Saturday, 08 November 2014 11:05

ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጦርነት ወዳመሳት የመን እየጎረፉ ነው

Written by  ዩሃንስ ሰ.
Rate this item
(4 votes)

በስድስት ወራት ከ40ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን የመን ገብተዋል
አማፂዎች በጥቂት ወራት ዘመቻ ሰንዓን እና ኤደንን ወርረዋል


               የመን “ታሪከኛ” አገር ናት - በአንድ በኩል ለረዥም ዘመናት የዘለቀ የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት፣... በሌላ በኩል ደግሞ፣ ለበርካታ አመታት አለምን “ግራ ያጋባች ጉደኛ” አገር! እስቲ አስቡት። ከሰሜን አቅጣጫ የጦርነት ዘመቻ ሲያካሂዱ የከረሙ አማፂዎች፣ የመንግስት መቀመጫ የሆነችውን ዋና ከተማ ተቆጣጥረዋል። መንግስት ደግሞ፤ “የአማፂው ቡድን ታጣቂዎች ከተማዋን ለቀው እንዲወጡና የወረሯቸውን ወታደራዊ ካምፖችንና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ይልቀቁልኝ” እያለ አቤቱታ ያሰማል። ሚኒስትሮች ወደ ቢሮአቸው ሲገቡ በአማፂ ታጣቂዎች ይፈተሻሉ። አይገርምም?
“መንግስት አለ ወይም የለም፤ አማፂዎች አሸንፈዋል ወይም አላሸነፉም” ለማለት ያስቸግራል። እውነትም የመን፣ ግራ የምታጋባ አስገራሚ አገር ናት። ምናልባትም፣ “አገሬው ሰላም ነው ወይስ አይደለም”፤ “የሚሰደዱባት ወይም የሚሸሿት አገር ነች” ለማለት ቢቸገሩ ይሆናል ብዙ የኢትዮጵያ ወጣቶች ወደ የመን መጉረፋቸውን ያላቋረጡት። ለነገሩ፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ለባራክ ኦባማም ጭምር፤ የየመንን ጭራና ቀንድ ለመለየት ተስኗቸዋል። የኦባማ ነገር! የአገራቸውን ፖለቲካና ኢኮኖሚ ያመሰቃቀሉት ፕሬዚዳንት ኦባማ፤ በአለማቀፍ ጉዳዮች ደግሞ የአሜሪካ ማፈሪያ ሊሆኑ ምንም አልቀራቸውም ማለት ይቻላል። እንደሳቸው ሃሳብማ፤ አሜሪካ ሁሉንም አገራት እንደእኩያ ብትቆጥርና መሪ ለመሆን ባትሞክር፣ ምድራችን ከዳር እስከ ዳር ሰላምና ደስታ ይሰፍንባት ነበር።

አሜሪካ የሁሉም ጥፋት ተጠያቂ ሳትመስላቸው አትቀርም።
ነገር ግን፣ የኮንጎ የእርስ በርስ ጦርነት ላይ፣ አሜሪካ ጣልቃ ስላልገባች ሰላም አልሰፈነም። ከስድስት በላይ አገራት ጎራ ለይተው በማዝመት ጦርነቱ ተባብሶ 5 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ለእልቂት የተዳርገዋል። ሙዓመር ጋዳፊ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ፣ በሊቢያ ግጭት ላይ አሜሪካ እጇን እንዳታስገባ ኦባማ ትዕዛዝ ከሰጡ በኋላስ ሰላም ሰፈነ? እንዲያውም ባሰበት። በርካታ አክራሪ ድርጅቶች፣ ከደርዘን በላይ የጎሳ ታጣቂ ቡድኖች፣ ወታደራዊ አምባገነንነት ለመመስረት የሚመኙ ብሔረተኞች የሚጫረሱባት አገር ሆናለች። በምርጫ የተዋቀረው ፓርላማ ከዋና ከተማዋ ተባርሮ፣ መኖሪያውና መሰብሰቢያውን፣ የኪራይ መርከብ ላይ አድርጎ ከርሟል - የግብፅ እና የአረብ ኤሜሬትስ በአየር ሃይል ድብደባ ጭምር ወታደራዊ ድጋፍ ቢሰጡትም፣ ፓርላማው አንዲት ደህና ከተማ ለመያዝ እንኳ አልቻለም።

