Saturday, 16 August 2014 10:56

የተሰነጠቀ መነፅር እይታ ያወላግዳል

Written by  መስፍን ጌታቸው (“የሰው ለሰው” ድራማ ደራሲ)
Rate this item
(0 votes)

“ሰው ለሰው” ድራማ ከሶስት ዓመት ተኩል በላይ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲታይ ቆይቶ በቅርቡ ተጠናቋል:: “አዲስ አድማስ ጋዜጣ”ም ድራማው ከተጠናቀቀበት ሳምንት አንስቶ ባሉት ሶስት ተከታታይ ሳምንታት ድራማውን የተመለከቱ አስተያየቶች ሲያስተናግድ ቆይቷል::
ጋዜጣውም ሆነ ፀሐፊዎቹ ለድራማችን ትልቅ ትኩረት በመስጠት የመወያያ ርዕሰ ጉዳይ በማድረጋቸው ምስጋና ይገባቸዋል:: ነገር ግን አስተያየቶቹ የድራማችንን ጉድለቶች ያስተጋቡትን ያህል ጠንካራ ጐኖቹን በጨረፍታ እንኳን ለማሳየት አለመሞከራቸው ቅሬታ ፈጥሮብናል:: “ሰው ለሰው”ን እዚህ ለማድረስ ከአራት አመት በላይ እጅግ በጣም ከፍተኛ መስዋዕትነት ተከፍሎበታል::
በድራማው ላይ አገራችን ውስጥ አሉ የሚባሉት ታላላቅ ተዋንያን በተለያየ ደረጃ ተሳትፈውበታል:: እነዚህ ተዋንያን ከራሳቸው ጥቅም ይልቅ የተመልካቹን እርካታ በማስቀደም ለቀረፃ ሲመጡ ከሚያወጡት ወጪ ባነስ ክፍያ የራሳቸውን አልባሳት እየተጠቀሙ፣ ከከተማ ውጪ ሲጓዙም ያለምንም የአበል ክፍያ ክብራቸውን በማይመጥን ደረጃ በደቦ በልተው፣ በደቦ እያደሩ አልባሌ ቦታ እየተኙ፣ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በጣም ውድ ዋጋ ከፍለዋል::
ድካማቸው ግን ከንቱ ሆኖ አልቀረም:: በቀላሉ ለማመን የሚከብድ ትልቅ ፍቅርና ክብር ከህዝብ ዘንድ አትርፎላቸዋል:: ከህፃን እስከ አዋቂ፣ ከምሁር እስከ መሀይም፣ ከሊስትሮ እስከ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት… በድራማው ተማርከዋል። ረቡዕ ምሽትንም አባቶች ቤታቸው በጊዜ ገብተው  ከልጆቻቸው ጋር በደስታ እየተጫወቱ የሚያመሹበት ተወዳጁ የቤተሰብ ቀን ለማድረግ ችለዋል፡፡ ድራማውም ሆነ አርቲስቶቹ ሦስት ዓመት ሙሉ ትልቅ የሚዲያ አጀንዳ ለመሆንም በቅተዋል፡፡
ይሄ ሁሉ ስኬትና ተወዳጅነት ቅንጣት ታህል ቦታ ሳይሰጠው ድክመት መስለው የታየቱን ብቻ ያውም በተወላገደ እይታ መርጦ መቀጥቀጥ ፍፁም ተገቢ ባለመሆኑ በእጅጉ ቅር ያሰኛል:: ድራማውን በተመለከተ ሂስ የቀረበው በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ብቻ አይደለም:: በተለያዩ ሬዲዮኖችና መፅሄቶች እንዲያውም በአንዳንድ የሬዲዮ ጣቢያዎች በአንድ ቀን በሚቀርቡ የተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ ሳይቀር ሁለቴና ከዚያም በላይ ተደጋግሞ ስለ “ሰው ለሰው” ብዙ ተብሏል::
