Saturday, 15 November 2014 11:18

ገጣሚ ሃይሉ ገ/ዮሃንስ (ጎሞራው) በ79 ዓመቱ አረፈ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ረጅም አመታት በውጭ አገራት ያሳለፈው ገጣሚ ሃይሉ ገ/ዮሃንስ (ጎሞራው)፤ ባደረበት ህመም በሚኖርባት ስዊድን በሚገኝ ሆስፒታል ህክምና ሲከታተል ቆይቶ፣ ባለፈው ማክሰኞ በተወለደ በ79 አመቱ ከዚህ አለም በሞት ተለየ፡፡እ.ኤ.አ በ1935 በአዲስ አበባ የተወለደው ሃይሉ፤ የቤተክህነት ትምህርት እየተከታተለ ያደገ ሲሆን በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ከተማረ በኋላ፣ በቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የስነ መለኮት ትምህርት ተከታትሏል፡፡
በመቀጠልም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት ተቋም ገብቶ የተማረው ገሞራው፤ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው በግዕዝ፣ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተለያዩ የስነጽሁፍ ስራዎችን በማቅረብ ታዋቂነትን አትርፏል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ይካሄድ በነበረ የግጥም ውድድር ላይ ባሸነፈበት “በረከተ መርገም” የተሰኘ ግጥሙም  ይታወቃል፡፡ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ በስፋት ይካፈል የነበረው ገጣሚው፤ ከዚሁ ጋር በተያያዘም ከዩኒቨርሲቲው ተባርሯል፡፡
በ1957 ዓ.ም የጻፈው “በረከተ መርገም” የተሰኘ ግጥሙ በ1966 ዓ.ም የታተመለት ሲሆን በ1980 ዓ.ም በስዊድን በድጋሚ ታትሞለታል፡፡ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ወቅት ለንባብ ባበቃው “አንድነት” የሚል አነስተኛ መጽሃፍ ሳቢያ ለእስር የተዳረገው ሃይሉ፣ ከእስር ከተፈታ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ በቴክኒክና በመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆች በመምህርነት አገልግሏል፡፡
ወደ ቻይና በማምራትም በቤጂንግ ዩኒቨርሲቲ የቻይናን ስነጽሁፍ ያጠና ሲሆን የቻይንኛ-አማርኛ መዝገበ ቃላትና የቻይንኛ-እንግሊዝኛ የሃረጋት መጽሃፍ አዘጋጅቷል፡፡ ወደ ኖርዌይ ሄዶ የፖለቲካ ጥገኝነት ካገኘ በኋላ ለጥቂት ጊዜያት ቆይቶ ወደ ስዊድን በመጓዝ ኑሮውን በስቶክሆልም አድርጎ ቆይቷል፡፡

Read 1393 times