Saturday, 02 August 2014 11:54

ፈጣሪው

Written by  አወል መሃመድ
Rate this item
(7 votes)

          ድም…ድም… ድርድም… ይላል፤ በአካባቢው የሚነፍሰው ድምፅ፡፡ የተመረጡ የድምፅ ጥርቅሞች ይወዛወዛሉ፤ ላላፊ ጆሮ ይደመጣሉ። ድምፅን ማላወስ የሚችል ጆሮ ካገኘ፣ ሰሚውን የሚያፀድቅ ጥዑም ዜማ ይነፍሳል፡፡ የአእምሮውን ምህዋር ተቆጣጥሮ መላ ገላውን ያድሳል፡፡ እነዚህ ድምፆች፣ ከጠቢብ ጆሮ ቢደርሱ፣ የዜማቸውን ቅኔ ለመፍታት በሚል ምክንያት ከድምፁ ጋር እንዲጋባ፣ የሚያስገድድ ኃይል አላቸው፡፡
ድምፆቹ የሚፈልቁት ከዝግ ቤት ውስጥ ነው። የዜማው ፈጣሪ ቤቱን ዘግቶ እነዚያን ውብ የነፍስ ምግቦች የሚዘራው ከአንዲት ደረቅ ወንበር ላይ ተቀምጦ ነው፡፡ በታፋዎቹ መሃል ያኖረውን የጊታር ማሳ፣ በስድስት ክሮቹ ጠምዶ እያረሰ በጣቱ ሲያርማቸው፣ በአካባቢው ረቂቅ ዜማ ያብባል፡፡
ዜመኛው ለአፍታ መፍጠሩን አቁሞ ቀና ብሎ ወደፊት ለፊቱ ሲመለከት ከውቡ ሶፋ ላይ ተቀምጣ ታዳምጠው የነበረችዋ ፀሐይ፣ ቆንጆ ፈገግታዋን ጋበዘችው፡፡ እንደማፈር እያለ “ገጥሜ እንዳልዘፍንልሽ ግጥም አልችልም” አላት፤ ፂም የወረሰው ፊቱን በቁጣ እየፈተገው፡፡
 “እንደዚህ አታድርግ አላልኩህም? ፂምህን አትቆጣው! እሱን የምትቆጣው ስለግጥም ባለማወቅህ እንጂ፣ ጠይሙ ዜማህ ውስጥ እኮ ግጥምም አለ” ስትለው ፈገግ አለ፡፡ ከጥቁር ከንፈሩ ስር ጐዶሎ ጥርሶቹ ታዩ፤ ፂሞቹም ላፍታ ከእጁ ነፃ ወጥተው በፈገግታ ተቃቀፉ፡፡
“ከማውቃት በላይ ታውቀኛለች፡፡ እቺን የመሰለችው ሁሉንም እንዴት አጣምራ ልትይዝ ቻለች? መላ እሷነቷ በፍፁምነት የተነከረ አስማት…” አለ ለራሱ ብቻ በሚሰማ ድምፅ አልባ የራስ ቋንቋ፡፡
ድንገት ቤቱ በሳቅ ድምፅ ታወደ፡፡ የድምፅ ማሳው ሥራውን ጀመረ፡፡ አጀብ የሚያስብል ጥዑም የሳቅ ድምፅ ተሰማ፡፡ ዜመኛው ከሃሳቡ ምልስ አለ። እንዲህ የምትስቅበትን ምክንያት ያውቀዋል። የውስጡን ሃሳብ አውቃ፣ እንደ ሕፃን እያባበለች ልትገስጸው ስትል እንደሆነ ከልምድ ያውቀዋል። በውስጡ ያነበነበውን ውዳሴ ሰምታ እንደሆነ ቢያውቅም፣ እንዲያው ለማወቅ ያህል ጠየቃት…
 “ምን ያስቅሻል?”
