Saturday, 23 August 2014 11:55

“ኑዛዜው”

Written by  መሐመድ ኢድሪስ
Rate this item
(12 votes)

ብቻውን ነው፡፡ በመንፈስም በአካልም፡፡ አባቱ ክዶታል፡፡ ፍቅረኛው ክዳዋለች፡፡ ጓደኞቹ ርቀውታል። አዱኛና ሲሳይ ከሱ ህይወት ዳግመኛ ላይመለሱ ተሰናብተውታል፡፡ ሌላው ቀርቶ ፈጣሪ ራሱ ጠልቶታል፡፡
አራት በአራት በሚሆነው የግንብ ቤት ውስጥ ወንበር ላይ ተቀምጧል፡፡ ፊት ለፊቱ አንድ ጠረጴዛ፤ ጠረጴዛው ላይ ደግሞ ወረቀት አለ፡፡ ጠረጴዛው ላይ በተቀመጠው የታሸገ ውሃ መያዣ ላስቲክ ውስጥ የሐበሻ አረቄ፣ አጠገቡ ደግሞ አራት ሲጋራዎችና አንድ ክብሪት ይታያሉ፡፡
 በግራ በኩል አንድ ታጣፊ አልጋ ሲኖር በክፍሉ ውስጥ ሌላ ምንም የቤት ዕቃ የለም፡፡
ወረቀቱ ላይ ሲያፈጥ ቆየና ቀና አለ፡፡ የክፍሉ ኮርኒስ ላይ የተንጠለጠለ ገመድ አለ፡፡ ይህንን ገመድ ያንጠለጠለው እሱ አይደለም፡፡ ከዘመናት በፊት አባቱ ለሱ ያዘጋጀው ነበር፡፡ ወደዚህ ክፍል ላለመምጣት የቻለውን ሁሉ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ምክንያቱም እዚህ ክፍል ውስጥ ወደ ሞት የሚወስደው መታነቅያ ገመድ እንጂ ሌላ ምንም ነገር እንደሌለ ያውቃል፡፡
“እንዴት ጨካኝ ነው” ሲል አሰበ፤ አባቱን ሲያስታውስ፡፡
አባቱ ቀጭን ረጅም፣ የሚያምር ሪዝ የነበረው የተዋጣለት ነጋዴ ነበር፡፡ ሐብቱን ያካበተው ከምንም ተነስቶ ሲሆን ገንዘብ ላይ በጣም ጠንቃቃ፣ ብዙ የማይናገር፣ ከስራ በኋላ ሲጋራውን እያጨሰ ማንበብ የሚያዘወትር፣ ፊቱ ፈገግታ የማይለየው ሰው ነበር፡፡
በልጅነቱ ከሚጠጣው የብርጭቆ ወተት ግማሹን አስተርፎ ለሱ ከሰጠው በኋላ ፀጉሩን ይዳብሰው እንደነበረ አስታወሰ፡፡
አይኖቹ እንባ እያቀረሩ ላስቲኩ ላይ ያለውን አረቄ ተጐነጨ፡፡ ከሰአታት በፊት ኑዛዜውን ፅፎ ጨርሷል፡፡ ለሱ አሟሟት ተጠያቂው እራሱ እንጂ ሌላ ማንም ሰው እንዳልሆነ በግልፅ አስቀምጧል፡፡ ወረቀቱ ላይ ይህንን ይፃፍ እንጂ ለዚህ ያበቃው ሌላ ማንም ሰው ሳይሆን አባቱ እንደሆነ ግን ልቡ ያውቃል፡፡
ከሁለት አመታት በፊት የአባቱ አርባ እንዳለፈ እሱ፣ ሁለት እህቶቹና ወንድሙ ውርስ ሲከፋፈሉ ነበር የአባቱ ክህደት የጀመረው፡፡ ለሁሉም አንዳንድ ሚሊዮን ብር፣ ህንፃዎችና ቪላዎች ሲደርሳቸው፤ ለሱ ግን አንድ ሚሊዮን ብርና ይህን ከከተማ ውጭ ያለ ቢሸጥ ቢለወጥ ዋጋ የማያወጣ አሮጌ አንድ ክፍል ቤት ተናዘዘለት፡፡ እሱ የበኩር ልጅ ሆኖ ሳለ፣ ይህ አይን ያወጣ አድልዎ ለምን እንደተፈፀመበት እስካሁንም ሰአት ድረስ አልገባውም፡፡
ከውርሱ ክፍፍል በኋላ የአባቱ ጓደኛ የነበሩ አዛውንት፤ አባቱ ህይወቱ ልታልፍ ስትል ለሱ የፃፈውን ማስታወሻ ሰጡት፡፡
