Saturday, 23 August 2014 11:04

አዳዲሶቹ አማተሮች ይወለዱ ዘንድ እናምጥ!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

          ባለፈው ሳምንት የአዲስ አድማስ እትም ዳዊት ንጉሱ ረታ፤ የአማተር የኪነ-ጥበብ ክበባቶቻችንን ጉዳይ አንስቶ እንነጋገርበት ዘንድ ጥሪውን አቅርቧል። ዳዊት በአባቱ ሥም አቋቁሞት በነበረው (በኋላ “እሸት” ወደተሰኘ ማህበር ተቀይሯል) እኔም ተሣታፊ ነበርኩ፡፡ ምንም እንኳን በጀመርኩበት ባልዘልቅም ጥሩ የጥበብ ወዳጅ እንድሆን አስችሎኛል፤ ዳዊት እጄን ይዞ ከኪነ ጥበብ ጋር አወዳጅቶኛል፡፡ እናም ታዲያ እንደነዚያ አይነቶቹ አማተር ክበባት እንደዋዛ የመጥፋታቸው ነገር ቢያሳስበው ዳዊት ብዙ ጠይቋል፡፡ በእኔ እምነት እነዚያ ክበባት የመጥፋታቸው ሰበበ ምክንያት በርካታና ዘርፈ ብዙ ነው፤ በጉዳዩ ላይ መወያየታችን የዘገየ ቢሆንም ምን ቢመሽ ጨርሶ አልጨለመምና፣ ዳዊት በቀደደው ገብቼ ጥቂት የማምንበትን ለማለት እሞክራለሁ፡፡

በከተማችን አዲስ አበባና በሌሎች ክልሎች ወጣቶች ለጥበብ ያላቸውን ፍላጎት፣ ተሰጥዖና ዝንባሌን መነሻ እያደረጉ፣በራሳቸው ተነሳሽነት በት/ቤቶችና ቀበሌ አዳራሾች የተፍጨረጨሩበትና ክበባቶቹ በርክተው የተስተዋሉበት ወቅት እንደነበረ ባይዘነጋም፣ ከ1990ዎቹ አጋማሽ ወዲህ እየተቀዛቀዙ… አሁን አሁን ከእነ አካቴው ጠፍተዋል። በእነዚያ ዓመታት ተሰጥኦና ዝንባሌን መሰረት አድርገው ከጥበብ ጋር በጥልቀት እያስተዋወቁ፣ በሙያዊ ሥነ ምግባር እያነፁ፣ እምቅ ችሎታንና ብቁ ክህሎት እያስታጠቁ፣ ልከኛ ጥበበኞችን ለመድረኮቻችን ያበረክቱ የነበሩ ክበባት ዛሬ ላይ የሉም፡፡ አፍላ ጥበበኞችን የሚኮተኩቱ፣ ጥሩ ባለሙያ የማያመርቱ ክበባት እንዲሁ ዝም ብለው አልከሰሙም፤ ደጋፊ፣ አጋዥና “አለሁ” ባይ እያጡ፣ ተሰባስቦ ጥበብን መከወኛ ሥፍራ እየተነፈጉ፣ ትላንት ኮትኩተው ያሳደጉት የዛሬው ዝነኛም አዙሮ የመመልከት አቅም አጥ ሆኖ፣ ውለታቸውን እየዘነጋ የሚተኩትን ተከታይ ባለተራዎችን ማገዝ የተሳነው የመሆኑን ነገር እንደ አንድ የመክሰማቸው ምክንያት ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡

