Saturday, 19 July 2014 12:35

የተማሪው ምኞት

Written by  አወል መሃመድ
Rate this item
(22 votes)

የአምስተኛ ክፍል የአማርኛ አስተማሪ የሆነው ዳዊት፣ ለተማሪዎች ስለደብዳቤ አፃፃፍ ካስተማራቸው በኋላ ለሚወዱት ሰው ደብዳቤ እንዲፅፉ አዘዛቸው፡፡ ከ10 ማርክ የሚያዝ ነው፡፡
ተማሪዎቹ፣ ደብዳቤ መጻፍ ጀመሩ፡፡
ዳዊት፣ ተማሪዎቹ ከፃፏቸው ደብዳቤዎች መካከል፣ የአንዱ ተማሪ ደብዳቤ  በጣም አስገረመው። በአንዲት ብጣቂ ወረቀት ላይ ያሰፈረውን ሃሳብ ከአንድ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ የመጣ ነው ለማለት ከብዶት፣ ደብዳቤውን ቤቱ ሆኖ ከአስር ጊዜ በላይ ቢያነበውም፣ አሁንም ከትምህርት ቤቱ ካፍቴሪያ ተቀምጦ ለሁለተኛ ጊዜ ደግሞ እያነበበው ነው፡፡
‹‹መምህር እኔ ለራሴ ብዙ የምመኛቸው ነገሮች ቢኖሩኝም ከሁሉም በላይ ግን እንዲሳካ የምመኘው ነገር ቢኖር ለኔ ሳይሆን ለእትዬ ነው፡፡ እትዬ ማለት እናቴ ነች፡፡ ስሟ እቴነሽ ሲሆን አባቴ በህይወት እያለ እቴ ብሎ አቆላምጦ ነበር የሚጠራት፡፡ እኛም ከሱ አፍ ለምደን ይሁን ልጅ እያለን እንድንጠራት አስተምራን ይሁን፣ ሳናውቀው እቴ እያልን ነው የምንጠራት፡፡ እቴ ብሎ የማይጠራት ሰው ለሷ ጥሩ አመለካከት እንደሌለው አድርጋ ነው የምትወስደው።
‹‹እኔ ለእቴ የምመኝላት ነገር ብዙ ቢሆንም በጣም አጥብቄ የምመኝላት ነገር ግን ሁሌ ስትስቅ እንዳያት ነው፡፡ ሁሌ እንድትስቅ ሊያደርጋት የሚችለውን ነገር ደጋግሜ ሳስብ የመጣልኝ ደግሞ ባል ነው፡፡ እናቴ ልክ እንደ አባቴ የምትወደው ባል ብታገኝ በጣም ደስተኛ የምትሆን ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም እናቴ እኛን ለማሳደግ ብቻዋን ስትለፋ ከሚፈጠርባት ጭንቀት የተነሳ ብዙ ጊዜ ስትስቅ አይቻት አላውቅም፡፡ አንዳንዴ እንኳን የምትስቀው ስላለፈው ጊዜ ስታወራና ስለ አባቴ ስትናገር ነው። ከዚያም አልፎ ከአባቴ ጋር ተቃቅፋ የተነሳቻቸው ፎቶዎች ላይ ያለው ምስሏ ብቻ ነው፡፡ እሱን ሳይ እትዬ እንደሳቀች አስባለሁ፡፡
‹‹ጥርሶችዋ እኮ ሲያምሩ፡፡ እኛ ክፍል ካሉ ሴቶች ሁሉ በጣም የሚያምር ጥርስ አላት የምትባለዋ ሳምሪ እንኳን ጫፍዋ ጋ አትደርስም፡፡ ይህን የምለው ያለማጋነን ነው፡፡
“መምህር ዳዊት፣ ማኪያቶህ እኮ ቀዘቀዘብህ” አለች ከፊቱ ተገተረች፤ የአስተማሪዎች ካፌ ባለቤት የሆነችው አልማዝ፡፡
ዳዊት በእጁ ከያዘው ብጣቂ ወረቀት ተላቆ፣ ቀና ብሎ ተመለከታት፡፡ ደብዳቤው ላይ የተገለፀችው እናትና ከፊት ለፊቱ የቆመችው አልማዝ፣ በዕድሜ እንደሚቀራረቡ ገመተ፡፡ በባህሪ ግን የተማሪው እናት ከዚች ትልቃለች፤ እ… ሷ… እ… ኮ…
“ዛሬ ምን ሆነሀል? እኔ ላይ መንቀባረርህ እንኳን የተለመደ ነው፡፡ የሰራሁልህ ማኪያቶ ላይ እንደዚህ መኩራትህ ግን በጤና አይመስለኝም፡፡” ብላ ፈገግ ስትል፣ በሽቦ የታጠረ ገጣጣውን ጥርሷን አይቶ ፈጠን ብሎ ዐይኑን ወደ ማኪያቶው አሸሸው፡፡ ማኪያቶውን አንስቶ ሲቀምሰው ቀዝቅዟል፡፡
“ሳይቀዘቅዝ አይቀርም፡፡ ላሙቅልህ?”