መጀመሪያ አካባቢ የነበረው የኛ አቋም በተለያየ መንገድ የሚነሱትን ሀሳቦች በጥሞና አድምጦ፣ በመጨረሻ የኛ ሀሳብ በሚቀርብበት የቴሌቪዥን የአስተያየት መስጫ ፕሮግራም ላይ አጠቃሎ ምላሽ መስጠት ነበር::
ነገር ግን አስተያየቶቹ ካሰብነውና ከጠበቅነው በላይ ከመብዛታቸው በተጨማሪ የተመልካቹንም ስሜት ሊበርዙ የሚችሉ ሆነው ስላገኘናቸው በቴሌቪዥን የምንሰጠው ምላሽ እንደተጠበቀ ሆኖ በዋናነት በተነሱት የህግ የበላይነት፣ የማህሌት የአስናቀ ገዳይ መሆን፤ የፍሬዘርና የልዑል ቆመው አስናቀን ማስገደል፣ የእነሶስና ታሪክ በተለይም ደግሞ የሞገስ የልኩን አባትነት አሳልፎ መስጠት ወዘተ በሚሉት ጉዳዮች ላይ ሀሳባችንን ለመግለፅ ወደናል::
የህግ የበላይነት
ድራማችን ላይ የህግ የበላይነት ጥያቄ የተነሳው አስናቀ በጊዜ ተይዞ ለፍርድ ባለመቅረቡ የተነሳ ነው:: በዚህም ሳቢያ ብዙዎች “ሰው ለሰው” አገራችን ውስጥ የህግ የበላይነት የለም የሚል መልክት እንዳስተላለፈ፣ ፖሊሶቹም ሆኑ አለቆቻቸው ደካሞችና ብቃት የሌላቸው አድርጎ እንዳቀረበ በመግለፅ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል::
ድራማው እንዲህ ያለ መልዕክት አስተላልፎ ከሆነ በጣም ያሳዝናል:: ድራማችን ገና ከመነሻው የህግ የበላይነትን እንዲሁም ፖሊስም ዝም ብሎ የሚፈራና ያገኘውን ሁሉ ያለ ማስረጃ የሚያስር ሳይሆን በእውነትና በምክንያት የሚመራ፣ እንደኛው ሰዋዊ ስሜት ያለው ህግ አስከባሪ መሆኑን ለማሳየት አልሞ የተነሳ መሆኑን ልንገልፅ እንወዳለን::
እንዲህም ሆኖ የአንድ አገር የህግ የበላይነት የሚለካው በህጉ አፈፃፀምና አተገባበር ነው እንጂ በፊልም፣ በቴአትር፣ በድራማና በሌሎች መሰል የኪነ-ጥበብ ውጤቶች አይደለም::
ይሄ ቢሆንማ ኖሮ ከራሷ አልፋ በመላው አለም የህግ የበላይነትን የማስከበር ሀላፊነት እንዳለባት ቆጥራ፣ ከፍተኛ የፖሊስና የሚሊቴሪ አቅም በመገንባት በሁሉም የአለማችን ክፍሎች ሀያ አራት ሰአት ሙሉ ደፋ ቀና የምትለው አሜሪካ ህግ የሌለባት አገር በተባለች ነበር::
