Monday, 06 October 2014 08:13

ኮሚቴ ኑሮ ነው፤ ኮሚቴ ጉሮሮ ነው!

Written by  ዘመላክ ስለሺ
Rate this item
(1 Vote)

               ኮሚቴ ጥሩ ነው፡፡ እቃ ቢጠፋችሁ፣ ታናሽ ወንድም ቢያናድዳችሁ፣ እቴቴ ከማለት ኮሚቴ ማለት ብልህነት ነው፡፡ ኮሚቴ ውሀን ከጥሩ፣ ነገርን ከስሩ ስለሚፈትሽ፣ በሰብሳቢው ወንበር ጐማና በነገሩ ብልት አላማ ላይ እየተሽከረከረ ጥሩ አድርጐ ስራን ያጓትታል፡፡ በፋይል ላይ ፋይል ይከፍታል፡፡ በመጨረሻም ጊዜያችሁን ለመቆጠብ፣ እንባችሁን ላለማንጠባጠብ በሚል ጉዳያችሁን ለሌላ ኮሚቴ አሳልፎ ይሰጣል፡፡ እና ኮሚቴ ጥሩ ነው፡፡ ኮሚቴ ውደዱ
በህይወት ሩጫ፣ በኑሮ ትግል ፍጥጫ ውስጥ ግባችሁ ማሸነፍ ከሆነ፣ በዚህም አለም በወዲያኛውም አለም ኮሚቴ ይኑራችሁ፡፡ ኮሚቴ ያላቸው አረመኔ ቢሆኑ ፃድቃን፣ ተራዎች ቢሆኑም ልሂቃን ናቸው፡፡ ሲያጠፉ እየታለፉ፣ ሲዘርፉ እየታቀፉ፣ ሲንዘላዘሉ እየተደላደሉ ይቀጥላሉ፡፡ ሰማይ ቢታመስ፣ መሬት ብትርመሰመስ ቅጠላቸውን ነፋስ፣ ግንዳቸውን ፋስ አያገኘውም፡፡ ኮሚቴ ከሌላችሁ ጉዳችሁ! ምን አመል ምን ሽመል፣ ምን ፍሬ ምን ጥንካሬ ቢኖራችሁ፤ ምን አዋቂ ምን አስደናቂ፣ ምን ጉደኛ ምን አስማተኛ ብትሆኑ፣ ራሳችሁን ትደፉ እንደሆነ እንጂ ሚዛን አትደፉም፡፡ ስለምታሳዩት ጐዳና፣ ስለምትለግሱት ፋናም እንቸብችብህ እንጂ ግዛን፤ እናጥቁርህ እንጂ አውዛን የሚላችሁም አታገኙ፡፡ እንደውም ስትባትሉ ልታስመስሉ፣ ስትታትሩ ልትቆነጥሩ፣ ስትማልዱ ልትቀልዱ ይሆናል፡፡ ስብሰባ ስትቀመጡ አለቃ ልታንጓጥጡ፣ አስተያየት ስትሰጡ ልታሳጡ፣ ፍትሀዊነትን ስታሞካሹ ስራ ልታበላሹ፣ መብት ስትጠይቁ ሰራተኛ ልትነቀንቁ ነው፡፡ እና ኮሚቴን ውደዱ፡፡ ኮሚቴን አትለፉ፤ ኮሚቴ ከሚያልፋችሁ ጡቷ እንደበሬ ቀንድ የተገተረ የገለጠች ኮረዳ ብታልፋችሁ ይሻላል፡፡
በበኩሌ በሌላው ህይወቴ የገጠመኝን እክል፣ የደረሰብኝን መሰናክል ስለማውቀው አኗኗሬ ብቻ ሳይሆን አሟሟቴም በኮሚቴ ይሆን ዘንድ ተናዝዣለሁ፡፡ ለኮሚቴ እስከባህር አንጀቴ የጠለቀ፣ እስከ ልቤ ገበር የዘለቀ አክብሮትም አለኝ፡፡ ቀን ወደ ርስቴ፣ ማታ ወደ ሚስቴ ስሄድ፤
ኮሚቴ ኮሚቴ
ግባ ወደ ቤቴ
ና ወደ ህይወቴ
እንቅልፍ ጥሩ ነው ለሰውነት ድካም
ግን እንደ ኮሚቴ አይገኝም መልካም
አስቤ ከስቤ ያልሞላልኝ ኑሮ
እድሜ ለኮሚቴ ሆነልኝ ዘንድሮ
እንግዲህ አልክም ገብሬልን ወደ አምላክ
ከስሬ  አገኘሁት የኮሚቴን መላዕክ፡፡
ስል የማንጐራጉረውም ይህንኑ አክብሮቴን ለመግለጽ ነው፡፡ መቼም ውጭ ነቀል፣ ሀገር በቀል የሆነው ኮሚቴ ግራ ቀኙን አይቶ፣ ደንብና ስርአቱን ተመልክቶ በየጊዜው ለሚያቀርብልን ፈተና፣ ያለ ስስት ለሚነፍገን ቅልጥፍና አክብሮት ቀርቶ አምልኮት አይበዛበትም፡፡ እስኪ እናንተም የኮሚቴ ፍቅሩ እንዲያድርብን፣ ፀጋው እንዲራገፍብን በምትሰሩበት መስሪያ ቤት አልያም በተከራያችሁበት ቤት ውስጥ በሰሪውና በአሰሪው፣ በአስኗሪውና በኗሪው መካከል ኮሚቴ ያለውን አስተዋጽኦ አጋሩን፡፡
