Saturday, 15 November 2014 11:20

“...ሶስት...መበደር ... የማንችልባቸው ድህነቶች...”

Written by 
Rate this item
(3 votes)

አስገድዶ መድፈር የፍቅር መግለጫ ይሆናልን?
ወንዶች ሴቶችን ወይንም ሴቶች ወንዶችን አስገድደው ሲደፍሩ ምክንያታቸው ምንድነው?
ከላይ ለተጠቀሱት ጥያቄዎች ባለሙያዎች የሚሰጡት ምላሽ፡-
አስገድዶ መድፈር የፍቅር መግለጫ አይደለም፡፡ ሰዎች በሚፋቀሩበት ጊዜ አንዱ ለአንዱ ከማሰብ ውጪ አካልንና ስነልቡናን የሚጎዳ ነገር በፍጹም አይፈጽሙም፡፡
ወንዶች ሴቶችን ወይንም ሴቶች ወንዶችን አስገድደው የሚደፍሩበት ምክንያት ኃይልን ለማሳየት፣ በተለያዩ ምክንያቶች በተለይም ተገዶ መደፈር እና ተመሳሳይ ጉዳት የደረሰባቸው ከሆኑም እንደ ብቀላ በመሳሰለው ምክንያት ነው፡፡
በዚህ እትም ለንባብ ያቀረብነው በአዳማ ከተማ በአንድ ወንድ ልጅ ላይ የደረሰ ተገዶ መደፈርን መነሻ ያደረገ ነው፡፡ ዶ/ር ዳዊት ደሳለኝ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና አቶ መኮንን በለጠ የስነልቡና ባለሙያ የሰጡትን ሐሳብም እናስነብባችሁዋለን፡፡
የልጁ ምስክርነት የሚከተለው ነው፡፡
“...ሰውየው አብሮኝ ለነበረው ሰው እንዲህ አለው፡፡ ...ያንን ጥቁር ልጅ ሌሊት አስር ሰአት ላይ ስራ ስለአለኝ ለዛ ጉዳይ ስለምፈልገው ጥራልኝ... አለው፡፡ እኔም ላነጋግረው ስወጣ አስቀድሞ እጄን ነበር የያዘኝ፡፡ ጊዜው እኮ መሽቶአል ስለው ...ግድየለም... ዋጋ እንነጋገራለን...በለሊትም ሰው ከምንቀሰቅስ ከእኔ ጋር ብታድር ይሻልሀል አለኝ፡፡ እኔም ግድ የለም ዋጋ ንገረኝና እመለሳለሁ ብዬ ተከተልኩት፡፡ ከዚያ በሁዋላ እቤቱ አስገብቶ በቃ...ልብስህን አውልቅ...ተኛ...የሚል ትእዛዝ ነው የሰጠኝ፡፡ በቃ... ስለፈራሁኝ ብቻ ልብሴን አውልቄ ተኛሁ...”
በአዳማ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ቢሮአቸው የሚገኘው የስነልቡና ባለሙያው አቶ መኮንን በለጠ የልጁን ሁኔታ እንደሚከተለው አብራርተዋል፡፡
“...የዚህ ልጅ ታሪክ... እድሜው 18 አመት ሲሆን ተወልዶ ያደገው ባሌ ሮቤ አካባቢ ነው፡፡ የዚህ ልጅ ወላጅ አባት በበሽታ ምክንያት በመሞቱ ምክንያት እናትየው ካገባችው ሰው ...ማለትም ከእንጀራ አባቱ ጋር መግባባት ስላቃተው ...ማለትም ከእንጀራ አባቱ ለተወለዱ ልጆች የሚደረገው እንክብካቤ እና ቤተሰቡ ለእርሱ የሚሰጠው ግምት ከፍተኛ ልዩነት ስለነበረው በበጎ ፍቃድ አሳዳጊዎች ምክንያት ወደ አዳማ መጥቶአል፡፡ ይህ ልጅ ወደ አዳማ ከመጣ ገና አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የወንድ ለወንድ አስገድዶ መድፈር ሰለባ ሆኖአል፡፡ አስገድዶ የደፈረው ሰው የልጁን ታሪክ በማጥናት እና በማባበል ...እኔ ሆቴል አለኝ... ስራ አስገባሀለሁ... በማለት ሊያግባባው ሞክሮአል፡፡ ከዚያም ባገኘው እለት አስገድዶ ሲደፍረው ልጁ የነበረውን ጉልበት ተጠቅሞ በላዩ ላይ የተቀዳደደ ልብሱን በእጁ ይዞ ... አምልጦ ...ማመን በሚያቅት ሁኔታ ነበር ወደነበረበት የሄደው...”