ዘጋርዲያን እንደዘገበው ሱዳንና ኳታር ደግሞ በሌላ ጎራ አክራሪ ቡድኖችን በማስታጠቅ ጦርነቱን ያቀጣጥላሉ።
አሜሪካ ጣልቃ አትገባም ማለት፤ ሌሎች በርካታ አምባገነን መንግስታት ጣልቃ ይገባሉ እንደማለት ሆኗል። ኦባማ ግን፤ በየቦታው ግጭት እየተቀሰቀሰ፣ ከአገር አገር ሲስፋፋ፤ ከሩቁ ሆነው “ተስማሙ፤ ዋናው ነገር መቻቻል ነው” በማለት ሰላም የሚያሰፍኑ ይመስላቸዋል። የእስራኤልና የፍልስጥኤም፣ የሊቢያና የሶሪያ ወይም የኢራቅና የሴንትራል አፍሪካ ጥያቄ ሲቀርብላቸው፤ የዘወትር ምላሻቸው... “ሁሉም ቡድኖች ተቻችለውና ስልጣን መጋራት ነው መፍትሄው” የሚል ስብከት ነው። ለመሆኑ፤ እነዚያ የአሜሪካ ስኬት ጠንካራ መሰረት ለመሆን የበቁ፣ “የግለሰብ ነፃነት፣ የነፃ ገበያና የህግ የበላይነት መርሆች” የት ገቡ? ያለ መርህ በዘፈቀደ መቻቻልኮ አይቻልም። እስቲ አስቡት። የየራሳቸውን ንብረት ይዘው የመጡ ገበያተኞች፤ የንብረት ባለቤትነታቸውን የሚያከብሩ ከሆነ ነው፣ ለግብይት መደራደር የሚችሉት - “ቀንስ፤ ጨምር” በማለት ተቻችለው ምርት የሚለዋወጡት። የንብረት ባለቤትነትን የማያከብርና ለመዝረፍ የሚፈልግ ሰው ሲመጣባቸውስ? አሁንም “ተቻችለው” ይደራደራሉ? “ሩብ ያህል ብቻ ዝረፍ” “አይ፤ ሙሉውን እዘርፋለሁ”፤ “ግማሽ ዘርፌ፣ ግማሽ ልተውልህ” በሚል የጋራ መፍትሄ ይፍጠሩ? በትክክለኛ መርህ ላይ ያልተመሰረተ ድርድርና መቻቻል፤ የሚያዛልቅ መፍትሄ አያስገኝም፤ መቋጫ የሌለው ግጭትን እንጂ። በአጭሩ፤ የባራክ ኦባማ ቀሽም አስተሳሰብ፣ ከአለም እውነታ ጋር ተጋጭቶ ለመፍረክረክ ጊዜ አልፈጀበትም ማለት ይቻላል። ታዲያ፤ ሰሞኑን በተካሄደ ምርጫ የባራክ ኦባማ ፓርቲ፣ በሰፊ ልዩነት በሪፐብሊካን ፓርቲ መሸነፉ ይገርማል?
እንዲያም ሆኖ፤ ባራክ ኦባማ የተሳሳተ አስተሳሰባቸውን ከማስተካከል ይልቅ፤ “ስኬቶችንም አስመዝግቤያለሁ” በማለት መከራከርን ይመርጣሉ። ስኬት ብለው የሚጠቅሱት ማንን መሰላችሁ? የመንን! ከሊቢያና ከግብፅ ጀምሮ፣ ማሊና ሴንትራል አፍሪካን ጨምሮ፣ ኢራቅና ሶሪያ በግጭት ቢታመሱም፤ ኦባማ “የመን፣ ለሁሉም አርአያ ልትሆን የምትችል አገር ናት” በማለት አወጁ። በግንቦት ወር ማለት ነው።
እንዲያው ስታስቡት፣ የመን በአርአያነት የምትሞገስ አገር ናት? የመንግስትና የአክራሪዎች ፋታ በማይሰጥ የአፈና ዘመቻ አገሪቱን አጨልመዋል። ኢኮኖሚዋ በድጎማና በሙስና ተዳክሞ የወጣቶች ስራ አጥነት ተባብሷል። በሰሜን በኩል ኢራን የምትደግፋቸውና በጎሳ የተደራጁ የሺዓ አማፂዎች፤ በደቡብ በኩል በጎሳ የተደራጁ ተገንጣይ አማፂዎች፤ ከመሃል በሳውዲ አረቢያ እና በኳታር የሚደገፉ ተቀናቃኝ አክራሪ ድርጅቶች... ከእነዚህም በተጨማሪ በነውጠኛነቱ የገነነ አልቃይዳ ቅርንጫፍ... በየፊናቸው