እኔ በምሰራበት አንድ የግል ተቋም ውስጥ ለመልካም አስተዳደር የሰራተኞችን ቅሬታና አቤቱታ ይዞ በአሰሪዎች ፊት የመቆምና ክፍተቶችን የመጠቆም አላማ ታጥቆ የተመሰረተ የሰራተኞች ተወካይ ኮሚቴ አለ፡፡ የዚህ ኮሚቴ አባላት በዝና ከሰራተኛው፣ በዝምድና ከአስተዳደሩ የሆድ ዕቃ የሚቀነጣጠቡ ጉበቶች ሲሆኑ ግብራቸው ከሰራተኛው የሚመነጩና ሃላፊዎችን የሚያግረጨርጩ አዳዲስ አስተሳሰቦችን መርዛማነት መቆጣጠር ነው፡፡ አስተሳሰቦቹ ለአለቆች ስልጣን ገደብ፣ ለሰራተኛው ባርነት ወደብ የሚያበጁ የመብትና የዕውነት፣ የልቀትና የእውቀት ጥያቄዎች ሆነው ሲያገኟቸው እንደ ጠላት መንጋ፣ እንደ የዕሳት አደጋ ባሉበት ከበው በደረሱበት ተረባርበው ያዳፍኗቸዋል፡፡ በነሱ ግምት ብዙኃኑን ሳይገዙ፣ ንፁሀኑን ሳይበርዙ፣ ቂላቂሉን ሳያነቁና ሆዳሙን ሳያስጠነቅቁ ያከስሟቸዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ አምልጦ በየግንኙነቱ አቆጥቁጦ፣ የአመራሩን ክፍተት፣ የስራ ሂደቱን አተት በመዘርዘር ሙስናን የሚያሳጣ፣ ልግመኞችን የሚቀጣ ነገር ግን ተቋሙን ከጉድ የሚያወጣ ሃሳብ ከተገኘ ደግሞ የሃሳቡን በኩር አቀንቃኞች ነቅሰው፣ ተከታዮቻቸውን አግበስብሰው፤ ገሚሱን ከስራ ቦታ፣ ቀሪውን ከዕድገት ኮታ በማፈኛቀል የተቋሙ ነባር የተፈጥሮና የእሮሮ ሚዛን ባለበት እንዲቀጥል ይተጋሉ፡፡ እንግዲህ የሰራተኞች ተወካይ ኮሚቴ ልክ እንደ ማንኛውም አይነት ዝነኛና ዘገምተኛ ኮሚቴ ንቦችን ረግጦ፣ አንበጣዎችን አስበልጦ የግልና የጋራ ህልውናን እንደ አሮጌ መኪና የሚያንገታግት፣ እንደ ወደቀ ፈረስ የሚጐትት፤ ጥቅሙ የላቀ፣ አገልግሎቱም የጠለቀ ኮሚቴ መሆኑ ነው፡፡
እና ኮሚቴን ወደዱ፡፡ በኮሚቴ መሳተፍ፣ በኮሚቴ መንተፋተፍ ልመዱ፡፡ ኮሚቴ ኑሮ ነው፤ ኮሚቴ ጉሮሮ ነው፡፡ ኮሚቴ የገነት በር፣ የኤሌትሪክ ወንበርም ነው፡፡ ኮሚቴ ዛሬ የምንጠይቀው ዕድገት፣ ነገ የምናጐነብስበት ስግደት፤ አሁን የምንቆርጠው ስጋ፣ ኋላ የሚደገስልን አደጋ ነው፡፡ ኮሚቴ ተገፍተን የምናልፍበት፣ ተሸንፈን የምንረታበት፣ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ነው፡፡ ኮሚቴ ሁሉም ነው፡፡ ኮሚቴ ኮሚቴ ነው፡፡ ኮሚቴ በቤት ይሁን በጐረቤት፣ በሰፈር ይሁን በጠፈር፤ ጊዜና ቦታ፣ ዕድሜና ፆታ፣ ብሔርና እግዜር ሳይለይ የሰው ልጆች ሁሉ በተሰማሩበት ፊና፣ በሚኖሩበት ቀጠና ውስጥ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ፣ ተጽዕኗቸውን ለማጥበቅ በተጨማሪም ምድር የፍሪዳ ብቻ ሳትሆን የፍዳ ገበታም መሆኗን ለማስተማር የሚገለገሉበት ተቋም፣ የሚራቀቁበት አቋም ነው፡፡ ይህን ተቋም አቋቋሙ፡፡ ይህን አቋም አጠራቅሙ፡፡
