Saturday, 28 June 2014 11:40

አብርሃም በአሜሪካ ኮንሰርት ያቀርባል

Written by  ኤልሳቤጥ እቁባ
Rate this item
(0 votes)

“በጨለማ ውስጥ ያለች ኮከብ በሩቁ ታበራለች”

ድምፃዊ አብርሀም ገብረመድህን “ማቻ ይስማአኒ ሎ” (ምቾት ይሰማኛል እንደማለት ነው) የሚል አልበም በቅርቡ ለአድማጮች ጆሮ አድርሷል፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ኤልሳቤት እቁባይ ከድምፃዊው ጋር በአልበሙና በአጠቃላይ የሙዚቃ ስራው ዙሪያ አጭር ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡

አሊብራን ከነነፍሱ ነው የምወደው፣ ዘፈኖቹን በሙሉ በጣም እወዳቸዋለሁ፡፡ እሱም በጣም በሳል ሰው ነው፤ ጀማሪዎችን በጣም ያበረታታል፡፡ አንድ ዘፈን ከሱ ጋር የመስራት ፍላጎት እንዳለኝ ነግሬው ደስ ብሎት መስማማቱን ገልፆልኛል፡፡

ምቾት እንዴት እያደረገህ ነው?
በሁሉ ነገር ምቾት ባይገኝም… ምቾት በጣም ጥሩ ነው፡፡ በዘፈኑ ላይ መግለፅ የፈለግሁት  ምንድን ነው? አንድ ሰው አሁን ባለው የፍቅር ግንኙነት በመደሰቱ፣ የተሰማውን የምቾት ስሜት ነው፡፡ ከብቸኝነት ህይወቴ አውጥተሽ ሰው እንድሆን እኔነቴን ተጋራሽኝ፤ ባንቺ ደስተኛ ነኝ፤ ምቾትም ይሰማኛል ነው - መልእክቱ፡፡
አልበምህ ላይ ካሉት ዘፈኖች ሶስቱ በተስፋ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው፡፡ ተስፈኛ ነህ እንዴ?
መፅሀፉም “በተስፋ የምታድር ነፍስ…” ይላል፡፡ ተስፋ ጥሩ ነው፤ ተስፋ ያለው ሰው  ጥንካሬ ይኖረዋል።
አንተስ ተስፈኛ ነኝ ትላለህ?
አዎ ነኝ፡፡ ቁጭ ብሎ አላሚ ሳይሆን እየተንቀሳቀሰ ነገን በተስፋ የሚጠብቅ፡፡
በአዲሱ አልበምህ ድምፅህ በጣም ጐልቶና ጠርቶ ይሰማል…እያንዳንዱ ቃልና ስንኝ በደንብ የሚደመጥ ነው፡፡ ይሄ ላንተ ታውቆሃል?
እያሻሻልኩ ነው ማለት ነው፡፡ ጊዜውም እኮ ቀላል አይደለም፡፡ “ሀበነይ” የሚለው  አልበሜ ከወጣ አስር አመት ሆኖታል፡፡ አሁን ከወጡት ውስጥ አንዳንዶቹ ዜማዎች አስር አመት ሙሉ አብረውኝ የኖሩ በመሆናቸው፣ እየተሻሻሉና እየበሰሉ የመጡ ይመስለኛል፡፡
ባለቤትህ ኤደን ገብረስላሴም ታዋቂ የትግርኛ ዘፋኝ ናት፡፡ ቤታችሁ ውስጥ የጥበብ መትረፍረፍ እንዴት ነው?
(ሳቅ) ይብራራልኝ
በግጥም፣ በዜማ መተጋገዝ ይኖራል ማለቴ ነው?
