Saturday, 08 November 2014 10:50

ኢትዮጵያ ለ20 ደቡብ ሱዳናውያን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ነፃ የትምህርት ዕድል ልትሰጥ ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

      ኢትዮጵያ ለአስር የደቡብ ሱዳን የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች (ሚኒስትር ዴኤታዎች) እና ለአስር የደቡብ ሱዳን የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሙያዎች በአጠቃላይ ለሃያ ሰዎች በድህረ-ምረቃ ደረጃ ነፃ የትምህርት ዕድል ለመስጠት ስምምነት ያደረገችበትን ሰነድ የሚያፀድቅ ረቂቅ አዋጅ ቀረበ፡፡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ አዋጁ፤ ለትምህርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡
በሁለቱ አገራት መካከል መጋቢት 24 ቀን 2005 ዓ.ም በጁባ የተፈረመውና ሁለቱ አገራት በትምህርቱ ዘርፍ ትብብር ማድረግ እንዳለባቸው የሚገልፀውን ስምምነት መሠረት አድርጐ የወጣው ረቂቅ አዋጁ፤ ኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ ከደቡብ ሱዳን መንግስት የተሻለ አቅም ያላት በመሆኑ በዘርፉ የቴክኒክ ድጋፍ ለመስጠትና ልምድ በማካፈል እገዛ ለማድረግ የተስማማች ሲሆን፤ ለሃያ የደቡብ ሱዳን የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ነፃ የትምህርት ዕድል እንድትሰጥ ተስማምታለች፡፡ ደቡብ ሱዳንን በትምህርት መርሃ ግብር ቀረፃ ለመደገፍ መስማማቷን ሰነዱ ያመለክታል፡፡
ስምምነቱ በየሀገራቱ የውስጥ አሠራር መሠረት ከፀደቀ በኋላ ለአምስት ዓመታት በሥራ ላይ እንደሚውል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የትብብር ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅ ያመለክታል፡፡

Read 2570 times