Saturday, 12 July 2014 12:37

ዳይኖሰር

Written by  ዮናስ ነማርያም
Rate this item
(9 votes)

የተከራየሁበት ቤት ልጅ ደመቀ ወደ ግሮሠሪዋ ገባ፡፡
ደመወዝ የምቀበልበትን ቀን አሥልቶ፣ እንደ ልክስክስ ውሻ አነፍንፎ የትም ልግባ ከች! ይላል፡፡ እናም አምስት ደብል ጂን የመጋበዝ ያልተፃፈ ሕግ ያስገድደኛል፡፡ ለምን? ደመቀ የአርባ ቀን እድሉ በዝቅጠትና ስካር የተጠቃለለ የሠፈር አውደልዳይ ነው፡፡
ከጐኔ ተቀመጠ፡፡ የጐን ውጋት፡፡ ደብል ጂን አዘዘ - አንገት ማስገቢያ፡፡ እንጥፍጣፊ ሳያስቀር ጨለጠ፡፡ እርቃኗን ቀርታ በባዶነት የምታዛጋውን መለኪያውን ትክ ብሎ አፈጠጠባት - በመቀጠል እኔን፡፡ እንደ ዱርዬ ድመት እየተቁለጨለጨ “ሚያው ጂን” ማለት ለቀረው ደመቀ ደብል ጂን አዘዝኩ - ለእኔም፡፡
“ምስኪን ፍጡር ነኝ” ሲል ጀመረ፤ እንደተለመደው
“ከሕይወት አገኘሁ የምለው ብቸኛው በጐ ነገር ከብሌን ጋር ያሳለፍኩት ንጹህ ፍቅርን ነው…ነበር…እህህ…”
ከብሌን ጋር ለተወሰነ ጊዜ አብረው ያሳለፉ መሠለኝ፡፡ አጠገቤ ዝር እንዳትል ብላ ካንባረቀችበት ግፋ ቢል አምስት ዓመት ቢያልፈው ነው፡፡ ጊዜው ረዘመ ቢያስብልም ከደመቀ እድሜ አንፃር (47) አምስት አመት ምን አላት፡፡ አንድ ቀን የግሉ እንደምትሆን ወደ ቅዠት ያደላ ህልም አለው፡፡
“ግን ጥቂት እንከኖቼን አልወደደችልኝም…ከጠዋት እስከ ውድቅት መጨለጤን -ጢምቢራዬ ዞሮ በየቦዩ ሥር መጋደሜ - ዘባተሎ አለባበሴ …ከሥራ አጥነቴ ጋር ተደማምሮ…እነዚህ ኢምንት ቅንጣት እንከኖቼ…እናም በስካር መንፈስ ተገፋፍቼ የፈፀምኩት ተራ ሌብነት ብሌን ጆሮ ሳይደርስ አልቀረም፡፡” ብሎ በሐፍረት አቀረቀረ፡፡
እንደ ጥጥ ቦጭቀህ አማኸው አትበሉኝና፣ ደመቀ በስካር መንፈስ ተገፋፍቶ ምን እንደፈፀመ ጠቆም ሳላደርግ አላልፍም፡፡
ፋሲካ ቡና ቤት፡፡ ደመቀ በሞቅታ ተገፋፍቶ ትንሹን አዋሽ ወይን ጠጅ ጉያው ስር ይወሽቃል። የጃኬቱን ዚፕ ዘግቶ ከቡና ቤቱ ሊወጣ በሩ ጋ ከመድረሱ፣ የወይን ጠጁ ጠርሙስ ከጉያው ሾልኮ ወለሉ ላይ ይከሰከሳል፡፡ ወይን ጠጅ ወለሉ ላይ የረጋ ደም መስሎ ተንጣለለ፡፡ ዌይተሩ ደመቀ ላይ ቡጢ አሳረፈበት፡፡ ሁለት የፊት ጥርሶቹ ረገፉ፡፡ በሕይወት ዘመኑ የረገፉበት ጥርሶች ብዛትም ወደ አምስት ከፍ ያሉት ያኔ ነበር፡፡
ደመቀ እየቀበጣጠረ ነው….”እንዲሁም በአጋጣሚ የምፈጽማቸው ስህተቶች….በቅርቡ በቤተሰብ ፊት የደረሰብኝን ቅሌት በአይንህ ያየኸው ነው”
ውድ አንባብያን - እኔ እከሌ ይህን በላ…ይህንን ለበሰ…እንዲህ አደረገ እያልኩ ማማት አልወድም። በተለይም የቤተሰብ ገበናን ለባዕድ መዘክዘክ ነውር ይመስለኛል፡፡ ቢሆንም ደመቀ በቤተሰብ ፊት የደረሰብኝ ቅሌት በሚል የጀመረውን ታሪክ የማሳወቅ የተራኪነት ግዴታ ያለብኝ ይመስለኛል - እህህ…ጉድ ነው!...
