Wednesday, 30 July 2014 07:51

“ትናንትን ናፋቂ” የሆነው “ሰው ለሰው” የቴሌቪዥን ድራማ

Written by  ይትባረክ ዋለልኝ (Yetebarek@yahoo.com)
Rate this item
(1 Vote)

   “…ሕይወት የበጋውን ወራት ለማሳለፍ እምድር ውስጥ እንደተቀበረ ህያው እንቁራሪት በረጅሙ አንቀላፍታ ትገኛለች፡፡ በሌላው አገር የምትፍለቀለቀው የምትንቦለቦለው ህይወት እዚህ እፎይ ብላለች… ሁሉ ወግ ነው፡፡ ወግ በልማድ ታስሯል፡፡ ልማድ የሚጥስ የለም፡፡ ለመጣስ የሚያስብ እንኳን የለም፡፡ ወግና ልማድ በሜዳዎቹና በተራሮቹ ላይ እንደረጋው አቧራ… ረግተዋል፡፡ ተጋግረው… ጠጥረዋል፡፡…” (ደራሲ ዳኛቸው ወርቁ፤ “አደፍርስ”)
የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በየሣምንቱ ረቡዕ ምሽት ለ3 ዓመት ገደማ ለተመልካች ሲያቀርብ የቆየው “ሰው ለሰው” ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ መጠናቀቅ ነው ለዛሬው ጽሑፌ ምክንያት ሆነኝ፡፡ እንዳልኳችሁ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማው ባለፈው ረቡዕ በግድና በሐይል እንዲቋጭ ተደርጓል፡፡ ይህን ስል ግን ለድራማው ከፍተኛ ፍቅር ስለነበረኝና እንዲሁ እየተንዛዛ እንዲቀጥል ፈልጌ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ።
መላው የኢትዮጵያ ህዝብ “የሰው ለሰው” ተዋንያንን እንደ ቤተሰቡ አካል ቆጥሮ፣ ጊዜውን ሰውቶ፣ በከፍተኛ ፍቅር፣ አክብሮትና ትህትና ድራማውን ሲከታተል ቆይቷል፡፡ ይህም ህዝቡ ለጥበቡና ለሙያተኛው ያለውን ትልቅ ዋጋና ክብር የሚያሳይ ነው፡፡ ነገር ግን ድራማው በህዝቡ ቁመትና ፍላጐት ልክ በጭራሽ ሊቆም አልቻለም፡፡ በዚህ ጽሑፌ የማተኩረው በድራማው፣ በደራሲውና ድራማውን ባስተላለፈው የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ነው፡፡
ከ“ሰው ለሰው” ድራማ ህዝብ ምን አገኘ? የድራማው ፀሐፊና አዘጋጆች ፍላጐት፣ ህልም ምንድነው? የቴሌቪዥን ጣቢያው ኃላፊነቱ ለህዝቡ ነው ወይስ ለድራማው አዘጋጆች? እነዚህን ጥያቄዎችን በማንሳት ከድራማው ፍፃሜ ጋር እያነፃፀርን እንመልከት፡፡
የ“ሰው ለሰው” ተከታታይ ድራማ በቴሌቪዥን መታየት በጀመረበት ወቅት የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ቀልብ መሳቡ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በዚያው ግን አልቀጠለም፤ እያደር መሔጃው  እንደጠፋበት ፈረስ መደናበር ጀመረ፡፡
የቴሌቪዥን ድራማ በባህሪው የህዝቦችን ማህበራዊ ንቃተ ህሊና ከፍ በማድረግ ትልቅ ሚና የሚጫወተውን ያህል የሰዎችን አእምሮ በማደንዘዝም አሉታዊ ተፅእኖ ያሳድራል፡፡ የአገራችን የቴሌቪዥን ተመልካች ከ “ሰው ለሰው” ምን አገኘ ብለን ብንጠይቅ፣ መልሱ ምንም ነው፡፡ በየሣምንቱ ወሬ ብቻ! በመግቢያዬ ላይ እንዳሰፈርኩት የዳኛቸው ወርቁ “አደፍርስ” ዛሬም ሁሉ ነገር እንደትላንቱ ነው፡፡
ሃቁን ለመናገር ከዚህ ድራማ ምንም አዲስ ነገር አላገኘንም፡፡ ደራሲው ከተደራሲያኑ ልቆ መታየት ይገባዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን በህዝቡና በከያኒው መካከል እምብዛም ልዩነት እንደሌለ የ“ሰው ለሰው” ድራማ ጥሩ ማሳያ ይመስለኛል፡፡
