Saturday, 23 August 2014 11:52

“አውሮራ”፤ ያልሻረ ቁስል የሚነካካው መጽሐፍ

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(5 votes)

         የመጽሐፍ ገበያው ዐይን ያጥበረብራል። በተለይ እንደ በቆሎ እሸት ክረምቱን ጠብቆ የሚዘንበው የመጽሐፍ ዶፍ ከመብዛቱ የተነሳ ፍሬን ከገለባ ለይቶ ለማጨድ ጊዜም ችሎታም የሚሻ እየሆነ ነው፡፡ ለገበያ ብቻ ተብለው የሚቀመሙ መጻሕፍት፣ ለነፍስ ከተጻፉቱ ጋር ሰርገው እየገቡ ክረምት በመጣ ቁጥር እንደበረዶ አንባቢ ላይ ይዘንባሉ፡፡ እንደኔ ታዲያ ክረምቱን ብቻ ጠብቆ የሚያነብ ፍዝ አንባቢ ለምን አይጭበረበር!
በእርግጥ ተኮናኝ እና ጻድቅ ጸሐፍት በየፊናቸው ያበጃጁትን፣ የአቅሜ ያሉትን የጥበብ ሥራ እንካቹህ መባል ምንም ይሁን ምን ደስ ያሰኛል፡፡ በበኩሌ መጻሕፍት እንዴትም ሆነው ይብዙልን ከሚሉት ወገን ነኝ፡፡ ለምን ቢሉ መጻሕፍት እንደ ጨቅላ በአንቀልባ ታዝለው በሚሸጡባት መዲናችን የአንባቢም የተነባቢም ቁጥር እየበዛ ሲሄድ የተሻለ ማስተዋል፣ የተሻለ መስከን፣ የተሻለ መብሰል፣ የተሻለ መግባባት ቀስ በቀስ እየተዋሀደን ይሄዳል ብዬ ስለማምን ነው፡፡
በእግረኛ መንገድ መጻሕፍት እንደ ጌሾ ሜዳ ላይ ተሰጥተው አንባቢን ሽቅብ እየተቁለጨለጩ ሲለማመጡ ያሳዝናሉ፡፡ ይሄኔ አዱኛን መዥረጥ አድርጎ መሸመት ይፈታተነናል፡፡ ኾኖም ብስሉን ከጥሬ ለመለየት አንዳንዴ እድልም ያስፈልጋል ልበል? በቅርብ ጊዜ በሳሳ የንዋይ አቅም መቀነቴን የፈታሁላቸው የጥበብ ሥራዎች መናኛ ሆነው ክፉኛ አስኮርፈውኝ ያውቃሉ፤ ከአንዴም ሁለት ሦስቴ፡፡ በዚያ ላይ ትክክለኛ ዋጋቸው ተፍቆ እጥፍ ዋጋ ከፍዬባቸው እንደነበረ የኋላ ኋላ ስረዳ ኩርፊያዬ ሰነበተብኝ፡፡ ከዚህ ልምዴ ተነስቼ መፃሕፍትን ከመግዛቴ በፊት የወዳጅ ዘመድ ጥቆማንና የሕትመት ሚዲያ ሂስን ‹‹እህ!›› ብዬ እሰማለሁ፡፡ እንዳለመታደል መጻሕፍትን የሚሰብኩን ጥቂት እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። በግሌ ከጋዜጣ አዲስ አድማስን፣ ከሬዲዮ ሸገርን በዚህ ረገድ አደንቃለሁ፡፡
እስኪ ዛሬ ከረዥም ጊዜ በኋላ ብዕር እንዳነሳ ምክንያት የኾነኝን አንድ ታሪካዊ ልቦለድ መጽሐፍ ላስቃኛችሁ፡፡ “አውሮራ” ይሰኛል፡፡ ደም የመሰለ የሽፋን ልባስ የተጎናጸፈ፣ ታንክ ላይ የቆሙ ታጋዮች ጥላ በስሱ የሚታይበት፣ ጦርነት ጦርነት፣ ባሩድ ባሩድ የሚሸት፣ በክብደቱም “ድልብ” የሚባል ዓይነት መጽሐፍ ነው፡፡ የገጹ ብዛት ከ350 በጥቂት ያነሰ፣ ለገበያ ከቀረበ ሁለት ወርም ያልሞላው የታሪክ ልቦለድ መጽሐፍ፡፡
ቅኝቴን ከሽፋኑ ብጀምርስ! በመጽሐፉ ጀርባ ላይ የተጻፈው ነገር፣ ይህን በይዘቱና ባነሳው ጭብጥ በደምሳሳው ግሩም ኾኖ ያገኘሁትን መጽሐፍ እንዳልገዛው አድርጎኝ ነበር ማለት እችላለሁ፡፡ አንድ ስማቸው ያልተጠቀሱ ዲፕሎማት ስለመጽሐፉ ተናገሩ ተብሎ የተቀመጠ አንቀጽ ነው ለዚህ አፍራሽ ስሜት የዳረገኝ። እንዲህ ይላሉ፡-“ …የተኖረን ሕይወት እየጻፉ ልቦለድ ብሎ ነገር የለም…በእውነቱ (ይህ መጽሐፍ) ከኦሮማይ በኋላ የመጣ ድንቅ የጥበብ ሥራ ነው ብዬ አፌን ሞልቼ እናገራለሁ…”
