Monday, 03 November 2014 08:25

“የፍላሎት መንገዶች”- የሕይወት መንትዮች!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

       ዘመንንና ትውልድን በድፍኑ የማጥላላት አባዜ አንድም በራስ ፍቅር መስከር አሊያም እውነታን የማየት አቅም ማጣት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ድፍን ትውልድ ቀሽም አይሆንም፡፡ በአብዛኛው ፈዛዛ ቀለም፣ ሀዲድ ሩጫ ሊኖረው ይችላ፡፡ እናም ይህንን ልናማ እንችላለን፡፡ ግን ደግ ሀሜት መፍትሄ አይደለም፡፡ የሚሻል ነገር ለማምጣት አይን ያወጡትን እንጀራዎች ወደ መሶብ አቅርቦ፣ ለሳሎን ክብር ማብቃትና ገና ምጣድ ላይ ሆነው ከሊጥ ያላለፉትን “ማዕድ ቤት ቆዩ” ብሎ መስመር ማበጀት ደግ ነው፡፡ ከአድልዎ የነፃ አስተያየት፣ ምክንያታዊ አድናቆትና ከፍታ መስጠት እንጂ በሰፈር ልጅነት፣ በጓደኝነትና በመጠጥ ቤት ስም መደጋገፍ የትም አያደርስም! ሁሌ አይሳሳቱም ባንልም በአብዛኛው ግን ይህንን ታማኝነት የፈፀሙ የጥበብ ሰዎች ነበሩን፤ አሁንም አሉን፡፡
ይህ በተመልካቹ/በታዛቢውና አስተያየት ሰጪው ወገን ያለው ነው፡፡ በደራሲያኑና በገጣሚያኑም በኩል ያለ ዕድሜያቸው ማተሚያ ቤት ሳይሮጡ፣ የተሻለ ሥራ ለመስራት የተጉ ከያንያን አሉ፡፡ እነርሱ የራሳቸው ብቻ ሳይሆን የትውልድ ባለውለታዎች ናቸው፡፡ ምንም እንኳ እውነተኛው የጥበብ ቀንበር ተፈጥሯዊ ተልዕኮ ቢሆንም ቦይውን ጠርገው፣ እልፍኝ አጣምረው፣ ባማረ አፀድ ውስጥ የጋበዙንን ሁሉ ማመስገን ህሊና ላለው ሁሉ ግድ ነው፡፡
በዚሁ ሀሳብ፣ በጥበቡ መንገድ፤ በግጥሙ ሰፈር በቅለዋል፣ ወደ ፊት ደግሞ የተንጨባረረ ቅርንጫፋቸው ቢከረከም ሰፈራችንን ያሳምሩታል፣ ዘመናችንን ያደምቁታል ብዬ ካመንኩባቸው መካከል የበአካል ንጉሴ “ፍላሎት” መጽሐፍ ውስጥ ያሉትን ግጥሞች በጥቂቱ እዳስሳለሁ፡፡
በዘጠና አንድ ገፆች የተቀነበበው ይህ መጽሐፍ፣ በ2006 ዓ.ም የታተመ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ የመጽሐፍት መግቢያዎች ላይ ካየኋቸው የተሻለ ፍሬ ሀሳብና ውበት አይቼበታለሁ፡፡ አንዳች የሚጥም መአዛ፣ ሚዛን ከፍ የሚያደርግ ውበትና እውነትም አለው፡፡ ለምሳሌ የመግቢያው የመጀመሪያ አንቀፅ ላይ እንዲህ ይላል፡፡ “ፍላጎት ያቀፈቻቸው ግጥሞቼ፣ ከጎጆዋ መንና ከግንዱም ከጥጉም እየተጋጨች እርግብነትዋን እንደምታውጅ ጫጩት፣ አለዚያም ከጋጣዋ ተሰዳ የነፃነትን ጥግ ፍለጋ እንደምትዘል ጥጃ ብዙ አጥሮችን ሰብረው የወጡ የሃሳብ ሰንሰሎች ናቸው፡፡ … ገጣሚ ከዘወትሯዊው ቋንቋና ሀሳብ ፈቅ ብሎ ሲታይ የኮረብታው ዜማ ይጣፍጣል፤ ይነዝራል!”