አገሪቱን ያተራምሳሉ። እህስ? ባለፈው ሚያዚያ ወር እንደታየው የአገሪቱ ጦር ሰራዊት በዘመቻ አንዲት ከተማ ያስለቅቃል፤ የአሜሪካ መንግስት ደግሞ በሰው አልባ የጦር አውሮፕን (ድሮን) አራት አምስት የአልቃይዳ አሸባሪዎችን ይገድላል። ይሄው ነው በኦባማ ያሞገሱትና በአርአያነት የሚጠቀስ የየመን ስኬት። በዚያው ግንቦት ወር፤ ወደ 7ሺ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች፣ በእግር የሶማሊያና የጂቡቲ በረሃዎችን አቋርጠው፤ በተጨናነቁ ጀልባዎች ባህሩን ቀዝፈው የመን ገብተዋል። በሚያዚያ ወርም እንዲሁ 7ሺ ያህል የኢትዮጵያ ስደተኞች የመን ደርሰዋል - የሚሸሿት ሳትሆን የሚሰደዱባት ምርጥ አገር የሆነች ይመስል! በእርግጥ የብዙዎቹ ስደተኞች ተስፋ፣ በየመን በኩል ሳውዲ አረቢያ መግባት ነው።
በሰኔ ወር፣ በሰሜን የመን በኢራን የሚደገፉ የሺዓ እምነት አክራሪዎች፣ “ሁቲ” በሚል የጎሳ ስያሜ ተደራጅተው ፀረመንግስት አመፃቸውን አላቋረጡም። በደቡብም የተገንጣይ ድርጅት ታጣቂዎች አላረፉም። የአልቃይዳ አሸባሪዎች በየከተማውና በየመንገዱ  ቦምብ ከማፈንዳት አልቦዘኑም። በየገጡም ሆነ በየመንደሩ፣ ሰዎች መታገታቸውም የዘወትር ዜና መሆኑ አልቀረም። ነገር ግን፤ በዚያው ወር እንደገና 4500 ገደማ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ የመን ፈልሰዋል።
ኦባማ፤ የየመንን አርአያነት ካበሰሩ በኋላ ሁለት ወር ሳይሞላቸው ነው፤ የአገሪቱ ትርምት የተባባሰው። በሰሜን በኩል የሚዋጉት የሁቲ ታጣቂዎች፣ ተከታታይ ዘመቻ በማካሄድ ሰፊ የአገሪቱን ግዛት የወረሩት በሐምሌ ወር ነው። የመንግስትን ጦር እንዲሁም ተቀናቃኝ የሱኒ አክራሪ ታጣቂዎችን እያሳደዱ፤ ከዋና ከተማዋ ከሰንዓ በ50 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ አርማን የተሰኘች ከተማን እስከመቆጣጠር ደርሰዋል። እንዲያም ሆኖ፣ በዚሁ በሐምሌ ወር፤ 5ሺ ገደማ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በስደት የመን ገብተዋል።
ከአራት አመት በፊት የመንግስት ጦር፣ በሳዑዲ አረቢያ የአየር ሃይል ድጋፍ አማፂዎቹን ለማንበርከክ ቢችልም፤ ሐምሌ ወር ላይ ያጣቸውን አካባቢዎች ለማስመለስ አልቻለም። በነሐሴም ብዙ ሞክሯል - አልተሳካለትም እንጂ። የሁቲ አማፂዎች ይባስኑ በሰንዓ ዙሪያ ከበባ እያጠበቁ የአገሪቱን መንግስት መላወሻ ማሳጣት ጀምረዋል። በየከተማውና በየመንገዱ የአልቃይዳ ፍንዳታዎች ሲጨመርበት አስቡት። በደቡብም፤ ተገንጣይ ታጣቂዎች ጉልበት እያገኙ፣ አገሪቱ እየተብረከረከች ነበር - በነሐሴ ወር። ቢሆንም፤ ከ8ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን፤ በዚያው ወር የየመንን ድንበር አቋርጠው የስደት እንደተመዘጉ የዩኤን መረጃ ያሳያል።