ይህ የጀርባ ጽሑፍ ብሽቅ አድርጐኛል፤ በሁለት ምክንያት፡፡ አንደኛ ይህንን መጽሐፍ ለማድነቅ አንድን ዘመን ተሻጋሪ ቱባ መጽሐፍ ስም አንስቶ ማወዳደር መልካም ዘዴ ኾኖ አልተሰማኝም፡፡ “ኦሮማይ” በሚሊዮን አንባቢዎች ዘንድ ብቻ ሳይሆን በሁለት አገር ሕዝቦች ዘንድ እንደ የጋራ አድባር የሚታይ ታላቅ የጥበብ ዉጤት ነው፡፡ አንድን አዲስ ሥራ ከዚህ ዘመን ተሸጋሪ የሥነ-ጽሑፍ ሥራ ጋር (ያውም ደራሲው ሕይወቱን ከፍሎበታል) ማነጻጸር ለኔ ቀሽምነት ብቻ ሳይሆን የ‹‹አውሮራ›› መጽሐፍ ደራሲን በሥራው እንዳይመዘንና ለጥቃት እንዲጋለጥ ያደረገ ነው። በቦክስ ስፖርት ቋንቋ ከመነዘርነው፣ የከባድ ሚዛን ሻምፒዮን የሆነን ቡጢኛ ከቀላል ሚዛን ተወዳዳሪ ጋር እንደማቧቀስ ያለ ነው፡፡
ሁለተኛው ምክንያቴ ይህንን የመሰከሩት ሰው (ዲፕሎማት) ስማቸው አለመገለጹ ነው፡፡ እንዲህ አፋቸውን ሞልተው ስለ መጽሐፍ የሚናገሩ ዲፕሎማት ስለማንነታቸው ያልገለፁት ለምንድነው? ስል ጠየቅሁ። ምናልባት የመጽሐፉ ማጠንጠኛ በአመዛኙ የኤርትራና የኢትዮጵያን ስስ ብልቶች የሚነካ በመሆኑ ፍርሃት ገብቷቸው ይሆን? ከፈሩ የሰው መጽሐፍ ሽፋን ላይ ምን ድቅን አደረጋቸው? መልስ ያላገኘሁለት ጥያቄ ነው፡፡
ለማንኛውም ወደ ውስጥ ገጾች ይዣችሁ ልዝለቅ፡፡
የመጽሐፉን የመጀመሪያ ገጾች ገልጬ ከሰዓታት በኋላ ራሴን የአንደኛው ምዕራፍ የመጨረሻው ገጽ ላይ ሳገኘው፣ ጊዜ ቆሞብኝ እንደነበር ተረዳሁ። እንደ ፊልም ከጅምር እስከ ምዕራፉ መቋጫ ዝም ብዬ ተወጣሁት ብል ይቀለኛል። ስሟ “ፍልይቲ” የምትባል ኤርትራዊት የኢሳያስ ልዩ ሰላይ ስታዲየም አካባቢ ከሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ ወጥታ ሒልተን ሆቴል ውስኪ እየጠጣ ከነበረ አንድ ጎልማሳ መልከመልካም ኢትዮጵያዊ ሚኒስትር ጋር ስተቀብጥ በምልሰት የሚተርክ ንዑስ ክፍል ነው እንዲህ ፉት ያልኩት፡፡ ወቅቱ (መቼቱ) ደግሞ ሁለቱ አገራት ነፍጥ ለማንሳት ጥቂት ወራት ሲቀራቸው ነው፡፡ ደራሲው የሁለቱን አገራት እፍ ያለ ፍቅር የመጨረሻ ቀናትን ነው እንግዲህ በዚህች ፍልይቲ በተባለች ኤርትራዊትና በዚህ ስሙ ባልተጠቀሰ መልከመልካም ኢትዮጵያዊ ሚኒስትር ዉሉ ያለየለት ግንኙነት ሊያሳየን የሞከረው፡፡ ተሳክቶለታል፡፡
አጠቃላይ የመጽሐፉ ጭብጥ በድንበር ውዝግብ የተነሳ ከኤርትራ ጋር ያካሄድነውን መሪር ጦርነት ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊና ፖለቲካዊ አመክንዮዎችን በተጨባጭ መረጃ እያዋዛ የሚተርክ ዘጋቢ ፊልም ይመስላል። እኛ እንደ ሕዝብ ከሚነገሩንና ከተነገሩን የጦርነቱ ምክንያቶች ጀርባ በምስጢር ይካሄዱ የነበሩ ጉዶችን ነው ልቦለዱ የሚተርክልን፡፡ አንዳንዶቹን በተባራሪ ሰምተናቸዋል፣ አንዳንዶቹ ደግሞ እንዲሁ 6ኛ ህዋሳችን ነግሮን እንጠረጥራቸው የነበሩ ጉዳዮች