አነሰም በዛ፣ አማረም ጠነዛ ኮሚቴ ለምትከውኑት ስራ፣ ለምትመኙት ጉራ፣ ለምትመሰርቱት ዕድር፣ ለምታሰለጥኗት ምድር፣ ለምታሳድጉት ልጅ፣ ለምታፈርጡት ብጉንጅ፣ ለምታዘጋጁት ስጦታ፣ ለምታቀርቡት ስሞታ፤ ለምትነፉት መለከት ፣ ለምታራምዱት አመለካከት ወሳኝ ነው፡፡ እያንዳንዳችን በኑሮ መልክ፣ በዕድሜ ተረክ ስንቀርብ የምንገለጽባቸው ቁም ነገርና አሌ፣ እውነትና ሀሰት፣ ቅንነትና ቂልነት፣ ደግነትና ክፋት፣ ልማትና ጥፋት የመሳሰሉት መስፍሪያ ባህርያት የኮሚቴ እይታዎች ስለሆኑ ለመነሳት ወይም ለመረሳት የኮሚቴ ደንታ፣ የኮሚቴ ይሁንታ ያስፈልጋል፡፡
የኮሚቴ ስጋዊ አስተምሮ፣ መንፈሳዊ ተከራክሮ ተገልጦላቸው በጥላው ስር የፈሰሱ፣ በቪላው ውስጥ የተኮፈሱ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በገድላቸው የሚነግሩን፣ በስንክሳራቸው የሚያስተምሩን ይሄንን ነው፡፡ ኮሚቴ ሲያጥሩ ቁመት፣ ሲሻሩ ሹመት፣ ሲወድቁ ዘብ፣ ሲየጡ ገንዘብ እየሆነላቸው ይለመልማሉ፡፡ ቅጥፈታቸው እውነትን፣ ነውራቸው ጌትነትን ይገበይላቸዋል፡፡
ቁጭ ብለው ሀኖስ፣ ተኝተው ውቅያኖስ ስለሚረግጡም ለዙሪያቸው ፈሪና ተለማማጭ፣ አድማጭና አላማጭ ሞልቷቸዋል፡፡
ለኮሚቴ ህይወት ያልታጩ፣ ደጅ ቆመው የሚቁለጨለጩት ግን ቢያለቅሱ ሰሚ፤ ቢያብቡ ቀሳሚ፣ ጉንጭ ቢያቀብሉ ሳሚ የላቸውም፡፡ በኮሚቴ እምነት፣ የኮሚቴ ሰውነት ስለሌላቸውም ንክ እንጂ ልክ፣ ከንቱ እንጂ አንቱ አይባሉም፡፡
እጆቻቸው የቅሬታ ደብዳቤ ሲያረቁ፣ ልቦቻቸው አንድ ምላሽ እየናፈቁ ይኖራሉ እንጂ ከኮሚቴው የሚላክላቸው ሆሄ፣ የሚሰጣቸው መፍትሔ የለም፡፡ እንዲያው በሲቃ እንዲያው በጥበቃ ይባዝናሉ፡፡
እስካሁን በክርስቶስ እድሜ ኖሬ፣ በማጅላን መርከብ ዞሬ በደረስኩበት አውራጃ፣ በተራመድኩበት ስጋጃ፣ ባየሁትና በሰማሁት ኮሚቴ አይነቱ የበዛ፣ ሃላፊነቱ የተንዛዛ ይሁን እንጂ ንዑስ ምግቡ፣ አብይ ግቡ ፈጣሪዎቹን ማገልገል፣ አማኞቹን መሸንገል ነው፡፡
 በመሆኑም በፊቱ ከቀረበለት ገበቴና ከሰብሳቢው ፎቴ ማዶ ያሉ ትዕይንቶች አይማርኩትም፡፡ ነዳይ ቢያፋጫ፣ ባለ ጉዳይ ቢንጫጫ ደንታ የለውም፡፡ የግፍ መብዛት፣ የፍትህ ርዛት የሚወልደውንም ዋይታ ወፎች ለንጋት፣ ጅቦች ለመውጋት በሚጮሁበት የተፈጥሮ ክበብ ውስጥ እንደሚፈጠር ማንኛውም አይነት ድምጽ በቸልታ ሰምቶ፣ በዝምታ ተኝቶ ያሳልፈዋል፡፡
እና ኮሚቴን ውደዱ፣ በኮሚቴ ተጠመዱ፤ ስለ ኮሚቴ ራሳችሁን ካዱ፡፡ ኮሚቴ የማያልፍበት ስንጥቅ፣ የማይገባበት ትንቅንቅ የለምና በምትሰቀሉበት ማማም ይሁን በምትከሰከሱበት አውድማ፣ በደንብ ለመኖርም ሆነ በደንብ ለመሞት ኮሚቴ ይኑራችሁ፡፡

Read 2546 times