“ደስ ይለኛል” ፈጠን ብላ አነሳችው፡፡
“ግን ሰላም ነው? ዛሬ ፈዘሃል” ደግማ ጠየቀችው።
“ሰላም ነው” አላት ቶሎ እንድትሄድ ስለፈለገ ፊቱን ፈገግታ ነስቶ፡፡ ፊት ቢነሳትም አልገባ ያላት አልማዝ እያጉረመረመች ሄደች፡፡ ዳሌዋን እያማታች ወደ ማሽኑ ስትራመድ ያለችውን ባይሰማትም ጀርባዋ ላይ የተተከሉት ዐይኖቹ ግን ይህ ዳሌ ባይወዛወዝ ማጐምጀቱ ከፍ እንደሚል እያሰበ፣ ለሁለት ቀን በሃሳቡ ስትመላለስ የነበረችው እትዬ፣ ሥርዓት ባለው አኳኋን ስትራመድ በሃሳቡ ተመለከታት፡፡
“ምን እየሆንኩ ነው? ስንት ቆንጆ ሴቶችን ፊት እየነሳሁ ያበረርኩት ኮስታራው ሰውዬ፣ በልጅ ጽሑፍ የተገለፀችውን አንዲት እናት ላፈቅር? ኧረ አይሆንም” አለ ለራሱ ብቻ በሚሰማ ድምፅ፡፡
“ኖ… ኖ ስለ ‘ሷ ካሁን በኋላ ማሰብ የለብኝም” ብሎ ወደ ብጣቂዋ ወረቀት ዐይኖቹን ላከ፡፡
“እትዬ የጠይም ቆንጆ መሆንዋን ብዙ ሰዎች ሲያወሩ ሰምቻለሁ፡፡ እንዲያውም ባለ ሱቁ አብደላ፣ የኢትዮጵያ ቁንጅና ውድድር አሸናፊ ከሆነችዋ ሃያት አህመድ ጋር ብትወዳደር እንደምትበልጣት አልጠራጠርም ብሎኝ ነበር፡፡ እኔ የሚያሾፍ መስሎኝ ስስቅ፣ “ዕውነቴን እኮ ነው ወላሂ! በጣም ነው የምትበልጣት” ብሎ ተቆጣኝ፡፡ እኔም አመንኩት ምክንያቱም ሙስሊሞች ወላሂ ብለው እንደማይዋሹ አውቃለሁ፡፡”
ዳዊት ወረቀቱን ለሁለት አጥፎ ጠረጴዛው ላይ አስቀመጠው፡፡
“ይህ ልጅ እያላገጠብኝ ይሆን እንዴ? ለነገሩ እንዴት ሊሆን ይችላል፡፡ የእኔን የሴት ምርጫ ማን ሊነግረው ይችላል? ምርጫዬን ለቅርብ ጓደኞቼ ብቻ ነው የተነፈስኩት፡፡ በደብዳቤው ላይ ያለችው ሴት፣ የሴት ውበት ምርጫዬን ሁሉ እኮ ነው የምታሟላው። ነገ ወላጅ እንዲያመጣ አስገድጄው ካልተዋወቅኋት  የሆነ ቅዥት ውስጥ ገብቼ ማበዴ የማይቀር ነው” ብሎ ሰዓቱን ተመለከተ “ያ የተረገመ ፈልፈላ ወዳለበት ክፍል ለመግባት አርባ አምስት ደቂቃ ይቀረኛል፡፡” ብሎ ተማረረ፡፡
የሆነ ፍርሃት በውስጡ ሲላወስ ተሰማው፡፡ እያሰበ ያለውን ነገር ቢያደርገው ከሥነ ምግባር ውጪ እንደሆነ በማወቁ ነው፡፡ በየግምገማው የአስተማሪ ጓደኞቹን ጉድ በይፋ እየተናገረ ሲያሳፍራቸው እና ሲያሳጣቸው የነበረው መምህር፣ራሱ ከሥነ ምግባር ውጪ ሆኖ ቢገኝ ምን እንደሚባል ሲያስበው ጨነቀው፡፡ ይህ እና ይህን የመሳሰሉ የሥነ ምግባር ጉዳዮችን እያሰበ፣ የተማሪውን እናት አስጠርቶ ለመተዋወቅ ያለውን ጉጉት ከባድ አደጋ ቢኖረውም ከማድረግ እንደማይመለስ ወሰነ፡፡ ህሊናውም ዝም ብሎ እጅ ላለመስጠት መግደርደሩ እንጂ፣ የወንድነት ስሜቱ  እንደሚያሸንፍ እርግጠኛ ነበር፡፡