ናቸው። ባድመ ጦርነቱን ለመጫር ህዝብን ለማነሳሳት ያገለገለች ክብሪት ከተማ እንጂ አንድም ጊዜ እውነተኛ የጦርነት ምክንያት እንዳልነበረች በመረጃና በማስረጃ ይነገረናል። የናቅፋ መታተም፣ ኤርትራዊያን ከኢትዮጵያ ያገኙት የነበረው ልዩ ጥቅማጥቅም መቋረጥ (ቡናን ወደ ዉጭ ገበያ መላክን ይጨምራል)፣ የኢሳያስ ኢትዮጵያን ጥሬ እቃ አቅራቢ፣ ኤርትራን አምራች አድርጎ የመገንባት ህልም ተግዳሮት ማጋጠሙ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ኤርትራዊያን ጭንቅላት ውስጥ ስለራሳቸው የሚሰጡት የተጋነነ ምስል… እንደ ካንሰር እየፈራረሰ መሄድ ወዘተ… እንዴት ጦርነቱን አይቀሬ እንዳደረጉት ከ “አውሮራ” መጽሐፍ ትርክት እንረዳለን፡፡ የመጽሐፉን እንዲህ ከኮብልስቶን የጠጠረ ጭብጥ፣ ፖለቲካ ጭራሽ ለማይስማማው አንባቢ ማቅረብ ደረቅ ጂን ያለ አምቦ ዉኃ እንዲጋት ከማስገደድ አይተናነስም፡፡ ኾኖም ደራሲው በዚህ ረገድ መለኛ መሆኑን ተገንዝቤአለሁ፡፡ “ፍልይቲ” የምትባል በቁመና የኦሮማይዋን “ፊያሜታ” የምትስተካከል፣ ሳህል በረሀ የተወለደች፣ ሃይላይ ከሚባሉ በሳልና አመዛዛኝ ኤርትራዊ ሚኒስትር የተገኘች፣ በድርጊቷም በአስተሳሰቧም ፍቅር የምታሲዝ ገጸባህሪን ቅልብጭ ቁልጭ አድርጎ ስሎልናል። ምናልባት በልቦለድ ዓለም መንታ መፍጠር የሚያስችል ዘረመል ካለ ፍልይቲ የኦሮማይዋ ፊያሜታ መንታ ገጸባህሪ ሆና የተወለደች ትመስለኛለች፡፡ ፍልይቲ መጽሐፉን አገባድጄውም ቢሆን ከአእምሮዬ ተሰንቅራ የቀረች፣ የሆነ ቦታ የማውቃት የማውቃት የምትመስለኝ ድንቅ ገጸባህሪ ናት፡፡ ደራሲው ይቺን ከሳሕል በረሀ ውጭ ዓለም ያለ የማይመስላት፣ በኤርትራ ስም ምላ፣ በወዲ አፈወርቂ ስም የምትስል የተቃጠለች ኤርትራዊት ብሔርተኛን፣ አስገደ ከሚባል አንድ ሚስኪን ኢትዮጵያዊ የቴሌኮሚኒኬሽን ኢንጂነር ጋር በፍቅር አስተሳስሮ የነገር መላ ቅጡን ያስጠፋታል፡፡ በዚህ የጦፈ የፍቅር ታሪክ ውስጥ ነው እንግዲህ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም የሚተነተንልን፡፡
እውነት ለመናገር በህወሓት እና ሻእቢያ የጫጉላ ሽርሽር መገባደድ ያልተስጓጎለውን ይህን ድንበር ዘለል የጦፈ የፍቅር ታሪክ ስለተከለሰበት ብቻ አይደለም “አውሮራ” መጽሐፍን ለመክደን የምንቸገረው። ህወሓት መቀሌ ላይ በምስጢር ያካሄዳቸው ስብሰባዎች፣ በስብሰባዎቹ ላይ የሚታየው የመለስ ዜናዊ ግትርነት፣ የገብሩ አስራት እልኸኝነት፣ የስዬ አብረሃ ጦረኝነት ወዘተ… ‹‹ልቦለድ›› በሚል የይለፍ ቃል መጽሐፉ ላይ ስለተዘከዘኩልን ጭምር ነው፡፡ በግሌ እነዚህ ስብሰባዎች ያለ በቂ ጥናት እንዲሁ በፈጠራ ተጽፈዋል ብዬ አላምንም፡፡ ምናልባት በኋላ ላይ በማኅበራዊ ድረገጾች እንደሰማሁት፤ ደራሲው ቀደም ሲል በኢህአዴግ መዋቅር ውስጥ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሆነው ለአጭር ጊዜ አገልግለዋል የሚለው ተባራሪ ወሬ እውነት ከሆነ፣ መጽሐፉ ላይ ይፋ የተደረጉልንን ምስጢራዊ ስብሰባዎች ቢያንስ ቃለ ጉባኤዎቹን የማግኘት እድል ገጥሟቸው፣ የኋላ ኋላ ደራሲው ከኢህአዴግ ቤት ወጥተው ለጻፉት ልቦለድ እንደ ግብአት ተጠቅመውበት እንደሚሆን እገምታለሁ። ተስፋዬ ገብረአብ ዛሬም ድረስ በኢህአዴግ ቤት ሳለ የሰበሰባቸውን ሀሜቶች እየመዘዘ እንደሚያስግተን አይነት መሆኑ ነው፡፡
