Saturday, 02 August 2014 11:52

የ”ሰው ለሰው” ስንደዶ እግሮች!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(7 votes)

የቤት ሆቨን የሙዚቃ ቅማሬ… የዳቪንቺ ቀለማዊ ህብርና መስህብ፣ የቶልስቶይ ድርሰት የነፍስ ጭፈራ፣ የዴቪድ ቶሩ የምድረ በዳ ምጥ፣ የሚካኤል አንጀሎ ምትሀታዊ ቅርፅ… የኤሚሊ ዲክንሰን ስንኞች ዳንስ… ሁሉ በየዘመናቸው ፍራሽ ዘርግተው፣ አጥር ገንብተው የተገኙ ዝንጉዎች ውጤት አይደለም። …. ይልቅስ ጥበባዊ ስልት አርግዘው፣ ዓለምን የሚያላውስ ሻምላ መዝዘው ስለተፋለሙ ነው፡፡
ጋንዲ ከቶሩ፣ … ሲቀበል ቶልስቶይ ሲያማክል፤… ሉተር ኪንግ የመጨረሻውን አበባ ሲቀበል፣ አንዱ ላንዱ ያቀበለው ዱላ፣ የደለደለው መንገድ ነበር፡፡… ስለዚህም ነው እውነትና ውበት ጥምረት ሰርተዋል ብለን የምናሞግሰው…!
ናፖሊዮን በአጭር ቁመናው፣ ዓለምን የሚሞላ ልብ ውስጥ ዳግም ባይወለድ፣… ዓለም ጨካኝ ብሎ የረገመው ስታሊን፤ ጉንጩን የፍቅር እምባ ሊያነድዳቸው በመቃብር ቦታ ባይታይ (ሚስቱ ሞታ)… የሲጋራ ጥም ማስታገሻ ሳንቲም ያጣው ጄኔራል ግራንት፤ በዋይት ሀውስ ተሹሞ ገዢ ባይሆን… የህይወት መልክ ዝንጉርጉርነት በጠፋን ነበር፡፡ ግን ሕይወት መስመርና ምስክር አላት፡፡ የቀለምዋ ውበትም ከኑሮ ጋር የታጠቀ ከመዐልትና ሴት ጋር የተሳሰረ ነው፡፡
ይሁንና ከሰው ልጅ ውስጣዊ ውስብስብነት ትይዩ፣ የሳይንስ ወንዞች ቀመር ለብሰው ሲፈስሱ፣ ብዙ እውነቶች መልክ እያገኙ መጥተዋል፡፡ ስለዚህም ሰው አካላዊነቱ ብቻ ሳይሆን ስነ ልቦናዊና ማህበራዊነቱ ፍጥጥ እያለ መጥቶ፣ በርካታ ድርሳናት በምርምር ማህደር ውስጥ ሊታጨቁ ግድ ሆኗል፡፡
ኪነ-ጥበብ በህብረ ቀለም፣ በዜማ ንክር ንጥቂያ …. በስሜት ምትሀት ጥንካሬዋ ከሰው ወስዳ ለሰው የምታጎናፅፈው የምናብ ትሩፋት ብዙ ነውና በተለያዩ ዘውጎችዋ “አጀብ” እያሰኘች የሰውን መንቻካ ገጠመኞች ሳይቀር አዋዝታ መልሳ ትመግብ ዘንድ ፈጣሪ ቸርነት አብዝቷል ብዬ አምናለሁ፡፡
“እውነታዊነት” ላይ ተመስርተው የሚሰሩ ስራዎችም ተፈጥሯቸው ባጠለቀላቸው ገመድ ምክንያት ከእውነት ወዲያ ወዲህ ፈቅ አይሉም። ምሁራኑ truthful treatment of material እንዲሉ፡፡
በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለሦስት ዓመታት ያህል የተላለፈው የ“ሰው ለሰው” ተከታታይ ድራማም የዚሁ መልክ አንዱ ገፅታ ተገንጥሎ የማይታይ ነው፡፡ ይህ የሶስት ዓመት ጎልማሳ ድራማ ሲጀመር የታምሩ ብርሃኑ ድርሰት እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ነቢዩ ተካልኝና መስፍን ጌታቸውም ታሪኩን አስፍተው አዝልቀውታል፤ ድራማውም በላቀ አወቃቀር በሀሳብ ብስለትና ጥልቀት ጣሪያ ነክቶ የነበረውን ታላቅ ደራሲ አዱኒስን “ገመና ክፍል ፩” ተመልካቾች ልብን ዳግመኛ መንጠቅ ችሎ ቆይቷል፤ ምንም እንኳ ባልታወቀ ሁኔታ የቀንድ አውጣ ጉዞው ማሽሟጠጫ እስኪሆን ቢያደርሰውና ለበሳል ተመልካቾች የጭብጡ ፋይዳና የገፀ ባህሪያት አሳሳሉ አባጣ ጎርባጣነት ቢያጠያይቅም፡፡
ስለገፀ ባህሪያት አሳሳሉ ስናነሳ፣ አስናቀ እንዝርት ሆኖ አጠቃላይ የታሪኩን ፈትል መጠቅለሉን አንክድም (ለዚያውም የአበበ ባልቻ ድንቅ ትወና ታክሎበት) ዋው!
ደራሲዎቹም ቢሆኑ እውንዋን ዓለም ፈልቅቀው፣ ሴራ አዋቅረው፣ በገፀ ባህሪያቱ ነፍስ ዘርተው፣ በሳቢያና ውጤት አዋቅረው፣ ይህንን የጥበብ ስራ ለህዝብ በማቅረባቸው የላቀ አክብሮት አለኝ፡፡
ይሁንና የዛሬው ትኩረቴ፣ የታሪክ አጨራረሱ ቁስልና ሕመም የፈጠረብኝን ሐዘን አስታክኬ ቅሬታዬን መግለጥ ነውና በዚህ ምዕራፌ የታሪኩን ገፆች አልነካም፤ ምክንያቱም ያስደነገጠኝ የታሪኩ በአንዳች መለኮታዊ ቅስፈት አይነት ሰዶምና ጎሞራን መሆኑ ነው! ስለዚህም ይህንን ፍትህ አልባ አጨራረስ አስመልክቶ አንዳች ብያኔ የሰጠውን አርስቶትልን ፍለጋ ወደ መጻሕፍት መደብር መሄድ ግድ ብሎኞል። አርስቶትል በዚህ ምድር ላይ በስጋና ደም ወዲያ ወዲህ የሚሉ ሰዎች ያላቸውን ሰብዓዊ ፍትህ፣ በጥበቡ ችሎትም አምጥቶ ህያው መሆን እንዳለበት ይናገራል፡፡ እስቲ ትንሽ ልዋስ:- “The mere spectacle of virtous man brought from prosperity to adversity moves neither pity nor fear; it merely shock us and here us, really the heart of the whole question. Suffering as an end itself is intolerable dramatically. ይህን ብቻ አይደለም ያለው፤ ጥቂት ልቀጥል:- “Such scenes would be exhibitions of fate over which why were in no sense responsible”
ደራሲው የገፀ ባህርያቱ ማንነትና ሰብዕና ሳይሸጥና ሳይለውጥ፣ የኖሩትን የሚሆኑትን በምክንያትና በአመክንዮ ካልሆነ በቀር በፊታችን በግፍ እንዳይገድላቸው አርስቶትልና ተከታዮቹ ምሁራን አስረግጠው ይነግሩናል፡፡… ደራሲ በጥበብ ስራ ላይ የሚጠየቅበት ኪናዊ ፍትህ እንዳለ ያሰምሩበታል!
