Monday, 06 October 2014 08:51

“ዘመቻ”- ለእዚህም ለእዚያም

Written by  ባዩልኝ አያሌው
Rate this item
(0 votes)

             እንደ ሀገር አብረውን የሚኖሩትን ችግሮች ለመቅረፍ መንግስት ዘመቻን መፍትሔ አድርጎ ሙጥኝ ካለ እነሆ በርካታ ዓመታት አለፉ፡፡ በዘመቻ ብቻ የምር የተቀየሩና ችግሮቻቸውን በዘላቂነት የቀረፉ ሀገሮች ይኖሩ ይሆን? አይመስለኝም!
ለእኛ ለኢትዮጵያውያንና በየዘመኑ ሀገሪቱን ለገዙ መሪዎች ዘመቻ እንግዳ አይደለም፡፡ “ይሄን ለማስወገድ፣ ይሄን ለማስቀረት፣ እንዲህ ለመፍጠር…” ለየችግሩ “ዘመቻ፣ ዘመቻ…” ሲባል ኖሮአል፡፡ አሁንም እዚያው ውስጥ ነን፡፡ ለየችግሩ የምንጠራው ዘመቻን ነው፡፡ ልብ ብላችኋል? በዘመቻ ለመፍታት የማይሞከርና ዘመቻ የማይገባበት ነገር የለም፡፡
ዘመቻ ፈጽሞ አስፈላጊና ጠቃሚ አይደለም፡፡ ወይንም በዘመቻ የሚፈቱ ችግሮች የሉም እያልኩ አይደለም፡፡ በዘመቻ የሚፈቱ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ያም ሆኖ ግን በዘመቻ የሚደረግ እንቅስቃሴ ወቅታዊ ሆኖ እንዳይቀርና ግልብ የቡድን መንፈስ እንዳያሸንፈው የራሱ የሆነ ከፍተኛ ዝግጅትንና ጥንቃቄን ይፈልጋል፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን ዘመቻ የሁሉም ነገር መፍትሔ አይደለም፡፡ በፍጹም!
እንግዲህ ተሸክመናቸው የምንኖረው አብዛኞቹ ችግሮችም ለዘለቄታው መቀረፍ ያልቻሉት (ሌሎችም ምክንያቶች መኖራቸው እሙን ሆኖ) ችግሮቹን ለመፍታት የሚሞከረው በዘመቻ በመሆኑ ነው፡፡ ችግሩን በጥልቀት በማጥናትና መፍትሔውን በማርቀቅ፣ በተረጋጋ መልኩ በሂደትና በዘላቂነት ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ በጥድፊያና በዘመቻ ለመፍታት ይሞከራል፡፡ እናም ሥር ያልያዘና መድረሻው የማይታወቅ የአንድ ሰሞን እንቅስቃሴ ሆኖ ይከስማል፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ እንቅስቃሴያችን ሁሉ በዘመቻ የተቃኘ ሆኖአል፡፡ በየጊዜው ተጀምረው የትም ሳይደርሱ የቀሩ ብዙ ጉዳዮችን ተመልከቱ፡፡ ልብ ብላችሁ ከሆነ ብዙዎቹ በዘመቻና በ“በል በል” ስሜት የተጀመሩ ናቸው፡፡ እናም የትም አልደረሱም፡፡ ዘመቻ ዘመቻ ነው፤ ጥልቀትና ዘላቂነት የለውም፡፡