አተራረክ
“አውሮራ” በበዓሉ ግርማ ኦሮማይ ከምናውቃት አስመራ ጋር ዳግም ለአይነስጋ የምንበቃበት የጥበብ ስራ ነው፡፡ ኾኖም አስመራን የናፈቀ ሰው መፅሀፉን ሲያነብ ናፍቆቱ ቢበረታበት እንጂ አይበርድለትም፡፡ አስመራ ከነጻነት በኋላ የኢሳያስ ሳሎን ሆናለች፡፡ ሕዝብ ኢሳያስን ያመልካል፤ ኢሳያስ ኤርትራን ያመልካል፤ ሁለቱም ሀሳቦች ግራ ለሆኑባቸው የአዲሱ ትውልድ አባላት ሁለት ምርጫ ተቀምጧል፤ ወይ ወደ ሳዋ ወይ ወደ ስደት ማዝገም፡፡ ለአዲሱ ትውልድ አባላት ኢትዮጵያ ቀኝ ገዢ ተደርጋ ትሰበካለች፣ ከአንድ ፕሬዝዳንት ውጭ ለማየት አልታደሉም፣ ሳዋ ዩኒቨርስቲ እንጂ የጦር አካዳሚ እንደሆነ አይነገራቸውም፡፡ በዚህች ምድር ላይ ለመቆየት ከሳዋ መመረቅ ወይም ቀይ ባሕርን ማቋረጥ ብቻ እጣቸው እንደሆነ ይረዳሉ፡፡ ያሳዝኑናል፡፡ እኛን እንደ ቅኝ ገዢ ከሚያስቡ የኤርትራ አዲስ ትውልድ ጋር መታረቅ እንዴት ፈታኝ እንደሚሆን ደራሲው ጠቆም አድርጎን ትረካውን ይቀጥላል፡፡
የአስመራ ሕዝብ ኢትዮጵያ ልትወረን ነው ብሎ ከልቡ አምኖ በሰላም አገር ክተት ያውጃል፡፡ አሁንም ድረስ በተጠንቀቅ ላይ እንደሆነ የምንረዳው “አውሮራን” ስናነብ ነው፡፡ “…አጋሜን እኛው ሹካ አያያዝ አስተምረናት፣ እኛው ለስልጣን አብቅተናት ዛሬ ጠግባ በኛው ተነሳች….!” እያለ ቁጭቱን በአደባባይ ይናገራል፤ የአስመራ ሕዝብ፡፡ በጥቅሉ ኤርትራዊያን አጋሜ ብለው ለሚጠሩት የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ተወላጆች ብሎም ለኢትዮጵያዊያን ያላቸውን ዝቅ ያለ ግምት የምንረዳው የመፅሃፉን ገጾች በገለጥን ቁጥር ነው፡፡
የኤርትራ የፍትህ ሚኒስትሩ አቶ ሀይላይና የፕሬዝዳንት ኢሳያስ ቁርሾ ፣ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ጄነራል ባህታ እና የነጻነት ድብቅ ግንኙነት፣ ‘የፍልይቲ እና የአስገደ እውነተኛ ፍቅር’፣ የአጋሜና የአስመራዊያን የስነልቦና ጦርነት በታሪኩ ውስጥ የተሰደሩ ጡዘትን የሚጨምሩ የስሜት እቶኖች ናቸው። ይህ ሁሉ ታሪክ ከገጽ ገጽ ሲንደረደር በድንቅ የአተራረክ ስልት በመታጀብ አንባቢው ሊገምተው በማይችለው መልኩ እየተቋጨ ስለሚሄድ የስሜት ገዢነቱ ደረጃ ከፍተኛ ነው።