ይህ እውነት ደግሞ ወደ እኛው አስናቀና ሌሎቹ ገጸ ባህሪያት ስናመጣው፣ ሬሣ ሆኖ መውደቁን እናያለን፡፡ በተለይ አስናቀን ፍፃሜው ላይ አጠቃላይ ማንነቱን ገፍፎ፣ አራቁቶት እንደነበር እናስታውሳለን። ሲጀመር በየታሪኩ አንጓ ያየነው አስናቀ ደፋር፣ ማንንም የማይፈራ፣ በሰዎች ስቃይ የሚረካ፣ በራሱ አጥርና አውድ የማይበገር ጀግና፣ ሰው ጤፉ ነበር፡፡ በታሪኩ ማምሻ አጥንቱን ነቅሎ የተጥመለመለ ትኩስ የቋንጣ ዝልዝል ሆኗል፡፡ ለምን? ቢባል ደራሲው እንደፈለገ ሊያደርገው ስለተመኘ፡፡ እንደዚያ ባይሆንማ ኖሮ፣ አስናቀ እንዴት በመስፍን ፊት የጨበጠው ሽጉጥ የወተት ጡጦ ይሆናል!.. ሽጉጥ እሣት የሚተፋ የሞት ድልድይ እንጂ ለልጅ የሚሸለም ከረሜላ አይደለም፡፡ እዚህ ቦታ አስናቀ ተሽጧል፡፡ ጥጃዋ ከሞተች በኋላ ላምን ለማታለል፣ የጥጃው ቆዳ ተገፍፎ ጭድ እንደሚታጨቅበት ነፍስ አልባ በድን ነው የተደረገው፡፡ ይህ ደግሞ ኢ-ፍትሃዊ ነው፡፡ ያ ብቻ አይደለም፤ ያ ለንቋሣ ሆኖ የተሳለ መስፍን፤ ያለምንም ምክንያት በአንዲት ቃለ ተውኔት ብቻ ነፍስ ዘርቶ፣ የአስናቀን ጀንበር የማጨለም ሀሳብ ከደራሲው ልብ ሰርቆ ሲያቅራራ፣ ሽጉጥ ይዟል ብለን እጅ እጁን አይተን ነበር፡፡ ግን የመዘዘው ደረቅ ምላስ ብቻ ነበር፡፡ ያን አጥመልምሎ ሆስፒታል ያንከራተተውን አንበሳ ልብና ሳንባ እንደ ድመት የጎረሰበትን ማንነት ከየት አመጣው? መልሱ ደራሲው ያለአግባብ ጫነበት የሚል ነው፡፡
በድርሰት ዓለም አንድ ገጸ ባህሪ ሲሳል፣ የገሃዱን ዓለም እውነቶችና አላባውያን የተከተለ መሆን አለበት፡፡ አንድ ሰው ደግሞ የራሱ የሆነ ውጫዊና ውስጣዊ መልኮች አሉት፡፡ በእውነታዊው ድርሰት ሰው ሆኖ የተሳለ ሰው፣ እንደሰው ከአካባቢው አስተሳሰብ ጀምሮ በትምህርት ደረጃው፣ በአስተዳደጉና ሥነ-ልቦናው ላይ ተመስርቶ ማሰብና ማድረግ አለበት እንጂ ደራሲው እንደጋሪ ሊነዳው አይገባም፡፡ አስናቀም ሰው ነው፡፡ የራሱ ቀለሞችና ማንነቶች ሊኖሩት ግድ ነው፡፡ የራሱ ክብር፤ የራሱ እውነትና የህይወት ዓላማ አለው፡፡ እንደማንኛውም ለራሱ ክብርና ሞት እንዳለው ሰው፣ አሟሟቱን ሊያሳምርና እንዳይቀደም ሊያደርግ ይገባ ነበር፡፡
በእውኑ ዓለም ከነበሩት ጀግኖች አንዱ ናፖሊዮን ብዙ ጠላቶች እንዳሉበት ስለሚያውቅ ከሞት ይልቅ ቅሌትን በመጥላት፣ በጣቱ ቀለበት ሥር መርዝ ይዞ ይሄድ እንደነበር ፀሐፍት ይመሰክራሉ፡፡ አስናቀም በሰዎች ላይ ግፍ የሚሰራ፣ የራሱ ሰፈርና አውድ ጀግና ነው፤ ግምቱም ትልቅ ነው፡፡ ታዲያ ምነው ተርመጥምጦ ይሞታል! ይህ የደራሲው ግፍ ነው፡፡ እግሩን አስሮ ከለከለው፡፡ የአርስቶትል ቁጣ ብልጭ የሚለው እዚህ ላይ ነው!.. መንገዱን ይዞ እንዳይሄድ ደራሲው ልጓም በአፉ ከተተበት!... ያናድዳል!