“ልጄ ሆይ፤ ገንዘብህን ጠብቅ፤ ይህ ካልሆነና ድህነት ካገኘህ ሌላ የትም ቦታ ሳትሄድ ወደ ግንቡ ቤት ሂድ፡፡ ከስቃይና ከውርደት ትድናለህ” ይላል፡፡
ወንበሩ ላይ እንደተቀመጠ አረቄውን ተጐነጨና ሲጋራ ለኮሰ፡፡ ይህ ሲጋራ በዚህ አለም ላይ የሚያጨሰው የመጨረሻ ሲጋራ መሆኑን ያውቃል፡፡ ኮርኒሱ ላይ የተንጠለጠለውን ገመድ ተመለከተ፡፡ ይህ ገመድ ከዘመናት በፊት ሸምቀቆውን አስፍቶ እሱን ይጠብቅ እንደነበረና እሱም አንገቱን ሸምቀቆው ውስጥ ለማስገባት ዕጣ ፈንታው እየጐተተው እዚህ መገኘቱ አስገረመው፡፡
ነገሩ የሆነው ቆም ብሎ ለማሰብ እንኳን ጊዜ ሳይሰጠው፣ እያሳሳቀው በዝግታ ነበር፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ የተጠናወተው የቁማር ሱስ ነበር ዋናው የሐብቱ ቀበኛ። የከተማውን ታላላቅ ቁማር ቤቶች እየጐበኘ በቀን እስከ አስር ሺህ ብር ድረስ ያጠፋ ነበር፡፡ ከስንት አንዴ ብቻ ሲበላ ብዙ ጊዜ ግን ይበላ ነበር፡፡ ሃብታም እንደሆነ ሁሉም ሰው ስለሚያውቅ የ”ፈላጩ” ቁጥር መንገድ ቀይሮ እስኪሄድ ድረስ አሰለቸው፡፡ እሱ የሚጠጣበት ጠረጴዛ ሁልጊዜ ከደርዘን በማያንሱ ሰዎች የተከበበ ሲሆን የሁሉንም ሂሳብ የሚዘጋው እሱ ነው፡፡ ሁሉም በፈገግታ እያየው በቁልምጫ ይጠራዋል፡፡ ይህንን ሲያደርግ ሰዎች ለሱ የሚሰጡት ክብር እየጣፈጠው መጣ፡፡ ያልገባው ነገር ግን ይህ ክብር የሚኖረው ገንዘቡ እስካለ ድረስ ብቻ መሆኑን ነበር፡፡
እሱ ሲመጣ ጠረጴዛው በጥንቃቄ ይወለወላል። ሴቶች እየሰረቁ ያዩታል፡፡ ደህና ገንዘብ ከያዘ ዊስኪ፣ ካልያዘ ደግሞ ቢራ የዘወትር ምርጫው ነው፡፡ አይፎን ስሪ ጂ ስልኩን እየነካካ የወሲብ ሳይቶችን ሲጐረጉር ያመሻል፡፡ አረብያን መጅሊስ፣ ዲኤስቲቪ፣ ውድ ጫት፣ ሺሻ፣ ድሪያ የለበሱ ቀያይ ሴት ካዳሚዎች ያለባቸው ውድ ጫት ቤቶች… መዋያዎቹ ነበሩ፡፡ ሐረግንም የተዋወቃት እዚያ ነበር፡፡
ውሸት ምን ያደርጋል ተወዳዳሪ የሌላት ቆንጆ ነበረች፡፡ ከዋክብት የመሳሰሉ አይኖችዋን እያስለመለመች በቁልምጫ ስትጠራው ልቡ እንደ ነጋሪት ይጐሰማል፡፡ ገላዋ ለስላሳ፣ ጠረንዋ ጣፋጭ፣ ድምፅዋ ሙዚቃ የሆነች የአልጋ ላይ ንግስት ነበረች፡፡ አንድ ችግር ግን ነበር። ሐረግ ያለገንዘብ ህዋሳቷ አይሰሩም፡፡ ገንዘብ ከሌለ ህይወት አልባ በድን ትሆናለች፡፡ ሰውነትዋ ይቀዘቅዛል፡፡ ንግግርዋ ይዘጋል፡፡ የአልጋ ላይ ዛርዋ ምሱ ወርቅ ወይም ውድ ገጸ በረከት አልያም በርካታ አረንጓዴ የብር ኖቶች ነበሩ፡፡
