Saturday, 28 June 2014 10:38

20 የኦሮሚያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ጋዜጠኞች ከስራ ታገዱ

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(21 votes)

ሃሳባችንን በነፃነት በመግለፃችን ነው ከስራ የታገድነው፡፡ - ጋዜጠኞች  

ከአዲስ አበባና የዙሪያዋ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ የኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ባካሄደው ግምገማ 20 ጋዜጠኞችን “ጠባብ የፖለቲካ አመለካከት አላችሁ” በሚል ገምግሞ ከሥራ ማገዱን ምንጮች ገለፁ፡፡ በማስተር ፕላኑ ዙሪያ በሚያዚያ ወር ፖለቲከኞች፣ ባለስልጣናትና ጋዜጠኞች የተሳተፉበት ውይይት በአዳማ ናዝሬት ተካሂዶ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ በማስተር ፕላኑ ዙሪያ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲዎች እንዲሁም በርካታ ከተሞች ተቃውሞና ረብሻ ከተከሰተ በኋላም ስብሰባዎችና ግምገማዎች በብዛት ቀጥለዋል፡፡
በሚያዚያ ወር በተካሄደው የአዳማ ውይይት ላይ ማስተር ፕላኑን በተመለከተ በርካታ ጋዜጠኞች የተለያዩ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን እንደሰነዘሩ የጠቀሱት ምንጮች፤ በማስተር ፕላኑ፣ በወቅታዊ ጉዳዮችና በሚዲያ ነፃነት ዙሪያ ለሁለት ወር በዘለቀው የጋዜጠኞች ስልጠና ላይም ተመሳሳይ ሀሳብና ጥያቄዎች እንደተሰነዘሩ ገልፀዋል፡፡
ስልጠናው ከተጠናቀቀ በኋላ ባለፈው ረቡዕ ወደ ሥራ ሊገቡ ሲሉ ወደ ግቢው አትገቡም ተብለው መከልከላቸውን የጠቀሱት ጋዜጠኞቹ፤ በስልጠናው ላይ በተነሱ ወቅታዊና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳባችንን በነፃነት በመግለፃችን ነው ከስራ የታገድነው ሲሉ ተቃውመዋል፡፡
ቀደም ሲል በማስተር ፕላኑ ላይ በተካሄደ ውይይት ጋዜጠኞቹ ጉዳዩን ወደ ህብረተሰቡ ለማስረጽ እንደሚቸገሩና ህዝቡም በጄ ብሎ እንደማይቀበላቸው በመግለፅ አወያዮቹን መገዳደራቸውን ተከትሎ “ጠባብ የፖለቲካ አመለካከት አላችሁ” የሚል ትችት እንደተሰነዘረባቸው ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡ ማስተር ፕላኑን በመቃወም የተነሳውን ረብሻ የፀጥታ ሃይሎች ጥይት በመተኮስ ሳይሆን አስለቃሽ ጭስ በመጠቀም መቆጣጠር ነበረባቸው በማለት ተናግረናል ብሏል ከታገዱት ጋዜጠኞች አንዱ፡፡ የኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ጋዜጠኞቹን ያገደበትን ምክንያት እንዲገልፅልን ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡ ከአዲስ አበባና ዙሪያዋ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ ባለፈው ሚያዚያ ወር የተጀመረው ውይይት አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች መቀጠሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 7683 times