ነገሩ እንዲህ ነው…ደመቀ አንዷን የመንገድ ላይ ጅራሬ ክፍሉ ይዟት ይገባል፡፡ እንደገቡ የአበሻ አረቄ ለብርድ በሚል መጠጣት ይጀምራሉ፤ ልጅቷ አረቄውን በላይ በላዩ ስትግፍ አብሾዋ ይነሳባትና ብርጭቆውን ወለሉ ላይ ታደቀዋለች፡፡ ጥፍሯን አሹላ…ጥርሷን እያንቀጫቀጨች ደመቀን ልትቦጭቀው ይሁን ልትዘነጥለው ስትል በሩን ከፍቶ ለማምለጥ ተውተረተረ፡፡
አንገቱን አነቀችው፡፡ እንደ ብረት ከጠነከረው እጅዋ አንገቱን ማስለቀቅ አልቻለም፡፡ ትንፋሽ አጠረው - ወደ ሞት ወሰድ አደረገው - ጨርሶ እንኳን አልወሰደውም - መለስ አለ፡፡ እንደጦስ ዶሮ አሽቀንጥራ ወረወረችው፡፡ ያኔ ይመስለኛል ትንፋሹ መለስ ሲልለት የድረሱልኝ ጩኸቱን የለቀቀው። ከወንድሞቹ ጋር ደመቀ ክፍል ገባን፡፡ ልጅቷን አረጋጋናትና ሰከን አለች፡፡ ከመውጣቷ በፊት “ሂሣቤን” ስትል ጠየቀች…
“ምንሽ ተነካና ነው የሚከፈልሽ?!”  አሳፋሪው የደመቀ ድምጽ ከተወተፈበት ሥርቻ፡፡ 100 ብር ዳኒ ሰጣት፡፡ ግድንግድ ደዘደዝ፡፡ ይችን ቋጥኝ የምታክል መጋዣ፣ ኮስማናው ደመቀ ምንስ… እንዴትስ ሊያደርጋት ነበር? ደመቀ ይህን የመሰሉ በኮሜዲ ፊልም ላይ እንጂ በቤተሰብ መሐል መታየት የሌለባቸው ኮሚክ ስህተቶችን ሲፈጽም አመታት ያስቆጠረ የ47 ዓመት “ጉድ” ነው፡፡…
ለደመቀም ለእኔም ደብል ጂን አዘዝኩ…
“…ብሌን በእኔ ላይ ግፍ ሠርታለች…እንከን የሌለበት ማንም የለም….ግን የእኔ ኢምንት…ቅንጣት ስህተቶቼ ለምን እንደሚጋነኑብኝ…” አለ - ደመቀ። “ቅንጣት እንከኖቼ ትላለህ እንጂ እንከኑ አንተው ነህ” ብለው ልቡ ሊሰበር ይችላል ብዬ ተውኩት፡፡ ስለደመቀ ልብ ካነሳን አይቀር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሳሳ ብላ እንደመደካከም እያደረጋት ነው - አንዳንድ ጊዜ በፍጥነት ደቅ! ደቅደቅ! ትልና እንደመቆ ይሁን መምታት ትንተፋተፋለች፡፡ ያኔ ዝልፍልፍ ብሎ አይኖቹ ግልብጥብጥ ይሉና ወሰድ ያደርገዋል፡፡ ጨርሶ እንኳን አይወስደውም፡፡ እንደ ደመቀ አይነት ሰዎች በቀላሉ ለሞት እጃቸውን አሳልፈው አይሰጡም። ከአደገኛ ጠጭነቱ ጋር የጨጓራ አልሠር፣ የጉበት መታወክ፣ …ደመቀ ከሚሰቃይባቸው በሽታዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በፈርጀ ብዙ የጤና ቀውስ በመሰቃየት ወደ ሞት መለስ ቀለስ ማለቱ በመደጋገሙ፣ አብሮ አደግ ጓደኞቹ ሁሌም እንደመከሩት ነው - “ደመቀ መጠጥ አቁም አለበለዚያ አይናችን እያየ አፈር ሊበላህ ነው”…የህይወት ምፀት ግን፣ ደመቀ ሳይሆን አብዛኛዎቹ መካሪ ጓደኞቹ የአፈር ሲሳይ ሆነዋል። አብሮ አደግ ጓደኞቹ በሞቱ ቁጥር “ወይኔ ጓዴ! መካሪዬ!” እያለ ስቅስቅ ብሎ እያለቀሰ ስንቱን የቀበረ ሰው ነው፡፡ “አለሁ በለኝ መካሪዬ” የምትለዋ የደመቀ ሙሾ በብዙዎች ቀብር ላይ ተደጋግማ በመሰማቷ፣ ሰዎች ደመቀን መምከር ፈሩ፡፡ ደመቀን መምከር ማለት ለመላዕከ ሞት “ከዚች ምድር ገላግለኝ” የሚል ቴክስት እንደመላክ ተቆጠረ፡፡
ደብል ጂን ለሞት እምቢ - ለእኔም አዘዝኩ። ደመቀ ሞቅታ በፈጠረበት መንተፋተፍ “ለፍቅር ያኘሁት ምላሽ ክህደት ንቀት ነው…እድለ ቢስ ነኝ፤ በተራ ምክንያት የ3ኛ ዓመት ዩኒቨርስቲ ትምህርቴን ያቋረጥኩት በእድለቢስነቴ ነው… ሳግ ተናነቀውና ማንባቱን ተያያዘው፡፡ እንባው እንደደራሽ ውሃ በጉንጩ ኩልል አለ፡፡ እንባውን ሳይ ሐዘን ልቤን ጠቅ አደረገው - ምክንያቱም ደመቀ ሥካሩን በእምባው እያበረደ፣ በአዲስ ኃይልና ጉልበት እንደሚጨልጥ ከልምድ አውቀዋለሁ፡፡ ከዩኒቨርስቲ የ3ኛ አመት ትምህርቱን ማቋረጡ ሀቅ ነው - ከ25 ዓመት በፊት። ሩብ ምዕተዓመት መሆኑ አይደል!
የፈራሁት ደረሰ - ደመቀ ስካሩን በእንባው አብርዶ በአዲስ መንፈስ ጂኑን ይቀነድበው ጀመር። 6ኛ ደብል ጂን በራሱ ጊዜ አዘዘ፡፡ አልገረመኝም… “እንባህ ነው ጠላቴ” በሚል ርዕስ የተፃፈ ግጥም ይኖር ይሆን?...ደመቀ መቀበጣጠሩን ቀጥሏል። “የገዛ ህይወቴ ለእኔ እንቆቅልሽ ናት - ቤተሰቦቼ አይገቡኝም፤ የመኖር ጥበብ - የህይወት ሕግ አይገባኝም፤ አልገባኝም…ከአለም አቀፍ ሕግ ጋር መዋሀድ ሳይችል ቀርቶ ከምድረገጽ የጠፋው ዳይኖሰር ማለት እኔ ነኝ…የህይወቴ ክር መበጠሻው ቀርቧል…”
…በመሰላቸት አዛጋው…
“ከልብህ አዳምጠኝ…ከአንተ የተሻልኩ ሰው ነኝ…አለኝ ከምትለው መናኛ ድግሪ የእኔ የ3ኛ አመት ትምህርት አሥር እጅ ይበልጣል”
ሂሣብ ዘጋሁ፡፡ የህይወቴ ቅዠት ለሆነው ደመቀ የስድስት ደብል ጂን ሂሳብ ውስጤ እያረረ ከፈልኩ። ደመቀ እየደነፋ ነው… “የማንም ልቅምቅም - የሰው ልክ አያውቅም!”….