አንድ አይነት ሙያ ላይ ስትሆኚ ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ እኔም ሆንኩ ኤዱ  ዜማ ለመስራት ስናስብ ወይም ስንሰራ በደንብ ጊዜ ሰጥተን ነው የምናየው። ለኛ በቀልድ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም፡፡ አንደኛ የዝንባሌ፣ ሁለተኛ የእንጀራ ጉዳይ ነው፡፡
ከሷ ዘፈኖች አንተ በብዛት የምታንጎራጉረው የትኛውን ነው?
ገና ያልወጡትን
ከወጡት ውስጥስ?
“በል በል” የሚለውን ነው፡፡ “ስውንዋኖን”ም በጣም አንጎራጉራለሁ፡፡ ብዙ ጓደኞቼ “ስውንዋኖ” ላይ ያለውን የእኔን ክፍል አያስፈልግም ነበር ባይ ናቸው። “አልበም ሳታወጣ ብዙ አመት ስለቆየህ፣ ይህ ዘፈን ደግሞ አሪፍ እንደሚሆን ስላወቅህ ለመጠቀም ፈልገህ ነው” ይሉኛል፡፡ እኔ ደግሞ በጣም እወደዋለሁ፤ የዘፈኑ ቅመም ነው፡፡
ባለቤትህስ የቱን ዘፈንህን ታንጎራጉራለች?
ስልኳን ልስጥሽና ጠይቂያት፡፡
የመጀመሪያው አልበምህ “ሀበነይ” ከወጣ በኋላ ሁለተኛውን ለማውጣት ለምን አስር አመት ቆየህ?
በመሃል ሶስት ነጠላ ዜማዎችን ለቅቄያለሁ፡፡ ከዚያ ውጪ ትኩረቴን ሌሎች ነገሮች ላይ አድርጌ ነበር፡፡
ዜማና ግጥም እንዴት ነው የምትሰራው?
በድንገት ነው የሚመጣልኝ፡፡ ዜማ አልረሳም፤ ደጋግሜ እለውና ውስጤ ይቀራል፡፡ አሁን ደግሞ እድሜ ለቴክኖሎጂ፣ ስልኬ ላይ እይዘውና ተቀጣጥሎ አንድ ዜማ ሲወጣው ይዘፈናል፡፡
በጣም የምትወደው ዜማህ የቱ ነው?
የእውነቴን ነው… ገና ወደፊት የምሰራውን ነው፡፡ ግን በአዲሱ አልበሜ ላይ “ጉዕዞ ህይወት” የሚለውን ስምንተኛውን ዘፈን፣ ዜማውንም ግጥሙንም በጣም እወደዋለሁ፡፡
“የጉዞ ውጣ ውረድ ቢኖርም አይዞን፣ ነገ ለራሱ ሲል ነው የሚነጋው፣ በጨለማ ውስጥ ያለች ኮከብ  በሩቁ ታበራለች፣ ትንሽ ተስፋ በውስጡ ያለው ሰው በጨለማ ውስጥ ሆኖ ነገን ያያል፣ በአይኑ ሳይሆን በተስፋው”  ይላል፡፡
የትግርኛ ዘፈን ከበሮ ካለው ዜማና ግጥም አይፈጅም የሚሉ አስተያየቶች አሉ፡፡ አንተ በዚህ ትስማማለህ?
የዚህን አስተሳሰብ ስፋት ባላውቅም ይሄን ዓይነቱን አስተያየት ከአንቺ ብቻ አይደለም የሰማሁት። ለኔ የትግርኛ ዘፈን ከበሮ ብቻ የሚያደምቀው ሳይሆን ዜማና ግጥም ላይም በደንብ መስራት የሚፈልግ ነው።
መድረክ ላይ ስትወጣ ምን አይነት ስሜት ይሰማሀል?
ውስጡ ነው የምገባው፡፡ የሚጨፍሩ ሰዎች መሀል እንዳለሁ ነው የሚሰማኝ፡፡
ትግራይ ውስጥ የተለያዩ ባህሎች አሉ፡፡ እነሱን የመስራት ሃሳብ የለህም?
አዎ አስባለሁ፡፡ ከተንቤን ፣ ከኢሮብ… በተለያዩ አካባቢዎች ያሉትን የተለያዩ ምቶች የያዘ አንድ ስራ ለመስራት አቅጃለሁ፡፡
ከትግርኛ ውጪ ስትሰራ የነማንን ታዘወትራለህ?