ወደተጎጂው ስንመለስ የሰውየውን አባባል እንደሚከተለው ይገልጸዋል፡፡
“...እኔ እኮ ወድጄህ ነው፡፡ አፈቅርሀለሁ፡፡ ገና ሳይህ ነው ልቤ የተሸበረው... ወዘተ ሲለኝ ...እኔ እኮ ሴት አይደለሁም፡፡ ለምን ታፈቅረኛለህ... ብዬ ገፍትሬው ነው ያመለጥኩት፡፡”
ዶ/ር ዳዊት ደሳለኝ እንደሚሉት፡-
“...አስገድዶ መድፈር ብዙውን ጊዜ የሚታወቀው ወንድ ሴት ልጅ ላይ በሚያደርሰው ቢሆንም በተለያዩ ጊዜያት እንደሚስተዋለው ግን ወንድ ወንድን እንዲሁም ሴት ወንድን የሚደፍሩበት አጋጣሚ አለ፡፡”
ወንድ ለወንድ አስገድዶ መድፈር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ መሆኑን የሚገልጹት አቶ መኮንን ቤተሰብ ይህ ነገር ሲፈጸም ቅድሚያ የሚሰጡት ሁኔታውን ለማድበስበስ እና ለመካድ እንጂ ልጆቹ የስነልቡና ድጋፍ ወይንም ፍትህ፣ ሕክምና እንዲያገኙ አይደለም፡፡ ይህ ብዙዎች የሚያደርጉት ሙከራ ሲሆን አንዳንድ ወላጆች፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች ግን በፍጥነት እርምጃ የሚወስዱ መሆኑ የሚያስመሰግናቸው ነው ብለዋል፡፡  
ዶ/ር ዳዊት ደሳለኝ እንደሚሉት፡-
“...ብዙ ጊዜ ሬፕ (አስገድዶ መድፈር) የሚያደርጉ ሰዎች ከተመሳሳይ ጾታም ይሁን ከተቃራኒ ጾታ ባጠቃላይም ከሰዎች ጋር ጥሩ አይነት ግንኙነት መፍጠር የማይችሉ ናቸው፡፡ የእነዚህ ሰዎች ምክንያትም ከአስተዳደግ ወይንም ከተፈጥሮ ሊሆን ይችላል፡፡ ሰዎች ከሰዎች ጋር     ጥሩ የሆነ መግባባትና ግንኙነት መፍጠር የሚያቅታቸው ከሆነ እንደዚህ ያለውን (አስገድዶ መድፈር) የመሳሰለውን ወንጀል እንዲፈጽሙ ያነሳሳቸዋል፡፡”
ተገዶ መደፈር የደረሰበት ልጅ እንደገለጸው፡-
“...ድርጊቱን ፈጻሚው ሰው በህግ እንዲጠየቅ በሚደረግበት ጊዜ... እኔ እነዚህን ሰዎች ከየት እንደመጡ አላውቅም፡፡ እንደዚህ አይነት ድርጊትም አልፈጸምኩም፡፡ ልጁንም አልጠራሁትም ...እንዲያውም አላገኘሁትም በማለት ነበር የካደው..” ብሎአል፡፡
አቶ መኮንን እንደሚገልጹትም፡-
“...ልጁ የደረሰበት ጉዳት ከፍ ያለ ስለነበር በጊዜው ሁሉንም አገልግሎት በአንድ ቦታ በሚያገኝበት በዚህ ስፍራ ሲመጣ ባለሙያዎች በህግ አንጻርም ሆነ በህክምናው እንዲሁም በስነልቡናው ተገቢውን አገልግሎት በፍጥነት እንዲያገኝ ጥረት አድርገዋል፡፡ አስገድዶ ደፋሪው ምንም እንኩዋን ለመካድ ቢሞክርም በወቅቱ ልጁ እራቁቱን ...የተቀዳደደውን ልብሱን በእጁ ይዞ መምጣቱ እና ሌሎች የተለያዩ መረጃዎች በመኖራቸው     እውነቱን ለማግኘት አስቸጋሪ አልነበረም፡፡”
አቶ መኮንን የህግ ባለሙያዎችን እና የህብረተሰቡን ትብብር በሚመለከትም፡-
“...ፖሊሶች ለሙያቸው ስነምግባር ተገዢ መሆን እንዳለባቸው ቢያምኑም በጣም የሚያሳዝነው ግን ...አንዳንድ ፖሊሶች ለወንጀለኛው የማገዝ ነገር ይታይባቸው ነበር፡፡ ተጎጂው ባለበት ሌላም ታዛቢ በሚገኝበት ካለምንም ፍርሀት ...እኔ ዋስ ሆኜ አስወጣዋለሁ... ምንም ችግር የለም ሲሉ የተስተዋሉ ነበሩ፡፡ አስገድዶ ደፋሪው በዚህ ድርጊቱ ቀደም ሲልም የሚታማ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሕግ ሳይቀርብ የቆየ መሆኑን እያወቁ እንደዚህ ያለ ንግግር በተናገሩ ላይ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ቢያዝኑም በሌላ በኩል ደግሞ  ለሙያቸው ተገዢ የሆኑ ጠንካራ የፖሊስ አባላት አቃቤ ሕጎች እና ዳኞች በመኖራቸው ጉዳዩን በጥንካሬ ይዘው ከዳር በማድረሳቸው ጥፋተኛው በስምንት አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ አስችለውታል፡፡ ምንም እንኩዋን ጉዳት የሚያደርሱ ባይታጡም ለትክክለኛው ስራቸው የቆሙትን በዚሁ አጋጣሚ ማመስገን እወዳለሁ...” ብለዋል፡፡