ምስኪን ነኝ - እድለቢስ…ሲል እንዳልነበረ እነሆ እኔን “የማንም ልቅምቅም” ከማለት ደርሷል ….ባጐረስኩ እጄን ተነከስኩ ቃል በቃል በእኔ ላይ ደረሰ፡፡ የመጨረሻዋን ጭላጭ ጨልጦ አፈጠጠብኝ። ዶቃ አይኖቹ አሁንም ለመጠጣት ያለውን ውስጣዊ ፍላጐት ያሳብቃሉ፡፡ እኔም በጥላቻ ትክ ብዬ አፈጠጥኩበት፡፡ ቡዳ ብሆን መሬት ላይ ጠብ ብሎ በተንደፋደፈ ነበር፡፡
ከግሮሠሪዋ ወጣን፡፡ ሞቅ ብሎኛል፡፡ ደመቀ ጢው ብሏል፡፡ …ቤት ልንደርስ ጥቂት ሲቀረን ደመቀ ዘፍ ብሎ መሬት ላይ ተቀምጦ ቀረ፡፡ “ተነስና እንሂድ”
“ወዴት ነው የምንሄደው?”
“ወደ ቤት እንግባ”
“ወደ መቃብር ነው መግባት የምፈልገው”
ሰዓቱ ገፍቷል - በዚያ ላይ ሠፈራችን ሕግና ፍትህ ዘግይተው የሚደርሱበት የእሪ በከንቱ እህት ከሆነ ቆይቷል፡፡ ጥዬው ልሂድ? ግራ ግብት ብሎኝ የደመቀን ዲስኩር ለመስማት ተገደድኩ፡፡ “ራሴን አንጠለጥላለሁ…ብሌንና ወንድሞቼ በእኔ ላይ የፈጸሙት ግፍ ትዝ እያላቸው በፀፀት እምባቸውን…ለእኔ እራስን ማጥፋት አዲስ አይደለም - ሞክሬዋለሁ…አልተሳካልኝም እንጂ…መኖርም መሞትም ያልቻልኩ…ወይኔ ደመቀ!”
…በቅርቡ በገመድ ቢጤ ተንጠልጥሎ ነበር። በቸልተኝነት ይሁን ከጥንቃቄ ጉድለት፣ ገመዱን ባግባቡ ስላልቋጠረው ቁልቁል ወለሉ ላይ በአፍጢሙ ተከሰከሰ…ደግነቱ የላይኛው ከንፈሩ ከመሰንጠቅ በቀር ከፊት ጥርሶቹ አንዱም አልረገፈም - የፊት ጥርሶቹ ከወራት በፊት በደረሰበት ቡጢ ስለመርገፋቸው የተረኩላችሁ መሰለኝ፡፡
ቤት ስንደርስ እኩለ ሌሊት አልፏል፡፡
…ሸለብ ሊያደርገኝ ሲል ከፍተኛ የማጓራት ድምጽ ብንን አደረገኝ፡፡ ወደ ደመቀ ክፍል ገባሁ፡፡ ደመቀ እያንቋረረ እያስመለሰው ነበር፡፡ የተቆራረጠ የረጋ ደም - ሙሉ ጉበቱን ተፋ ማለቱ ይቀላል፡፡ ወንድሞቹ ቢኒና ዳኒ ተሸማቀው ያዩታል፡፡ ደመቀ እየተንተፋተፈ “ወንድሞቼ፤ ሽንት ቤት በድብቅ ማስመለስ አላቃተኝም - በናንተ ፊት ደም የተፋሁት የመጠጥን ገዳይነት እንድታውቁት ነው - እኔን ያየ ተቀጣ” ደመቀ ትንፋሽ አጠረው መሰል ንግግሩን አቋርጦ ዳኒ ክንድ ላይ ዝልፍልፍ አለ፡፡ አልጋው ላይ ተሸክመን አጋደምነው፡፡ እንቅስቃሴ አልባ በድን ሆኗል፡፡ የወንድሞቹ አይኖች እንደ ጦር ወደ እኔ ሲወነጨፉ ተሸማቀቅሁ - “እንዲህ እስኪሞት ድረስ አጠጣኸው” በሚል፡፡