አብዛኞቹ የሆሊውድ ድራማዎች፣ ፊልሞችና ሌሎች የኪነ-ጥበብ ውጤቶች ከአገራቸው አልፎ በሌሎችም አገራት ለማመን የሚከብዱ ዘግናኝ ወንጀሎች እንደሚፈፀሙ፣ በጥቂት ግለሰቦች ሴራ አገሮች በከፍተኛ ወረርሽኝ እንደሚጠቁ፣ ግለሰቦች የኒኩሊየር መሳሪያ በመታጠቅ እንዴት ለአለማችን ጠንቅ እንደሚሆኑ ወዘተ ደጋግመው አሳይተውናል:: በአብዛኛው በጥበብ ስራዎቹ እንደሚታየውም እነዚህን አደገኛ ሰዎች በጀግንነት የሚያሸንፈው አንድ ብርቱ አሜሪካዊ እንጂ ፖሊስ አይደለም::
ይህም ሆኖ ግን ፊልምና ድራማ ፈፅሞ የአንድ አገር የህግ የበላይነት ማሳያዎች ባለመሆናቸው አሜሪካንን ህግ አልባ ምድር አላሰኟትም:: ፊልሞቿና ድራማዎቿ በተደጋጋሚ ጥቂት ወሮበሎች ሰብሰብ ብለው መሳሪያ በመያዝ ከተሞቿን ሲቀውጡና ከዳር እስከዳር ሲያነዱ እንደማሳየታቸው ቢሆን አገሪቱን ፈፅሞ ለኑሮ የማትመች መጥፎ አገር እንደሆነች አለም አምኖ እንዲቀበል ማድረግ በቻሉ ነበር::
እውነቱ ግን እንደዚያ አይደለም፡፡ ፊልምና ድራማ የሰው ልጆች ጭንቅላት የፈጠራቸው ልቦለዶች እንጂ እውነተኛ የህይወት ግልባጮች ባለመሆናቸው አገራችንን ጨምሮ በበርካታ አገራት የሚገኙ ወጣቶች አሜሪካንን የተስፋ ምድር አድርገው በመቁጠር፣ ቪዛ ያግኙ አያግኙ እንኳን ሳያውቁ ብዙ ሺህ ብሮችን እየከፈሉ የኤምባሲዎቹን ደጃፍ ሲያጨናንቁ ይውላሉ::
እንደውም እንደኛ እምነት “ሰው ለሰው” እስከዛሬ በአገራችን የኪነ-ጥበብ ስራዎች ባልታየ መልኩ ስለህግ የበላይነት ትልቅ ትምህርት ማስተላለፍ የቻለ ድራማ ነው፡፡
በነገራችን ላይ በርካታ የሚዲያ ውጤቶች ድራማው በአገሪቱ የህግ የበላይነት የለም የሚል መልዕክት አስተላልፏል ያሉትን ያህል አያሌ ተመልካቾች ህግን በተመለከተ ድራማው ትልቅ ግንዛቤ እንደሰጣቸው ገልፀዋል፡፡
እነዚህ ሁለት የአስተሳሰብ ፅንፎች መፈጠራቸው ለእኛ እንደ ትልቅ ስኬት የሚቆጠር ነው፡፡ ምክንያቱም ድራማው በህግ የበላይነት ዙሪያ ከፍተኛ ክርክርና መነቃቃት መፍጠሩ ሰዎች ስለህግ የበላይነት ያላቸውን ግንዛቤ ያሰፋዋል ብለን እናምናለን፡፡
አሁን ወደ ድራማችን ታሪክ እንመለስ:: በየትኛውም አለም የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሚችሉ ሁለት መሰረታዊ ነጥቦች አሉ:: እነሱም:-
ወንጀል ሲፈፀም ወንጀለኛውን በበቂ ማስረጃ በቁጥጥር ስር አውሎ ለፍርድ በማቅረብ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ ማድረግ ሲሆን
አንድ ሰው የቱንም ያህል የከፈና ተደጋጋሚ የሆነ ወንጀል ቢፈፅም እንኳን በቂ የሆነ አሳማኝ ማስረጃ እስካልተገኘበት ድረስ ያለ አግባብ ተይዞ እንዳይጉላላ መከላከል ናቸው::