ገጣሚው በመጽሐፉ አደራደር በሁለተኛነት ያሰፈራት ግጥም “ትንቢት እና ሀበሻ” ትላለች፤
እየተራመደ ወደ ላይ አንጋጦ
ድንጋይ ሲወስድለት - አውራ ጣቱን ቆርጦ  
ትንቢተኛ አበባ - “ገድ ነው!” ይለኛል
በግር ሳይጓዙ - ገድ ወዴት ይገኛል፡፡
*  *  *
እጁን ሲያሳክከው - ሳይታጠብ ውሎ
“ገንዘብ ላገኝ ነው!” ይላል ቶሎ ብሎ፡፡
*   *   *
አፉን ይከፍትና ወሬ እያዳመጠ
ዝንብ ባፉ ገብታ
አካላቱን ተፍቶ - መርዟን እየዋጠ
“ርዘቅ ነው!” ይለኛል ትንቢተኛ አበሻ
በሽታ ነው እንጂ - መች ርዘቅ ይሆናል - መርዝና ቆሻሻ፡፡
የመጀመሪያዎቹ አራት መስመሮች ራሳቸውን ችለው የሚተቹት ነገር አለ፡፡ ምናልባት ገጣሚው ወደ ላይ ማንጋጠጥን ከሰማይ ተዐምር እንደመጠበቅ የወሰደው ይመስላል፡፡ የእግሩ ጣት መቆረጥ ደግሞ ጉዳት ሆኖ ሳለ አበሻው “ገድ ነው!” እያለ ደሙን ይረጫል፡፡ ተራኪው ግን በአራተኛዋ መስመር ልኩን ይነግረዋል፣ ገድ /ሲሳይ/ ለማግኘት‘ኮ እግር ያስፈልገዋል፡፡ ታዲያ የምን ቅዠት ነው--- የሚል ዓይነት ድምፀት አለው፡፡
ለጥቆ ያሉት ሁለት መስመሮችም ስለ እጅ ማሳከክና ገድ ነው እሚያወሩት፡፡ ቀጣዮቹ ኮከቦቹን ዘልለው ያሉት አምስት መስመሮች ደግሞ አፍ ከፍቶ ለዝንብ እየሰጡ፣ ዝንብ እየቃሙ፣ ገድ ነው ማለትን ያወግዛሉ፡፡ አጥብቀው ይተቻሉ፡፡
ቀጣዮቹ ስንኞች ደግሞ - እንዲህ ይላሉ፤
ልታልፍ ህይወቱ - ስታጣጥር ነፍሱ
ማለት ይጀምራል
“የዛሬው ቁርጥ ነው፤ ወደቁ ተነሱ፡፡”
*    *    *
ዕድሜ ልኩን ኖሮ - ከትንቢቱ ጋራ ሲጫወት ዕቃቃ
ደግ ነው አበሻ - ሕይወቱን ተኝቶ - ሲሞት የሚነቃ፡፡
ግጥሙ የሚለው እንዲህ ይመስላል፡፡ አበሻ ዕድሜ ልኩን በምኞት ክንፎች ሲበርር ይኖራል፣ ተዓምር ይጠብቃል … ከመስራት ይልቅ አፉን ከፍቶ አምላክ እንዲያጎርሰው ይመኛል፣ በዚያ በተከፈተ አፍ ደግሞ ዝንብ ይስቅበታል፤ ተደስቶ ዘፍኖ ይሞትበታል፣ አይነት ነው፡፡ ይልቅስ የሚባንነው የሞቱ ቀን ነው፣ ሞቱ ሲመጣም፣ እንዲኖር ሰው አልቅሱልኝ፣ ተነሱ ውደቁ ደረት ምቱ ይላል! … የሞተው‘ኮ ዕድሜውን ሙሉ ነው፡፡ ይልቅ የኖረው የሞት ቀን ነው! አበሻ ጉዳችን ፈላ፤ ገጣሚያን ቀዳዳ ሲያገኙ ይለምጡናል! እኛም ሰንበሩን እያከክን፣ ራሳችንን እንመለከት ይሆን?  ግጥም መስታወት ነዋ! ሳንሞት እንኑር … ነገር ነው፡፡
“የኛ እድገት” የሚለው ግጥም፣ ተራኪው ራሱን ጨምሮ እኛንም ቋቱ ላይ የሚያስቀምጥበት ወፍጮ ነው፡፡ ገብተን ደቀቅንም፣ ጓል ሆነንም ወጣን እንዲህ ይላል ግጥሙ፤
ዝናብ ያካፋ‘ለት - ስቧቸው ሿሿታ
እናት፣ አባታችን - አምሯቸው ጨዋታ
“ሂዱ ተጫወቱ፤ አሳድገኝ በሉ፤
ህፃን ልጅ የሚያድገው
ዝናብ ሲመታው ነው፣ ሲረጥብ አካሉ
ያሉንን አንግበን
“ዝናቡ አሳድገኝ!
ዝናቡ አሳድገኝ!”
ነበር ጨዋታችን፤
ነበር ዘፈናችን፡፡
ግጥሙ እዚህ ጋ ትንፋሽ ይወስዳል፡፡ በልጅነት ዘመን ዝናብ ያሳድጋል ተብሎ “ዝናቡ አሳድገን!” እያልን እንደ አንቴና ልንመዘዝ በስብሰን እንገባ ነበር፡፡ ጨዋታችንም ሙዚቃችንም ነበር፡፡ እውነት ነው ብለንም አምነናል፡፡
ደ‘ሞ ሲቀጥል - ብዙ ጊዜ አልፏል፤ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ ምናልባት የመልክ የቁመና ልዩነትም ተፈጥሯል፡፡ እንዲህ ይላል፤-
እልፍ ዘመን ጠብቶ
ብልኮ ደርቦ - ነጠላው ዕድሜያችን
ዜማ ያልለወጠ
    “ዝናቡ አሳድገኝ!
