Saturday, 08 November 2014 11:39

ከእንቅልፌ በፊት የምናገረው እውነት…

Written by  አሸናፊ መለሠ ashusheger@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

ምናባዊ ወግ

ያቺ ምስኪን ነርስ ወደ እኔ ስትመጣ ተመለከትኩ፡፡ ምስኪን … አሁንም እኔን ለመጥራት የትኛውን ማዕረጌን ማስቀደም እንዳለባት ግራ እንደገባት ታስታውቃለች፡፡ ፈረንጆቹ በለገሱኝ “የዓለም ሎሬት” ትጥራኝ ወይስ የሃገሬ ዩኒቨርሲቲዎች በሰጡኝ የክብር ዶክትሬት? ነው ወይስ ያ ዝነኛ ጋዜጠኛ እኔን ለመጥራት በሚጠቀምበት “ታላቁ” የሚል ቅፅል ትጠቀም? የቸገረ ነገር!
አሁን በዚህ ዓለም ላይ የሚያስፈልገኝን የሚያውቅ ይሄ ሆስፒታል ብቻ ይመስለኛል፡፡ የምለውን የሚረዳኝ ሳይሆን የምፈልገውን የሚያውቅ ነው ያልኩት፡፡ ይኸው በዚህች ግራ በተጋባችና ፍርሃት በሚያርዳት ነርስ እጅ ላይ ለኔ የሚሆን የእንቅልፍ ክኒን አለ፡፡
መተኛት እፈልጋለሁ፤ ያለእረፍት፡፡ ይሄ መድኀኒት ደግሞ ያንን ይሰጠኛል፡፡
ግራ የገባው ፊትዋን፣ በፍርሃት የሚንቀጠቀጥ ጉንጯን አይቼ አዘንኩላት፡፡
“እንዲሁ ያለ ማዕረግ ‹በላይ› ብለሽ ልትጠሪኝ‘ኮ ትችያለሽ፤ ማክበር ካማረሽ ደግሞ ‹ጋሽ በላይ› በይኝ” አልኳት፤ በእጇ ያለውን ክኒንና ውሃ እየተቀበልኳት፡፡
በስጋት ሳቅ አለች፡፡
መድኀኒትና ውሃውን ተቀብዬ በፍጥነት ወደ ሆዴ ሰደድኳቸው፡፡
ከደቂቃዎች በኋላ የሚመጣውን እንቅልፍ መናፈቅ ጀመርኩ፡፡ ግን ከመተኛቴ በፊት ለምን እዚህ እንደተገኘሁ አላጫውታችሁም? ማን ያውቃል፣ ከዘመናት በኋላ ከናንተ መሃል አንዱ የምናገረውን ያምን ይሆናል….
ሰዓሊ ነበርኩ፡፡ በስዕሉ ከሚገኘው ገንዘብ ሳይሆን ከራሱ ከጥበቡ ፍቅር የያዘኝ ምስኪን ሰዓሊ፡፡ በስዕል ስቱዲዮዬ ውስጥ ተሸጉጬ በመስመሮች ተዓምራዊ ቅንብር ውስጥ ታላቅ ውበትን ለመከሰት የምዳክር የጥበብ አምላኪም ነበርኩ፡፡ እንደ እድል ሆኖ ግን የዝናውን ማማ ለመቆናጠጥ የሚያስችል ታላቅ ስራን ምናቤ ለመከሰት ባለመቻሉ ተራነትን ማዕረጌ አድርጌ እኖር ነበር፡፡
አንድ ቀን ግን የቀለም ቋቶቼ ከተቀመጡበት ድንገት ተንሸራተው በስሌትና በእውቀት ልነድፍበት ብዬ በወጠርኩት ሸራ ላይ ፈስሰው ተቀየጡ፡፡ እንደ ድፋት መጠን፣ እንደ ቅድሚያ ክትያ፣ እንደ ንጥረት ፍንጥርጥሮሻቸው ቀለማቱ ተገማሽረው በቀለም ቋቶቹ እየተዳጡ ባለዳገትና ቁልቁለት፣ ባለከፍታና ዝቅታ ዝብርቅርቅነት ፈጠሩ፡፡ ይህን ድንገት ወለድ፣ ከስርዓት፣ ከእውቀትና ከስሌት የተፋታ የቀለማት መገማሸር ስመለከት፣ እስከ ዛሬ ሰርቻቸው ከማውቃቸው ስዕሎች ሁሉ የላቀ ውበት፣ የላቀ ጥልቀትና የላቀ ምጥቀት እንዳለው አስተዋልኩ፡፡
ይህንን ድንቅ የተዓምር መድረክ ስዕል ብሎ መጥራት ከበደኝ፡፡ ይህንን አስማተኛ ጥበብ የኔ ነው ለማለት ከቶ ድፍረት አጣሁ፡፡ ለዚህ ታላቅ “ጉድ” ርዕስ የሚሆን ውብ ቃል መቼም እንደማላገኝ ተገነዘብኩ፡፡
