Saturday, 11 October 2014 15:54

ቅዳሴ፣ አቋቋምና ዝማሬ መዋስእት

Written by  ኦርዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(59 votes)

ባለፈው ሳምንት “ዜማ ቤት፤ ድጓ ጾመድጓ” በሚል ርእስ አንድ ጽሁፍ ማስነበቤ ይታወሳል፤ ዛሬም የዜማ ዘር ስለሆኑት አቋቋም፣ ቅዳሴና ዝማሬ መዋስእት ትምህርቶች መጠነኛ ቅኝት በማድረግ ስለምንነታቸውና አገልግሎታቸው ማስነበብ ይሆናል - ዓላማዬ፡፡
 ቅዳሴ
ቅዳሴ “ቀደሰ አመሰገነ” ከሚለው የግዕዝ ቃል የመጣ ሆኖ “ማመስገን፣ ማወደስ፣ ማገልገል” የሚል ትርጉም አለው፡፡ አገልግሎቱም በቤተክርስቲያን ብቻ የተወሰነና በዜማና በንባብ ፈጣሪን ማመስገን ነው፡፡ የቅዳሴ ዜማን የደረሰው ልክ እንደ ድጓውና ጾመድጓው ሁሉ ቅዱስ ያሬድ መሆኑ ይነገራል፡፡ ዜማው የተዘጋጀውም “ዕዝል” እና “ግዕዝ” በሚባሉ ሁለት የዜማ ይትበሃሎች (ዘዴዎች) ነው፡፡ በግዕዝ የሚዜመው በጾም ወቅት ሲሆን እዝል ግን ከጾም ውጭ ባሉት ጊዜያት ነው፡፡ የቅዳሴ ቁጥር 14 ሆኖ እንደየበዓሉ ሁኔታ ይለያያል፤ ለምሳሌ በጾመ ማርያም የሚቀደሰው “ቅዳሴ ማርያም” የሚባለው ሲሆን በበዓለ እግዚእ ደግሞ “ቅዳሴ እግዜእ” በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ ቅዳሴ ልክ እንደ ድጓው ሁሉ ዘሩ (ንባቡ) አንድ ሆኖ በአዚያዚያም ልዩነት የተነሳ የተለያዩ ስያሜዎች አሉት፤ እነሱም “ደብረ ዓቢይ፣ ሰደድኩላ፣ አጫብር” በመባል ይታወቃሉ፡፡ ሁሉም ስያሜያቸውን ያገኙት ትምህርቱ በቀዳሚነት ከሚሰጥባቸው ቦታዎች ተወስዶ ነው፡፡
ለአብነት “ደብረ ዓባይ” ትግራይ ውስጥ፣ “ሰደድኩላ” ሰሜን ወሎ፣ እና “አጫብር” ጐጃም ውስጥ የሚገኙ ቦታዎች ናቸው፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በተለይ በከተሞች አካባቢ ጐልቶ የሚታወቀው “ደብረ ዓባይ” የተባለው የቅዳሴ ዜማ ነው፡፡
“ሰደድኩላ” በሰሜን ወሎ አካባቢ፣ “አጫብር” ደግሞ በጐጃም የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ሰፊ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ “ደብረዓባይ” እና “ሰደድኩላ” ቋሚ ትምህርት ቤቶች (ጉባዔያት) ያሏቸው ሲሆን “አጫብር” ግን በትውፊት መልኩ ከአባቶች ለደቀመዛሙርት (ተከታዮች ወይም ተማሪዎች) እየተላለፈ እስከ አሁን ድረስ አገልግሎት ከመስጠት አላቋረጠም፡፡
አቋቋም
ሌላው የዜማ አይነት “አቋቋም” በመባል የሚታወቀው የትምህርት ዘርፍ ነው፡፡ አቋቋም “ተፈጠረ” የሚባለው በጐንደር ዘመነ መንግሥት በተለይ ደግሞ በታላቁ ኢያሱ (አድያም ሰገድ) ዘመን ነው፡፡ ዜማውን “ደረሱት” ተብሎ የሚታመነው “አባ ኤስድሮስ” የተባሉ ባህታዊ (መናኝ) ናቸው፡፡ አባ “ጐሐ” ሆቴል ከተሰራበት ቦታ (ያኔ “ገነት ተራራ” የሚባል ጫካ ነበር) ሆነው ዘወትር ሌሊት በዜማ ይጸልዩ ነበር፤ ዜማው ከዚያ ቀደም ተሰምቶ የማይታወቅ ስለነበር የብዙዎችን ቀልብ ሳበ፡፡ ቀስ በቀስም የዜማው ምስጢር ከአፄ ኢያሱ ጆሮ ደረሰና በአግባቡ አዳመጡት፤ ግን ማን እንደሚያዜመው አልታወቅ አለ፡፡