በእግር ኳስ የስፖርት ሜዳ ተጋጣሚ ቡድኖች ወደ ሜዳ ሲገቡ ታዳጊ ህፃናትን አስከትለው የሚገቡት ለምን ይመስለናል? ተኪነትን ለማጎልበትም አይደል? በአገራችን የጥበብ ሜዳችን ላይስ? ገጣሚና ጋዜጠኛ ነቢይ መኮንን በአንድ ግጥሙ “የሀገሬ ሰው እኮ መሠላል አወጣጥ ያውቃል” እንዳለው፤ የሃገሬ ዝነኛ ከያኒያን መሰላሉን እየወጡ የረገጡትን እየነቀሉ ይሆን? ለአማተር ክበባቶቻችን መክሰምና ለአዳዲስ ክበባቶች አለመፈጠር እንደ ጉልህ ምክንያት ሊወሰድ የሚገባው ሌላ ነገር መንግስታዊ ቸልተኝነትና ዝንጋታ ነው! ጥቂት ማሳያዎችን እንመልከት፡- መንግስት የወጣቶችን የሥራ አጥነት ለመቅረፍ “የጥቃቅንና አነስተኛ ሥራዎች ልማት ፕሮግራም” አዘጋጅቶ እየተገበረ እንደሆነ ይታወቃል። ግን ደግሞ በኪነ ጥበባዊ ሥራዎች ላይ ተደራጅቶ ስለመስራት መንግስታዊ ፕሮግራሙ የሚለው ነገር የለም፤ ቴአትር ለማዘጋጀት፣ የግጥም መፅሐፍ ለማሳተም ወይ ደግሞ ፊልም ሰርቶ ለማሳየት ብድር አይሰጥም… ማበረታቻም የለም፡፡ በመላው አገሪቱ ባሉ ክልሎችና ከተማዎች (እስከታችኛው መንግስታዊ መዋቅር ድረስ) ባህልንና ኪነ-ጥበብን የማስፋፋት ኃላፊነት የተጣለበት በአዋጅ የተቋቋመ “ባህልና ቱሪዝም መ/ቤት” ቢኖርም አማተር ክበባትን ለመፍጠር ሲጨነቅ አይስተዋልም፡፡

በአንድ ወቅት እኔው እራሴ ወደ አዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሄጄ፣ አማተር ክበብ ለመመስረት ሞዴል /መነሻ/ መተዳደሪያ ደንብና ሌሎች መስፈርቶች ጠይቄ ማግኘት አልቻልኩም፤ ግን ደግሞ ካፒታል ኖሮት፣ ንግድ ፈቃድ አውጥቶና ሰፊ በጀት መድቦ ፕሮሞሽንና የፊልም ፕሮዳክሽን በማቋቋም በጥበባዊ ንግድ ስራ ላይ መሰማራት ለሚፈልግ ሰው፣ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ለመስጠት ግልፅ መሥፈርት ወጥቶ፣ ባለሙያ ተቀጥሮ፣ የስራ ሂደት ቢሮ ተከፍቶላት አይቻለሁ፡፡ ይህ ቢሮ በከተማ ደረጃ ከቅርብ አመታት ወዲህ አማተሮች የሚወዳደሩበት የባህል ፌስቲቫል በአመት አንድ ጊዜ ብቻ እያዘጋጀ ይገኛል፤ ለአማተር የኪነ ጥበብ ባለሙያ አፍላ ወጣቶቻችን ነፃና የአጭር ጊዜ የተሰጥኦ ማጎልበቻ የሥልጠና እቅድ ይዞ መስራት እንኳን አልተቻለውም፡፡

ቴአትር ቤቶቻችንም ለአማተሮቹ በራቸው ዝግ ነው፤ የተተመነውን የአዳራሽ ኪራይ ክፍያ መክፈል ካልቻሉ በስተቀር በነፃ ወይም በዝቅተኛ የኪራይ ዋጋ መድረኮቻቸውን አይቸሩም፡፡ በየት/ቤቶቻችን “የተጓዳኝ ትምህርት ክፍል” በሚል የሚኒ ሚዲያ፣ የቴአትርና የሙዚቃ ክበባት ተመስርተው ተማሪዎች ከመደበኛው የትምህርት ክፍለ ግዜ ውጪ ይሳተፉባቸው የነበሩ ቡድኖች ዛሬ የሉም፤ ቢኖሩም በጣት የሚቆጠሩና የተፋዘዙ ናቸው፡፡ በርካታ የሬድዮ ጣቢያዎች፣ ሁለትና ሶስት የቴሌቪዥን ቻናሎች እያሉን ለአማተሮች የሚሆን ነፃ የአየር ሠዓት ግን የለንም፤ የተለያዩ የኪነ-ጥበብ (በተለይ የሥነ-ፅሁፍ) ሥራዎች በአማተሮች አማካኝነት ይቀርቡባቸው የነበሩ ማዕከላት እነ ፑሽኪን (የሩሲያ የሳይንስና ባህል ማእከል)፣ ኢትዮ አሊያንስ ፍራንሴስ እና ገተ… እንኳን ዛሬ ዛሬ ተፋዘዋል፡፡ እነዚህም ቢሆኑ በውጭ ሀገራት ኤምባሲዎች መልካም ፈቃድ የተቋቋሙ ማዕከላት መሆናቸውን ስናስተውል እንደ ሀገር አማተሮች ምን ያህል እንደተዘነጉ እንረዳለን፡፡ አስገራሚው ነገር ደግሞ ትላንት ከትላንት ወዲያ የመከወኛና የመሰባሰቢያ ሥፍራ ባልነበረበት እንደ አሸን የፈሉ ክበባት፣ ዛሬ በተለይ በከተሞቻችን “የወጣት ማዕከላት” በየመንደሩ ተገንብተው እያለ፣ የማዕከላቱ አዳራሾች ተሰብሳቢ ጭብጨባ እንጂ የአማተሮቻችን ድምፅ አይሰማባቸውም፡፡