ንጽሕናን ለመጠበቅ ዘመቻ፣ የትራፊክ አደጋን ለማስቀረት ዘመቻ፣ ዛፍ ለመትከል ዘመቻ….. ሁሉም ነገር የሚደረገው በዘመቻ ነው፡፡ ታዲያ ዋናው የዘመቻ ችግር ምን መሰላችሁ? የአንድ ሰሞን እንቅስቃሴ በመሆኑ በፍጹም ዘላቂነት የለውም፡፡ ዘላቂነት ስለሌለውም በዘላቂነት ችግርን መፍታት አይችልም፡፡ ዘመቻ ምን አልባት አንድ ጥቅም ይኖረው ይሆናል- ለፕሮፓጋንዳ  ፍጆታ ማገልገሉ፡፡
የዘመቻ ባህል ምን ያህል ችግራችንን መቅረፍ እንዳልቻለ ጥቂት ማሳያዎችን እያነሳን እንመልከት፡፡ በዘመቻ ለመፍታት ከምንታገለው ችግር አንዱ የትራፊክ አደጋ ነው፡፡  በርካቶችን ህይወትና ንብረት የሚያሳጣ ችግር ለመቅረፍ በሀገራችን የሚደረገውን እንቅስቃሴ ልብ ብላችኋል፡፡ ለጥቂት ቀናት የትራፊክ ፖሊሶችና የመንገድ ትራንስፖርት ሠራተኞች በየመንገዱና አደባባዩ ላይ ቆመው መንገደኛውን ስርዓት ለማስያዝና ደንቡን ለማስከበር በሞራል ሽር ጉድ ሲሉ እንመለከታለን፡፡ ሰዉም እነሱ አድርግ የሚሉትን ሲያደርግ ይታያል፡፡ ሆኖም ይሄ የሚሆነው እጅግ ለጥቂት ቀናት ብቻ ነው፡፡
ከዚያስ? ከዚያማ ህይወት በነበረችበት ትቀጥላለች፡፡ መንገደኛውም እንደፈለገው ይሄዳል፡፡ እነዚያ ከቀናት በፊት ስርዓት ለማስከበር ጎንበስ ቀና ሲሉ የነበሩት አካላትም ሁሉን ትተው ሰዉ እንዳሻውና እንደፈቀደው ሲተራመስ በዝምታ መመልከታቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ለምን?
ምክንያቶችን ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ አንደኛ ባለሙያዎቹ በዘመቻው ላይ የተሳተፉት ታዘውና በወቅቱ ቁጥጥር ስለሚኖር ከቅጣት ለመዳን ነው፡፡ ሌላ ብዙም ከዚህ የዘለለ ምክንያት የላቸውም፡፡ ሁለተኛ ህዝቡም እነሱን በመፍራትና ከቅጣት ለመዳን ሲል ነው እንጂ አድርግ ያሉትን ያደረገው በችግሩ ላይ የጠራ ግንዛቤ የለውም፤ እንዲኖረውም አልተደረገም፡፡ እናም ሁለቱም አካላት እንደምንም ብለው በማስመሰል ያቺን የዘመቻ ወቅት ያሳልፏታል፡፡ ይኸው ነው፡፡ ምክንያቱም ችግሩን ለመፍታት የተኬደበት መንገድ ቀጣይና ዘላቂነት ያለው ሳይሆን በጥቂት ቀን የሚከስም ዘመቻ ነበር፡፡ እናም አደጋውና ጥፋቱ ባለበት ይቀጥላል፡፡ ዘመቻ የአንድ ወቅት እንቅስቃሴ እንጂ ቀጣይና ዘላቂ አይደለም፡፡  
