ)፣ ምህረት (የሪፖርተርዋ)፣ ተስፋዬ መሰለ (ካፔ)፣ ዮሐንስ አስፋው (አኳሪየስ)፣ ጌታሁን መሰለ (ሳጅ)፣ ሞገስ ገብረማርም (ስኮርፒዮ)፣ አራጌ ይመር (ፓይሰስ)፣ ሙባረክ ኑሩ (ሳጅ)፣ ዳንኤል (ቶረስ) እና ባለቤቱ (ሳጅ) ፣ ፍስሐ ስሜ (ካፔ)፣ ማርሸት ጐሳዬ (ፓይሰስ)፣ አባይ ጐሳዬ (ካንሰር)፣ ሚሊዮን ገብረመድኅን (ካፔ)፣ ምኞቴ አሰፋ (ካፔ)፣ ትእግስት ደምሌ (ፓይሰስ)፣ ሐመልማል ጌታቸው (ቶረስ)፣ አደይ (ስኮርፒዮ)፣ ሙሉነሽ ሐይለሥላሴ (ካንሰር)፣ ዮርዳኖስ ሽፈራው (ኤሪስ)፣ ንጉሴ ፍስሐ (ቶረስ)፣ አሳምነው (ቪርጐ)፣ የሉሊት (አኳሪየስ) ባለቤት ጐበና (ቪርጐ)፣ መለሰ (ሊዮ)፣ ታደሰ ኃይሉ (ሊዮ)፣ አበበ (አኳሪየስ)፣ የሙሴ (ሳጅ) ህይወት (ቪርጐ)፣ ቤዛ ሙሉጌታ (ኤሪስ)፣ ዮናስ (ሊዮ)፣ ያሬድ እንደሻው፣ ሳምራዊት በቀለ (ካፔ)፣ ………።
አጠቃላይ የመጽሐፉ አወቃቀር ሲታይ፣ አማካይ አንባቢ በቀላሉ እንዲረዳው ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ፍካሬ ኢትዮጵያ፣ በይዘቱ መለስተኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ቢባል የማያንስበት፣ በመጠኑ አንጀት አርስ፣ በአጻጻፉ ደግሞ አካዳሚያዊ ደረጃውን የጠበቀ፣ በምሁራዊ ሃላፊነትና በብርቱ ጥንቃቄ የተዘጋጀ፣ ባዮግራፊክ የአጻጻፍ ስልትን የተከተለ ድንቅ መጽሐፍ ነው። እየተዝናናችሁ ብዙ ቁምነገር ታተርፉበታላችሁ።

Read 18091 times