ዝናቡ አሳድገኝ!”
ዛሬም ዘፈናችን፡፡
የዘመን ጎርፍ በላያችን ፈስሶዋል፤ ምናልባት እኛ የተኛን ይመስለኛል፡፡ ባለፈ ቁጥር በነጠላ ላይ ነጠላ፣ እየደረበልን ብልኮ ሆኖዋል፡፡ … የተኛ ሰው የግጥምን ለውጥ ያያል?... ህልምና ቅዠት ካልሆነ መኝታ ውስጥ ከፍታ የለ! … ስለዚህ ውስጣችን አልተለወጠም፤ ግጥማችን አልተቀየረም፣ ዜማችን አልጣፈጠም፡፡ ያው ነው! ያንኑ የልጅነታችንን ጨቅላ ዘፈን እንዘፍናለን፡፡ እንዲያሳድገን የምንፈልገው ዝናቡን ነው፡፡ ራሳችን አናድግም፡፡ አሁን ይህ ግጥም እንደ ቡሄ ጅራፍ የሚጮኸው ከእንቅልፍ ተነሱ እያለ ነው፡፡ ማህበራዊ ሂስ ነው፡፡
ሌላው ግዙፍ ታሪክ ውስጥ ጠጠር ታህል ቦታ ያጡ፣ ነገር ግን ቀና ተብሎ የሚታይ ሀውልት ያቆሙ ሃያላንን የሚጠይቀው ግጥም “የት አለ?” እያለ ሲጮህ፣ ድምፁ ወደ ልብ አደባባይ ገብቶ የሚያስተጋባ ይመስላል፡፡ እውነትም የት አለ? … በማን ጥላ ውስጥ ተደብቆ፣ ማን ሸፍኖት ነው?
መፈብረኪያው ሳይኖር
    የብነ በረድ ድንጊያ
        አለት መፈልፈያ
አክሱምን አቁሞ
    ላሊበላን ጠርቦ
ዓለምን አጅቧል፤ አጅቧል አበሻ
ሲሚንቶ  ሳይፈጭ፣ ሳይኖር ቅርጽ ማውጫ
ሐረርን ተልሟል፣ ፋሲልን አቁሟል፤ በኖራና ሙጫ፡፡
*     *    *
ሰለሞን የቃኘው - አንድ ጥበበኛ
ባያቶቹ ታሪክ - መኮፈሱን ትቶ
ዓለምን ሊያስደምም - በር መስኮት የሌለው
ሌላ ላሊበላ ፣ ፋሲለደስ ሰርቶ
ኖራና እንቁላሉን ፣ ሙጫ የጣን ፍሬ - ላመታት አቡክቶ
ግንቡንም ጨርሶ፣ ጣራውን ጀመረ
ለምርቃን ቀኑም - ዓለም ተቀጠረ፡፡
(ያኔ)
የሐሳቡ ጠንሳሽ - ሁሉን ያስጀመረ
ማገር እንደያዘ - ቤት ውስጥ ነበረ፡፡
ይህ የትልልቅ ኪነ ህንፃዎች ጠንሳሽና ሰሪ፣ አደባባይ ላይ ያሰፈራቸውን ውበቶች የራሱ ፎቶግራፍ አላደረጋቸውም፡፡ ምጡ የርሱ ነው፤ ትግሉ የርሱ ነው፣ ስራው የርሱ ነው፡፡ ዓለም ተጠራርቶ - ለጥበቡ ክብር ሲወራና ሲዘመር ግን እርሱ አሁንም ሌላ ቤት ለመደገፍ ማገር ይዟል፡፡ ይሰራል እንጂ አደባባይ አይመከርም፡፡ ለጥበብ ይዘምራል እንጂ ጥበብ የርሱን ስም አትዘምርም፡- ሕሊናው ግን ወደ ሰማይ ከፍ ብላ “መዝሙር ባይሉት መካን ልቦች ትስቃለች፡- የእርሱ ከፍታ በጥበብ ደመና መጋለብ ነው! … የገጣሚው ቁጭት ግን - “የታለ እርሱ?” ነው፡፡ አምጡትና ይድመቅ፡- ስሙ በማይደርቅ ቀለም ተጽፎ መዐዛው ነፍሳችን ያስደንሳት ነው! … የፍትህ ጥያቄ
የ “ፍላጎት” ግጥሞች ብዙ ናቸው፣ ያሳዝናሉ፣ ያስቃሉ፣ ያስተክዛሉ፣ የሕይወት መንትያ ናቸው፡፡ ራሷን ይመስላሉ፡፡ ሙዚቃቸውም ደስ ይላል፡፡ ም‘ታቸውም ሰባራ አይደለም፡፡ ሁሉንም ማለቴ ግን  አይደሉም፡፡

Read 1486 times