Wednesday, 30 July 2014 08:00

ከእሳት አደጋ የተረፈው ድምፃዊ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

“እንሾሽላ”፣ “ኬር ይሁን”፣ “የአሜሪካ ዲቪ”  በሚሉትና በሌሎች ተወዳጅ የጉራጊኛ ዘፈኖቹ የሚታወቀው ድምፃዊ ፈለቀ ማሩ፤ ላለፉት 10 ዓመታት በሙዚቃ ሙያ ቆይቷል፡፡ የሶዶ ጉራጌ ተወላጅ የሆነው ታዋቂው ድምፃዊ፤ ከሁለት ሳምንት በፊት ቤቱ ውስጥ በደረሰ ድንገተኛ የእሳት ቃጠሎ ሶስት ክፍል ቤቱን ጨምሮ ንብረቱ በሙሉ በእሳት የጋየ ሲሆን ሁለት ልጆቹንና ባለቤቱን ተዓምር በሚመስል ሁኔታ ለማትረፍ ችሏል፡፡ ወደ ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረቱን በቃጠሎው እንዳጣ የሚናገረው ድምፃዊ ፈለቀ፤ “እንደ አዲስ ጎጆ ወጪ ሆኛለሁ” ብሏል፡፡ ስለ እሳት አደጋው ፣  የቤተሰቡን ህይወት እንዴት እንዳተረፈና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከድምፃዊው ጋር አውግታለች፡፡

መቼና እንዴት ነበር የእሳት አደጋው የተከሰተው?
አደጋው የተከሰተው ከሁለት ሳምንት በፊት ነው፡፡ መንስኤው ኤሌክትሪክ ነው፡፡  ፍሪጁ ተሰክቶ ሳለ ማከፋፈያው ቀለጠ፡፡ እንዴት እንደሆነ አልገባኝም፡፡
ሌሊት ነው ወይስ ቀን?
ከሌሊቱ 9፡00 ሰዓት ነው ቃጠሎው የተነሳው። ከፍሪጁ አካባቢ ያለው መጋረጃ በእሳት ተያይዞ እሳቱ ወደ ሶፋው ደርሶ ነበር፡፡ በእንቅልፍ ልቤ የሆነ ነገር ይሸተኛል፤ ግን ሙሉ ለሙሉ አልነቃሁም ነበር። ሙሉ ለሙሉ የነቃሁት ሳሎኑ ከግማሽ በላይ ተያይዞ፣ ሶፋው ተቃጥሎ ካለቀ በኋላ ነው፡፡
ግን እንዴት ልትነቃ ቻልክ?
የሚገርምሽ ጭሱ አፍኖን አድክሞናል፤ በተለይ የሶፋው ስፖንጅ ሽታ እስካሁን በውስጤ አለ። በጣም የሚያስጠላ ሽታ ነበረው፡፡ ቤት ውስጥ ሁለት ልጆቼ፣ ባለቤቴና እኔ ነበርን፡፡ ባለቤቴ “ኧረ ፈሌ፤ የሆነ ነገር ይሸተኛል” ስትለኝ የእኔም ስሜት ስለነበር በደንብ ነቃሁ፡፡ ከመኝታ ቤት ወጥቼ ወደ ሳሎን ስሄድ፣ ሙሉ በሙሉ እየነደደ ነው፡፡ በጣም ደነገጥኩ፤ ባለሁበት ቆሜ ቀረሁ፡፡
ከዚያስ?
ከዚያማ አዕምሮዬን ማሰራት ጀመርኩኝ። ንብረቱ አንዴ ወድሟል ግን ልጆቼን እንዴት ላትርፍ የሚለውን ማሰብ ነበረብኝ፡፡ የለበስኩት ቱታ ነው፡፡ ደግነቱ ሻማ ቱታ አልነበረም እንጂ እላዬ ላይ ቀልጦ እኔም ሟች ነበርኩኝ፡፡ ከዚያ በእሳቱ መሃል አቋርጬ በመሄድ፣ ዋናውን በር ከፍቼ ወደ መኝታ ቤት መስኮት ሮጥኩኝ፡፡ ልጆቼን በመስኮት ለማውጣት፡፡
ወደ ውጭ ከምትወጣ ከመኝታ ቤት ወደ ውጭ ብታስወጣቸው አይቀልም ነበር?  ወይስ ድንጋጤው ይህን እንድታስብ እድል አልሰጠህም?