ብዙ ጊዜ ክለብ ሰርቻለሁ፡፡ የኤፍሬም ታምሩን፣ የጌታቸው ካሳን፣ የመሀሙድ አህመድን እንዲሁም የአሊብራን… ከትግርኛ ደግሞ የተክለ ተስፋእዝጊን ዘፈኖች እጫወት ነበር፡፡
የአሊብራን የቱን መጫወት ትወዳለህ?
አሊብራን ከነነፍሱ ነው የምወደው፣ ዘፈኖቹን በሙሉ በጣም እወዳቸዋለሁ፡፡ እሱም በጣም በሳል ሰው ነው፤ ጀማሪዎችን በጣም ያበረታታል፡፡ አንድ ዘፈን ከሱ ጋር የመስራት ፍላጎት እንዳለኝ ነግሬው ደስ ብሎት መስማማቱን ገልፆልኛል፡፡ እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ እንሰራዋለን፤  ጊዜና ሁኔታ እየጠበቅን ነው፡፡ ከተሳካ ለኔ ትልቅ ነገር ነው፡፡
ኦሮሚኛ ትሰማለህ?
አልሰማም
እንዴት ነው የምትጫወተው?
በመጀመሪያ ዘፈኑ ስለምን እንደሆነ እጠይቃለሁ። ትርጉሙን ካገኘሁ በኋላ ውስጡ ገብቶ ለመዝፈን ስለማልቸገር፣ ልክ እንደ ቋንቋው ባለቤት ስሜት ውስጥ ገብቼ እሰራዋለሁ፡፡
ፌስቡክ ላይ “የአብርሀምን ዘፈን እያንጎራጎርኩ ነው፤ ምን አለ ቋንቋውን አውቄ የሚለውን ባውቅ” የሚል አስተያየት ያሰፈረ አንድ ፀሐፊ አለ…
የእጄን አገኘሁ ማለት ነው፡፡
አንተ አልበም ስታወጣ የባለቤትነት ውዝግብ አብሮ ይመጣል፡፡ ለምንድን ነው?
ይህ በእኔ ላይ ብቻ አይመስለኝም፡፡ ቀና ለማለት የሚሞክር ሰው በሙሉ የሚያጋጥመው ነው፡፡ እኔ በበኩሌ መስረቅና መዋሸት አልወድም፡፡
አሁን ክለብ ትሠራለህ?
አልሠራም
የአካውንቲንግ ሙያህ ተረሳ ማለት ነው?
በጣም የሚያሳዝነኝ ነገር ነው፡፡ ከአንድ ሙያ ወደ ሌላ ስትሄጂ ዝንባሌም አብሮ ይለወጣል፡፡ አሁን ስለሱ ምንም አስቤ አላውቅም፡፡ አንዳንዴ ግን መዝገብ ይዞ ሽው ሽው ማለት ያምረኛል፡፡
ከመዝገብና ከማይክ?
ለጊዜው ማይክ ይሻላል
በአካውንቲንግ የት ነበር የሠራኸው?
በሙያው ሰባት አመት ሠርቻለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ገቢዎች ባለስልጣን ልደታ ክ/ከተማ ገቢዎች የታክስ ኦዲተር ሆኜ ሠርቻለሁ፡፡
አባትነት እንዴት ነው?
በጣም ደስ ይላል፡፡ አንደ አመት ከስምንት ወሩ ነው፡፡ ከእናቱ እና ከአባቱ አሪፍ አሪፍ ነገሮችን ወስዷል፡፡
ኮንሰርት የማቅረብ ሃሳብ አለህ?
አዎ አለኝ፡፡ ሰኞ ወደ አሜሪካ ኮንሰርት ለማቅረብ እሄዳለሁ፤ ስመለስ እዚህ ኮንሰርት ይኖረኛል፡፡
አድናቂዎችህን ምን ትላቸዋለህ?
አንድ ነገር ሰርተሽ የሰጠሽው ወገን ሲወድልሽ እጅግ ደስ የሚል ስሜት ይሰጣል፡፡ አድማጮቼን በሙሉ በጣም አመሰግናቸዋለሁ፤ እነሱን ይበልጥ ለማስደሰት እሰራለሁ፣ ኦሪጅናል ካሴት በመግዛት አግዙኝ እላቸዋለሁ፡፡ እወዳቸዋለሁ፡፡

Read 1772 times