  “ይኸው ማኪያቶህ! ትኩስና ያጐደልከውን በራሴ ወጪ ሞልቼ ነው ያመጣሁልህ››  ብላ ጠረጴዛው ላይ በታላቅ ትህትና አስቀመጠችለት፡፡
“አመሰግናለሁ” ብሎ የማኪያቶውን ብርጭቆ አነሳው፡፡ ማኪያቶውን እንደቀመሰ በጥንቃቄ እየተመለከተችው እንደሆነ ስለሚያውቅ፣ እርሷን ለማስደሰት ሲል ጣዕሙን ሳያጣጥም፣ “በጣም ይጣፍጣል” ብሎ ጠቀሳት፡፡ በፈገግታ ተውጣ እየተሽኮረመመች ጥላው ሄደች፡፡
የካፌው ደንበኞች የሆኑት አስተማሪ ጓደኞቹ፣ አልማዝ ለእርሱ ያላትን ፍላጐት ተገንዝበው ሲጫወቱባት፣ “ጥርስሽ ቢያምር እኮ ይጠብስሽ ነበር” አልዋት፡፡ እርሷም ሳትውል ሳታድር እንደፀበል ዕቃ ውጪ ያድሩ የነበሩትን ጥርሶቿን ለማሳመር ስትል፣ በአስተማሪ ደሞዝ ሲተመን ከአንድ ዓመት ደሞዝ በላይ በሚሆን ብር ጥርሷን በብረት አሳጥራ መጣች፡፡
“አሁንስ?” አለቻቸው፣ ማኪያቶ በነፃ እየጋበዘች።
“አሁንማ ተስፋ አለሽ” አሏት፡፡ ድጋሚ መጋበዝ ፈልገው እንጂ ጃንደረባው የሚል ቅፅል ስም ያወጡለት ጓደኛቸው ምኞቷን እንደማያሳካላት ያውቃሉ፡፡
ጠቆር ያለ ማኪያቶ በፍቅር የሚወደው ዳዊት፣ በቀድሞ ልማዱ ከጠረጴዛው ላይ ያነሳትን የማኪያቶ ብርጭቆ ወደ ቦታዋ የሚመልሳት በቅጽበት ጭልጥ እንዳደረጋት ነበር፡፡ ዛሬ አንዴ ቀምሶ አስቀመጣት። ብጫቂ ወረቀቷን እያመነታ አነሳት፡፡ ደጋግሞ በማንበቡ ብዛት በቃሉ የሸመደደው ቢሆንም፣ የማንበብ ፍላጐቱን መግታት አልቻለምና ማንበብ ጀመረ፡፡ የወረቀቷ ጀርባ በጣቶቹ ላብ ነጭነቷን ለቃ ቆሽሻለች፡፡
‹‹አንድ የምፈራው ነገር አለ፤ ምኞቴ እንዳይሳካ የሚያደርግ፡፡ የመጀመሪያው ራሷ እትዬ ስትሆን፣ እኛን አሳድጋ ለወግ ለማዕረግ ካልበቃች ሌላ ባል እንደማታገባ ደጋግማ ነግራኛለች፡፡ እትዬ ደግሞ ቃልዋን የማጠፍ ልማድ የላትም፡፡ ሁለተኛ እኛ ነን፤ እትዬን ወዶ የመጣ ወንድ እኔን እና ሁለት ወንድሞቼን ጠልቶ የሚሸሽ ይመስለኛል፡፡ ሦስተኛው ችግር ግን ትንሽ ቀለል ያለ ቢሆንም፣ ከችግሮቹ መካከል እንደ አንዱ መታየት ይችላል፡፡ እትዬ በገባችው ቃል ላይ አንድ ተአምር ተፈጥሮ የሆነ ሰው ወዳ ብታመጣ እኛ ጠልተነው ችግር እንዳንፈጥርባት እፈራለሁ፡፡