እንደሱ አስቤያለሁ ግን ግድግዳው ከመስኮቱ ሩቅ ስለሆነ፣ ውስጥ ሆኜ ወደ ውጭ ከወረወርኳቸው ሌላ አደጋ ይፈጠራል በሚል፣ ውጭ ሆኜ ባለቤቴ ቶሎ ቶሎ እንድታቀብለኝ ነው ያደረግሁት፡፡ እነሱን ካቀበለችኝ በኋላ እሷም እንደምንም በመስኮት ወጣች፡፡ ለንብረቱ አላሰብኩም፡፡ ዋናው ነገር ልጆቼና ባለቤቴን ማትረፍ ነበር፡፡
እግዚያብሔር ረድቶኛል፤ እነሱ ተርፈውልኛል። ሳሎኑ እየነደደ በር ለመክፈት ስወጣ፣ ግንባሬ ሁሉ ተለብልቦ ነበር (ግንባሩ ላይ እስካሁን ጠቁሮ የሚታይ የእሳት ግርፋት አለ)
የምትጠቀምባቸው ማከፋፈያዎች ይሆኑ እንዴ ለአደጋው መንስኤ የሆኑት?
የማከፋፈያው ችግር አይመስለኝም፡፡ ከዚህ በፊት ቲቪው እንደተሰካ መብራት ጠፋና ሲመጣ ኃይል ጨምሮ ስለነበር ቴሌቪዥኑ ተቃጠለ፡፡ ሌላ ጊዜ እንዲሁ ተንቀሳቃሽ ስልኬ ቻርጅ እየተደረገ ሳለ፣ መብራት ጠፍቶ ሲመጣ ተቃጠለ፡፡ ይሄኔ ቆይ ስታብላይዘር እገዛለሁ እያልኩ ሳስብ ነው ፍሪጁ በተሰካበት ይሄ አደጋ የተከሰተው፡፡
ምን ያህል ንብረት ወደመ?
ቤቱን ሳይጨምር የእኔ ንብረት ብቻ ወደ 500 ሺህ ብር የሚያወጣ ነው፡፡ የቤተሰቤ ልብስ ከለበስነው ፒጃማ ውጭ የባለቤቴ የወርቅ ጌጣ ጌጦች፣ ለመጠባበቂያ ብዬ ቤት ውስጥ ያስቀመጥኩት ገንዘብ፣ የቤት ቁሳቁስ፣ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች፣ ስልኮቻችን፣ ብቻ ከነፍሳችን በስተቀር የተረፈ የለም፡፡ ቤቱ ራሱ ሶስት ክፍል ቤት ነው፡፡ ምንም የቀረ የለም። መኪናዬና የባንዱ የሙዚቃ መሳሪያም የተረፉት ቤት ውስጥ ስላልነበሩ ነው፡፡ እግዚአብሔር በኪነ-ጥበቡ ቤተሰቤን አትርፎልኛል፡፡ የሚገርምሽ የልብስ ማጠቢያ ማሽንና ሌሎች ማሽኖች በረንዳ ላይ ነበሩ፤ እነሱን እንኳን ማዳን ይቻል ነበር። ድንጋጤ ስለነበር ያስታወሰ የለም፤ አብረው ወድመዋል፡፡
ቤቱ የራስህ ነው ወይስ ተከራይተህ?
ተከራይቼ ነው፡፡ ቤት አልሰራሁም፡፡ ቤቱ ከእነንብረቱ ሙሉ በሙሉ ነው የወደመው፡፡  ብዙ ጊዜ በርና መስኮቶች ከውስጥ መስታወት ሆነው ከውጭ በብረት ይበየዳሉ፡፡ የእኔም መስኮት በብረት የተበየደ ቢሆን ኖሮ ልጆቼና ሚስቴ ቤት ውስጥ ከንብረቱ ጋር አልቀው ነበር፡፡ አሁን ሳስበው ይዘገንነኛል፡፡ ምክንያቱም በዚያን ሰዓት ብረቱን ለመፈልቀቅ መሳሪያ ያስፈልጋል፡፡ እሳቱ ደግሞ ሳሎኑን ጨርሶ ወደ መኝታ ቤት እየተጠጋ ነበር፡፡ ብቻ ፈጣሪ ትረፉ ብሎን ነው እንጂ መጥፎ ሁኔታ ውስጥ ነበርን፡፡
ለእሳት አደጋ መከላከያ አልደወላችሁም ነበር?