እንግዲህ ድራማችን ሲጀመር እነዚህን ሁለት መሰረታዊ ነጥቦች በዋነኛነት ይዞ ነው የተነሳው:: ወንጀለኛን ይዞ ለፍርድ ማቅረብ የሚያስፈልገውን ያህል ዜጎች ያለበቂ ማስረጃ ያለመያዝ መብት ያላቸው መሆኑን በአግባቡ ማሳየት ስንችል ብቻ ነው ስለ ህግ የበላይነት ሙሉ መልክት ማስተላለፍ የምንችለው በሚል እሳቤ ነው  የድራማችንን ታሪክ የቀረፅነው::  
በዚህ መሰረት በርካታ ወንጀለኞች ድራማችን ውስጥ በፖሊስ ጥረትና ጥበብ ተይዘው ለፍርድ ሲቀርቡ ተመልክተናል:: ከእነዚህ ውስጥ መጀመሪያ አካባቢ በህክምና ስህተት ለታማሚዋ ሞት ምክንያት የሆነችው ነርስ፣ ለሚስቴ ነፍስ መጥፋት ምክንያት ሆናለች ብሎ ያሰባትን ነርስ ገድሎ የተሰወረው አባወራ፣ ከወንጀለኞች ጋር ተባብሮ ምስጢር ሲያሾልክ የነበረው የፖሊስ ባልደረባ፣ ማህሌት፣ የብሩክ ወጊዎች፣ ናርዶስ የፍሬዘር ሚስት፣ ጠላፊዎችና የመሳሰሉት በዋነኛነት ሊጠቀሱ ይችላሉ::
በተለይ ፖሊስ ነርስ ገድሎ የተሰወረውን አባወራ፣ የሚወደውን ልጁን በመጠቀም ከተደበቀበት ወጥቶ ፖሊስ ቀለበት ውስጥ እንዲገባ ያደረገበት ጥበብና ይጥናን ለመያዝ የከፈለው መስዋዕትነት እንዲሁም ምስኪኗን እህቱን አሳልፎ የሰጠበት መንገድ… ወንጀልን ለመከላከልና ወንጀለኛን ለህግ ለማቅረብ ምን ያህል ርቆ እንደሚጓዝ ማሳየት የሚችል ይመስለኛል::
በኛ እምነት እነዚህ ታሪኮች አንደኛውን የህግ ልዕልና ማረጋገጫ ማለትም ወንጀለኞች በበቂ ማስረጃ በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ለህግ የሚቀርቡበትን ለማሳየት ከበቂ በላይ ይመስሉናል:: ወይም ናቸው ብለን በማመናችን ነው የተጠቀምንባቸው፡፡
ሌላውና ትልቁ ወንጀለኛ አስናቀ ነው፡፡ አስናቀን እስከ መጨረሻው ድረስ ሳይያዝ እንዲቆይ ያደረግነው ሁለተኛውን የህግ ልእልና ማረጋገጫ ማለትም ማንኛውም ሰው በቂ የሆነ ማስረጃ  እስካልተገኘበት ድረስ የህግ ተጠያቂ ሊሆን አይችልም የሚለውን እንዲያሳይልን በማሰብ የፈጠርነው ገጸ-ባህሪ ስለሆነ ነው።
ደግሞም ሳይያዝ እንዲቆይ ስለፈለግን ብቻ አይደለም እንዳይያዝ አድርገን ያቆየነው፡፡ መጀመሪያ አካባቢ በቂ ማስረጃ ስላልተገኘበት፣ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ እሱን በቁጥጥር ስር በማዋል ሊመጣ የሚችልን ታላቅ አገራዊ ጥፋት ለመከላከልና በኋላ ለመያዝ በማሰብ ነው፡፡
እስኪ እዚህ ጋ አንድ አፍታ ሃሳባችሁን ሰብሰብ አድርጋችሁ በጥሞና አስቡት፡፡ የትኛው በበቂ ማስረጃ የተደገፈ ወንጀል ነው አስናቀን ተጠያቂ ሊያደርገው የሚችለው?