ሌላው አነጋጋሪው ነገር ሽምግልና ነው፡፡
ተገዶ የተደፈረው ልጅ እንደገለጸው “...የእኔ ወገኖች በሽምግልና ሲጠየቁ አይሆንም... አንቀበልም በማለት አሻፈረኝ ብለዋል፡፡ ምክንያቱም ይህ ጥፋት ተደግሞ በሌላ ሰው ሊደርስ እንደማይገባ ማስተማሪያ እና ደፋሪው ሰው በህግ መጠየቁ ለተደፋሪውም የሞራል ካሳ ስለሆነ... የሚል ነበር፡፡ ስለዚህም ገንዘብ እንክፈል... ሌላም ካሳ እንስጥ ሲባል... መልሳቸው አንቀበልም የሚል ስለነበር ወደህግ ቀርቦ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ ሆኖአል፡፡” አቶ መኮንን በዚህ ላይ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
“...ሰው ለሰው መድሀኒቱ ነው፡፡ መድሀኒት የሚሆነው ግን ተገቢውንና በጎውን ነገር ሲያደርግ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ካላደረገ ግን ሰው ለሰው መድሀኒት መሆኑ ቀርቶ መርዝ ይሆናል፡፡ ሽምግልና በሰው ልጆች ዘንድ የታወቀ በጎ ባህርይ ቢሆንም አንዳድ ጊዜ የሚውልበት ቦታ ግን ጎጂ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ወንዶችም ሆኑ ሴት ልጆች ተገደው ሲደፈሩ አስገድዶ ደፋሪው በህግ እንዳይጠየቅ ገንዘብ እንክፈል... የሞራል ካሳ እንስጥ የሚባለው ነገር ምክንያቱ ከጥቅም ጋር የተሳሰረ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ለማንኛውም... ይህ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች የስነልቡና፣ የሞራል፣ የአካል ደህንነታቸው የሚጠበቀው ጉዳት አድራሹ በሚከፍለው ገንዘብ ሳይሆን በህግ ተገቢውን ፍትሕ ሲያገኙ ነው፡፡     እንደ አቶ መኮንን አባባል ሰው ሶስት ድህነቶችን ማስወገድ ይጠበቅበታል፡፡  
ሰው መንፈሳዊ ድህነትን ማሸነፍ ይገባዋል፡፡ ሁሉም ሰው እንደየእምነቱ ፈሪሀ እግዚአብሄር ሊያድርበት ይገባል፡፡ ልጆች ተገደው መደፈር ሲደርስባቸው ለጥፋት አድራሹ ወገንተኛ ሆኖ መቆምና ስለልጆቹ የወደፊት ሕይወት አለማሰብ ተገቢ አይደለም፡፡
ሰው ማህበራዊ ድህነትንም ማሸነፍ ይጠበቅበታል፡፡ በማንኛውም ጊዜ ሰው ለገንዘብና ለጥቅም ሳይሆን  ለእውነት ተገዢ መሆን አለበት፡፡
ሰው በሶስተኛ ደረጃ ማሸነፍ ያለበት ድህነት የአእምሮ ድህነትን ነው፡፡ ሁሉም ሰው የተቻለውን ያህል እውቀት ሊኖረው ይገባል፡፡ ሕይወት እራስዋ ትምህርት ቤት እንደመሆንዋ ማንኛውም ሰው እውቀት እንዲኖረው እራሱን ካዘጋጀ እውቀት ይኖረዋል፡፡
ስለዚህ ... እነዚህ ሶስቱ መበደር የማንችልባቸው ድህነቶች ሲሆኑ ተበድረን ልናሸንፍ የምንችለውን የኢኮኖሚ ድህነትን ለማስወገድ በሚደረገው ፍላጎት ከአጥፊዎች ጋር በመተባበር ወይንም ወንጀልን ለመደበቅ ሙከራ ማድረግ ያስጠይቃል ...ሰው... ሽምግልናን ከአግባብ ውጪ ለመተግበር መሞከር የለበትም፡፡

Read 6581 times