Saturday, 25 October 2014 10:54

ገንዘቤ የዓመቱን ምርጥ ብቃት አሳይታለች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

በ2014 የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ የዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ በሴቶች ምድብ ከመጨረሻዎቹ ሶስት እጩዎች ተርታ የገባችው የ23 ዓመቷ  ገንዘቤ ዲባባ፤ ቢያንስ በዓመቱ ምርጥ ብቃት የመሸለም እድል እንደሚኖራት ተገመተ፡፡
የዓለም ኮከብ አትሌት ምርጫ አሸናፊዎች ከ3 ሳምንት በኋላ በፈረንሳይ ሞናኮ ውስጥ በሚደግ ልዩ ስነስርዓት ይታወቃሉ፡፡ በሁለቱም ፆታዎች ለመጨረሻ ፉክክር ሆነው የቀረቡ አትሌቶች የተለዩት  ለሁለት ሳምንት በአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ድረገፅ  በተሰበሰበ ድምፅ ነው፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ቤተሰብ በሚል የሚጠቃለሉት የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ እና የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ አትሌቲክስ ፋውንዴሽን ምክር ቤት አባላት፤ የየአገሩ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች፤ የውድድሮች ዲያሬክተሮች እና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃናት ተሳትፈውበታል፡፡የዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫን በሞናኮ የሚገኘው አለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፋውንዴሽን ምክር ቤት ያዘጋጀዋል፡፡ በሁለቱም ፆታዎች የዓለም ኮከብ አትሌት ሆነው የሚመረጡ አትሌቶች ልዩ የዋንጫ ሽልማት እና 100ሺ ዶላር ቦነስ ይበረከትላቸዋል፡፡
 በሴቶች ምድብ የመካከለኛ ርቀት ምርጥ አትሌት የሆነችው ኢትዮጵያዊቷ ገንዘቤ ዲባባ፤ ከኒውዝላንዳዊቷ አሎሎ ወርዋሪ ቫለሪ አዳምስ እና ከሆላንዳዊቷ የሄፕታተሎን ስፖርተኛ ዳፍኔ ሺፐርስ ጋር በመጨረሻ እጩነት ቀርባለች፡፡ በወንዶች ምድብ ደግሞ የመጨረሻዎቹ 3 እጩዎች የሆኑት ዘንድሮ የዓለም ሪከርድ በማራቶን ያስመዘገበው ኬንያዊው ዴኒስ ኪሜቶ፤ የኳታሩ ሙታዝ ኢሳ እና የፈረንሳዩ ሬናውድ ላቪኔ ናቸው፡፡
በውድድር ዘመኑ ከ8 ወራት በፊት ገንዘቤ ዲባባ በ15 ቀናት ልዩነት በ1500 እና በ3000 ሜትር የቤት ውስጥ ውድድሮች እንዲሁም በ2 ማይሎች ሩጫ ሶስት ሪከርዶችን ማስመዝገቧ ለኮከብ አትሌት ምርጫው ልዩ ተቀናቃኝ አድርጓታል፡፡ ገንዘቤ 2014 ከገባ በኋላያስመዘገበቻቸው ሌሎች ትልቅ ውጤቶች ለዚህ እጩነቷ አስተዋፅኦ አላቸው፡፡ በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና በዓለም አትሌቲክስ ኮንትኔንታል ካፕ በ3ሺ ሜትር ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን ተጎናፅፋለች፡፡
የዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፋውንዴሽን ምክር ቤት እና በአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር (IAAF) ቅንጅት  መካሄድ የጀመረው በ1988 እኤአ ላይ ነው፡፡ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ተሸላሚ በ1998 እኤአ ላይ ኃይሌ ገብረስላሴ ነበር፡፡ ኃይሌ በዚያን ወቅት በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳልያ በ10ሺ ሜትር ባርሴሎና ላይ ከማስመዝገቡም በላይ በ10ሺ እና በ5ሺ የዓለም ሪከርዶችን በመያዝ ከፍተኛ የበላይነት ስለ ነበረው ኮከብ ሆኖ ለመመረጥ ብዙም አልተቸገረም፡፡ ከዚያ በኋላ በ2004 እኤአ ላይ ቀነኒሳ በቀለ ሁለተኛው የዓለም ኮከብ አትሌት ለመሆን በቃ፡፡ ቀነኒሳ በዚህ የውድድር ዘመን  እስካሁን በእጁ የተያዙትን የ10ሺ እና የ5ሺ ሜትር የዓለም ሪከርዶችን አስመዝግቧል፡፡ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናም በድርብ የወርቅ ሜዳልያዎች በማግኘትም የነገሰበት ዘመን ነበር፡፡ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በ2005 እኤአ ላይም በረጅም ርቀት እና በዓለም አገር አቋራጭ ውድድሮች የበላይነቱን ቀጠለበት፡፡ ስለሆነም ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት የዓለም ኮከብ አትሌት ሆኖ ለመሸለም በቅቷል፡፡ ቀነኒሳ በዓለም ኮከብ አትሌትነት ሽልማቱን ለሁለት ጊዜ በመቀበሉ  ብቸኛው ኢትዮጵያዊ አድርጎታል፡፡ በሴቶች ምድብ ከቀነኒሳ በቀለ  ጋር ሁለቱንም ተከታታይ ዓመታት የዓለም ኮከብ አትሌት ሆና ለመሸለም የበቃችው ራሽያዊቷ የምርኩዝ ዘላይ ዬሌና ኢዝንባዬቫ ነበረች፡፡ ከቀነኒሳ በኋላ በዓለም ኮከብ አትሌትነት ለመሸለም በመብቃት የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊ ሴት አትሌት ለመሆን የበቃችው ደግሞ መሰረት ደፋር ናት፡፡ በ2007 እኤአ በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና እንዲሁም በ5ሺ ሜትር ከፍተኛ ስኬት ያገኘችው መሰረት ደፋር በወቅቱ ለመጀመርያ ጊዜ በዓለም ኮከብ አትሌትነት የተሸለመች ኢትዮጵያዊት ሴት አትሌት ሆናለች፡፡ በዚያ የውድድር ዘመን በወንዶች ምድብ አብሯት ለመሸለም የበቃው አሜሪካዊው የአጭር ርቀት ሯጭ ታይሴን ጌይ ነበር፡፡ ከዓለም ኮከብ አትሌትነት ባሻገር አይ.ኤ.ኤፍ በሚያዘጋጀው ዓመታዊ የሽልማት ስነስርዓት ሌሎች ክብሮችን ያገኙ ኢትዮጵያውያን የአትሌቲክስ ጀግኖችም አሉ፡፡ አሰልጣኝ ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ ብቸኛውን የአይኤኤኤፍ የህይወት ዘመን ስኬት ሽልማት ተቀብለዋል፡፡ በ2005 እና በ2008 እኤአ ላይ ደግሞ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የዓመቱ ምርጥ ብቃት ያሳየች አትሌት ተብላ ለሁለት ጊዜያት ተሸልማለች፡፡

Read 1991 times