ምናልባት ትርክቱን አልፎ አልፎም ቢሆን የሚያናጥቡት የመልከዓ ምድር ገለጻዎች እዚህም እዚያም መሰንቀር ሊሆን ይችላል፡፡ ገጸ ባህርያት ቃለምልልስ ሲያደርጉ “…አለው” “…አላት” የሚሉ ማሳረጊያ አንቀጾች ቢቻል መገደፍ ካልሆነም መቀነስ ነበረባቸው፡፡ ኾኖም በብዙ ጸሐፊዎቻችን ላይ የማናስተውለው ስለሚጽፉት ነገር ግልብ ሳይሆን ጥልቅ መረጃን ይዞ መነሳት እንዲሁም አንድ ርዕሰ ጉዳይን ጥንቅቅ አድርጎ መገንዘብ፣ የ “አውሮራ” ጥንካሬ ሆኖ ጎልቶ ስለወጣ የመጽሐፉን ድክመቶች አንሰው እንዲታዩ ያደረገው ይመስለኛል፡፡  ደራሲው ከየት እንዳመጣው ባላውቅም የውትድርናውን ዓለም ቋንቋና ሳይንስ ከበቂ በላይ በሆነ ሁኔታ የተረዳ፤ የሁለቱን ሕዝቦች ባህልና የጦርነት ስነልቦና ከፍ ባለ ደረጃ መተንተን የቻለ፣ ጠንቅቆ የሚያውቀውን ጉዳይ ብቻ በጥንቃቄ ለመጻፍ የተነሳ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
ይህንንም በበርካታ ማሳያዎች መመልከት ይቻላል። በጦር ሜዳ ውሎ አሸናፊው የሚሆነው ወገን ማሟላት ስለሚገባው የሞራል እና የብቃት ስንቅ፣ ወታደራዊ ስትራቴጂክ ቦታዎችን ለመቆጣጠር የኃይል አሰላለፍ ምን ሊሆን እንደሚገባው፣ የዉጊያ መልክአምድርና ስነልቦና እንዴት እንደሚገነባ፣ የጦርነት ፕሮፓጋንዳ ሕዝብን እንዴት እንደሚያውር በወከላቸው ገጸ ባህሪያት አማካኝነት በአንባቢያን አእምሮ ውስጥ ምስል እየከሰተ፣ ከምዕራፍ ምዕራፍ ይዞን ይነጉዳል። ይህም የመረጃ አቀራረብ የታሪኩን ልብወለድነት መቀበል እስኪያዳግትን ድረስ ለእውነታው ዓለም ቅቡል የሆነ ስሜት ሲፈጠርብን መልሰን እንገረማለን። መጽሐፉን አጋምሰንም ልቦለድ መሆኑን በመዘንጋት ቱግ እንላለን፡፡ ደረቅ ሀቆችን ሳይታሹ እንደወረደ በማቅረብ አንባቢያንን ገጽ በሚያስቆጥሩ አሰልቺ መፃህፍት ላይ የሚታይ የአተራረክ ረሃብ እዚህ ጋ አይስተዋልም። ገጸ ባህሪያቱ የሚያደርጉት ምልልስ የተመጠነ፣ደረጃውን የጠበቀ የቋንቋ አጠቃቀም ያለው፣ የደራሲው ጣልቃ ገብነት በጣም ኢምንት የሆነ ድንቅ የጥበብ ስራ ነው ብዬ ለመመስከር እገደዳለሁ።
በቋንቋ አጠቃቀም ረገድ ምናልባት ደራሲው ሊተችበት የሚገባ ነጥብ ቢኖር፣ የትግርኛ ገለጻዎችን አቻ ትርጉም ሳይሰጥ የማለፉ ጉዳይ ነው፡፡ ምናልባት የታሪኩን ግስጋሴ ላለመግታት ሊሆን ይችላል፡፡ ኾኖም አልፎ አልፎ ወሳኝ ለሆኑ ቃላት በግርጌ ማስታወሻም ቢሆን ትርጉም መስጠት ተገቢ ይመስለኛል፡፡
ፍቅር እና ጦርነት
ፍልይቲ የመጻሐፉ ታሪክ ሃዲዱን ሳይስት ሚዛኑን ጠብቆ እስከ ፍጻሜው ድረስ በአማረ መልኩ እንዲዘልቅ የፊትአውራሪነቱን መንበር ተቆናጣ የሾፈረች ገጸ ባህሪ ናት። ፍልይቲ አንዳንዴ የምትሄድበት የመሰጠት ደረጃ ከደራሲው ምናብ ውጪ በእውኑ ዓለም የማትገኝ የፍቅር ሰማእት አድርገን እንድንቆጥራት ታስገድደናለች። ከኢትዮጵያዊው አስገደ  ሙሉጌታ ጋር እፍ ክንፍ የምትልበት ፍቅር፣ የታሪኩ አስኳል ሆኖ የተቀመጠ ሲሆን ይህንን ኢትዮጵያዊ በማፍቀሯ  የተነሳ የምታየው ውጣ ውረድ አንባቢን በስሜት አብሮ ከፍ ዝቅ የሚያደርግ ትእይንት ነው። የጦርነት ታሪክ ውስጥ ፍቅር መነስነስ የተለመደ ነው፡፡ የፍልይቲና የአስገደ ፍቅር ግን ይለያል፡፡ በሁለቱ ገጸ ባህርያት ፍቅር በኩል የሚነገረን ታሪክ የአገር ታሪክ ነው፡፡ የሁለት አንድ ነን የሚሉ ሕዝቦች ታሪክ፡፡ የሁለት በነፍስ የሚፈላለጉ ወንድማማች ህዝቦች ታሪክ፡፡