ደመቀ ለዘመናት ከስንቱ ትውልድ ጋር ሲጠጣ እንዳልኖረ ዛሬ በእኔ የግብዣ ጦስ ህይወቱ ሊያልፍ በቋፍ ነው፡፡ ብርክ ያዘኝ፡፡ “እኔን ያየ ተቀጣ” የሚለው ቃሉ የመጨረሻም ኑዛዜውም መሰለኝ። ለወንድሞቹም ህይወቱን አሳልፎ ክልትው ያለም መሰለኝ፡፡ ከዚህ የቁም ቅዠቴ ያወጣኝ ደመቀ “ውጡልኝ ልተኛበት” ብሎ ሲያንባርቅ ነው፡፡ እንኳን ህይወቱን የአንድ ቀን እንቅልፉን አሳልፎ ያልሰጠው ደመቀ፡፡
ድህረ ታሪክ
የክረምትን መግባት ተከትሎ የደመቀ የጤና ቀውስ ተባባሰ፡፡ ያቺ አመታዊ ሳል ተነስታ ታንተከትከው ጀመር፡፡ በቅዝቃዜ ሰውነቱ ራደ። “ለቅዝቃዜው” በሚል የሚወስዳት አረቄ ሰበብ፣ ጫና የበዛባት ጨጓራው ሆድ እየባሳት የአሲድ እንባዋን ትረጨውም ጀመር፡፡ እናም እንደቃር ይሁን እንደ ጣር እያንቋረረ ያስመልሰዋል፡፡ ሐሞት መሳይ ወደ ቢጫ የሚያደላ ዝልግልግ ትውከት፡፡ ሕመሙ ፋታ አልሰጥ ብሎት በጽኑ ቢሰቃይም፣ በሥራ አጥነትና በፍቅር ደረሰብኝ ከሚለው ሌላኛው ሐሳቡ አላቆት ይሆናል፡፡
የኢንዶስኮፕ ምርመራ ውጤቱ የጨጓራውን በከፍተኛ ሁኔታ መታወክ የሚያሳይ በመሆኑ የተወሰነ የጨጓራ ክፍሉ በኦፕራሲዮን መወገድ ግድ ሆነ፡፡……ከኦፕራሲዮን በኋላ ደመቀ ከገባበት ሰመመን መንቃት አልቻለም፡፡ ደቂቃ፣ ሰዓታት፣…እንደዘበት ነጐዱ፡፡ ነርሶቹ ባለመረጋጋት ወጣ ገባ ይላሉ፡፡
ዳኒና ቢኒ እየተንሰቀሰቀሱ ማንባት ጀምረዋል። አይ ደመቀ እድለቢስ፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ባቋረጠ አመት የእናቱ ህልፈት ቅስሙን ሰብሮታል። የብሌንን ፍቅር ማጣቱ፡፡ የተሰበረ ቅስም፡፡ የተሰበረ ልብ፡፡ ማን ከጐኑ ነበር - ማንም፡፡ ምንም፡፡ እነሆ የህይወት ወንዝ ከሞት ደለል ላይ… እንባዬን ልቆጣጠረው አልቻልኩም፡፡ በደመነፍስ ደመቀ ወደተኛበት ሪከቨሪ ክፍል አመራሁ፡፡ ነርሷ “ክልክል ነው” እያለች ብታንባርቅም ወደ ውስጥ ዘለቅሁ፡፡ የሚቀፍ የዝምታ አዚም ነግሷል፡፡ አየሩ በሞት ጠረን ታጅሏል፡፡ የደመቀ ህይወት አልባ በድን አካል ላይ አይኔ ተጣበቀ፡፡ ነርሷ በመደናገጥ “ለዚህን ያህል ሰዓት አለመንቃቱ አደጋ ነው…ተተኪውን ዶክተር ልጥራው” ብላ እግሯ ከመውጣቱ ደመቀ “በተተኪ የምትሠሩት ትያትር ነው እንዴ?” በማለት ከገባበት ሰመመን ነቃ  - ሰርፕራይዝ!
ውድ አንባቢያን - እንደደመቀ አይነት ሰዎች እንዲህ በቀላሉ ለሞት እጃቸውን አሳልፈው አይሰጡም - እየሳሱ - እየከሱ - እየከሰሙ…ከወንዝ ዳር እንደሚገኝ አለት እየተሸራረፉ ዘመናት ያስቆጥራሉ፡፡  

Read 4356 times