የአስናቀ የመጀመሪያው ወንጀል የመዲን ወንድም በይጥና ማስገደሉ ነው፡፡ በመጀመሪያ ፖሊስ፤ ይጥናም ሆነ አስናቀ እንዲሁም ማህሌት፣ መስፍን፣ ብሩክ፣ ሶስና… የሚባሉትን ሰዎች አያውቃቸውም፡፡
ፖሊስ መጀመሪያ ያገኘው የመድሃኒት ወንድም የሆነውን የታምራትን አስከሬን ነው፡፡ እሱም ግድያው ከተፈጸመበት ቦታ በጣም የራቀ መንገድ ዳር  መኪናው ውስጥ  ሞቶ   ምንም አይነት ፍንጭ በሌለበት ቦታና ሁኔታ ነው፡፡
በዚህ መሰረት  ብሩክን በቁጥጥር ስር አውሎ ገዳይ ብሩክ አለመሆኑን የሚያሳይ መረጃ ሲያገኝ እሱን በዋስ ለቆ ማንነቱ ያልታወቀውን ወንጀለኛ መፈለግ ጀመረ፡፡
ፖሊስ አስናቀ የሚባል ሰው ከወንጀሉ ጀርባ እጁ ሊኖርበት እንደሚችል ማስረጃ ሳይሆን መረጃ ያገኘው ከብዙ ጊዜያት በኋላ (ክፍል 80 አካባቢ) ማህሌት እና ጸደይ ቃላቸውን ሲሰጡ ነው፡፡
ከእነሱ ቃል የተገኘው መረጃ ደግሞ አስናቀን በወንጀል  ማስጠየቅ የሚያስችል አይደለም፡፡ ማህሌት ቤቷ በር ላይ ያገኘችው አስከሬ አስደንግጧት ስትደውልለት፤ “አርቀሽ ጣይው” ብሎ እንደመከራት ነው የተናገረችው፡፡
ጸደይም ብትሆን አስናቀ ቀኑን ሙሉ ከቤት ሳይወጣ ከይጥና ጋር እየተደዋወለ  ስራውን በደንብ እንዲሰራ ሲያዘው እንደነበር፣ እኩለ ሌሊት ላይም “ ጨርሰው”  የሚል ትእዛዝ እንዳስተላለፈ ፣ከዛ በኋላም ድርጊቱን ሲፈጽም አይታ የጠፋችውን ልጅ ባለማግኘቱ ሲጣሉ እንደነበር ነው የገለጸችው፡፡
እነዚህ ሁሉ መረጃዎች እንጂ ማስረጃዎች አይደሉም። መረጃዎች ደግሞ መርማሪው ፖሊስ ከወንጀሉ ጀርባ ያሉትን ዋነኛ ተጠርጣሪዎች አውቆ በእነሱ ዙሪያ ማስረጃዎች ማሰባሰብ እንዲጀምር ያደርገዋል እንጂ ተጠርጣሪዎችን ፍርድ ቤት አቅርቦ ለማስቀጣት አያስችለውም፡፡
ስለዚህ የወንጀሉን አፈጻጸም በአሳማኝ ሁኔታ ለፍርድ ቤት አስረድቶ ወንጀለኞችን ለማስቀጣት ፖሊስ ግድያው ሲፈጸም አይታለች የተባለችውን ማንነቷ የማይታወቅ ወጣት  ሴትና ይጥናን ፈልጎ ማግኘት ፣ማግኘት ብቻም ሳይሆን ቃላቸውን ማውጣጣት ነበረበት፡፡
ቃላቸውን አውጣጥቶ በቂ ማስረጃ ካገኘ በኋላ አቶ አስናቀን በቁጥጥር  ስር ለማዋል ሲነሳ ደግሞ ሌላ አስደንጋጭ መረጃ ደረሰው፡፡ አስናቀ ትልቅ አገራዊ ጥፋት ሊያደርሱ  የሚችሉ የተበላሹ ወተቶች እያስገባ ነበር፡፡    
እነዚያ የተበላሹ ወተቶች የበርካታ ህፃናትን ህይወት ሊያጠፉ ይችላሉ:: በዚህ ላይ በቀላሉ ሊያዙ በሚችሉበት ሁኔታ አይደለም ወደ አገር ውስጥ እየገቡ ያሉት:: በተበታተነ ሁኔታ በኮንትሮባንድ ነው የሚገቡት::