የመን እንዲያ እየታመሰች በአርአያነት ስትጠቀስና ኢትዮጵያውያን ያለማቋረጥ ሲሰደዱባት ያየ ሰው፤ “ይህችስ ጉደኛ አገር ናት” ቢል ይገርማል? ካላመናችሁ፤ ባለፈው መስከረም ወር የተከሰተውን ታሪክ ተመልከቱ። በሺዓ እምነትና በጎሳ ተወላጅነት የተደራጁት አማፂዎች፣ ሰሜን የመንን በመውረር ለወር ያህል በሰንዓ ዙሪያ ከበባ ካካሄዱ በኋላ ነው፤ በመስከረም ሁለተኛው ሳምንት የከባድ መሳሪያ ድብደባ ማካሄድ የጀመሩት።
የድብደባው በሁለት ዋና ዋና ኢላማዎች ላይ ያነጣጠረ ነው - በአንድ የጦር ካምፕ እና በአንድ ዩኒቨርስቲ ላይ! በመገረም፣ “ዩኒቨርስቲ?” ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል። አዎ፤ ዩኒቨርስቲ! ግን፣ ሳይንስንና ቴክኖሎጂን የሚያስተምር አይደለም። እንደ ግብፁ ሙስሊም ብራዘርሁድ ጋር ዝምድና ባለው ፓርቲ የሚተዳደርና፣ በየመን “የሱኒ አክራሪነትን ለማስፋፋት” የሚያገለግል ዩኒቨርስቲ ነው።
ታዲያ፤ ሁቲዎች ዩኒቨርስቲውን የጠሉት፤ “አክራሪነት”ን ስለሚያስፋፋ አይደለም። የሺዓ ሳይሆን የሱኒ አክራሪ ስለሆነ እንጂ! ከአልቃይዳ ጋርም ፀባቸው ከዚህ የተለየ አይደለም። ባለፉት ሳምንታት፣ የሱኒ አክራሪ የሆነው አልቃይዳ አጥፍቶ ጠፊዎችን እያሰማራ ሲያፈነዳ የሰነበተው፣ በአሜሪካ ኤምባሲ ወይም በመንግስት ተቋማት ላይ ሳይሆን፤ በሁቲ የሺዓ ታጣቂዎች ላይ ነው። መስከረም መጨረሻ ላይ፣ የሺዓ ታጣቂዎች ላይ አልቃይዳ በፈፀመው የአጥፍቶ ጠፊ ፍንዳታ ከ60 ሰዎች በላይ ሞተዋል። የኢራንና የሳዑዲ አረብያ መንግስታት እርስበርስ እንደ ደመኛ ጠላት የሚተያዩትን ያህል፤ በየመንም የሺዓ እና የሱኒ አክራሪዎችም በጠላትነት ይጠፋፋሉ፤ ይገዳደላሉ። ለዚህም ነው፤ የሺዓ ታጣቂዎቹ የከባድ መሳሪያ ድብደባው በዩኒቨርስቲው ላይ ያነጣጠረው።
ሁለተኛው ኢላማ፤ በአገሪቱ “ወደርለሽ ነው” በሚባልለት ‘1ኛው ሜካናይዝድ ክፍለጦር ካምፕ” ላይ ያነጣጠረውስ ለምን ይሆን? ለምን ቢባል፤ በጄነራል አሊ አልአህማር የሚመራው ይሄው ክፍለጦር ነው፤ ለበርካታ አመታት በአማፂዎቹ ላይ ተከታታይ ዘመቻ ያካሄደው። የሁቲ አማፂዎች፣ ከምፑንና ዩኒቨርስቲውን ከደበደቡ በኋላ፤ ወደ ከተማዋ ለመግባት ጊዜ አልፈጀባቸውም። ሊመክታቸው የሚሞክር ተዋጊም አላጋጠማቸውም። የተኩሱ መዓት አይጣል ቢሆንም፤ ለውጊያ ሳይሆን እንደ ርችት ድል ለማብሰር ነው የተጠቀሙበት። የመንግስት ጦር ስንቁንና ትጥቁን ሁሉ ለአማፂዎቹ ትቶ ሲበተን፤ የከተማዋ ፖሊስ በየቤቱ ተከቷል። ሰንዓ በአማፂዎቹ ቁጥጥር ስር ዋለች።አስገራሚው ነገር፤ አማፂዎቹ የመንግስት መቀመጫ የሆነችውን ከተማ ቢቆጣጠሩም፤ የቀድሞው መንግስት አልፈረሰም። አሁንም አለ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፕሬዚዳንት መንሱር ሃዲ ጋር ተጣልተው ስልጣናቸውን ከመልቀቃቸው በቀር፤ የወትሮው የመንግስት መዋቅር አልተለወጠም፤ የመንግስት ባለስልጣናት አልታሰሩም፤ ከስልጣንም አልተሻሩም። አማፂዎቹ ጥርሳቸውን የነከሱት፣ በሱኒ አክራሪ ቡድኖችና በአንድ ባለስልጣን ላይ ብቻ ነው - በሜካናይዝድ ክፍለጦር አዛዥ ጄነራል አልአህማር