አረቄውን ደህና አድርጎ ተጎነጨና ሲጋራውን ለኮሰ። የተንጠለጠለውን ገመድ እያየ የሲጋራውን ጭስ ወደ ላይ ለቀቀው፡፡ ሰዓት ስለሌለው ስንት ሰዓት መሆኑን በትክክል ባያውቅም፣ እኩለ ሌሊት እንዳለፈ ግን እርግጠኛ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ከሚሰማው የውሾች ድምፅ በስተቀር ሌሊቱ ፀጥ እረጭ ብሏል፡፡ ሐረግን ለመጨረሻ ጊዜ ሲለያት አስታወሰ፡፡
አውሮፕላን ማረፍያ ውስጥ ነበር ለመጨረሻ ጊዜ ያያት፡፡ “ጠብቀኝ፣ የኔ ማር… ካንተ ተለይቼ መኖር አልችልም” ብላው ነበር ስትሰናበተው፡፡ የመኖርያ ፈቃዴን ላድስ በሚል ሰበብ፣ ዱባይ ስትሄድ የአውሮፕላን ቲኬትዋንና ሙሉ ወጪዋን የሸፈነው እሱ ነበር፡፡ ነገር ግን ተመልሳ አልመጣችም፡፡ ስልክም አልደወለችም። ደብዳቤም አልፃፈችም፡፡ የእስዋ ነገር በዚህ ሁኔታ ተጠናቀቀ፡፡
የባንክ ደብተሩ ላይ የቀረው ገንዘብ ሃምሳ ሺህ ብር ብቻ መሆኑን ያየ ዕለት ከያዘው አፍዝ አደንግዝ ባነነ፡፡ ያኔ ነው ገንዘብ ምንም ቢከማች ካልተሰራበትና በላዩ ላይ ካልተጨመረበት አላቂ መሆኑን የተረዳው፡፡
መጀመሪያ የወሰደው እርምጃ ወጪውን መቀነስና የቀረውን ገንዘብ ስራ ላይ ማዋል ነበር፡፡ ነገር ግን ሁለቱም አልተሳኩም፡፡ ገንዘቡ በየትና እንዴት እንደሚወጣ አይታወቅም፡፡ ንፋስ እንደበተነው አቧራ ተበተነ፡፡ አዋጪ መስሎት የገዛውም አክሲዮን ምንም የረባ ጥቅም አላስገኘለትም፡፡
ይባስ ብሎ የድርጅቱ ፕሬዚዳንት የባለ ድርሻዎችን ገንዘብ በሙሉ ጠራርጎ ከአገር መኮብለሉንና በፖሊስ እየተፈለገ መሆኑን ሰማ፡፡ የመጨረሻውን አንድ ሺህ ብር ከባንክ አውጥቶ ፊቱን አዙሮ ከባንኩ ሲወጣ፣ ገንዘብ ከፋይዋም በሀዘኔታ ከንፈርዋን ስትመጥ ሰማት፡፡ ያን ቀን ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ፡፡
አንድ ሺህ ብሩ ሶስት ቀን አልቆየም፡፡ ከዚያ በኋላ የነበረው ዕድል ከዚህ በፊት ውለታ የሰራላቸውን ሰዎች እየዞረ ብድር መጠየቅ ነበር፡፡ ሁሉም ሰው መክፈል እንደማይችል ስላወቀ የሚያበድረው ጠፋ፡፡ ከሚክስድ ግሪልና ከላዛኛ ወደ ምስርና ሽሮ፣ ከቢራና ዊስኪ ወደ ሐበሻ አረቄ ወረደ፡፡ ከበውት ሲስቁ የነበሩት ሰዎች ሁሉ የት እንደገቡ እስኪገርመው ድረስ አንዳቸውንም ማየት አልቻለም፡፡ ሁለቱ እህቶቹ ነዋሪነታቸው አውሮፓ ነው፡፡ አስተሳሰባቸውም እንደፈረንጅ ስለሆነ ችግሩን የሚረዱለት አልነበሩም፡፡
“ችግርህን እራስህን ችለህ መወጣት አለብህ፣ እኛ ከዜሮ በታች በሆነ ብርድ ነው በቀን 18 ሰዓት እየሰራን ቤተሰብ የምናስተዳድረው፡፡ ይሄ የምልክልህ የመጨረሻ ገንዘብ ነው” ብላ ነበር ትልቋ እህቱ መቶ ዶላር የላከችለት። ከዚያ በኋላ ድምፅዋ ጠፋ፡፡
ታናሽ ወንድሙ በመኪና ስራ ነው የሚተዳደረው፡፡ ችግሩን የነገረው ቀን በጣም ያዘነ መስሎ ሁለት መቶ ብር ሰጠው፡፡ በሁለተኛው ቀን መቶ ብር ብቻ፡፡ በሶስተኛው “የለም” አስባለ፡፡ ከዚያ በኋላ የእሱን ስልክ ማንሳት አቆመ፡፡
