Saturday, 21 June 2014 14:47

የስፔን በጊዜ መባረር ብዙ ግምቶችን አበላሽቷል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)

           ስፔን የሻምፒዮናነት ክብሯን ማስጠበቅ ሳትችል በምድብ ማጣርያ ከተሰናበተች በኋላ በርከታ የውጤት ትንበያዎች እና ግምቶች ተበላሽተዋል፡፡ ለ20ኛው ዓለም ዋንጫ አዲስ ሻምፒዮን ይጠበቃል፡፡ ከስፔን መሰናበት በኋላ 20ኛው ዓለም ዋንጫ ለብራዚል 6ኛ፤ ለጣሊያን አምስተኛ፤ ለጀርመን አራተኛ፤ ለአርጀንቲና እና ለኡራጋይ ሶስተኛ፤ ለእንግሊዝ እና ለፈረንሳይ ሁለተኛ የሻምፒዮናነት ክብር ትበቃለች ወይንስ በታሪክ 9ኛው የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ቡድን ይፈጠራል? የእግር ኳስ ውጤቶች ለግምት እና ለትንበያ አስቸጋሪ ቢሆኑም  ከ20ኛው ዓለም ዋንጫ በተያያዘ ዋንጫውን ማን እንደሚያሸንፍ የተደረጉ ልዩ ጥናቶች፤ የዳታ ስሌቶች እና የንፅፅር ሁኔታዎች ከመቼውም ግዜ በላቀ ሁኔታ ተስተውለዋል፡፡
የምድብ ማጣርያ የመጀመርያ ዙር 16 ጨዋታዎች ከተደረጉ በኋላ ስፖርት ኢንተለጀንስ የተባለ ድረገፅ በተለያዩ ግምቶች ዓለም ዋንጫን ማን እንደሚያሸንፍ የተሰጡ ትንበያዎችን ትክክለኛነት በመመርመር ልዩ ዘገባ አጠናቅሯል፡፡ የትኛው ግምት ትክክል ለመሆን እንደተቃረበ ግን የጥሎ ማለፍ ምእራፉን መጠበቅ ግድ ይላል፡፡
የስፖርት ኢንተለንጀንስ ልዩ ሪፖርት ዳሰሳውን በተለያየ መንገድ በተሰሩ 11 ትንበያዎች ላይ አድርጓል፡፡ ከትንበያዎቹ መካከል የተሳታፊ አገራትን የኢኮኖሚ አሃዞች በመተንተን፤በተለያዩ ወቅታዊ የእግር ኳስ ደረጃዎች መነሻነት በተሰሩ ስሌቶች፤ በታሪካዊ ውጤቶች እና በወቅታዊ የቡድኖች ብቃት፤ በየቡድኖቸ ባሉ ተጨዋቾች የዋጋ ግምት እና ጥንካሬ ላይ መሰረት አድርገው የተሰሩ ይገኙበታል፡፡
በስፖርት ውርርድ ተቋማት እና በአቋማሪ ኩባንያዎች የዋንጫው ግምት በአንደኛ ደረጃ ለብራዚል ቢያጋድልም፤ አርጀንቲና፤ ስፔንና ጀርመን በቅደምተከተል ዋንጫውን እንደሚያሸንፉ ግምት ነበራቸው፡፡ በተለያዩ ግምቶች ግማሽ ፍፃሜ እንደምትደርስ በአንዳንዶቹም ዋንጫውን በማሸነፍ የሻምፒዮናነት ክብሯን እንደምታስጠብቅ የተጠበቀችው ስፔን ከምድብ ማጣርያ መሰናበቷ የብዙዎቹን ስሌቶች ትክክለኛነት አጠያያቂ አድርጎታል፡፡ በተለያዩ ሁኔታዎች በተሰሩ 11 ግምቶች እና ትንበያዎች ብራዚል በ9 የዋንጫው አሸናፊ ትሆናለች ተብሏል፡፡ አርጀንቲና ከእነዚህ ግምቶች አንዴ ብቻ የሻምፒዮናነት ግምት ስታገኝ በስምንት ግምቶች ሁለተኛ መሆን እንደምትችል በአንዱ ግምት ደግሞ በ4ኛ ደረጃ ውድድሩን  እንደምትጨርስ ተገልጿል፡፡ ጀርመን በስምንት ግምቶች 3ኛ ደረጃ ተሰጥቷታል፡፡ በሁለት ግምቶች ዋንጫ እንደምትወስድ የተተነበየላት ስፔን ለግማሽ ፍፃሜ ይደርሳሉ ከተባሉ 4 ቡድኖች ተርታ በተደጋጋሚ መጠቀሳ የብዙዎችን ግምት ፉርሽ አድርጎባቸዋል፡፡
በስፖርት ኢንተለጀንስ ሃተታ መሰረት የዓለም ዋንጫው በሜዳ ላይ ከሚደረገው ፉክክር ውጭ ከሜዳ ውጭ በሚሰራ የተለያየ ስሌት ማን ሊያሸንፍ ይችላል ብሎ በዝርዝር ተንታኔውን አቅርቧል፡፡ በደቡብ አሜሪካ በተዘጋጀ ዓለም ዋንጫ ለግማሽ ፍፃሜ የመድረስ እድል ያላቸው አራት ቡድኖች ብራዚል፤ ጀርመን፤ ኡራጋይ እና አርጀንቲና ሲሆኑ ለዋንጫ ብራዚል እና አርጀንቲነና ተገናኝተው አርጀንቲና ታሸንፋለች፡፡ በፊፋ ደረጃ ዓለም ዋንጫውን ማን ያሸንፍ ከተባለ ደግሞ ለግማሽ ፍፃሜ ብራዚል፤ ጀርመን፤ ስፔንና አርጀንቲና፤ ስፔን ከጀርመን በሚያደርጉት የአውሮፓ ደርቢ ስፔን ታሸንፋለች፡፡ በተጨዋቾች የደሞዝ ክፍያ መጠን ጀርመን በፍፃሜ ጨዋታ ስፔንን ታሸንፋለች፡፡ በአጠቃላይ የቡድን ስብስብ የዋጋ ግምት ብራዚል፤ ፈረንሳይ፤ ስፔንና አርጀንቲና ለግማሽ ፍፃሜ ይደርሳሉ፡፡ ዋንጫውን አሁንም ብራዚል አርጀንቲናን በማሸነፍ ትወስዳለች፡፡

Read 2595 times