ላይ! በአማፂዎቹ የሚታደኑት ጄነራል፤ ካለፈው ወር ወዲህ የት እንደገቡ አይታወቅም። የአማፂዎቹ ንዴት ግን የበረደ አይመስልም። ሰንዓ የሚገኘው የክፍለጦሩ ካምፕ ፈርሶ መናፈሻ ይሆናል ብለዋል አማጺዎቹ። የአገሪቱ ፕሬዚዳንትና ሌሎች ባለስልጣናት ግን፤ (በርካታዎቹ ባለስልጣናት ወደ ቢሮ ሲገቡ ለጥበቃ በተሰማሩ አማፂዎች የሚፈተሹ ቢሆኑም) ይሄውና አሁንም ስልጣናቸውን እንደያዙ ነው - ከአማፂዎቹ ጋር የሰላም ስምምነት ስለተፈራረሙ።
ነገር ግን፤ መንግስት አለ ለማለትም ያስቸግራል። የዛሬ ወር ገደማ ፕሬዚዳንቱ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር የሾሙ ጊዜ ምን እንደተፈጠረ ይታወቃል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስልጣን ዘመን ለአንድ ቀን አልዘለቀም፤ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ነው የተሻሩት - አማፂዎቹ አልወደዷቸውማ። የመን ነገር ግራ አያጋባም? “መንግስት አለ ወይም የለም” ብሎ ለመናገር አስቸጋሪ የሆነባት አገር!
ተስፋ ያልቆረጡት ፕሬዚዳንት፤ ለአማፃ ቡድኑን ታጣቂዎች አቤቱታና ጥሪ ከማቅረብ ወደኋላ አላሉም። “እባካችሁ፤ በስምምነታችን መሰረት ዋና ከተማዋን ለቅቃችሁ ውጡልን፤ የመንግስት መስሪያቤቶችንና የጦር ካምፖችን አስረክቡን፤ የወሰዳችኋቸው ታንኮችንና የጦር መሳሪያዎችን መልሱልን” በማለት አቤቱታ ሲያቀርቡ፣ ወር አለፋቸው። የአማፂዎቹ ዘመቻ በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍልና በሰንዓ ከተማ ላይ ብቻ ተገድቦ አልቆመም። በቅርቡ ወደ ደበቡ አቅጣጫ በመግፋት፤ የወደብ ከተማ ኤደንን ተቆጣጥረዋል። ከመስከረም ወዲህ የመን እንዲህ ነች - ጭራና ቀንዷ የማይታወቅ የትርምስ አገር!
እንዲያም ሆኖ፤ በመስከረም ወር 9500 ገደማ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ የመን ገብተዋል። በአጠቃላይ ባለፉት ስድስት ወራት ከ40ሺ የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን ወደ የመን ተሰደዋል። ለምን? የየመን ትርምስ በግልፅ ስላላወቁ ሊሆን ይችላል። ቢያውቁ እንኳ ብዙ አያሳስባቸው ይሆናል - ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመሻገር እንጂ የመን ውስጥ ለመቆየት ስለማያስቡ። በዚያ ላይ፣ በህጋዊ ምዝገባ ወደ ሳዑዲ አረቢያና ወደ ሌሎች የአረብ አገራት ለመጓዝ የሚያስችል አሰራር ካለፈው አመት ጀምሮ በመንግስት “ጊዜያዊ እገዳ” ስለተዘጋ፤ አማራጭ በማጣትም ሊሆን ይችላል።

በ6 ወር ወደ የመን የተሰደዱ ኢትዮጵያውያን
ሚያዚያ 2006    6,865
ግንቦት 2006    6,820
ሰኔ 2006    4,468
ሐምሌ 2006    4,917
ነሐሴ 2006    8,150
መስከረም 2007    9,443
በስድስት ወር    40,663


Read 3894 times