Saturday, 28 June 2014 10:31

“የታሰሩት ኮሚቴዎች ይፈቱ” የሚለው የሙስሊሞች ተቃውሞ ቀጥሏል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

በፍ/ቤት የመከላከያ ምስክሮች እየተደመጡ ነው
የረመዳን ፆም ዛሬ ወይም ነገ ይጀመራል

ከአወሊያ ት/ቤትና ከእስልምና ምክር ቤት ምርጫ ጋር ተያይዞ የተጀመረው ተቃውሞ ያዝ ለቀቅ እያለ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ በየሳምንቱ አርብ ከጁምአ ፀሎት በኋላ የተለያዩ መፈክሮችን በማንገብ የታሰሩ የኮሚቴ አባላት እንዲፈቱ ጥያቄ ይቀርባል፡፡
በአወሊያ ት/ቤት መነሻነት “ድምፃችን ይሰማ” በሚል ከተፈጠረው መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ጋር በተያያዘ በእነ አቡበከር መሃመድ መዝገብ ስር 18 ግለሰቦች በሽብር ወንጀል ተከሰው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ሲሆን የመከላከያ ምስክሮቻቸውን ለፍ/ቤት እያስደመጡ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ቀደም ሲል በተከታታይ ሲካሄድ የነበረው የተቃውሞ ድምፅ የማሰማት ስነ-ስርአት “የእፎይታ ጊዜ” በሚል ለ4 ወራት ከተቋረጠ በኋላ፣ በድጋሚ የተጀመረው መጋቢት 19 ቀን 2006 ዓ.ም ነበር - በታላቁ አንዋር መስጂድ ከአርብ የጁምአ ስግደት በኋላ በተደረገ ተቃውሞ፡፡ በእለቱ ከፀሎትና ስግደት በኋላ ሁሉም በተመሳሳይ ደቂቃ ነጭ ሪቫን በማውለብለብ “አሜን! አሜን! አሜን!” የሚል መፈክር ያሰሙ ሲሆን ፖሊሶች ዳር ቆመው ጉዳዩን ሲከታተሉ ነበር፡፡
በቀጣዩቹ ሳምንታትም በማህበራዊ ድረ-ገፆች በሚተላለፉ መልእክቶች አማካይነት በታላቁ አንዋር መስጂድ፣ በፒያሳው ኑር መስጂድና በኒ መስጂድ ተመሳሳይ ተቃውሞዎች ሲቀርቡ የሰነበተ ሲሆን በክልል ባሉ አንዳንድ መስጂዶችም ተመሳሳይ ተቃውሞዎች ተደርገዋል፡፡
በተመረጡ መስጂዶች በየሳምንቱ አርብ በሚደረገው ሰላማዊ የተቃውሞ ድምፅ ማሰማት ላይ ተቃዋሚዎቹ “እኛም ኮሚቴው ነን፣ ፍትህ ለኮሚቴዎቻችን፤ ፍትህ ተነፍገን ትግላችን አይቆምም” የሚሉ መፈክሮችን በተደጋጋሚ ሲያስተጋቡ ቆይተዋል፡፡
ሁለት እጅን ከፍ አድርጎ በማጣመር የመታሰር ምልክትን ማሳየት፣ ነጭ ሪቫንን ማውለብለብ የመሳሰሉ ትዕይንቶችንም ለተቃውሞ መግለጫነት ተጠቅመውበታል፡፡
ተቃውሞው በሃገር ቤት ብቻ አልተወሰነም፡፡ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችም የተለያዩ ተቃውሞዎችን አድርገዋል፡፡ ሚያዚያ 13 ቀን 2006 ዓ.ም በዋሽንግተን ዲሲ፣ የኮሚቴዎቹን መታሰር በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ የተደረገ ሲሆን በሌሎች የተለያዩ ቀናትም በደቡብ አፍሪካ እንዲሁም በለንደንና በኖርዌይ ዳያስፖራዎች ተመሳሳይ ዓላማ ያለው ሰላማዊ ሰልፎችን ማድረጋቸው ታውቋል፡፡
“ድምፃችን ይሰማ” የተሰኘው ድረ-ገፅ ሰ፣ኑን በለቀቀው መረጃ፤“አዳማ ከተማ በግራፊቲ አሸብርቃ አደረች” ሲል ባወጣው ፅሁፍበከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች ተቃውሞውን የሚያስተጋቡ መልዕክቶች በየግድግዳዎቹ ላይ መለጠፋቸውን አመልክቷል፡፡ በድረ-ገፁ እንደተጠቀሰው፤ “ሙስሊሙን በማሰር ትግሉን ማስቆም አይቻልም”፣ “ኮሚቴው ይፈታ”፣ “ትግላችን ይቀጥላል”፣ “መንግስት ከዲናችን ላይ እጁን ያንሳ”፣ “በደማችን ይከብራል ዲናችን” የሚሉና ሌሎች መልዕክቶች ይገኙበታል፡፡
በአማርኛ፣ በትግርኛና በኦሮምኛ ቋንቋዎች የኮሚቴ አባላቱን የፍርድ ቤት ውሎ ጨምሮ ተያያዥ መረጃዎችን የሚለቀው “ድምፃችን ይሰማ” ድረ-ገፅ፤ ያለፉት ሁለት የረመዳን ወቅቶች በሰላማዊ ትግል ያለፉና በርካታ ሴራዎች የከሸፉበት እንደሆኑ ጠቅሶ፤ ከቀናት በኋላ በሚጀመረው የረመዳን ወርም ትግሉ ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያድግ አስታውቋል፡፡
“በረመዳን በሁሉም ጁምአዎችና በተመረጡ ቀናት ውስጥም ልዩ መሰናዶዎች ይኖራሉ” የሚለው ድረ - ገፁ፤ “ረመዳንና ተሃድሶ” በሚል ተከታታይ ፕሮግራም ህዝብ አሳታፊ ስራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁሟል፡፡
ሰሞኑንም “ለረመዳን እንደርደር” በሚል መሪ ቃል በአወሊያ፣ በኮልፌ እፎይታ እና በኮልፌ አቅሳ መስጂዶች የፅዳት ዘመቻ መከናወኑን በፎቶግራፎች አስደግፎ አውጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ታላቁ የረመዳን ፆም ዛሬ ወይም በነገው እለት እንደሚጀመር የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት አስታውቋል፡፡ መጀመርያ ላይ ከእንቅስቃሴው ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ 28 ግለሰቦች በሽብር መከሰሳቸው የሚታወስ ሲሆን አስሩ መከላከል ሳያስፈልጋቸው ፍርድ ቤት በነፃ እንደለቀቃቸው ይታወሳል፡፡ አስራ ስምንቱ ተከላከሉ በተባሉት መሰረት፤ ካለፉት ሳምንታት ጀምሮ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን እያሰሙ እንደሆነም ይታወቃል፡፡
የኢፌዲሪ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም በየሳምንቱ አርብ ስለሚካሄደው ተቃውሞ መረጃው እንደሌላቸው ገልፀው ዝርዝር መረጃው ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እቅድ አፈፃፀም ጋር እንደሚሰጡ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡        

Read 3253 times