Saturday, 12 July 2014 12:13

የካርል ሔንዝ - እሸቶች

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

ደመና የሚታከኩ ፎቆች…በሥልጣኔ ምህዋር የሚሽከረከሩ ትዕይንቶች…በፍስሀ ሣቅ - የሚፍለቀለቁ - የአዳም ልጆች ከታደሙበት፣ በጥቀርሻ ቀለሙን ወዳጣ …ደሳሳ ጐጆ… እምባ ወዳነቀው ምድር…ረሃብ ወዳሳከከው ሕዝብ መምጣት… ከሰማይ ለወረደው መሲህ በስተቀር ምድራዊ ተልዕኮ ላነገበ ሰው ቀላል አይደለም!
የዘር ሃረግ ክፋይ - የባንዲራ ጥላ ሥር ያገር ልጅ፣ ከአገር ልጅ አፍ እየነጠቀ ኪሱን ሲያሳብጥ፣ የራሱን ወገን ኪስ ፈትሾ - ለባዕድ ሀገር ሰው ጉርሻ ይዞ ውቅያኖስ ማቋረጥ ከእውንነት ይልቅ ወደ ቴአትርነት ይቀርባል፡፡
ይህንን ያደረገ አንድ የጥበብ ሰው ተገኝቷል… አንድ የጥበብ ሰው ተወልዷል። አንድ ደግ - ሰው ኮከብ ሆኖ ከሰማይ ወርዶዋል!!...ሰማይ ማለት ሰማያዊው ሰማይ አይደለም! የደመቀ ኑሮ፣ የጣፈጠ ሕይወት፣ ያማረ ከተማ፣ የተወለደበት ቀዬና ባህል - ሳያሳሳው - የፍቅር ጧፍ ሆኖ በዓለማችን ነድዶዋል!...
ዶክተር ካርል ሃንዝ፤ - የሀገራችን ብቻ ሳይሆን የዓለማችን ትልቅ ሰው ነው፡፡ ከተወለደባት ሀገር ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ - የጠማው ስም - አይደለም። ስም ጠግቧል፣ ዝናው አድማስ ናኝቷል፡፡ የርሱ ሕልም ሌላ ነበር፤ ሕልማቸው ለሞተባቸው ሰዎች - የሕልም ትንሳዔ መስጠት! ገጣሚው አበባው መላኩ በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ ለእድምተኛው ባቀረበው ግጥም እንዲህ ብሎ ነበር:-  
የራስን ምቾት በመተው፣ ከተራበው ጋር ተርቦ፣
ከሚያለቅሰው ጋር ለማዘንም
ዓለምን በማስተዛዘን …ቀሪ ዕድሜን መገበር
የቻለ ምርጥ ተዋናይ ከዚሁ ሁሉ መንጋ ዝነኛ
እኔ ነኝ ያለ ማን ነበር?