ዜማውን በመረዋ ድምፁ የሚያንቆረቁረውን ሰው ለማወቅ ባለሙያዎች ቢመደቡም ሊያገኙት አልቻሉም፤ ምክንያቱም አባ ሌሊት በዜማ ሲጸልዩ ያድሩና ቀን ይሰወራሉ፡፡ ስለዚህ ምርጥ የሆኑና በቀለም አቀባበላቸው የተመሰገኑ ጥቂት ሊቃውንት ዜማውን እንዲያጠኑ ንጉሡ ትእዛዝ ሰጡ፡፡ ማንነቱ ከማይታወቀውና ሌሊት ብቻ ከሚያዜመው ሰው ትምህርት እንዲቀስሙ የተመደቡት ሊቃውንት፤ ከገነት ተራራ ስር ቆመው ማደር ግድ ሆነባቸው፡፡ በዚህ የተነሳ “የዜማው መጠሪያ አቋቋም” ሆነ የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡
በሌላሙ በኩል “ዝማሜ” ብለው የሚጠሩት ሊቃውንት ቁጥርም ቀላል አይደለም፡፡ ለዚህ አባባል እማኝ ሊያደርጉ የሚሞክሩት “ዜማው ጐንደር የነበረው የሸንቆ ተክል ዘመም ዘመም ሲል በማየት አለቃ ገብረሐና ፈጥረውታል፣ ከሙ ዝማሜ የተባለው ለዚህ ነው” የሚል ነው፡፡ ይህ ግን ብዙም የሚያራምድ አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ሸንበቆ መቼም ቢሆን ነፋስ በነካው ቁጥር ዘመም ማለቱ (ጐንበስ ቀና ማለቱ) የተለመደና አዲስ ክስተት ባለመሆኑ ነው፡፡
ሆኖም አለቃ ገብረሐና ለአቋቋም ትምህርት መዳበር ምንም ድርሻ አልነበራቸውም ማለት አይቻልም፡፡ እንዲያውም እሳቸው ያስተማሩት የሥጋ ልጃቸው አለቃ ተክሌ የአቋቋሙን ዜማ በማሻሻል የላቀ ሚና ተጫውቷል፤ “ተክሌ” በመባል የሚታወቀውና መልካም ድምፅ ባላቸው ሊቃውንት ሲዜም መንፈስን የመመሰጥ ብርቱ ኃይል ያለው ይህ ዝማሜ፣ በተክሌ የተቀነባበረ ነው ተብሎ ይታወቃል፡፡ አለቃ ገብረሐና ለልጃቸው ተክሌ አስተማሩ፤ ተክሌ አሳምሮ ቀመረውና መጠሪያው ሆነ፡፡
የአቋቋም ትምህርት በሶስት ይከፈላል፤ እነሱም “ታችቤት (ተክሌ)፤ ላይቤት” እና “ፋኖ” በመባል ይታወቃሉ፡፡ “ላይቤት” ዋና ጉባዔ ቤቱን ጐንደር በዓታ አድርጐ በተለያዩ ቦታዎች የሚሰጥ ሲሆን ይበልጥ የሚታወቀውም በጸናጽል ነው፡፡ “ታችቤት (ተክሌ)” ግን ደብረታቦር ከተማ በምትገኘውና “እናቲቱ ማርያም” ተብላ በምትታወቀው ታላቅ ደብር ጉባዔውን ዘርግቶ፣ ከዚያ በሚወጡ ደቀመዛሙርት አማካይነት በተለያዩ የአገራችን ቦታዎች ትምህርቱ እየተሰጠ ይገኛል፤ ከላይቤት የሚለይበት ዋና ምክንያት በመቋሚያ ይትበሃሉ ሲሆን በዘር ከላይቤቱ የሚለይበት መንገድ የለም፡፡ በዝማሜው ግን እጅግ የተመሰገነ የትምህርት አይነት ነው፡፡
ለአቋቋም አገልግሎት የሚያስፈልጉት መሳሪያዎች መቋሚያ፣ ጸናጽልና ከበሮ ናቸው፡፡ በተለይ መቋሚያ በሁዳዴ ጾም ወቅት ብቸኛው መሣሪያ ነው፡፡ ሊቃውንቱ መቋሚያቸውን አንዴ ከፍ፣ እንደገና ዝቅ፤ አንዴ ወደ ግራ፣ መልሰው ወደ ቀኝ በመወዝወዝ ዜማውን ሲያንቆረቁሩት ከአምላክ ጋር በአካል የተገናኙ ይመስላሉ፡፡ ዜማው ግሩም ነው፤ ቢሰሙት፣ ቢያዳምጡት፣ የማይጠገብ፤ ዝማሜው ታይቶ የማይሰለች ፍፁም ውብ ጥበብ፡፡
