Wednesday, 30 July 2014 07:56

ዲያብሎስ

Written by  ዮናስ ነማርያም
Rate this item
(7 votes)

       መርካቶ - ሲዳሞ ተራ፡፡ የቀለጠው ሠፈር። የማይታይ ዘረ - ሰብ የለም፡፡ እዚህ ሌላ ቋንቋ፣ ዘወር ሲሉ ሌላ፡፡ የማይሰማ የቋንቋ አይነት የለም። የተደበላለቀ ቋንቋ - የባቢሎን ግንብ፡፡ ሁሉም ጥድፊያ ላይ ነው፡፡ ደላላው ተካልቦ እያካለበኝ ወደ ቴፒ ለመሄድ ሸቀጥ የጫነች አይሱዙ ላይ አሳፈረኝ። ወደ 10 ሰዓት ገደማ ጉዞ ጀመርን - ወደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ቴፒ፡፡
…12 ሰዓት ወሊሶ ደረስን፡፡ በስንብት ላይ ያለችው ጀንበር ወርቃማ ጨረሮቿን ፈንጥቃ -  የአድማሳቱን ከንፈር ስማ ጠለቀች፡፡
ወልቂጤን አልፈን…ወደ ጊቤ በረሃ እየተቃረብን ነው፡፡ ሹፌሩ የጊቤ በረሐ ዘራፊዎችን ከሰብአዊ ፍጡራን አውጥቶ ደም የጠማቸው አውሬ አድርጐ ይስላቸው ገባ፡፡ … “የመዘዙት ሰይፍ በቀላሉ ወደ አፎቱ አይመለስም - መቀንጠስ አለበት! ያው የሰው አንገት መሆኑ ነው…ደም መፍሰስ አለበት - ለበረሐው ዛር!”
ጥግ የተቀመጠው ረዳት ስለ ዛር ሲሰማ፣ እንደመንዘፍዘፍ አደረገው፡፡ ሹፌሩ ረዳቱን ሰረቅ አድርጐ እያየ “አሁንም ከዚያ መሠረተ ቢስ ፍርሐትህ አልወጣህም…በፍፁም ያየኸው ነገር የለም - አእምሮህ የፈጠረው ነው…”
“በዐይኔ በብረቱ ያየሁትንማ አልክድም” ረዳቱ ቅዝዝ ብሎ መለሰለት፡፡
ስለምን እንደሚያወሩ እንቆቅልሽ ሆነብኝ፡፡ ሹፌሩ ወደ እኔ ዘወር እያለ “ምን መሰለህ ከሦስት ቀን በፊት ከጅማ ወደ አዲስ አበባ ስንመጣ… አጅሬ ጊቤ በረሃ መሐል ሰይጣንን አየሁኝ ነው የሚለው…ለማመን የሚከብድ እኮ ነው”
ረዳቱ ቀበል አድርጐ “አዎን አይቼዋለሁ! ዲያብሎስን…በረዣዥም ጥፍሮቹ ጨበሬውን እያከከ…አይኖቹን እያሽከረከረ … ቀንዶቹን ዚግዛግ እየመታ…”
ከፊት ስትሄድ የነበረችው ጃጓር ሚኒባስ በድንገት ቀጥ ብላ ቆመች፡፡ ሁለት ጊዜ ክላክስ አሰማች፡፡ የእኛው ሹፌር “ሠላም ነው - እኛም ለሽንት” ብሎ ወረደ፡፡ እኔም ተከተልኩት፡፡ ከምሽቱ 5 ሰዓት። ከዋክብት በጥቁሩ ሰማይ እንደአሸዋ ፈሰዋል፡፡ አቤት ጨረቃዋ… ድምቀቷ፤ ምትሀቷ። ንጽህት፡፡ ፅርህት፡፡ አስፓልቱ ጠርዝ ላይ ቆሜ፣ አይኖቼን ወደ ገደሉ ላኩኝ፡፡ ጭው ያለ ድቅድቅ ጨለማ፡፡ ረዳቱ ሰይጣንን እዚህ መቀመቅ ይሆን ያየው? ቶሎ አይኔን ነቀልኩ፡፡ በዚህ ሰዓት ሰይጣንን ለማየት አንዳችም ፍላጐት የለኝም፡፡ የራሴ ጅል ሐሳብ እያሳቀኝ ወደ አይሱዚዋ ገባሁ፡፡ ጉዞአችንን ቀጠልን…ሹፌሩና ረዳቱ እየተቀባበሉ የሚናገሩትን መስማቱ ጆሮን ያግላል፡፡ …ስለ ጥልቁ የመናፍስት ዓለም፡፡ ስለበረሐው የዛር ውላጅ፡፡ ጊቢ ወንዝ ስለሚተፋቸው ሬሳዎች፡፡ ሴቷ ሰይጣን፡፡ የሰይጣን የጡት ልጅ፡፡…
የሚያወሩት ነገር ከእውነታው የራቀ ቢሆንም በዚያ ፅልመት መስማቱ ያንቀጠቅጣል፡፡