‹‹አምላኬ አሁን የጠቀስኳቸውን ችግሮች አልፎ የግልዋ ባል ይስጣት እንጂ፣ በእኛ በኩል የሚገጥማትን ችግር እኔ እንዲስተካከል አደርጋለሁ፡፡ በፍፁም በየትኛውም መንገድ እኛ ለእርሷ እንቅፋት እንደማንሆንባት ደጋግሜ ቃል እገባለሁ፡፡
‹‹አምላኬ እባክህን ለእትዬ የእኔ የምትለውን ሰው ስጣት! በአሥራ ሰባት ዓመቷ ተድራ በማከታተል ሦስት ልጆችን ወልዳለች፡፡ ስምንት ዓመት የቆየው ትዳርዋ በሚያሳዝን መንገድ ከተቋጨ አምስት ዓመት ሞላው፡፡ ታዲያ አታሳዝንም? ገና እኮ አንድ ፍሬ ልጅ ነች፡፡ ብዙ ደስታ ማግኘት አለባት፡፡ እባክህ አምላኬ አንድ መልዓክ መሳይ ተወዳጅ ሰው ላክላት፡፡››
 ዳዊት ካቀረቀረበት ወረቀት ቀና ሳይል የተጀመረው የትምህርት ክፍለ ጊዜ መቋጨቱንና የሚቀጥለው የሚጀምርበት ሰዓት መድረሱን የሚያስተጋባው ኤሌከትሮኒክ ጡሩንባ አንባረቀ፡፡ በሰማው ድምፅ ተደስቶ፣ የጀመረውን ማኪያቶ ጠጥቶ ሳይጨርስ፣ ከካፌው በፍጥነት ወጣ፡፡
       አምስተኛ ‹‹ሀ›› የሚል ፅሑፍ በሩ አናት ላይ የተለጠፈበትን ክፍል ከርቀት ሲመለከት ደነገጠ፡፡ ሩጫ የሚመስል ፈጣን እርምጃው ወደ ሕፃን ልጅ ዳዴ በአንድ ጊዜ ተቀየረ፡፡ ሁልጊዜ ለመግባት የሚጓጓለት ክፍል መሆኑን ዘነጋው፡፡ የልቡ ምት እንደ ትግርኛ ዘፈን የሙዚቃ ምት ‹‹ድም፣ ድምድም… ›› እያለ ነው፡፡
‹ብመለስስ… ኖ… ኖ… ኖ… ለምን አይቀርብኝም? በቃ ገብቼ እንደ ዱሮዬ አስተምሬ እወጣለሁ፡፡ ኖ…ኖ… ኖ ይሄማ ቀሽምነት ነው› ብሎ መራመድ እንደጀመረ ድንገት ፈገግ አለ፡፡
“ወንዳታ! አሪፍ ሃሳብ… እንዲያውም እንዲህ ነው የማደርገው…” ብሎ በፍጥነት እየተራመደ ወደ ክፍሉ ገባ፡፡ እርሱ ሲገባ በክፍሉ ይሰማ የነበረው ጫጫታ ከመቅፅበት “ፖዝ›› አደረገ፡፡ ከሰኮንዶች በፊት የጠፋው ፍርሃቱ፣ የፈረስ ኮቴ በሚመስል ምት፣ ልቡን እየደለቀ መጣበት፡፡ ተማሪዎቹን ቀና ብሎ ማየት ፈርቶ እንዳቀረቀረ የክፍሉን አለቃ ጠርቶ እንዲከተለው ነግሮት ወጣ፡፡ የክፍል አለቃው ወጥቶ በጭንቀት የሚንጐራደደውን መምህሩን በአትኩሮት ተመለከተው፡፡ መምህሩ እጁ ላይ ያለውን የተማሪዎች ደብዳቤ ዘረጋለት፤ አለቃውም ተቀበለው፡፡