አቋቋም የሚያገለግለው ልክ እንደ ቅዳሴው ሁሉ አምላክን ለማመስገን ነው፡፡ ንባቡ የተቀመረውም ቅዱስ ያሬድ ከመጽሐፍ ቅዱስ አውጣጥቶ ከአዘጋጀው “ድጓ፣ ጾመድጓና ዚቅ” ከተባሉ የዜማ መጻሕፍት ነው፡፡
ከድጓ፣ ከጾመድጓ፣ ወይም ከምዕራፍም ሆነ ከመዋስእት ለበዓሉ (ለዕለቱ) ተስማሚ የሆነው ተመርጦ ሥርዓቱ በሚፈቅደው አዚያዚያም መሠረት (ግዕዝ ወይም ዕዝል) መጀመሪያ ይዜምና ቀጥሎ በመቋሚያ በመታጀብ ዝማሜው ይከናወናል፤ ከዝማሜው (በአቋቋም የታጀበው ዜማ) ሲጠናቀቅ በጸናጽል እና በከበሮ እየተደጋገመ ይዜማል፤ የዜማዎቹ መጠሪያም “ንዑስ (ትንሽ) መረግድ” በሚባል ቀስ ያለ የዜማ ስርዓት ይጀምርና ወደ ከፍተኛ (ዐባይ) መረግድ (የዜማ አይነት) ይሸጋገራል፤ ከዚያም ምቱ ፈጣን ወደሆነ ዜማ (ጽፋት) ተቀይሮ በመቋሚያ የተጀመረው ምስጋና ይጠናቀቃል፤ ሆኖም ይህ ድርጊት በአንድ ቀን፤ ግን በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ሊደጋገም ይችላል፡፡
 ዝማሬ መዋስእት
ዝማሬ መዋስእት የተደረሰው በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በቅዱስ ያሬድ ሆኖ፣ የተደረሰበት ቦታም በደቡብ ጐንደር ዞን የሚገኝ ሲሆን “ዙር አምባ” ይባላል፡፡
ዝማሬ መዋስእት የሚያገለግለው ለሁለት ጉዳዮች ነው፤ አንደኛ ከቅኔ በኋላ በቤተክርስቲያን ውስጥ በሚከናወን ሥርዓት ላይ ከእጣነ ሞገር (ቅኔ) በፊት የሚፈጸም ነው፡፡
መጀመሪያ መምህሩ ወይም ለዚህ ተግባር የተመረጠ ባለሙያ እየመራ፤ እሱ የሚመራውን ዜማ ሌላ ሰው ከፊት ለፊቱ እግሮቹን ገጥሞ ቆሞ በዜማ እየተመራ ዘሩን (የዕለቱን ዝማሬ መዋስእት) ይዘልቃል፡፡ ከዚያ ካህናቱ በዝማሜ ሊደግሙት ይችላሉ፤ ወይም በጸናጽልና ከበሮ ብቻ በማዜም ሊያጠናቅቁት ይችላሉ፡፡
ካልሆነም አንድ ሰው ብቻውን በዜማ ሊዘልቀውና ሥርዓቱ በዚሁ ሊጠናቀቅ ይችላል፡፡ከዚህ በተለየ ሁኔታ ዝማሬ መዋስእት ሰው ሲሞት ለፍትሐት አገልግሎትም ይውላል፤ ከመዝሙረ ዳዊት የተወሰነውን በዜማ በማጀብ የያሬድ መዋስእት ሥራ ላይ ይውላል፡፡
የዜማው ሥርዓት በአብዛኛው ሐዘንን የሚገልፅና ጠንከር ያለ ነው፡፡ከዚህ ሌላ ዜማ ወጥቶላቸው ሥርዓት ተበጅቶላቸው የሚዜሙ በርካታ የትምህርት አይነቶች አሉ፤ ለምሳሌ የሰባቱ ቀኖች ውዳሴ ማርያም፣ መልክአ ማርያም፣ መልክአ ኢየሱስ፣ አርባዕት፣ ሰለስት፣ ወዘተ በዜማ የሚጸለይባቸውና በተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ናቸው፡፡መልኮችም ሆኑ ውዳሴ ማርያምና ሌሎች ዘሮች የተደረሱት ለተለያዩ ሰዎች መሆኑ ቢታመንም የዜማው ምንጭ ግን ቅዱስ ያሬድ መሆኑን ሊቃውንት ይስማሙበታል፡፡ ቸር ይግጠመን!

Read 19917 times