ገፀ-ባህሪያት አሳሳል ላይ ያጠኑና የፃፉ ምሁራን የሚቃወሙት እውነትም ይህ ነው። እነርሱ በተሰራላቸው ዓለም በነፃነት የመኖር፣ የተመጠነላቸውን አቅምና ጊዜ፤ ሁኔታና ዕድል ተጠቅመው እንዲኖሩ ነፃ መሆን አለባቸው፡፡ ይህን በተመለከተ ሩሲያዊው ደራሲ ሊዮ ቶልስቶይ፤ አንዲት ገፀ ባህርይ የባቡር ሀዲድ ውስጥ ገብታ በመሞትዋ ለተጠየቀው ጥያቄ የሰጠው መልስ የሚገርም ነበር። ያንን ነገር ያደረገው እርሱ ሳይሆን ገፀ ባህሪዋ ራስዋ ያደረገቻቸው ድርጊቶችና የሕይወትዋ መንገድ መሆኑንን ነበር የተናገረው፡፡ ይህን የሚመስል ነገር የኛ ሀገሩ ደራሲ ብርሃኑ ዘሪሁንም የ “ማዕበሉ”ን ገፀ ባህሪ አያ ሙሄን አስመልክቶ ተናግሮ ነበር፡፡
ገፀ ባህሪያትን በግድ አፍኖ የማይመርጡበትና ባህርያቸው ባልሆነ ሁኔታ ጠምዶ ፍርድ መስጠትን በሚመለከት ሀንጋሪያዊው የፊልም ዳይሬክተር፣ ደራሲና ገጣሚ ላጆስ ኤግሪ ያለውን ሀሳብ እወድደዋለሁ፡፡ “አንድ ገፀ ባህሪ ከተፈጠረበት ማንነት ውጭ የሆነ ሰብዕና መጫን፣ አንድን ሰው ከሚተኛበት አልጋ ቁመት ጋር ለማጣጣም ሲባል ከአካሉ ላይ እንደመቁረጥ ነው፡፡” በማለት ሰፋ ያለ ትንታኔ ይሰጣል፡፡
የ“ሰው ለሰው” ተከታታይ ድራማ ይህንን ያደረገው በአስናቀ ላይ ብቻ አይደለም፡፡ የሌሎቹንም ተፈጥሮና ማንነት አሽቀንጥሮ ጥሎ፣ እንደደራሽ ውሃ ድንኳናቸውን ነቃቅሎ ማንነታቸውን አመሳቅሎ ጥሏል፡፡ ሌላው ቀርቶ የአስናቀ ልጅ ከሰው የተፈጠረ ሰው እስከማይመስል ድረስ የአባቱን ሞት ትርዒት ተመልካች ሆኖዋል፡፡ ለመሆኑ በኢትዮጵያዊ ባህል ይህ ልጅ አባቱን ቆሞ አስገድሎ እምን ጉድጓድ ውስጥ ለመግባት ይሆን?... የእስራኤሉ ንጉስ ዳዊት እንኳ ከሥልጣን ሊያሽቀነጥረውና ዙፋኑን ሊወርስ ከጅሎ ጦርነት ያወጀበት ልጁ ሲሞት፣ ጨርቁን ጥሎ ነበር ያለቀሰው፡፡ “ትንሽ ሥጋ እንደመርፌ ትወጋ!” ከሚለው ያለፈ ፋይዳ ያለው የአባት ፍቅር፣ እንዴት ባለ ላጲስ ይሆን የጠፋው? ልፅፍበት የተነሳሁበት ዓላማ ጥበባዊ ፍትህ ስለሆነ አሁንም የአጨራረሱን “ዕቃ - ዕቃ ጨዋታ” ነው የምከተለው፡፡ ለመሆኑ በዚያ የመጨረሻ ቀን የሁለቱ ሴቶች አንድ ላይ መውለድ ምን የሚሉት ቀልድ ነው?...እንዲያውም ትርጓሜው ተመልካችን ወደ መናቅ ያመጣል፡፡