ይህን ከወጠርኩት ሸራም ጭምር ተርፎ የሚፈስ ታላቅ ጥበብ፣ በምልዐት የማደንቅበት ጉልበት በማጣቴ፣ ለቀናት በዚያ የመሳያ ክፍሌ እየተመላለስኩ በጥንቃቄና በስስት ያንን ድንቅ ተዓምር ስኮመኩም ከረምኩ፡፡
ከሳምንታት በኋላ ሸራውን ከወደቀበት ወለልና ተርፎ ከተርከፈከፈው የውበት አዝመራ መሃል አንስቼ ግድግዳው ላይ ሰቀልኩት፡፡
ከወራት በኋላ ያንን አስማተኛ ሸራ ያዩ ሁሉ ስለ ታላቅ ሰዓሊነቴ በሰፊው ያወሩ ጀመር፡፡ ስራውን እኔ እንዳላቀናበርኩት፣ ህብሩን እኔ እንዳልሸመንኩት፣ ውበቱ ከኔ ምናብ እንዳልመነጨ በተናገርኩ ቁጥር ጩኸቴን የሰሙ ታላላቅ የሃገሪቱ ሊቃውንት ንግግሬን ከየእውቀት መስካቸው አንፃር መተንተን ጀመሩ፡፡ የስነልቡና ምሁራኑ ስዕሉን የየድብቁ የአዕምሮ ክፍል (subconscious) ታላቅ ብቃት ማሳያ ነው” ሲሉ፣ የስዕል ጠቢባኑ ደግሞ “በላይዝም” የተባለ፣ ‹ድብቁን የአዕምሮ ክፍል በመግራትና ለጥበብ በማዋል የሚፈጠር የጥበብ አይነት› በሚል የሚብራራና ስሜን ተተግኖ የተሰየመ አዲስ አይነት የጥበብ ዘውግ መውለዴን አወጁበት፡፡ የሂሳብና የፊዚክስ ቀመር አዋቂዎች ከስበት ህግ ጋር የሚፋተግ፣ ከእንቅስቃሴና ከቁስ አመክንዮ ጋር ደመኛ የሆነ አዲስ የፊዚክስ ቀመር  ስለማብሰሬ ተግተው ጮሁ፡፡ የፍልስፍና ሊቃውንትም የኔ “ስዕል” የሰበከውን፣ ከህልማዊነት ጋር ድንበር የሚጋራ፣ ከእውናዊነት ጋርም ያልተፋታ የፍልስፍና ዘውግ፣ ማን እንበለው በሚለው ጉዳይ በየሚዲያው ላይ ተነታረኩበት …
ያን ጊዜ ፈፅሞ የድሮውን ማንነቴን መሆን አቃተኝ፡፡ ያለልኬ የተሰፋልኝን አዲሱን ሰብዕና መሸከም ካልቻልኩ እብደት ቀጣዩ እጣዬ መሆኑ ሲገባኝ፣ እነሆ ስለ ታላቁ ስዕሌ በኩራት ማውራት ጀመርኩ፡፡ በብሩሽ ሳይሆን በቀለማት ፍንጥርጣሪ መሳልን ምርጫዬ አደረግኩ፤ በመስመር ሳይሆን በፍሰት ማቅለምን ወደድኩ፤ በስሌት ሳይሆን በዕድል ማዋቀርን ተጋሁ፤ ከመሳሌ በፊት ምንን እንዴት ልሳል? በሚለው ሳይሆን “ከሳልኩ” በኋላ በስዕሉ ፍቺ መፈለግን ለመድኩ …
ይህን የጥበብ ፈለጌን የተከተሉ አያሌ ደራሲያን በአዳዲስ ቃላት የታጨቁ፣ ከሰዋሰው ስርዐት የተፋቱና ስለ ምንም የማያወሩ ልቦለዶችን አሳትመው አንቱ ተባሉበት፡፡ የፊልም ባለሙያዎች ከታሪክ የተፋታ፣ ከምስል የጎሪጥ የሚተያይ፣ ከድምፅ ጋር ፀብ የፈጠረ ስራቸውን እነሆ ብለው የአመቱን ታላቅ የባለሙያነት ካባ ያለተቀናቃኝ ተጎናፀፉ፡፡ የሃገር ባህል ተወዛዋዦች ከመፈራገጥ ባልተለየው ንቅናቄያቸው፣ ከእብደት በሚያምታታው ውዝዋዜያቸው፣ ከአንድነት በተፋታው ህብረታቸው አድናቂዎቻቸውን ጉድ አስባሉበት …
የሃገሬ ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክትሬት ከመስጠት አልፈው አዲስ የክብር ደረጃ ሊፈጥሩልኝ ተንደፋደፉ፡፡ ለአንድ ሚዲያ የምሰጠው ቃለ ምልልስ በ50 ሚዲያዎች እየተተነተነ የሚፍታታ፣ እየተሸነታተረ የሚበየን፣ እየተሰነጣጠቀ የሚያፈላስፍ ጥቅል የጥበብ ማኒፌስቶ ሆነ …..