ሁለቱ አገሮች ወደለየለት ጦርነት ለመግባት አፋፍ ላይ በነበሩበት በዚያ ቀውጢ ወቅት የአስገደ እና የፍልይቲ ፍቅር በሀገሬውም ሆነ ስልጣን ላይ በነበረው የፖለቲካ አመራር ዘንድ ጥርስ የሚያስገባ ተግባር ቢሆንም ጥንዶቹ በጀብደኝነት የሚነጉዱበት ወሰን እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ የሚዘልቅ ነው። በተለይ ኤርትራያውያን ኢትዮጵያ ውስጥ እንደጸጉረ ልውጥ በሚታዩበት በድንበር ግጭት ዋዜማ፣ ለፍልይቲ የሀገሯ መንግስት የሰጣትን ከፍተኛ ሃላፊነት ገሸሽ በማድረግ ከአስመራ እስከ ደብረሲና ድረሰ የምታደርገው በውጥረት የተሞላ ጉዞ፣ የታሪኩን የልብ አንጠልጣይነት ደረጃ ከጫፍ ላይ ያደርሰዋል። ደራሲው የፍልይቲን ለፍቅር የሚከፈል ፈተና ልብ ሰቃይ በሆነ አተራረክ እስከ ታሪኩ መገባደጃ ድረስ እያዋዛ አብረነው እንድንዘልቅ ስለሚጋብዘን፣ መፅሐፉን ሳንከድን በአንድ ትንፋሽ ለመጨረስ ዳገት አይሆንብንም። በአጠቃላይ ደራሲው በልብ ሰቀላው ረገድ እጅግ በጣም እንደተዋጣለት ዋቢ የሚሆኑ ታሪኮችን ለማግኘት ብዙ መድከም አይጠበቅብንም። ጥንዶችን በጦርነት ውስጥ አፋቅሮ ልብን መስቀል በፊልምም በመጽሐፍም ብዙ የተሰራበት በመሆኑ አሰልቺ ሊመስል ቢችልም ደራሲው በአዲስ አካሄድ ሞክሮት ተሳክቶለታል፡፡
የስነልቦና ጦርነት- በ“አጋሜ” በአስመራዊያን መሐል
የህወሓት እና ሻእቢያ አፍላ ፍቅር እስከ ድንበር ግጭቱ ድረስ ንፋስ አልገባውም ነበር። ሁለቱ ግንባሮች ምንም እንኳን ለተመልካች የሚያስቀና የእርስ በእርስ ግንኙነት ያላቸው ቢመስሉም በስነልቦናው ረገድ የነበራቸው መቃቃር ግን አስደንጋጭ የሚባል ነው፡፡ ደራሲው ሳያስበውም ይሁን አስቦት የነገረን አንድ ትልቅ ጭብጥ ቢኖር ይህንኑ ነው፡፡ ሻዕቢያ በተለይም ቆለኛው ኤርትራዊ ለአጋሜዎች ያለው ንቀት ስር የሰደደ ነው፡፡ ጦርነቱ የመነጨውም ከሻዕቢያ የባድመ ይገባኛል ጥያቄ ሳይሆን ለህወሃት ካለው ፍጹም የዘቀጠ ንቀት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ከመጽሐፉ ልብወለድነት የተነሳ ይህን መሰሉ ደረቅ የታሪክ እውነታ ተደፍጥጦ ቢታለፍ የደራሲውን ገለልተኛነት በተጠራጠርን ነበር። ይህ ግን አልሆነም። ከዚህ በተቃራኒው ደራሲው ከታሪክ የሚቀዳ እውነታን ለዚህ ዓላማ በተፈጠሩ ገጸ ባህሪያት አማካኝነት መጠነኛ ግንዛቤ ያስጨብጠናል። ሻእቢያ ህወሓትን እንደ ሎሌ የሚመለከትበትን ስነልቦና ከድህረ ደርግ በኋላም እንዳልተወው በተለያዩ ገጾች ላይ በሰፈሩ ኃይለ ቃላት እንረዳለን። በገጽ 78 ላይ የኤርትራ መከላከያ ሚኒስትር የሆኑት ሰው (ጄኔራል ስብሐት እንደሆኑ ይገመታል) አዲስ አበባ በሄዱ ጊዜ በህወሓት ሊቀመንበር ሞቅ ያለ መስተንግዶ እንዳልቀረበላቸው በማመካኘት ውስጣቸው የተዳፈነውን የንቀት አመለካከት እንዴት እንደሚያፈነዱት ያሳያናል…
“…ትናንት እሽኮኮ ብለን ለስልጣን ያበቃነው የወያኔ አለቃ ከኤታማዦር ሹሙ ጋር ተነጋገር ብሎ ሆቴል ውስጥ ጎልቶኝ የአውሮፓ መሪ ለመቀበል ቦሌ ይሄዳል እንዴ?....(እስከዚህ ድረስ ንቀውናል)….”