ለምን?? የሙያ ማህበሮቻችንስ? የደራሲያን ሆነ የፊልም ሰሪዎች፣ የሙዚቀኞች ይሁን የቴአትር ባለሙያዎች… ብቻ የቱም ይሁን፤ ጊዜ ቀንቷቸው በፕሮፌሽናል መድረኩ ላይ ላሉት እንጂ ለአማተሮቹ ምን ቦታ አላቸው? ምንም! በደራሲያን ማህበር አባል ለመሆን መፅሐፍ ማሳተም እንጂ መፃፍና ሥነ-ፅሁፋዊ ተሰጥኦ እንደመስፈርት አይቆጠርም፡፡ የትላንቶቹ አማተር ክበባት ለበርካታ ማህበራዊ ችግሮቻችን መወገድ ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ የኤችአይቪ/ኤድስ በሽታ ዛሬ ላይ ስርጭቱ እንዲቀንስ፣ ታማሚዎች ላይ ይደርስ የነበረው አድሎና መገለል እንዲቀር እነዚያ ክበባት መዝሙር ዘምረው፣ ድራማ ሰርተውና ግጥም ፅፈው ህብረተሰቡ አዎንታዊ የባህርይና የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጣ ተረባርበዋል፡፡ ኤችአይቪ/ኤድስ የስርጭቱ መጠን እየቀነሰ ቢመጣም ሌሎች ችግሮች የሉብንም? የባህልና ትውፊት መጥፋቱስ? ከምዕራብ ሀገራት በአስገራሚ ፍጥነት እየወረሩን ያሉ መጤና ጎጂ ልምዶችስ?... የአማተር ክበባቶቻችን ጥበባዊ ውጊያ አያሻቸውም? በሁለንተናዊ የ“ህዳሴ” ጉዞ ላይ እንደምንገኝ በተደጋጋሚ ይገለፃል፡፡

ለመሆኑ የ“ህዳሴ ጉዞ” ጥበባዊ እገዛ አያስፈልገውም? በዜጎች ደረጃ የአመለካከት ለውጥ ሳይመጣ ያደገና የበለፀገ ሃገር የትኛው ይሆን? አብዝቶ የሚወራለት “ልማታዊ ኪነ-ጥበብ” እንዴትና በማን አማካኝነት ነው ሊሰራ የሚችለው? በአማተሮችና በክበባቶቻቸው አይደለምን? ሀገር ያለወጣት ምንም ናት! መተካካት ደግሞ ተፈጥሮአዊ ህግ ነው! ኖሮ ኖሮ ማለፍ ግድ ነው!... አይቀርም! ስለ ነገው የኪነ-ጥበብ ኢንዱስትሪያችን ሥናስብ፤ ተተኪን ኮትኩቶ ስለማሳደጉ ካልተጨነቅን ነገን ማሰብ ትርፉ ድካም ይሆናል፡፡ የንጉሱ ረታ ልጅ ዳዊት እንዳለው፤ ማንም በነሸጠው ግዜ አሊያ ደግ ገንዘብ ስላለውና መንገዱ አልጋ ባልጋ ስለሆነለት ወይም መልክና ቁመናው ስላማረለት ብቻ ወደ ጥበብ ባህር ዘሎ እየገባ “ልዋኝ” ካለ መንቦጫረቅ ይሆንና ባህሩ ይረበሻል፤ ሲብሥም ሊደርቅ ይችላል፡፡ የባህል ፖሊሲያችን ሊከለስ፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ፕሮግራሙም ሊሻሻል፣ የባህልና ቱሪዝም መ/ቤቶቻችንም ቆም ብለው ሊያጤኑ፣ ባለ ጊዜዎቼ “ጥበበኞችም” አንገታቸውን አዙረው ሊመለከቱ ግድ ነው! የጠፉት ክበባት ይመጡ ዘንድ እንትጋ! አዳዲሶቹ አማተሮችም ይወለዱ ዘንድ እናምጥ!!

Read 2117 times