ከለተ ኪሮስ አባት ከካርል ሔንዝ በም በቀር
መሀል አውሮፓን ትቶ ሀዊያን ሊረዳ መጥቶ
ኤረር ሸለቆስ ማን ሊቀር? ጋሽዬ ካንተ በስተቀር
እውነትም ይህ ደግ ሰው፤ እውነትም - ይህ ገራም ሰው፣ ሀገራችን በሞት ጥርሶች መካከል በተንጠለጠለ ተስፋ ስትዳክር ነበር፣ አንድ ሻንጣ ይዞ ብቅ ያለው፡፡
ኢትዮጵያዊ ካርል የተወለደው ግን ከደሳሳ ጐጆዎች መካከል በድህነት ከሚያዛጉ መንደሮች አብራክ አልነበረም፡፡ መጋቢት 16 ቀን 1928 ዓ.ም የሙዚቃ አቀናባሪ ከነበሩት ኦስትሪያዊ አባቱና ከታዋቂዋ ድምፃዊት እናቱ ቲያ ሊንሀርድ በዳርምሽታት ከተማ ጀርመን ውስጥ ነበር፡፡ ለአባቱና ለእናቱ ብቸኛ የነበረው ካርል፤ ልቡ ግን እልፍ ወንድሞችና እህቶች ያረገዘ ባለ ሠፊ አድማስ ነበር፡፡
ይህ ብቻ አይደለም፣ ከሁለቱ የጥበብ ሰዎች የችቦ ፍም መሀል የተወረወረው ይህ ሰው፤ የጥበብ አፍቃሪ ብቻ ሳይሆን፣ የጥበብ ሻማም ነበር፡፡ ለነፍሱ የመጣው የጥበብ ጥሪ ማርኮት በትወና ፍቅር ወደቀ። እናም በ1948 ዓ.ም የትወና ሥልጠና ወስዶ ከ45 በማያንሱ ፊልሞች ላይ ተጠበበ፡፡ በተለይ “ሉሲ” የተሰኘውና የቀድሞው የኦስትሪያ ንጉሠ ነገስት የሆነውን ፍራንስ ዮሴፍን በሚዘክረው ሶስት ተከታታይ ፊልም ስሙ ቀና እያለና ዝናው አድማስ እየናኘ ቀጠለ፡፡
እናም ሕይወት በሀገር ሰማይ፣ በራስ ቋንቋና የጥበብ ሕብር ደመቀች፡፡ እንደ ጧፍ የሚነድደው ዕድሜ የሚሰጠው የጥበብ ትሩፋት ብዙዎችን አማለለ፡፡
ከዚያ ቆይቶ ዘመን ሲከነዳ፣ ዓመታት ወደፊት ሲሮጡ፣ እጅ ለእጅ ተያይዞ በስኬት እየሮጠ ሳለ፣ ከሀዲዱ ላይ ድንገት የሚያቆም ድምጽ፣ ነፍስን የሚለበልብ እሳት አስቆመው፡፡ ጆሮውንና ልቡን የዓላማውንም ርቀት ተነጠቀ፡፡ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር በቡዳ በላችው፤ ሲሄድ ሲነሳ ሲቆም ሲተኛ፣ የኢትዮ ፍቅር በልቡ መዝሙር ሆኖ እንደ ፏፏቴ ፈሰሰ፡፡ ውቅያኖስ እንዲያቋርጥ፣ ደሙን እንዳይመዝን፣ ሀረጉን እንዳይቆጥር ቀለሙን እንዳያስተውል ተከላከለችው፡፡
ደጉ ሣምራዊ ካርል ሔንዝ የደም ኪዳኑን፤ የዘር ሀረጉን ጥሶ በፍቅር ጥሪ ያዘኑትን ሊያጽናና፣ መዝሙሩን በሻንጣው ከትቶ ሙሾ ሊሰማ መጣ፡፡ ክፉ ዘመን ነበር፤ ጠባብ መንገድ ነበር ለኢትዮጵያ! የቀደመው መንግስት የእርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ኮሚሽነር በነበሩት አቶ ሽመልስ አዱኛ በመጀመሪያ ከጀርመን በመጣ ቀን፣ ሀገራችን ስለነበረችበት ሁኔታ ሲነገረው የካርል ልብ ተሸንፏል።
ገጣሚና ተዋናይ አበባው መላኩ ለዚህ ሃሳብ የሚገጥሙ ስንኞች አሉት:-
ቄጠማ በተነሰነሰው የብሔራዊ ቴአትር መድረክ
አማልክት ተለምዶን ሽረው እንግዳ ስርዓት ሲያመጡ
ኦስትሪ ጀርመን ተሻግረው የሲሲሊን አክተር መረጡ።
እናም የሰው ሕላዌ፣ በሌጣ ነፍስያ እንዳይቀር፣
    ጐልማሳው ግብሯን ቀየረው
በሺ ልብ እልፍ ሆኖ አዳሪ፣ ክብሩን ለሰው ክብር የሰጠው