ይህ ራስን ማማ ላይ ሰቅሎ የማየት አመለካከት በፖለቲካ አመራር ላይ በተቀመጡት ሰዎች ዘንድ ብቻ የሚያበቃ አይደለም። ተራው የሀገሬው ህዝብ ሳይቀር የሚጋራው ነው።
..በገጽ 131 ላይ አስመራ ውስጥ ፍልይቲን የጫነው አካል ጉዳተኛ ባለታክሲ እንዲህ ይናገራል…………
“..ሰላሳ ዓመት ሙሉ ተዋግተን አማራን ስንጥል አሁን ደግሞ አጋሜ በተራዋ ልትቀልድብን ተነሳች።ይህንን በዐይኔ ከማይ በቃ……የቀረውን አካሌን ብገብር ይሻለኛል ብዬ ከማንም በፊት (ለመዝመት) ተመዘገብኩ …” ይላል፡፡
ሁለቱም ግለሰቦች ስለ ህወሓት እና ስለትግራይ ሕዝብ ያላቸውን አመለካከት በምልልሳቸው ሹክ ይሉናል። ይህ ከአስመራዊያን አንጻር ብቻ አይደለም የተብራራልን፡፡ የህወሓት ጎበዝ አለቆች የኤርትራ አቻዎቻቸውን እንዴት እንደሚመለከቱም በጥልቀት ተብራርቶልናል፡፡ በተለይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ በኤርትራዊያን ላይ የሚጨክን አንጀት እንዳልነበራቸውና ይህም የኋላ ኋላ ለህወሓት መሰንጠቅ እንደዳረጋቸው አቶ ስዬ አብረሃን በሚወክሉ ገጸ ባህሪ በኩል ተነግሮናል፡፡ በወቅቱ የትግራይ ክልል ገዢ የነበሩት አቶ ገብሩ አስራት ስማቸው አይጠቀስ እንጂ ግብራቸውና ገጽታቸው እዚህም እዚያም ተጠቅሷል፡፡
ለምሳሌ ገጽ 97-98 ላይ  እኔ በግሌ እሳቸውን ይወክላሉ ያልኳቸው ገጸ ባህሪ እንዲህ ተገልጸዋል፡-
“…ከዐይኖቻቸው ተለይቶ የማያውቀውንና ከኮካ ጠርሙስ ቂጥ የተሰራ የሚመስለውን ነጭ የዕይታ መነጽር በእጃቸው አስር ጊዜ ከፍ ከፍ እያደረጉ፣ አንዴ የቀኝ ወዲያው ደግሞ የግራ ጆሯቸውን በእጆቻቸው ሌባ ጣቶች እየጎረጎሩ....ዝቅ ባለ ድምጽ መናገር ጀመሩ፣ “…አዲስ አበባ ያለው የ’ኛ አመራር በጣም ዝቅ ሲል ሀሳባዊ ነው፣ በጣም ከፍ ሲል ግን እንዝህላል ሆኖ አግኝቼዋለሁ:: እኛ ‘ፍቀዱልን፣ ከጎረቤት መንግሥት ጋር ጦርነት እንግጠም...’ ብለን አልጠየቅናችሁም እኮ:: እኛ የጠየቅናችሁ ‘እንደማንኛውም ዘመናዊ መንግሥት ዝግጅት ጀምሩ ነው:: የኤርትራ መንግሥት የወረራ ዝግጅት እያለ ይቅርና እንዲሁም ቢሆን ያበደ ነው:: ምን ለማለት ፈልጌ ነው….ፈረንጆች እንደሚሉት ‹ጦርነትን ማስቀረት የሚቻለው ለጦርነት በመዘጋጀት ነው›::’’
‘…የኤርትራ መሪዎች ኢትዮጵያን ለመውረር የሚጋብዛቸው አንዳችም መዋቅራዊ ምክንያት የለም::’ ነው የምትሉን:: ከዚህ ያለፈ መራመድ አልቻልንም:: ስለዚህ ያው ታሪክ ራሱን ይደግማል እንደሚባለው፣ ያልታደለው የትግራይ ሕዝብ በጂኦግራፊ እውነታና አዲስ አበባ ባላችሁ መሪዎች ስህተት ምክንያት የኢትዮጵያ ሕዝብ እስከሚደርስለት ድረስ እንደተለመደው ንጹህ ደሙን የሚገብርበት ጊዜ ቀናት ብቻ ቀርተውታል::’’
በታሪክ የምናወቀው ደረቅ እውነታ በዚህ መሰሉ የፈጠራ ስራ ላይ መካተቱ የአንባቢን የንቃት እና የግንዛቤ ደረጃ ከፍ በማድረግ የሚጫወተው ሚና አሌ የሚባል አይደለም።
የታሪክ አረዳድ ድክመት
የ“አውሮራ” ደራሲ ብዙ ጉዳዮች ላይ አንጀትን ቢያርስም በአንዳንድ ጥቃቅን ጉዳዮች ግን ጨጓራ መላጥም ያውቅበታል። ይኸውም የታሪክ አረዳድ ላይ እንደቀላል የተዋቸው ቁምነገሮች ኋላ ላይ ምን ያህል ክፍተት እንደሚፈጥሩ ማየት ይቻላል። ይህንንም የኤርትራ የፍትህ ሚኒስትር ተደርገው በተሳሉት አቶ ሀይላይና ሊጽፉት አስበውት በነበረው ረቂቅ መጽሐፍ ላይ እናስተውላለን። በመሰረቱ የአቶ ሃይላይ ረቂቅ መጵሐፍ የኤርትራ ታሪክ ላይ ያጠነጥናል። በመጽሐፉ መግቢያ ላይ የኢትዮጵያ መሪዎች ኤርትራ የምትባለው ሀገር እንድትፈጠር የተጨዋቱትን ሚና ያትታል።
ለምሳሌ ገጽ --61 …