ዐይኖቿ በገላው ላይ ሲያርፍ፣ ከሰማየ ሰማያት እንደሚወርድ የፀሐይ ጨረር በፍቅር እያጉረመረመ፣ መላ ሰውነቱ በእይታዋ ሞቀ፡፡
“ሃሳብህን መግለፅ አታቅበትም፤ ግጥም አልችልም ትላለህ… ስለኔ ውበት ግን ከግጥም በላይ ትፅፋለህ፡፡” አለችው ዘለግ ያለው አንገቷን ለስለስ ባለ ውዝዋዜ ስልት እየሰበቀችው፡፡
“አባባልሽ ልክ ነው፡፡ ሃሳቤን መግለፅ ይቅርና ይህቺን ከእቅፌ ጠፍታ የማታውቀውን ጊታሬን እንኳን እንደልቤ ማዘዝ አልለመድኩም፡፡ ላንቺ እንኳን ላሰማሽ ከማስበው የጥዑም ዜማ ደረጃ ሩብ ያህሉን እንኳ ላደርስ አልቻልኩም” አላት በሀዘን፡፡
እንደ ጨረቃ በርጋታ ከተቀመጠችበት ዙፋን ላይ ሆና የሚናገረውን የምታደምጠው ፀሐይ፣ ፈገግታዋን በየመሃሉ ብቅ እያደረገች ነበረ። ዐይኖቿ መላ አካሉን ለብ ባለ ሙቀት ከበው እየተመላለሱበት እንዳለ፣ ድንገት ሻምላ እጅዋን ብድግ አድርጋ ወደ ሃር ፀጉርዋ ላከችው… ጣቶቿ በሀር ፀጉሯ ውስጥ ሰጥመው ሲርመሰመሱ፣ የፈለቀውን መዓዛ በአፍ በአፍንጫው እየተስገበገበ ማገው፡፡ በውስጡ የነበረውንም ቆሻሻ አየር ተፀይፎ ተፋው፡፡
“ላንቺ ከዚህ በላይ ላዜምልሽ በወደድኩ፤ ግን…” ብሎ ንግግሩን በእንጥልጥል ተወው፡፡ መቼም ቢሆን ዐይኖቹ ከገላዋ ላይ ከዋሉ ሁኔታዋን እየተከታተለ ከመደሰት ውጭ በተሟላ መልኩ ምንም ነገር መሥራት አይችልም፡፡
ንግግሩ ከመንገድ እንዲቀር ያደረጉ ጣቶችዋ፣ ከፀጉርዋ ተሰደው ታፋዋ ላይ ካረፉ በኋላ የተሰበሰበው ሀምራዊ ቀሚሷ የእግሯን ጣቶች ስላጋለጠባት ሳብ አድርጋ ሸፈነቻቸው። እንቅስቃሴዋን ሲከታተል የነበረው አዝማሪው የገላዋ ቅርፅ ታወሰው፡፡ ተቀምጣ እንኳን ምትሃታዊ ምስሏ ገንኖ ያሰግዳል፡፡
‹ፈጣሪ ግን እንዴት እንዴት አድርጐ ነው የሠራት? እርግጠኛ ነኝ ፈጣሪ እንዲህ አድርጐ የሠራት የራሱን ጥበብ ምን ያክል የላቀ እንደሆነ ለማስመስከር መሆን አለበት! አለበለዚያማ እንዴት ከሁሉ አብልጦ እላይ ሰቅሏት ሌሎች እሷን በማየት ብቻ እራሳቸውን እንዲያጠፉ ያደርጋል?› በማለት ከውስጠቱ ጋር የተነጋገረውን ሊነግራት ቀና ሲል፣ ፊቷ ተለዋውጧል፡፡ የግንባርዋ ቆዳ ተሸበሸበ፡፡ ከዐይኖቿ ይመገበው የነበረው ሙቀት ገነተረበት፤ ስትቆጣ እይታዋ ከማሞቅ አልፎ ያቃጥለው ጀመር፡፡
ሁልጊዜ ስትቆጣ ፈገግ ይላል፡፡ በቁጣዋ ቢቃጠልም ሕመሙን ቸል ብሎ እሷን ለመመልከት ይጣደፋል፡፡ በዚህ ጊዜ የሚያየውን ውበቷን በዜማ መግለፅ ከቻለ ታላቅ የዜማ ፈጣሪ እንደሚሆን ስለሚያውቅ፣ ለቅፅበት ዐይኖቹን ከፊቷ ላይ ማንሳት አይወድም፡፡ ምን እንዳስቆጣት ግን ያውቃል፡፡ እሷም እንደሚያውቅ ስላወቀች መቆጣት ጀመረች፡፡
