Tuesday, 08 July 2014 08:00

ብዙ ሚሊዮን ብር የፈጀው የኤድናሞል መዝናኛ ማዕከል ማስፋፊያ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የዛሬ ስድስት ዓመት ገደማ ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ኤድናሞል የመዝናኛ ማዕከል፤ ከሲኒማ ቤቱ በቀር ሌላው የልጆች መዝናኛ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡
በቅርቡ በተከናወነው የማስፋፊያ ፕሮጀክት ግን ማዕከሉ አዋቂዎችንም የሚያካትት ሆኗል። የተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ታፍ ኮርፖሬት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሰይፈ አምባዬ እንደሚሉት፤ የማዕከሉ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ብዙሚሊዮን ብር ፈጅቷል፡፡ በኤድናሞል የማስፋፊያ ሥራ ዙሪያ
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው
ከአቶ ሰይፈ አምባዬ ጋር አጭር ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡

እስቲ ስለኤድናሞል የማስፋፊያ ስራዎች ይንገሩኝ..
ኤድናሞል የልጆች መጫወቻ ብቻ ነበር፡፡ አሁን ግን ለወጣቶችና ለታዳጊዎች በሚመጥን መልኩ የማስፋፊያ ስራ ተከናውኗል፡፡ የቀድሞ ይዘቱ ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል፡፡ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የወጣበት የማስፋፊያ ሥራ ነው የተከናወነው። ከኢንቨስትመንቱ ከሚገኘው ፋይዳ ይልቅ ለህብረተሰቡ የሚሰጠው አገልግሎት የላቀ ነው፡፡ እዚህ የዋለው ኢንቨስትመንት ሌላ እህት ኩባንያ ላይ ቢውል በአንድ አመትና በሁለት ዓመት ሊመልስ ይችላል፤ ይሄ ግን በአስር ዓመትም አይመልስም። ለማስፋፍያው ይሄን ያህል ገንዘብ አወጣን ብሎ ለመናገር ቢቸግርም ከ20 ሺ እስከ 70 ሺ ዶላር (ከ2ሚ.ብር እስከ 7ሚ.ብር ገደማ ማለት ነው) ድረስ የተገዙ ዘመናዊ የመጫወቻ መሳሪያዎች ገብተዋል፡፡
በከተማው ፈር ቀዳጅ መሆናችንን ስንናገር በእርግጠኝነት ነው፡፡ ዘመናዊዎቹ የልጆች፣ የታዳጊዎችና የወጣቶች መጫወቻ መሳሪያዎች ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓና ከዱባይ ተገዝተው የመጡ ሲሆኑ አብዛኛዎቹም የቴክኖሎጂ ውጤቶች የ2014 ስሪቶች ናቸው፡፡
ይሄ ደግሞ የመዝናኛ ማዕከሉን ደረጃ ከፍ ያደርገዋል፡፡ እንዲህ ያለው መዝናኛ በሌላው ዓለም ቢሆን የአገልግሎት ክፍያው በጣም ውድ ነው። የእኛ ዋጋ ግን የተጠቃሚውን አቅም ያገናዘበና ተመጣጣኝ ነው፡፡
የመዝናኛ ማዕከሉ ለከተማዋ ያለው ፋይዳ ምንድነው?
በመዝናኛ ኢንዱስትሪው ጉልህ ሚና በመጫወት ረገድ ኤድናሞል ግንባር ቀደም ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ኢትዮጵያ በመዝናኛ ኢንዱስትሪው ከሌሎች አገሮች ተርታ እንድትሰለፍ ትልቅ አስተዋፅኦም እያበረከተ ነው፡፡ አዲስ አበባ ለነዋሪዎችዋም ሆነ ለውጭ ሀገር ዜጎችና ጎብኝዎች ምቹ እንድትሆን በሲኒማና በመዝናኛው ዘርፍ ፈር ቀዳጅ ስራዎችን እየሰራን ነው፡፡ በኤድናሞል ደረጃ እንኳን ብታይ በአፍሪካ ገና ያልገቡ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆኑ ቴክኖሎጂዎች ነው የምንጠቀመው፡፡ በርካታ ሚሊዮን ብሮች የወጣባቸው ናቸው፡፡
አዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንደማምጣታችን የዓለማቀፉንም ልምድ ለማወቅ አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ ዱባይና ሲንጋፖር በመሄድ ጥናት ተደርጎ ነው ያንን ልምድ ወደ ኢትዮጵያ ያመጣነው፡፡ እነዚህ ሁሉ የምታያቸው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙት በአገር ውስጥ ባለሙያዎች አይደለም፡፡ የህንድና የቻይና ባለሙያዎች ናቸው የሰሩት፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ስራዎችን የሚሰሩ ባለሙያዎች የሉም፡፡
የሲኒማ ቤቱ ከ3ዲ እስከ 7ዲ ድረስ ያሉት ቴክኖሎጂዎች… በአውሮፓ ስታንዳርድ የተፈበረኩ፣ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የፈጠራ ውጤቶች ናቸው። ለምሳሌ ሳውንድ ሲስተሙን አፍሪካ ህብረት ውስጥ ብቻ ነው የምታገኝው፡፡ የምስል ጥራትን በሚመለከት በቀዳሚ ደረጃ የሚቀመጥ ሲኒማ ቤት ነው ያለን፡፡ ኤድናሞል ከ6 ዓመት በፊት ሲከፈትም ይዞት የመጣው ቴክኖሎጂ ለኢትዮጵያ አይደለም ለአፍሪካም አዲስ ነበር፡፡ 21ኛውን ክፍለ ዘመን ያገናዘበ የረቀቀ ቴክኖሎጂ ነው ያስተዋወቀው፡፡ በአሜሪካ /ሆሊውድ/ ሲኒማ ሲለቀቅ ኤድናሞልም እኩል ነው የሚለቀቀው፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ከሆሊውድ እኩል ሲኒማዎችን የሚለቁ አንድ ሁለት አገራት ቢኖሩ ነው፡፡ ምክንያቱም እነሱ የሚፈልጉትን የሲኒማ ቤት ስታንዳርድ ካላገኙ ሲኒማዎችን አይለቁም፡፡ በርካታ የአፍሪካ አገሮች ፊልሙ ከወረደ በኋላ ነው የሚያገኙት፡፡ ከዚህ አንፃር ኤድናሞል በአፍሪካም በኢትዮጵያም ፈር ቀዳጅ ነው ማለት ይቻላል፡፡
የወደፊት ዕቅዳችሁ ምንድነው?
በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ተመሳሳይ መዝናኛዎችን የማስፋፋት እቅዶች አሉን፡፡ የ5 ዓመት መርሃ ግብር ነድፈን እየሠራን ነው፡፡ ደረጃ በደረጃ የሚከናወኑ ናቸው፡፡  ሲኤምሲ፣ ጎተራ… ቦታ አለን፡፡ ወደፊት ትልልቅ ሞሎችና ሲኒማ ቤቶች እንገነባባቸዋለን የሚል ዕቅድ አለን፡፡ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እንደሚጠይቀን እናውቃለን፡፡ ቢሆንም ግን ዓላማችን የመዝናኛ ኢንዱስትሪውን በአለማቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ማድረግና አማራጮችን ማስፋት ነው፡፡

ኢትዮጵያ በመዝናኛ ኢንዱስትሪው ከሌሎች አገሮች ተርታ እንድትሰለፍ ትልቅ አስተዋፅኦም እያበረከተ ነው፡፡ አዲስ አበባ ለነዋሪዎችዋም ሆነ ለውጭ ሀገር ዜጎችና ጎብኝዎች ምቹ እንድትሆን በሲኒማና በመዝናኛው ዘርፍ ፈር ቀዳጅ ስራዎችን እየሰራን ነው፡፡

Read 3459 times