ሌላ ማሳያ እናንሳ፡፡ የችግኝ ተከላ፡፡ እንደ መንግስት ሚዲያዎች “ዘገባ” ባሳለፍናቸው ጥቂት ዓመታት ውስጥ በዘመቻ የተተከሉት ችግኞች ብዛታቸው ያህላል የለውም፡፡ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች ተተክለዋል፡፡ የጸደቁት ምን ያህሉ ናቸው? ብለን ብንጠይቅ ግን መልሱ እጅጉን አስደንጋጭ እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡ ለምን መሰላችሁ? ችግኞቹ የተተከሉት ለአንድ ቀን ታይቶ በሚጠፋ ዘመቻ ነው፡፡ እርግጥ ነው ችግኞችን በዘመቻ መትከል ይቻል ይሆናል፤ በዘመቻ እንዲጸድቁ ማድረግ ግን አይቻልም፡፡ ስለማይቻልም ይደርቃሉ፡፡ ይህንን ያህል ሚሊዮን ችግኞች ተተከሉ የሚለው ዜና ግን አሪፍ የፕሮፓጋንዳ ግብአት ሆኖ ያገለግላል፡፡ ዘመቻ ከዚህ ያለፈ ጥቅም የለውም፡፡
የጽዳት ዘመቻውን ተመልከቱ፡፡ “ከዚህ ቀን እስከ እዚህ ቀን ድረስ የጽዳት ዘመቻ ነው” ይባላል፡፡ ነዋሪውም አምኖበትም ሳያምንበትም በዘመቻው ይሳተፋል፡፡ እናም በአስገራሚ መልኩ ዘመቻው የተካሄደበት አካባቢ ፍጹም ንጹህ ሆኖ ይጸዳል፡፡ አበቃ፡፡ ሁሉም “ዘማች” ወደቤቱ ይመለሳል፡፡ ከዚያስ? ከዚያማ በቀጣዩ ቀን አካባቢው መቆሸሹን ይቀጥላል፡፡ የሰው ልጅ ቆሻሻን የሚፈጥረው በዘመቻ አይደለም፡፡ በእለት ተእለት እንቅስቃሴው ውስጥ ነው፡፡ በመሆኑም የንጽህና ግንዛቤ ኖሮት፣ አካባቢውን በንጽህና መጠበቅ ያለበትም በዘመቻ ሳይሆን በእለት ተእለት እንቅስቃሴው ነው፡፡
የዘመቻ እንቅስቃሴ በርካታ ችግሮች አሉበት፡፡ አለመሳካቱም ከእነዚህ ችግሮቹ የሚመነጭ ነው፡፡ ሲጀመር በዘመቻ ላይ የሚሳተፉት ሰዎች የሚሳተፉት ስላመኑበትና በችግሩ ጉዳት ላይ የጠራ ግንዛቤ ስላላቸው ሳይሆን፣ አንድም ስለታዘዙ አሊያም ከሌሎች ተነጥለው መቅረት ስለማይፈልጉ ነው፡፡ እናም በዘመቻው ላይ በመሳተፍ ከጥራት ይልቅ ቁጥር ላይ ትኩረቱን ያደረገ ተሳትፎ ያደርጋሉ፤ በቃ፡፡ አሁንም በሌላ ዘመቻ ተጠርተው ወይም ተመልምለው እስከሚገኙ ድረስ በድርጊቱ ውስጥ አይኖሩም፤ የሉም፡፡ እናም ችግሩም ላይ ላዩን ይጠረግና ከስሩ ሳይነቀል ባለበት ይቀጥላል፡፡
በየመስኩ በዘመቻ ሊከወኑ የሚሞከሩ ሆኖም ተነካክተው የሚቀሩ ሌሎች ብዙ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ብዙ ብዙ! በዘመቻ ለመፍታት የምንሞክረው ችግር ያህላል የለውም፡፡ ግን ለምን? ባለፈው ስርዓትም ሆነ አሁን ባለንበት ስርዓት የዘመቻ ባህል ችግሮቻችንን በዘላቂነት አልፈታም፡፡ ዘመቻ ትርፉ ምንም ነው፡፡ ምንም! ሆኖም ግን አሁንም እሱኑ የሙጥኝ ብለናል፡፡ እናም ከችግሮቻችን ጋር እያዘገምን አለን፡፡
ታዲያ መንግስት ይህንን እያወቀ ዘመቻን ለምን ባህል አደረገው? መልሱ ቀላል ነው፡፡ ለመንግስት የሚያስገኝለት “ያልተገባ ጥቅም” ስላለ፡፡