ከጥበብ አድናቂ እስከ ሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ከተትረፈረፈው ሃብታም እስከ በቃው ጠቢብ ድረስ እኔን ለማግኘት ይራኮት ጀመር፡፡
አንድ ቀን እግሮቼን ለማፍታታት ጭር ባለው ጎዳና ላይ ስጓዝ፣ አንድ እድሜው በግምት 11 ዓመት የሚሆነው ልጅ ገና ሲመለከተኝ እንደ መባነን አለና፤
“አንተ… ጃን የዓለም ሎሬት የክብር ዶክተር በላይ ሰለሞን ነህ አይደል?” አለኝ፡፡
“አዎን” አልኩት ፈገግ ብዬ
“ስላንተ ባለፈው ተምረናል…” አለና ትንሽ አሰብ አድርጎ፤ “እኔም ሳድግ አንተን መተካት ነው የምፈልገው” አለኝ፡፡
ይህ ንግግሩ ሰላሜን አሳጣኝ፡፡ ይህ የኔ እብደታዊነት ቀጣዩን ትውልድም ሊበክለው መሆኑን ሳስብ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለብኝ ተሰማኝ፡፡
ለሳምንታት በመሳያ ክፍሌ ውስጥ ተሸጉጬ ከረምኩ፡፡ በዚህ ክራሞቴ ውስጥም ይህንን የሃሳብ ምስቅልቅሎሼን ማሳየት የሚችል አንድ ታስቦና ታቅዶ የተሰራ፤ የኔን የማሰብ ጥግ የሚያሳይ አንድ ታላቅ ስዕል ለመሳል ቻልኩ፡፡
ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም አንድ ታላቅ መድረክ ለማዘጋጀት ደፋ ቀና ማለት ጀመርኩ፡፡ ሽፋን በሰጠሁበት የስዕሎቼ ኤግዚቢሽን ሰበብ በርካታ መገናኛ ብዙሃን፣ አያሌ ታላላቅ ሊቃውንት፣ በርካታ ታላላቅ ሰዎችና ባለስልጣናት እንዲሁም የጥበብ አድናቂዎች በስፍራው እንደሚገኙ ለማወቅ ቻልኩ፡፡ ሁሉም አዲሱን ድንቅ ስዕሌን ለማየት ከመጓጓትም አልፈው አንዳንድ ግምታዊ አስተያየቶችንም መስጠት ጀመሩ፡፡
የኤግዚቢሽኑ እለት እንደተባለው ሁሉም በዘመናዊው አዳራሽ ግጥግጥ ብለው ታላቁንና እውነተኛውን ስዕሌን ለማየት በፀጥታ ተዋጡ፡፡ እነሆ ወደ መድረኩ በመውጣት ከኔ ምናብ፣ ከኔ እውቀትና ከኔ የጣት ተዓምር የፈለቀውን እውነተኛ ስዕሌን ለእንግዶቼ አቀረብኩ፡፡
ምን ተፈጠረ?
ሎሬቱ አበደ ተባለ፡፡ ይሄ ታላቅ ሰው ታላቁን እውቀቱን የሚቋቋምበት ጉልበት አጣ፤ በታላቁ እውቀቱ ሸክም አዕምሮው ተደፈጠጠ፤ ለእውቀት ኖሮ በእውቀት ተረታ ተባለ፡፡  ድሮውንስ አንድ ጤናማ ሰው ይህን ያህል እውቀት ይዞ ከዚህ በላይ እንዴት በጤና መኖር ይችላል? ተባለ፡፡
አለመታመሜን፣ ጤንነቴን ለማስረገጥ ስላለፈው የውሸት ህይወቴ በተናዘዝኩ ቁጥር ንግግሬ የአዲሱ የእውቀት ግንፈላ በሽታ ምልክት ሆኖ ይተረጎም ጀመር፡፡ በጤንነቴ በሳልኩት በዚያ ታላቁና እውነተኛው ስዕሌ ላይ ያሉ መስመሮች፣ የበሽታዬን ደረጃ ሳይጠቁሙ አይቀርም ተብለው በመታሰባቸው፣ ያ ስዕል ወደ ሙዚየም ሳይሆን ወደ ላቦራቶሪ ተወሰደ…
እናም የሚሰማኝ እንደሌለ ሳረጋግጥ ከዓለም ሽሽት፣ ለኔ ከሚመጠጥ ከንፈር ሽሽት፣ ለኔ ከተዘጋጁ የሃዘን ፕሮግራሞች ሽሽት፣ ለኔ ከሚደለቅ ደረት ሽሽት… እንቅልፍን የሙጥኝ ማለትን ለመድኩ፡፡፡
እንኳንም እሱን አልወሰዱብኝ ልበል ይሆን?
ተመስገን፤ ይኸው እንቅልፌ መጣ …፡፡   

Read 1850 times