Saturday, 14 June 2014 12:38

ከተጨዋቾች 75 በመቶው በአውሮፓ ሊጎች ይጫወታሉ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

        ከ32ቱ ብሔራዊ ቡድኖች በተጫዋቾች ስብስቧ አጠቃላይ የዋጋ ግምት አንደኛ ደረጃ የተሰጣት የዓለም ዋንጫ አዘጋጇ ብራዚል ስትሆን በ718,299,900 ዶላር በመተመኗ ነው፡፡ስፔን በ673,587,107 ዶላር፣ አርጀንቲና በ654,482,640 ዶላር፣ ጀርመን በ621,815994 ዶላር ዋጋ  የተጨዋቾች ስብስባቸው ተተምኖ እስከ 5 ያለውን ደረጃ አከታትለው ይወስዳሉ፡፡ በተጨዋቾች ስብስቧ ዝቅተኛውን የዋጋ ተመን ያስመዘገበችው ሆንዱራስ ስትሆን በ45,053,928 ዶላር  ነው፡፡  
በዓለም ዋንጫው በሚሳተፉት 32 ብሔራዊ ቡድኖች የተመዘገቡት 736 ተጨዋቾች በዝውውር ገበያው ወቅታዊ የዋጋ ተመን እስከ 9.6 ቢሊዮን ዶላር ያወጣሉ፡፡ እነዚህ 736 ተጨዋቾች በ53 የተለያዩ አገራት በሚካሄዱ ሊጎች ላይ በሚወዳደሩ ክለቦች የተመዘገቡ ሲሆን፤ 476 ተጨዋቾች (65%) ከአገራቸው ውጭ ባሉ የሊግ ውድድሮች የሚጫወቱ እንደሆነ ታውቋል፡፡  በዓለም ዋንጫው በአገሯ ሊግ የሚጫወቱ ተጨዋቾችን ሙሉ ለሙሉ በማሰባሰብ የምትሳተፍ አገር ሩስያ ብቻ ናት፡፡ ለዓለም ዋንጫው በመላው ዓለም የሚገኙ 290 ክለቦች ተጨዋቾችን አቅርበዋል፡፡ የአውሮፓ የእግር ኳስ ክለቦችና ውድድሮቻቸው  ለዓለም ዋንጫ ድምቀት እና  ከፍተኛ ትርፋማነት አስተዋፅኦ ማድረጋቸው የተረጋገጠው ከዓለም ዋንጫው ተጨዋቾች 75 በመቶ ድርሻ በመያዛቸው ነው። በዓለም ዋንጫው የሚሳተፉ 190 ተጨዋቾች በአውሮፓ አህጉር በሚካሄዱ ታላላቅ የሊግ ውድድሮች የሚጫወቱ ሲሆኑ አውሮፓን ከወከሉ 13 ቡድኖች 12ቱ  በአውሮፓ ትልልቅ ሊጎች በሚሳተፉ ክለቦች  ተጨዋቾች ብቻ ተዋቅረዋል፡፡  የእንግሊዙ ፕሪሚዬር ሊግ 105 ተጨዋቾችን በማቅረብ አንደኛ ሲሆን፤ የጣሊያን ሲሪኤ በ81፣ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ 71፣ የስፔን ላሊጋ 62፣ የፈረንሳይ ሊግ 47 ተጨዋቾችን በማሰለፍ ተከታታይ ደረጃ አላቸው። ለዓለም ዋንጫ ያላለፈች ቢሆንም ቱርክ ደግሞ በአገሯ የሊግ ውድድር በሚሳተፉ ክለቦች ያሉ 26 ተጨዋቾችን በማስመረጥ ልዩ ተጠቃሽ ትሆናለች፡፡
በክለብ ደረጃ በ32 ብሔራዊ ቡድኖች 15 ተጨዋቾችን በማስመልመል የሚመራው የጀርመኑ ክለብ ባየር ሙኒክ ነው፡፡ የእንግሊዙ ማን. ዩናይትድ በ14፤ የስፔኑ ባርሴሎና በ13፤ ቼልሲ፣ ጁቬንትስ፣ ናፖሊና  ሪያል ማድሪድ እያንዳንዳቸው 12 እንዲሁም አርሰናል፣ ሊቨርፑል፣ ማን. ሲቲና ፒኤስጂ በ10 ተጨዋቾች የዓለም ዋንጫ ውክልና አግኝተው ተከታታይ ደረጃ አላቸው፡፡  

Read 1184 times