Saturday, 28 June 2014 10:35

የእለት ደራሽ እርዳታ ድርጅት፤ ብዙ ሚሊዮን ብሮች በሙስና ተመዝብሯል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

ጠቋሚዎች ህይወታችን ለአደጋ ተጋልጧል አሉ

በመንግስት የልማት ድርጅትነት የተመዘገበው የእለት ደራሽ የእርዳታ ትራንስፖርት ድርጅት ለከፍተኛ ሙስና መጋለጡን የገለፁ ጠቋሚዎች፤ ጉዳዩን ለፀረ-ሙስና ኮሚሽን በተደጋጋሚ ቢያሳውቁም እስካሁን መፍትሄ አለማግኘታቸውን፤ ህጋዊ ከለላ እንዳልተሰጣቸውም ተናግረዋል፡፡
ግዢዎች ያለጨረታና ትክክለኛ ባልሆኑ የጨረታ ሂደቶች ከመፈፀማቸውም በተጨማሪ፣ ጭነት ከማስጫን ጋር በተገናኘ የሂሳብ ማወራረጂያ ደጋፊ ሰነዶች በተለያየ ጊዜ በማጥፋት ብቻ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ተመዝብሯል የሚሉት ጠቋሚዎቹ፤ በህገ ወጥ መንገድ በድርጅቱ ውስጥ በተቀጠረ ግለሰብ አማካይነት ከመለዋወጫ እቃዎች ጋር በተያያዘ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ መመዝበሩንና በወቅቱ ለሚመለከተው አካል ቢያመለክቱም ጉዳዩ ተድበስብሶ መቅረቱን ይናገራሉ፡፡
የድርጅቱ በርካታ ተሽከርካሪዎችም የግለሰቦች የግል መጠቀሚያ ሆነዋል ይላሉ፤ ጠቋሚዎቹ፡፡ ህገወጥ ግዢዎች እንደሚከናወኑ በመግለጽም በርካታ ዝርፊያ ይፈፀማል ባይ ናቸው፡፡ ያለጨረታ በተከናወነ የኢንጀክሽን ፓምፕ ግዢ 107 ሺህ ብር እንዲሁም  ከችቡድ ግዢ ጋር በተያያዘ 119 ሺህ ብር ተመዝብሯል ያሉት ጠቋሚዎቹ፤ ይሄንንም በማስረጃ አስደግፈን ለፀረ - ሙስና ብናቀርብም እርምጃ አልተወሰደም ብለዋል፡፡
ተሽከርካሪዎች በተለያዩ ምክንያቶች ከአገልግሎት ውጪ ሲሆኑ በካኒቫላይዜሽን ስርአት አስፈላጊ የመለዋወጫ እቃዎችን በመፍታት ለሌሎች ተሽከርካሪዎች እንዲውል ይደረጋል የሚሉት ጠቋሚዎቹ፤ በድርጅቱ መመሪያ መሰረት ካኒቫላይዜሽን ለመፈፀም የቦርድ ውሳኔ የሚያስፈልግ ቢሆንም ከመመሪያ ውጪ እየተሰራ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ንብረት የት እንደገባ አይታወቅም፤ ለዚህም ማስረጃዎች አሉን ብለዋል፡፡
የጭነት ማዘዣ ሰነዶችን፣ የነዳጅ መጠየቂያ ፓዶች (ደረሰኞች) ሆን ብሎ በማጥፋትም በብዙ ሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ መመዝበሩን እናውቃለን ይላሉ፡፡ በእጃችን የገቡ የሙስና ተግባሮችን ማስረጃ በመያዝና ከኪሳችን ገንዘብ እያወጣን ፎቶ ኮፒ በማድረግ ለፀረሙስና ኮሚሽን ብናስገባም ጥቆማችን ዋጋ ሳያገኝ እኛንም ለጥቃት ዳርጐናል ሲሉ ምሬታቸውን ገልፀዋል - ጥቆማ አቅራቢዎቹ፡፡
በቅርቡ የድርጅቱ የፋይናንስ ሁኔታ በውጭ ኦዲተሮች ተመርምሮ ድርጅቱ የግዥ መመሪያ አፈፃፀም መመሪያን፣ የግዥ እቅድ በተሟላ መልኩ እንደሌለው፣ የጨረታ ውጤት በጨረታው ለተሳተፉ ተጫራቾች ሆን ተብሎ በጽሑፍ እንደማይገለጽ የሚሉትን ጨምሮ   25 ሚሊየን ብር የሚጠጋ የመንግስት ገንዘብ መጉደሉ ተረጋግጦ ነበር የሚሉት ጠቋሚዎቹ፤  ሰሞኑን ደግሞ የጎደለው ገንዘብ መሟላቱን የስራ ኃላፊዎቹ ለኦዲተሮቹ እየገለፁ ነው ብለዋል፡፡
እነዚህን የመሳሰሉ የሙስና ድርጊቶችን በየጊዜው ለማጋለጥ በመሞከሬ ሁለት ጊዜ በጥይት  የግድያ ሙከራ ተደርጐብኝ ተርፌአለሁ ያሉት የህግ ክፍል ኃላፊው አቶ ያለው አክሊሉ፤ “የላባችን ዋጋ የሆነውን የወር ደመወዝ በየጊዜው ከመቁረጥ ጀምሮ ወከባ፣ ዛቻ፣ መገለልና ለስነ ልቦና ቀውስ እንድንጋለጥ ብሎም ተማረን እንድንለቅ የተቀነባበረ ሴራ እየተፈፀመብን ነው” ብለዋል፡፡
ባለፈው ሰኔ 6 ቀን 2006 ዓ.ም ለመጨረሻ ጊዜ በሚል ለፀረ ሙስና ኮሚሽን ለዳይሬክተሩ ዳይሬክተር ጥቆማቸውን እንዳቀረቡ የጠቆሙት የድርጅቱ የህግ ክፍል ኃላፊ አቶ ያለው አክሊሉ፣ የድርጅቱ የሥነ ምግባር መኮንን አቶ ሰማኸኝ ተፈሪና የድርጅቱ መሰረታዊ ሰራተኛ ማህበር ም/ሊቀመንበር አቶ መንግስቱ ሞላ፤ ዳይሬክተሩም “እኛ እንዲህ አድርጉ፣ አታድርጉ እያልን ማባበልና መለመን ሰልችቶናል፤ ከአሁን በኋላ የመጨረሻ እርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅተናል” በማለት እንደሸኟቸው ይናገራሉ፡፡ ሆኖም እስካሁን ምንም እርምጃ እንዳልተወሰደና ህይወታቸው ይበልጥ ለአደጋ እየተጋለጠ እንደመጣ ገልፀዋል - ጠቋሚዎቹ፡፡  
የእለት ደራሽ እርዳታ ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ጀማል መሃመድን አግኝተን ለማነጋገር ጥረት ብናደርግም በፀሃፊያቸው በኩል ስብሰባ ላይ ናቸው የሚል ምላሽ የተሰጠን ሲሆን በሞባይል እጅ ስልካቸው ላይ በተደጋጋሚ ብንደውልም ስልካቸው ባለመነሳቱ ሊሳካልን አልቻለም፡፡
የፌደራል የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን የስነ-ምግባር የትምህርት እና ስልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አሰፋን ስለጉዳዩ ጠይቀናቸው፤ ጥቆማዎቹን በተመለከተ ምንም መረጃ እንደሌላቸው ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

Read 2809 times