“….ኤርትራዊነት ተጸንሶ የተወለደው በኢትዮጵያ ገዢዎች ስህተት ነው። እነዚህ ገዢዎች ኤርትራን በሚመለከት ምንጊዜም እርስበእርሱ የሚቃረን ፖሊሲ በመከተል ሂደቱን አፋጥነውታል። በጊዜው ስሜት ባይፈጥርም አሁን ግን ትዝታ ትቶ ካለፈው የአጼ ምኒልክ ድርጊት እንጀምር። አጼው በአንድ በኩል ኤርትራ የግዛቴ አካል አይደለችም ብለው በውጫሌ ስምምነት ለኢጣሊያ አሳልፈው ሰጡ። ነገር ግን ከአድዋ ድል በኋላ ለኢጣሊያ ተቀጥረው ሲዋጉ የማረኳቸውን 400 ኤርትራውያን አገራቸውን በመክዳት ወንጀል ከስሰው እግርና እጃቸው እንዲቆረጥ አደረጉ።…”
ይህ አይነት የታሪክ አረዳድ በእርግጥ በሻእቢያ እና በህወሓት ቤት ውስጥ እንግዳ እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ሁለቱም ዘውጌ ተኮር ግንባሮች ኤርትራን በተመለከተ የጊዜ ችካል የሚቸክሉት ከምኒልክ ዘመን መንግስት ጀምሮ ነው። ከምኒልክ ይነሱ እና ለጥቀው ኢትዮጵያን በመሩት መንግስታት ላይ የወቀሳውን ዶፍ ያወርዳሉ። ደራሲው በአቶ ሃይላይ በኩል አድርጎ ይህንን ሊደግምልን መነሳቱ እንድታዘበው አድርጎኛል፡፡ የፍትህ ሚኒስትሩ አቶ ሀይላይ በደራሲው የተሳሉት ሚዛናዊ፣ ከስሜት የጸዱ እና ባለስል አእምሮ ተደርገው ነው፡፡ ይህም በመሆኑ እንደ ገጸባህሪ የሚናገሩትንና የሚጽፉትን ነገር ሁሉ በታላቅ አክብሮት ስንቀበል እንቆያለን።
ደራሲው ይህን ባለ ስል አእምሮ ገጸባህሪ የፈጠረልን ታሪክ አንሸዋሮ ለማቅረብ ይሆን እንዴ ብለን እስከመጠራጠር የምንደርሰውም ግን በኋላ ነው፡፡ በአቶ ሀይላይ በኩል ደራሲው እንደ መሰል የትግል አጋሮቹ የኤርትራ ታሪክን በተመለከተ አጼ ዮሐንስን ከጨዋታ ወጪ አድርጓቸዋል። ወደድንም ጠላንም አጼ ዮሐንስ ኤርትራ የምትባል ሀገር እንድትፈጠር የበኩላቸውን ጡብ አቀብለዋል። አጼው ከእንግሊዝ ጋር በገቡት የ “ሂወት ስምምነት” ምክንያት በተፈጠረባቸው ተላላነት ኢጣሊያ ምጽዋና ቀይ ባህር ላይ በእንግሊዝ አማካኝነት ተደላድላ እንድትቀመጥ ሳያውቁት ትልቅ እገዛ አድርገዋል።
እንደ ማስረጃ “መክሸፍ ኦንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” በፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያም ገጽ 110 ላይ የተጠቀሰውን ማየት ይቻላል፡፡    
“…ብሪታኒያ ሂወት የሚባል የባሕር ሀይል አዛዥ ልካ ከአጼ ዮሐንስ ጋር አንድ ውል እንዲፈጽም አደረገች። በምስራቅ በኩል ኢትዮጵያን በምጽዋ ወደብ የመጠቀም መብት ለማጎናጸፍ በምእራብ በኩል ቦጎስን ለኢትዮጵያ ለመመለስ ውል ተፈራረሙ…”
እዚሁ መጽሐፍ ላይ እልፍ ብሎ በገጽ 114 የሚከተለው ነጥብ ሰፍሯል:-
“…ብሪታኒያ ምንም ሳታወጣ በኢትዮጵያ ኪሳራ በሱዳን ላይ ተጠናክራ ተደላደለች። ኢጣሊያም በሰሜን-ምስራቅ ኢትዮጵያ ተተከለች። አጼ ዮሐንስ ለብሪታኒያ ስለተንበረከኩ ኢጣልያ በቀይ ባሕር ላይ ተተከለች፡፡”
እንግዲህ ከላይ የምንረዳው የ“ሂወት ስምምነት ጦስ የባህር በር እንዲዘጋብን ኋላም ለአጼ ዮሐንስ ሞት ምክንያት መሆኑን ነው። ደራሲው አቶ ሀይላይን በኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ ፍጹም ሚዛናዊ አድርጎ ከሳላቸው አይቀር በነካ እጃቸው ሁሉንም የታሪክ ዳራዎችን በበቂ ሁኔታ እንዲሸፍኑ አለመድረጉ እንደ ከባድ ድክመት የሚተች ነው፡፡ ይህም በ “አውሮራ” ደራሲ ላይ ጥያቄ ፈጥሮብኛል። ከዚህ በተረፈ አንባቢያን መጽሐፉን አንብበው የራሳቸውን ፍርድ እንዲሰጡ ትቼዋለሁ፡፡ እኔ ግን ቅኝቴን በዚሁ ቋጨሁ።


Read 3137 times