ወተቶቹ በጣም አደገኞች ስለሆኑ ሙሉ ለሙሉ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋል አለባቸው:: በኮንትሮባንድ የሚያጓጉዙትን ሰዎች ቀጥሮ የሚያሰራቸው ደግሞ አስናቀ ነው:: ስለዚህ አስናቀ ከታሰረ ኮንትሮባንዲስቶቹ የሚያስረክቡት ሰው ስለማይኖር፣ የሰሩበትን ገንዘብ ለማግኘትም በማሰብ ወተቶቹን በራሳቸው መንገድ ለገበያ ሊያቀርቧቸውና ትልቅ ጥፋት ሊያደርሱ ይችላሉ::
አሁን ፖሊስ ያለው አማራጭ ሁለት  ብቻ ነው:: አንድም የመጣው ይምጣ ብሎ አስናቀን በቁጥጥር ስር ማዋል አሊያም ወተቶቹ ተጠቃለው እስኪገቡ ድረስ አስናቀን በስውር የፖሊስ ክትትል ስር አውሎ መጠበቅ:: ማንም ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰው በቀላሉ እንደሚረዳው፤ ሀላፊነት የሚሰማው ፖሊስ ማድረግ የሚገባው ሁለተኛውን በመሆኑ፣ በዚሁ መሰረት ፖሊስ ወተቶቹ ተጠቃለው እስኪገቡ ድረስ በትዕግስት ጠብቆ ጊዜው ሲደርስ አስናቀን በቁጥጥር ስር ለማዋል ተንቀሳቅሷል:: በየትኛውም መለኪያ ብንመዝነው፣ ትክክለኛው የፖሊስ ስራ ይሄ ነው:: ከዚህ ውጪ አስናቀ ማህሌትን በማስገደድ ብዙ ገንዘብ ዘርፎ፣ ሊያን ጫካ ውስጥ አስደብድቦ ወዘተ ተደራራቢ የሆኑ ብዙ ወንጀሎችን ሰርቷል::
ነገር ግን የወንጀሎቹ ሰለባ የሆኑት ግለሰቦች በተለያዩ የራሳቸው ምክንያቶች ወንጀሎቹን ለፖሊስ ማመልከት አልፈለጉም:: ፖሊስ ደግሞ ራሳቸው ተበዳዮቹ ደፍረው ሊገልፁት ያልፈለጉትንና በድብቅ የተፈፀመን ወንጀል ሊያውቅ የሚችልበት ምንም አይነት መንገድ የለውም::
ሌላው እንደችግር የተነሳው ነጥብ፣ አስናቀ በቁጥጥር ስር ሲውል ሳይታይ ድራማው ማለቁና አስናቀ በህግ አለመሸነፉ ነው:: ግን እውነት አልተሸነፈም እንዴ?... አስናቀ መንኮታኮትና ተስፋ ቢስ መሆን የጀመረው እኮ በፖሊስ ክትትል ስር መውደቁን ካወቀ በኋላ ነው:: ፖሊስ ዙሪያ ገባውን አጥሮ መግቢያ፣ መውጫ ሲያሳጣው የሚመካባቸውን ወተቶች በጠቅላላ በቁጥጥር ስር አውሎ ሙልጭ ሲያስቀረው አይደል እንዴ መውጫ ቀዳዳ መፈለግ የጀመረው? በመጨረሻስ በፖሊስ ቁጥጥር ስር አልዋለም ማለት ይቻላል እንዴ?...
የዚህን መልስና መልሱንና ሌሎች አነጋጋሪ ጉዳዮችን ሳምንት እመለስባቸዋለሁ ለዛሬው አንባቢዎቼን አመስግኜ እሰናበታለሁ:: ሰላም!!

Read 1781 times