የተፈጠረ አንዳችም ነገር አልነበረም፡፡ ጊቤን ለቀን ወጣን፡፡ ጅማ በውድቀት ሌሊት ገባን፡፡ ከቦንጋ ስንወጣ ሌሊቱ እያከተመ፣ ከዋክብቱ ደብዘዝ እያሉ ወርቃማ የብርሐን አምዶች ተሰትረው - ጐህ ቀደደ፡፡
በሰፊው የተንጣለለው ደን ምትሐታዊ ውበት ተጐናጽፏል፡፡ የመላው ኢትዮጵያ እንጥፍጣፊ ድንግል ደን እዚች ምድር ግብአተ መሬቱን ሊፈጽም የተሰበሰበ ይመስላል፡፡
በሐይል ይዘንብ ጀመር፡፡ ዶፍ ወረደ፡፡ አስፈሪ ቁጡ! የመብረቅ ብልጭታዎች እንደ ሰይፍ ብልጭ ብለው ድርግም!! ግም!! ሹፌሩ አይሱዙዋን ጥግ አስይዞ አቆማት፡፡ የዝናቡ ውርጅብኝ፣ የነጐድጓዱ ብርቅርቅታ፣ እንደ ምጽአት ቀን ሰማይ ምድር ተደበላለቀ፡፡
ዝናቡ በመጠኑ ጋብ አለ፡፡ አይሱዙዋ በቆመችበት ጭቃው እንደማስቲሽ አጣብቆ አለቅ አላት፡፡ ሹፌሩ ማርሽ እየለዋወጠ ቢላት ቢሠራት አንድ ጋት ፈቅ ማለት አልቻለችም፡፡
ወጠምሻው ረዳት መኪናዋን ሊገፋ ወረደ፡፡ አንድ! ሁለት! ሦስት! ፎርሳ!...አይሱዚዋ ከገባችበት የጭቃ አረንቋ ወጣች፡፡ ወደፊት 100 ሜትር የሚሆን ሄዳ ቆመች፡፡ ረዳቱን ብንጠብቀው አልመጣም። ከመኪናዋ ወረድን፡፡ ዝናብ አርግዘው የነበሩ ደመናዎች ሰማዩን እርቃኑን ትተው ብን ብለዋል፡፡ እላይ ታች ሽቅብ ቁልቁል ባተልን፤ ረዳቱን ማግኘት አልቻልንም፡፡ ሹፌሩ የረዳቱን ስም እያምባረቀ ቢጠራም ምላሽ አልተገኘም፡፡ ከጥቅጥቅ ደኑ የሚሰማው የገደል ማሚቴ ልብን በፍርሃት ያርዳል። አንድ ሁለት መኪናዎች ምንም ሳይጠይቁን አልፈውን ሄዱ፡፡ ረዳቱ መኪናዋን የገፋባት ቦታ ላይ ቆምን፡፡ የከስክስ ጫማ አሻራው ጭቃው ላይ ታትሟል፡፡ የተሰነጣጠቀው መሬት ላይ አፈጠጥኩ። ምን አልባት በዚያ ስንጥቅ፣ ምድር ውጣው ይሆን? በሚል፡፡ እምጥ ይግባ ስምጥ አልታወቀም፡፡ እንደ እንፋሎት አየር ላይ በነነ? ወይስ ተነነ? “እንደ ኤልያስ በእሳት ሠረገላ ወደ ሰማይ አርጐ ይሆን?” በሚል ወደ ሰማይ ቀና አልኩኝ፡፡ አይኖቼ ብዙም ሳያማትሩ ከአንድ ረጅም ዛፍ ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ፡፡ ምንድን ነው የማየው?! ህልም ነው ወይንስ ቅዠት?ደንዝዤ ቀረሁ፡፡ በግዙፍ ዛፍ ግንድ ላይ የተጠመጠመ ዘንዶ!! አፉ ላይ ጥንድ ከስክስ ጫማዎች፡፡
ሹፌሩ ያየው ነገር ምትሀት ሆኖበት ጭቃው ላይ እንደታረደ ዶሮ እየተንደፋደፈ “እሪ!” ብሎ እየጮኸ ነበር፡፡ ከሰመመን እንደነቃ ሰው ፍዝዝ…ድንግዝ ብዬ ዳግም አይኖቼን ወደ ዛፉ…ዘንዶው የለም! በደመነፍስ በርግጌ ሹፌሩን ከጭቃው ላይ ጐትቼ እየተፍገመገምን…የህልም በሚመስል ሩጫ አይሱዙዋ ውስጥ ገባን፡፡
ሹፌሩ እንባው ኮለል ብሎ እየወረደ “ከሦስት ቀን በፊት መልአከ ሞትን አይቶት ነበር” አለ፡፡ “ማንን?”
“ዘንዶውን…”
“ማንን እያልከኝ ነው?” ከድንዛዜዬ ሳልወጣ፡፡
“ራሱን - ሰይጣንን!!” ሹፌሩ አንባረቀብኝ፡፡  

Read 5634 times