እስቲ ደግሞ ለቀጣዩ ሀሳቤ በቅርብ ዓመታት ከተፃፈ የሥነ ፅሁፍ መጽሐፍ ላይ ስለ ባህላዊ ሂስ፣ ሬይመንድ ዊልያምስን በቀኜ ይዤ ልነሳ። እርሳቸው እንደሚሉት፤ አንድ ተንታኝ ከሥነ ጽሑፋዊ ቅርፅ ባሻገር፣ የባህል ጥቅልልንና ሂደትን መበርበርና መተርጎም አለበት ይላሉ፡፡ እኔም ይህን ሃሳብ ይዤ፣ እኛ ስናየው ዓመታት ወዳስቆጠረው የ“ሰው ለሰው” ተከታታይ ድራማም አመጣዋለሁ፡፡ የባህላዊ ማንነታቸውን ድርና ማግ እንድንፈትሽ የሚያደርገን አንድ ሁነት አለ፡፡ ያም ሞገስ የሚባለው ገፀ ባህርይ የወለደውን ልጁን ከሶሲ ጋር ተስማምቶ ለተቀናቃኙ መስጠቱ “የማይመስል ነገር ለሚስትህ አትንገር” ዓይነት ነው፡፡ ለመሆኑ እጅግ በጣም ስር የሰደዱና የተደራጁ ባህላዊ ሰንሰለቶች ባሉበት ሀገር፣ እንዴት ሆኖና ከዚያስ በኋላ በህብረተሰቡ መካከል እንዴት ለመኖር ይሆን ያንን ያደረገው? ያቺ ሶስና የምትባል ሴትስ አይንዋን በምን ጨው ልታጥብ ያንን አደረገች?
ይህ ብቻ አይደለም የተዓማኒነት ጥያቄው፣ ማህሌት ኢንስፔክተሩን አልፋ ሽጉጥ የምትተኩስበት ልብ ከየት ተወለደ? ይህ አርቴፊሻል ነው፡፡ ሥጋና ደም፣ ነፍስና መንፈስ ካለው የሰው ልጅ ሊከሰት የሚችል እውነት አይደለም፡፡ ሌላው አንድ ህግ አስከባሪ ኢንስፔክተር የሰው ልጅ ያለ ሕግ፣ ያለ ፍርድ ቤት ውሳኔ ሲገደል፣ ኮሚሽነር ተብዬዋ በዚያ ህገወጥ ሥራ “እንኳን ደስ ያለህ!” ማለትዋ ከቅሽምና ያለፈ መውረድ አይመስልም? ሀንጋሪያዊው ደራሲና ገጣሚ እንደሚሉት፤ የደራሲው ውስጣዊ ብስለት የሚያስፈልገው ለዚህ ጊዜ ነው፡፡
በአጠቃላይ ሳየው “ሰው ለሰው” ደራሲው (ደራሲዎቹ) ታቅፈው ሳይፈለፈል ያፈረጡት እንቁላል ነው፡፡ ምክንያቱም ታሪኩን በወጉ ይዘውት ሄደው ቢሆን ኖሮ፣ እንደ ሀይሉ ፀጋዬ የሬዲዮ ድራማዎች የንስር ክንፍ ኖሯቸው፣ ከትውልድ አድማስ ወደ አድማስ በተሻገሩ ነበር፡፡  ትልልቅ ሁነቶችን ያቀፈውን ወፍራም ድራማ፣ በስንደዶ እግሮች ቆሞ ማየት አሳዛኝ ነው፡፡

Read 4539 times