አንድ ሰው ስንት ነው ለሚል፣ የትንግርት መልሱን አመጣው
አንዱ ካርል ሔንዝ በም፤ የብዙ ሚሊዮን ነፍሳት
    ታላቅ ቤተሰብ ሲወጣው
ቃል የእምነት ዕዳ ሲሆን ዕዳ ብቻ እንጂ
    የተናገሩት እንዳይፈርስ
የራስ ሕላዌን ዘግቶ ለሌሎች ልኑር ማለትን
    መቼም ወላጅ አያወርስ …
እያለ አበባው ስንኞቹን እንደ ጥንቅሽ ልጦ፣ ፍቅር ለራባቸው የአዳራሹ ልቦች አጉርሷቸዋል፡፡
ካርል  ሔንዝ በም፤ ከሠላሣ ዓመታት በላይ  ኢትዮጵያ ውስጥ ኖሯል፡፡ ካርል ሔንዝ በም እኔን አንድ የማደንቀውን ጀግና ቀምቶኛል፡፡ በትዝታዬ መም ላይ ለዓመታት የሚሮጠውን አንድ የጥበብ ሰው ነጥቆ ሜዳሊያውን አጥልቋል፡፡ ታላቁ ሩሲያዊ ደራሲ ሊዮ ኤን ቶልስቶይ የቸርነት ጀግናዬ ነበር፡፡ ምክንያቱም የሀገሩን የደሀ ልጆች ሰብስቦ ትምህርት ቤት ከፍቶ አስተምሯል። ሀገሪቱ ላይ ችግር በገባ ቀን አዳራሽ ውስጥ ደግሶ ደሀ ገበሬዎችን መግቧል፡፡ ልብሶቹን አሟልቶ ሰጥቷል፡፡
እውነት ነው ቶልስቶይ ድንቅ ነው!...ለድሆች ኖሮ በድሆች መካከል አርፏል፡፡
ካርል ግን ይበልጠዋል፡፡ በገዛ ወገኖቹ መካከል፣ አንድ ቋንቋ ከሚናገሩ፣ በአንድ የባህል መድረክ ከሚዘክሩ ወገኖቹ ውስጥ ቢሆን ባልደነቀኝ! ድሆችን አብልቶ በራሱ ሸጋ ቪላ ውስጥ ተንደላቅቆ ቢሆን ባልገረመኝ! ግን ከድሆች ጋር ውሎ ከድሆች ጋር እያደረ፤ ክረምትና በጋ ሳይመርጥ እንደለፉ፣ ለድሆች ኖሮ ለድሆች አለፈ፡፡ የማደንቀው ጋዜጠኛ ተመስገን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን “የድሆች አባት ሠራው
ዳኛ - ዶክተር ካርል ሔንዝ በም ብሎ”
***
ታዲያ ብሔራዊ ቴአትር ቅዳሜ ምሽትን በክብር የሽኝትና የምሥጋና ፕሮግራም ብሎ አደመቀው፡፡ ቄጠማ ጐዝጉዞ፣ ወታደራዊ ማርሽ ባንድ አሠልፎ ካርል ሔንዝ በምን ዘከረው፡፡
እውነት ለመናገር ካርል ኢትዮጵያ ውስጥ ሀውልት የቆመለት ውድ ሰው ነው፡፡ ግና ከዚያ አደባባይ ላይ ከቆመው ምስል ይልቅ በደማችን ውስጥ የሚፈስስ፤ በልባችን የሚዘምር ታላቅ መታሰቢያ አለው፡፡ ደግሞም ቢያንስበት እንጂ አይበዛበትም፡፡ የ “ሪፖርተር” ጋዜጣው ፀሐፊ ሔኖክ ሥዩም እንዳለው፤ ሀገሬ እርም ካልበላች በቀር ካርል ሁልጊዜ የሚከበር በዓላችን ሊሆን የሚገባ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ካርል በየቤታችን የምናለቅስለት ሰው ሳይሆን መስቀል አደባባይ ወጥተን ደመራ የምንለኩስለት ባለውለታችን ነው፡፡ ምናልባትም ባንዲራችንን አድርገን የምናዝንለት አጋራችን ነው፡፡ እግዚአብሔር የሰጠንን ጀግና ከእጁ በልተን ባናከብረውና ባንዘክረው ነገ የጀግና ጡር  እንዳይይዘን እፈራለሁ። “ከእንግዲህ ወዲያ እኔ ኢትዮጵያዊ እንጂ ፈረንጅ አይደለሁም!” ያለው ካርል፤ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን የመጣበትን አይነት የርህራሄ ድምፀት አለው - ፍቅር!