በተለይ በሐገራችን በጐ ምግባርን፣ ሚዛናዊነትን፣ ግብረገብነትን፣ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህልንና የስልጣኔ አስተሳሰብን በህብረተሰቡ ውስጥ ማስረፅና አመለካከቱን መቀየር ያለበት ከያኒው ነው - በጠንካራ የጥበብ ሥራዎቹ፡፡ ግን አልተሳካም፡፡ “ሰው ለሰው” ድራማ እንኳንስ እያዝናና ሊያስተምር ይቅርና በቅጡ የሚያዝናና የቴሌቪዥን ድራማ እንኳ ሊሆን አልቻለም፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ ሣምንታዊ ድራማ ያገኘው፣ ያው እስከዛሬ በሀገራችን ውስጥ ጐልቶ የሚታየውን አሪስቶክራሲያዊ (በጉልበት፣ በአፈሙዝ) የሚገኝ የበላይነትን ወይም አሸናፊነትን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የዘመናት ባህላችን ሆኖ የቆየው የፊውዳል ሥርዓትና የጦርነት ታሪካችን ነው፡፡  
የኢትዮጵያ ህዝብ በጉጉት ሲከታተለው የቆየው የቴሌቪዥን ድራማ፤ የሰው ልጅን የሞራል ውድቀት እንጂ የሞራል ጥንካሬውን የሚያሳይ አይደለም፡፡ አንድ ሰው መራራና ፈታኝ ሁኔታዎች ሲገጥሙት ለሐቅ ሲል የሚወስደውን ትክክለኛ ምርጫ ሊያሳየን አልቻለም፡፡ ከዚህ ይልቅ ሰዎች እውነትን በሃይል ለማሸነፍ ሲሞክሩ ያሳየናል፡፡ ህብረተሰቡ ጥበብና ብልሃት ያልታደለ፣ በፍትህና በሚዛናዊነት የማያምን፣ ለሐቅና መርህ ደንታ የሌለው፣ ለግላዊም ሆነ ለብሔራዊ ክብር ዋጋ የማይሰጥ ሆኖ ነው የተቀረፀው፡፡ ከድራማው የተማርነው ነገር ቢኖር፣ ከኋላቀርና ያረጀ አስተሳሰብ መውጣት እንደማይቻልና ዛሬም በትላንቱ ዓይነት ህይወት ውስጥ መዳከር ዕጣፈንታችን መሆኑን ብቻ ነው፡፡
ለመሆኑ የዚህ ድራማ ፀሐፊና አዘጋጆች ፍላጐት ምንድን ነው? በድራማቸው ውስጥ ለሚኖሩበት ማህበረሰብ ምን ራዕይ ሊያሳዩ ፈልገዋል?
አንዳንድ ችግኝ ተተክሎ ይፀድቃል፡፡ አብቦ ያፈራል፡፡ ሌላ ዘር ይተካል፡፡ ዘሩን ያበዛል፡፡ አንዳንድ ችግኝ ደግሞ ቢፀድቅም አብቦ አያፈራም፡፡ ሌላ ዘር አይተካም፡፡ ዘሩን አያበዛም፡፡ ለብቻው ደርቆ ይቀራል፡፡ “ሰው ለሰው” ድራማም አብቦ የማያፈራ፣ ዘሩን የማይተካ መሆኑን ደራሲውና አዘጋጆቹ በሚገባ አሳይተውናል፡፡
ከሁሉም ያልገባኝ የድራማው ቁንጮ የሆነውን በሁለት ቤተሰቦች ላይ የሚያተኩር ታሪክ እንዲህ በተሽመደመደ መልኩ መቋጨት ለምን እንደተፈለገ ነው፡፡ ፖለቲካዊም ሆነ ማህበራዊ ጠቀሜታው አልታየኝም፡፡
የ“ሰው ለሰው” ድራማ ፀሐፊና አዘጋጆች ዋና ዓላማቸው የነበረው በተቻለ መጠን የአብዛኛውን የቴሌቪዥን ተመልካች ስሜት በሚገዙ ድርጊቶች ላይ በማነጣጠር (ሳቅ፣ ፍርሃት፣ ውጥረት፣ ሽብር…) ጊዜያዊ ብጥስጣሽ ሃሳቦችን ማቀበል ነው። (በነገራችሁ ላይ በቴሌቪዥን ድራማው ላይ ለተሳተፉት ተዋንያን ትልቅ አክብሮት አለኝ፡፡ ሁሉም ጥሩ የትወና ብቃታቸውን አሳይተዋልና፡፡)
የደራሲው ፍላጐት ዛሬም ህይወት ለውጥ እንደሌላት፣ እንደትላንቱ መሆኗን ማሳየት ይመስላል። ለዚህም ነው ለችግሮቻችን መፍትሔው ጉልበት፣ ጠመንጃና ሌላውን መስዋዕት ማድረግ እንደሆነ በድራማው ላይ የተመለከትነው፡፡
በአጠቃላይ “ሰው ለሰው” ለኔ ትላንትን የሙጥኝ ያለ (ትናንትን ናፋቂ እንዲሉ)፣ አዲስ ህይወት፣ አዲስ ተስፋ፣ በጐ የአስተሳሰብ ባህልና የህግ የበላይነት የከሸፉበት እንዲሁም የሃይል ሥርዓት የሰፈነበት ማህበረሰብን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ድራማ ነው። ብዙ ተመልካቾች እንዳሉትም ኢቴቪና “ሰው ለሰው” በኢትዮጵያ ፍትህ እንደሌለ አሳይተውናል፡፡   
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዛሬም በህዝብ ላይ እየቀለደ እንደሆነ “ሰው ለሰው” ድራማ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ነገም እንዲሁ “ዝም ብላችሁ መርጬ የሰጠኋችሁን ድራማ ተመልከቱ” ማለቱን ይቀጥላል። የቴሌቪዥን ፕሮግራም ያለተፎካካሪ በሞኖፖል ይዞ ከሚመራ ጣቢያ ከዚህ በላይ መጠበቅ ተገቢ አይመስለኝም፡፡

Read 3527 times