ተደውሎላቸው መጥተዋል፤ ግን ዘግይተው ነው የመጡት፡፡ የእኔ ቤት ሙሉ ለሙሉ ወድሞ ወደ አከራዮቻችን ቤት ሊዛመት ሲል መጡ። የእኔን ማዳን ባይችሉም ወደ ሌላው ቤት እንዳይዛመት ለማድረግ ችለዋል፡፡
የራስህን ቤት አልሰራህም?
ምንም እንኳን 10 ዓመት በሙዚቃው ብቆይም ወደ ሙዚቃው በደንብ ዘልቄ የምገባበትን ሁኔታ ሳመቻች ነው የቆየሁት፡፡ ከአሁን በኋላ ነው ቤት ብሰራም፡፡ እስካሁን የሰራሁበት ለቤት መስሪያ የሚበቃ አይደለም፡፡ መኪና የገዛሁትም ከቤተሰብም ከምንም ብዬ ነው እንጂ ዘፍኜ አይደለም፡፡
አሁን እንደ አዲስ ጎጆ እየወጣሁ ነው ብለሃል። እንዴት ነው ወዳጅ ዘመድ ረዳህ?
“ሀ” ብዬ እቃ እየገዛሁ ነው፡፡ እንዳልኩሽ ከለበስነው ቢጃማ በስተቀር ምንም አልተረፈም። እስካሁን በውጭ የሚኖሩ የባለቤቴ እህቶችና ቤተሰቦች ድጋፍ እያደረጉልን ነው፡፡ አሁን ሌላ ቤት ተከራይቼ ኑሮን እንደ አዲስ እየጀመርኩኝ ነው፡፡
አከራዮችህ ቤታቸው በመውደሙ ምን አሉ?
አከራዮቼ በጣም የተባረኩ እንደቤተሰቤ የማያቸው መልካም ሰዎች ናቸው፡፡ እነሱ ጭራሽ ቤቱን አላሰቡትም፡፡ ያስደነገጣቸው የእኛ ጉዳይ ነው፡፡ እኛ በመትረፋችን ተፅናንተዋል፡፡ የቤቱ ጉዳይ ጭራሽ አልታሰባቸውም፡፡
በአሁኑ ሰዓት ምን እየሰራህ ነው?
ለጊዜው ነጠላ ዜማዎችን እየሰራሁ ነው፤ የሰራኋቸውም አሉ፡፡
ሙሉ አልበም ለመስራት አላሰብክም?
አላሰብኩም! ምክንቱም አዋጪ አይደለም። የቅጂ መብት ጉዳይ አሳሳቢ ነው፡፡ አንቺ ለፍተሸ ደክመሽ የሙዚቃ ቪዲዮ ሰርተሽ፣ ለግጥምና ዜማ ከፍለሽ፣ ለስቱዲዮ፣ ለተወዛዋዥ፣ ለካሜራና ኤዲቲንግ … ወጪ አውጥተሽ፣ ሰው በኢንተርኔት በብሉቱዝ ተቀባብሎት ቁጭ ይልና ድካምሽ መና ይቀራል፡፡ ይህ ሁኔታ ሳይስተካከል ሙሉ አልበም ለመስራት ፍላጎት የለኝም፡፡
ባይሆን ነጠላ ዜማው ላይ አተኩሬ እሰራለሁ። እስካሁን ሶስት አልበሞችን ሰርቻለሁ፤ በእነሱም ጥሩ ተቀባይነትና እውቅናን አትርፌያለሁ፡፡ በገንዘብ ብዙ ተጠቃሚ ባልሆንም፡፡
በመጨረሻ ምን ትላለህ?
 በዚህ አጋጣሚ በአደጋው ጊዜ ከጎኔ ሆነው ላበረታቱኝ፣ አሁንም ድረስ መልሼ እንድቋቋም ድጋፍ እያደረጉልኝ ላሉት የባለቤቴ እህቶችና ቤተሰቦች፣ እንዲሁም ለእኔም ቤተሰቦችና መልካም ባህሪ ላላቸው አከራዮቼ በሙሉ ከፍ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ፡፡

Read 2557 times