ብሔራዊ ቴአትር ከ “ሰዎች ለሰዎች” ጋር ተባብሮ ይህንን ታላቅ ዝክር ፈጽሟል!
በቴአትር ቤቱ መድረክ ላይ ሁለት ፎቶግራፎች ተሰቅለው፣ ከምስባኩ ግርጌ የሚነድድ ሻማ የካርል ተምሳሌት ሆኖ ልቤን ነጠቀኝ፡፡ ካርል ሻማ ነበር። እኛ በብርሃኑ ብርሃን ጨለማችንን ሸርክተን ጣልነው፡፡ ካርል ሻማ ነበር፤ እምባውን እያሰሰ ለሌሎች ብርሃንን የሰጠ፡፡
መድረኩ ላይ የሚጤሰው እጣንም ትርጉም ነበረው፤ እየጤሰ የሌሎችን የሕይወት መዓዛ የቀየረ! ካርል ሻማ ነበር፤ ካርል ፈጣን ነበር! ካርል ሽቱ ነበር! ካርል ጥበብ ነበር፡፡
የብሔራዊ ቴአትሩ ዝክር ላይ የመንግስት ባለሥልጣናት ማለትም የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ፣ የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ አዲሱ ለገሰና ሌሎችም መገኘታቸው፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጆቻቸው የሚሰጠው ትርጉም ይኖራል፡፡
እኔና መሠሎቼም በአርቲስት ግሩም ዘነበና በአርቲስት ሙኒት መሪነት እጆቻችን እስኪነድዱ ለክብራቸው አጨብጭበናል፡፡ እኔ ግን ያ ብቻ አልበቃኝም፤ ምነው ስቅስቅስ ባልኩና ባወጣሁት! እርም እንዳይሆንብኝ! ሐረርን ያበላ፣ እኔን የበላ ነው፤ መርሀቤቴን ያበላ እኔን ያበላ ነው! ያበላኝ እጁ እንዳይወቅሰኝ እምባዬ ሆዴን ባልነከሰኝ፡፡
ገጣሚና ተዋናይ አበባው በስንኞቹ የሚለውን ተስፋ እኔም አብሬ እላለሁ፡፡ ሀገሬም ይህን ትበል፡፡
ኡርጂ ከመላ ኬኛ ሚልኪዌይ ባበሻ ቃሉ አንተኮ ነህ፤
ባለሰማንያ መርገፍ ብርሃን፤ ህይወት ህላዌን የምትለግስ
ለሁሉ ነው ያለህ፣
አየህ…አንተ በቀደድከው ጐህ ድንቁርና ተሰዶ
የእውቀት ፀዳል ይበራል
ጤናም እሩቅ ሳይሄዱ ለአርሶአደር፣ አርብቶ አደሩ
ጐረቤታቸው ይሆናል፤
የካርል የዘወትር ቃል ተምኔት ሆኖም አይቀርም
ትንቢት ሆኖ ይሠራል፡፡
በባለቤቱ አልማዝ፣ በልጆቹ ኒኮላይና አሜን - ትንቢቱ ይሠራል፡፡ ካርል በልባችን፣ በአደባባያችንና በሕዝባችን ውስጥ - በፍሬ ይወለዳል!…በትውልዳችን ውስጥ መዝሙሩ ይቀጥላል፤ የካርል ሔንዝ እሸቶች ገና ሁዳዱን ይሞሉታል፡፡ ሀገር ትጠግባለች!

Read 2063 times