“ለምንድን ነው ግን ሁሌ እራስህን የምታሳንሰው? ለሌላው ፈጣሪ ችሎታህን በግድ የምታጋራው? ካንተ በላይ የጥዑም ዜማ ጌታ አለ? ካንተ በላይ በዜማው ድንቅ ውበት የሚፈጥር አለ? ካንተ በላይ እኮ ፈጣሪ የለም የኔ ዉድ!” አለችው፣ መልስ ፍለጋ ትክ ብላ እየተመለከተችው። በተደጋጋሚ እንዲህ እያለች ተቆጥታዋለች፡፡ እንዲህ ስትቆጣው፣ “ልክ ነሽ፤ አዎ፣ ከእኔ ሌላ ፈጣሪ የለም” እንዲላት ብትፈልግም አንድም ቀን ግን ብሏት አያውቅም፡፡ ለእርሷ ግን ከሱ በላይ ፈጣሪ የለም፡፡
ምላሹን ጥበቃ ላይ እንዳለች ዐይኖቿ ወደ በሩ በድንጋጤ ተመልክተው በዚያው ደርቀው ቀሩ። በቅፅበት ከሰውነቷ ላይ የነበረው ነብስ መሸሽ ጀመረ። ሁለመናዋ እንደ ጉም ተነነ፤ መዓዛዋ ጠፋ፤ የውበቷ ሁለንተና ተሰወረ፡፡
የውበት ንግሥቱ ድንገት እንዲህ የምትሆነው በምን ምክንያት እንደሆነ ያውቃል፡፡ ሁሌ ይህን ላለማየት ሲል ቀድሞ እንዲሞት ቢመኝም፣ አልተሳካለትም፡፡ ቤቱ ውስጥ የነበረው ድባብ እንዲህ ሲረግፍ በመመልከቱ በራሱ ተበሳጨ። በፍርሃት ተወጥሮ ለበሩ ጀርባውን ሰጥቶ የሚቀመጠው ከቤቱ ያለችው ንግሥት እንዳትወጣ ለማንገራገር፣ ከዚህም አልፎ ከውጭ ወደ ውስጥ ሌላ ሰራጊ ሙት ነብስ እንዳይገባ ለመከላከል ነበር። ግን… በሩ ተከፍቶ አንዲት ሴት ገባች፡፡
“እንዴት ነህ የኔ ቆንጆ” ብላ ጉንጩን ሳመችው፤ እሱ አልመለሰላትም፡፡ ጀርባውን እንደሰጣት ጆሮው በሰማው ሙት ድምፅ እያለቀሰ ነበር፡፡ የገባችዋ ሴት ሄዳ ከፊት ለፊቱ ካለ አሮጌ ሶፋ ላይ ስትቀመጥ፣ ሶፋው ሲጥጥ አለ፡፡ የዐይኖቹ ብሌኖች እየተንጫጩ ቦታቸውን ለሌላ ተራ ብሌኖች አስረክበው ተሰወሩ።
አፍጥጣ እየተመለከተችው፣ “እንዲህ በፍቅር ስትመለከተኝ ነብሴ በደስታ ትሰክራለች” አለችው፡፡
“ሰውን ተመልክተሽ መረዳት አትችይም” አላት በቁጣ፡፡
“በጣም እችላለሁ፤ ስለምችልም መሰለኝ አንተን የሰማንያ ባሌ ያደረኩህ” አለችውና ኳኳታ የመሰለ ድምፅ እያሰማች ተንከተከተች፡፡ በእቅፉ የነበረውን ጊታር አሽቀንጥሮ ወረወረው፡፡
“ዛሬ ደግሞ ፈገግታህ ልዩ ነው” ብላ ከተቀመጠችበት ተነስታ እየተንጐማለለች ተጠጋችው… አጠገቡም ተቀመጠች፡፡ “አንዳንዴ እንዲህ ነው፤ የሀዘን ስሜት በፈገግታ ማህፀን ውስጥ ይቀበራል” አላት፡፡
ይህን ግን አልሰማችውም። በጣም የተጠጋችው ቢሆንም፣ እንዲህ ዓይነቱን ንግግር የመስማት ኃይሏ ሙት ነው…

Read 3531 times