ይህንን እንመልከት፡፡ ደጋግመን እንዳልነው ዘመቻ በአብዛኛው ቁጥር ላይ ትኩረቱን ያደረገና በአንድ ወቅት ታይቶ የሚከስም እንዲሁም በርካታ ሰዎች የሚሳተፉበት እንቅስቃሴ ነው፡፡ እንግዲህ መንግስትም የሚያገኘው ጥቅም ከእነዚህ ከላይ ከጠቀስናቸው ሦስት የዘመቻዎቻችን መልኮች (ቁጥር ላይ ትኩረቱን ያደረገ፣ ወቅታዊ የሆነ እና በርካታ ሰዎች የሚሳተፉበት) የሚመነጭ ነው፡፡
አንደኛ ተሳታፊዎቹ አምነውም ይሁን ሳያምኑ በሚሳተፉበት ዘመቻ ውስጥ ገዢ የሚሆነው የቡድን መንፈስ በመሆኑ የዘመቻው ተሳታፊዎች ከዚህ መንፈስ ውጪ አይደሉም፡፡ እናም ቆይቶ በማይኖር ትኩስ ወኔ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በዚህም በዘመቻው በከፍተኛ ቁጥር ሊገለጽ የሚችል ስራ ይከናወናል፡፡ የዘመቻው ትኩረት (ከጥራት ይልቅ) ቁጥር በመሆኑም እሱን ያሳካል፡፡ እንግዲህ ይኸው ቁጥርም “ዜና” ሆኖ እንደሚታወጅ አንዘንጋ፡፡
ሁለተኛው ጉዳይ ዘመቻ በአንድ ወቅት ታይቶ የሚከስም (ወቅታዊ) መሆኑ ነው፡፡ እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴዎች የህዝብን ትኩረት በማስቀየር ረገድ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ እናም ትኩረታችን ተቀይሮ ማሰብ ያለብንን ሳይሆን የሌለብንን እንድናስብ እንሆናለን፡፡
ሦስተኛውና መንግስት ከዘመቻዊ እንቅስቃሴዎች የሚያገኘው ጥቅም፣ ዘመቻ በባህሪው በርካታ ሰዎች በአንድ ላይ የሚሳተፉበት እንቅስቃሴ ከመሆኑ የሚመነጭ ነው፡፡ በዘመቻ ላይ በርካታ ሰዎች በአንድ ላይ እንዲሳተፉ ይደረጋል፡፡ በርካታ ሰዎችን በአንድ እንቅስቃሴ ውስጥ ማሰለፍ ደግሞ በመንግስት የሚደረጉትን እንቅስቃሴዎች የህዝብ ድጋፍና ይሁንታ ያላቸው አስመስሎ ያሳያል፡፡ እንዲሁም ሌሎችም ልብ የማንላቸውና ልብ ብንላቸውም ነገሬ የማንላቸው በርካታ ጥቅሞች አሉት- ለመንግስት፡፡
የምር የዚህችን ሀገር እድገት የምንናፍቅ፣ ለዘመናት ተተክለውባት የኖሩትን ችግሮቿንም መንቀል የምንፈልግ ከሆነ፣ አንዱ መፍትሔ ከ“ዘመቻ አስተሳሰብ” መውጣት ነው፡፡ ለዚህም ችግሮቹን በጥልቀት ማጥናት፣ በችግሮቹና በጉዳታቸው ላይም የጠራ ግንዛቤ እንዲኖር ማድረግ፤ መፍትሔዎቹን አጥንቶ መለየትና ዘላቂና ታይቶ የማይከስም እንቅስቃሴ ማድረግ ይገባናል፡፡ መፍትሔው ይኸው ነው፡፡ ሌላው ሌላው ከንቱ ነው፤ ከወቀሳና ከታሪክ ተጠያቂነት አያድንም፡፡
መልካም ሰንበት!  

Read 2472 times