“እ… ይኸውልህ የቤት ሥራው ታርሟል፡፡ ስማቸውን እየጠራህ ለሁሉም ስጣቸውና ስትጨርስ እያንዳንዳቸው በተራ ቁጥራቸው እየተነሱ የፃፉትን ደብዳቤ እንዲያነቡ አድርግ! እኔ ትንሽ ስላመመኝ ዛሬ አላስተምርም” ብሎ ሳይጨርስ አለቃው ወደ ክፍሉ ሊገባ ሲል በፍጥነት ጠራው፡፡
“አቤት ቲቸር”
“እ… እ… ዮሐንስ ደስታን ጥራልኝ”
አለቃው ራሱን በአዎንታ ነቅንቆ ወደ ክፍሉ ገባ፡፡ መርዶ ለመናገር የተላከ መልዕክተኛ ይመስል እየተቁነጠነጠ፣ ሰረቅ እያደረገ ወደ በሩ ሲመለከት፣ ከተጠራው ተማሪ ጋር ዐይን ለዐይን ተጋጩ፡፡ መምህር ዳዊት ሲሰርቅ እንደተያዘ ሌባ በፍርሃት ዐይኖቹ ማረፊያ አጥተው ተረበሹ…
“አቤት ቲቸር” ዮሐንስ ተናገረ፡፡
“እ… እ… ነገ ጥዋት ወላጅ እንድታመጣ”
ተማሪ ዮሐንስ፣ መልሱን ሳይሰማ በእፎይታ መክነፍ ሲጀምር፣ መምህሩ አንድ ነገር ትዝ ብሎት ባለበት ተገተረ፤ “ወላጅ እኮ ነው ያልኩት! ሌላ ሰው ይዞ ቢመጣስ? ምን አይነት መከራ ውስጥ ነው የገባሁት? …   ድጋሚ ላስጠራው? እያለ በሃሳብ ሲደናበር፣
“ቲቸር ምን አጥፍቼ ነው?” የሚል አሳዛኝ ድምፅ ሰማ፡፡ ዳዊት ሲዞር  ሹራብ የለበሰ ጠይም ልዑል የመሰለ ሕፃን፣ ዕንባ ያቀረሩ ትላልቅ ዐይኖቹን መደበቅ ተስኖት ይከተለዋል፡፡ ዮሐንስን ሲመለከት ከሀዘኔታ ይልቅ በውስጡ የታሰበው እናቱ እንዴት በሥርዓት እንዳሳደገችው ነበር፡፡
“ይኸውልህ ዮሐንስ እናትህን አምጣ ያልኩህ ስላጠፋህ ሳይሆን ጉብዝናህን ለእናትህ ነግሬ ላሸልምህ ፈልጌ ነው፡፡” ዮሐንስ በሰማው ዜና ተደስቶ መዝለል ሊባል በሚችል የሰውነት እንቅስቃሴ ሲፍለቀለቅ፣ ዳዊት ትክ ብሎ ጥርሱን እየተመለከተ የእናቱ ጥርስ ምን እንደሚመስል መገመት ጀመረ፡፡
“ቲቸር! ስለ ደብዳቤው ግን አትነግራትም አይደል!?” ካለ በኋላ በፍጥነት የመምህሩን ጣቶች በአትኩሮት ተመለከተ፡፡
“ብነግራት---ምን ችግር አለው? መልካም ምኞት እኮ ነው የተመኘህላት” ብሎት ፈገግ አለ፡፡ የዮሐንስ አይኖች ካረፈበት ተከትሎት ሲሄድ ግን፣ ከገዛ ራሱ ጣት ላይ አረፈ፡፡ ዮሐንስ ከግራ እጁ ጣት ላይ ቀለበት ሲፈልግ፣ የነበረ ስለመሰለው ተደስቶ ቀና ሲል፣ ዮሐንስ በፈገግታ እንደበራ ዘሎ ተጠመጠመበት፡፡
ዳዊት የሁለት ቀን ፍቅረኛውን ያገኛት ይመስል በሀሴት ተሞላ፡፡ አባት ልጁን እንደሚዳብስ፣ ዳዊትም የዮሐንስን ፀጉር፣ ፍቅር በተሞላባቸው ጣቶቹ በስስት ተመላለሰባቸው፡፡

Read 4262 times