የቤት አከራዩ ኪራይ አልከፈልክም በሚል ሰበብ አንድ ቀን ማታ ዕቃውን በር ላይ አስቀምጠው ጠበቁት። ምርጫ ስላልነበረው በትኋንና በቁንጫ እየተሰቃየ፣ አንሶላው ታጥቦ የማያውቅ ርካሽ አልጋ ላይ በየቀኑ እየከፈለ ማደር ጀመረ፡፡ ስልኩ፣ ሰአቱ፣ ልብሶቹ… ተሸጠው አልቀዋል፡፡ ማንኛውንም ስራ ለመስራት ቢሞክርም ተያዥና ዘመድ ስለሌለው የሚቀጥረው ጠፋ። መራብ ጀመረ፡፡ ወደማይታወቅበት ሩቅ ሰፈር እየሄደ መለመን ጀመረ፡፡ ሁኔታውን ያዩ እያዘኑ ይሰጡታል፡፡ አንዳንዶቹ ያመናጭቁታል፡፡
አንድ ቀን መንገድ ዳር ቆሞ ሽንቱን ሲሸና፣ አንድ ከዚህ በፊት በአይን የሚያውቀው ሰውም አጠገቡ ቆሞ ይሸናል፡፡ እሱ ግን እየሸና እንባው ጉንጩ ላይ ይፈሳል። ሰውየው ምን እንደሚያስለቅሰው ጠየቀው፡፡ ምሳ እንዳልበላ ነገረው፡፡ ሰውየው ትከሻውን ያዘና አይኑን ትኩር ብሎ እያየው “ወንድ ልጅ እንደወርቅ በእሳት ይፈተናል፤ ፈጣሪህን እመን፤ ድቅድቁን ጨለማ ብርሃን ማድረግ ይችላል፤ ስለሌለኝ ገንዘብ አልሰጥህም፤ ይህን ቃል ግን እሰጥሃለሁ” አለውና ሄደ፡፡
እሱ ግን ያን ቀን ወሰነ፡፡ የእሱ ነገር ያከተመና ምንም ሊለወጥ እንደማይችል ስለደመደመ ሲሸሸው ወደነበረው ግንቡ ቤት መጣ፡፡ ገመዱም ተንጠልጥሎ እሱን እየጠበቀ ነበር፡፡ እሱም አሳምሮ ያውቃል፡፡ ስለዚህ ኑዛዜውን ጻፈ።
ሲጋራውን ረግጦ ካጠፋ በኋላ ከተቀመጠበት ተነሳ። አሁን ሰአቱ ደርሷል፡፡ ወንበሩን አንስቶ ከተንጠለጠለው ገመድ ስር አስቀመጠው፡፡ ወንበሩ ላይ ወጣና የገመዱን ሸምቀቆ አንገቱ ላይ አጠለቀ፡፡ “ፈጣሪዬ በምህረትህ ታረቀኝ” አለና በእግሩ ወንበሩን ገፍትሮ ጣለው፡፡ ገመዱ አንገቱ ላይ ሲጠብቅና የቤቱ አምፖል ሲፈነዳ አንድ ሆነ። አንዳች ናዳ እላዩ ላይ ወረደና በጀርባው መሬት ላይ ተዘረረ፡፡ ጨለማ ስለሆነ አይታየውም፡፡ ግን እንዳልሞተ እርግጠኛ ነው፡፡ ምክንያቱም ይተነፍሳል፡፡
በጀርባው እንደተዘረረ ወደ አቅሉ ተመለሰ፡፡ ድንገት ትዝ አለው፡፡ ኪሱ ውስጥ ጋዙ ያለቀ ግን ባትሪ ያለው ላይተር ነበረው፡፡ ላይተሩን አወጣና ባትሪውን አበራ። ያየውን ማመን አልቻለም፡፡ ገመዱ ተንጠልጥሎበት የነበረው ኮርኒስ ተገንጥሏል፡፡ መሬቱ ላይ ረብጣ ብር ተከምሯል፡፡ በግምት ሶስት ሚሊዮን ይሆናል፡፡ ቁና ቁና እየተነፈሰ ከክምሩ ብር መሃል ያለች አንዲት ወረቀት አነሳ። የአባቱ እጅ ፅሁፍ ነው፡፡
“ልጄ ሆይ፤ ያለህን ጨርሰህ ወደዚህ እንደምትመጣ አውቅ ነበር፡፡ አሁን ሰው፣ ገንዘብ፣ ህይወት ምን መሆኑን አውቀሃል፡፡ ከሞት በላይ ምንም ስለሌለ ከአሁን በኋላ አትታለልም፡፡ ስለዚህ ይህ ሃብት ያንተ ነው፤ ጸልይልኝ” ይላል፤ እውነተኛውና ዋናው ኑዛዜ፡፡  

Read 3595 times