Saturday, 10 May 2014 12:04

የሃበሻ ሊግ መስራች እና ኮሜንታተር- ብርቱካን አካሉ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(4 votes)

          የ24 ዓመቷ ብርቱካን አካሉ ትውልዷ ጎጃም ውስጥ በምትገኘው ደምበጫ የተባለች የገጠር ከተማ ነው፡፡ ከ4 ዓመት በፊት በዛሚ ኤፍ ኤም ሬድዮ 90.7 ላይ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን በሬድዮ ቀጥታ ስርጭት የሚያስተላለፍ ሃበሻ ሊግ የተባለ ፕሮግራም መስራች ነች፡፡ ከዚያ በፊት በስፖርት ጋዜጠኝነት በተለያዩ ጋዜጦች ላይ የአገር ውስጥ ዘገባዎችን በማቅረብ ሰርታለች፡፡ ብርቱካን በሬድዮ የቀጥታ ስርጭት የአገር ውስጥ የሊግ ውድድሮች እና የብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎችን በማስተላለፍ የመጀመርያዋ ኢትዮጵያዊ የሴት ኮሜንታተር ናት ማለት ይችላል። ከፍተኛ እውቅና ያገኘችበት እና ከልቧ የምትወደው ሙያ የስፖርት ጋዜጠኝነት እና ኮሜንታተርነት በመሆኑ በተማረችው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ብዙም አልሰራችበትም፡፡

ብርቱካን ከሌሎች እውቅ የስፖርት ጋዜጠኞች ጋር በመስራት የኢትዮጵያን የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች በሬድዮ ስርጭት ሽፋን በመስጠት እና በማሟሟቅም ፈርቀዳጅ ናት፡፡ በተለይ በየክልሉ የሚደረጉ የሊግ ጨዋታዎችን በሬድዮ ስርጭት በቀጥታ በማስተላለፍ ለስፖርት ቤተሰቡ ባለውለተኛ ነች። በክልል ከተሞች አዲግራት ፤ አርባምንጭ፤ ሃረርና ድሬዳዋ አድካሚ ጉዞዎችን በማድረግ ያስተላለፈቻቸው የሊግ ጨዋታዎች የበርካቶችን የመረጃ ፍላጎት ናቸው፡፡ በአዲስ አአባ አቅራቢያ ባሉት የአዳማ፤ አሰላ እና ሃዋሳ ከተሞችም በተደጋጋሚ በመጓዝ የሰራቻቸው ስርጭቶች በርካታ ደጋፊዎች ላሏቸው ክለቦች ከፍተኛ ጠቀሜታ ነበራቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከ31 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉን ተከትሎ የቀድሞው የእግር ኳስ ፌደሬሽን ለብርቱካን አካሉ አስተዋፅኦ እውቅና ሰጥቶ የምስክር ወረቀት ሸልሟታል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ክለቦችም በየትኛውም ስፍራ እና በማናቸውም ጊዜ የሚያደርጓቸውን ጨዋታዎች እንድታስተላልፍ የድጋፍ ደብዳቤ በመስጠት እና በማመስገን አበረታተዋታል፡፡ ኢትዮጵያ ከተሳተፈችበት 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኋላ ግን ብርቱካን አካሉ በኮሜንታተርነቷ እንደልቧ መስራት አልቻለችም፡፡ እንደውም ካለፈው 1 ዓመት ወዲህ ስራ አቁማለች ለማለት ይቻላል፡፡

ከእግር ኳስ ርቆ ሌላ ስራ መስራት ይከብደኛል የምትለው ብርቱካን ስታድዬም ገብታ ጨዋታዎችን መከታተሏን ባታቆምም የኮሜንታተርነት ሙያዋን በተሻለ ተጠቃሚነት እና አቀራረብ እያሳደገች ለመቀጠል አልቻለችም፡፡ ከ2005 አጋማሽ ወዲህ ይህን ስራዋን ታከናውንበት በነበረው የዛሚ ኤፍኤም 90.7 ሬድዮ ጋር በስፖንሸርሺፕ ገቢ በምትከፋለፈለው ድርሻ በተፈጠረ አለመግባባት የሃበሻ ሊግ ፕሮግራሟ ተቋርጦባታል፡፡ ሃበሻ ሊግ ፕሮግራም ከ2 የውድድር ዘመናት አድካሚ ሂደት በኋላ በመላው ኢትዮጵያ እውቅና አግኝቶ፤ ከስፖንሰሮች ጋር ተደጋግፎ መስራትን ካዳበረ እና መሰረት እየያዘ በመጣበት ወቅት ያለበቂ ምክንያት መቋረጡ ሞራሌን ነክቶታል የምትለው ብርቱካን አካሉ፤ የእግር ኳስ ስፖርትን የቤተሰብ ያህል ስለማፈቅረው ስራዬን ለመስራት ባልችልም ግን ተስፋ አልቆረጥኩም ትላለች፡፡ በቀና አስተሳሰቧ የምትከበር የስፖርት ባለሙያ የሆነችው ብርቱካን አካሉ፤ ኮሜንታተርነቷ ለጊዜው ብትራራቅም ከቅርብ ወራት ጀምሮ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ኦፊሴላዊ ድረገፅ (www.cafonline.com) ላይ የኢትዮጵያን እግር ኳስ የሚመለከቱ ዘገባዎች እያቀረበች ነው፡፡ ብርቱካን አካሉ ከስፖርት አድማስ ባደረገችው ቃለምምልስ የስፖርት ጋዜጠኝነቷን እንዴት እንደጀመረች እና የት እንደሰራች ፤ሃበሻ ሊግ ስለተባለው ፕሮግራሟ አመሰራረት በስፖርቱ ላይ ስለነበረው አስተዋፅኦ እና አላግባብ ስለተቋረጠበት ሁኔታ፤ ስለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ፤ የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ገድሎች እና በኮሜንታተርነት ስላሳለፈቻቸው ገጠመኞቿ እንደሚከተለው ተወያይታለች፡፡ ባለፈው ሳምንት ካይሮ ነበርሽ፡፡ ለ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ድልድል ለማውጣት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ) ያዘጋጀውን ስነስርዓት በቀጥታ ለማስተላለፍ ነው ወይንስ ለምንድነው? ወደ ካይሮ የሄድኩት በካፍ የሚዲያ ቻናል አማካኝነት ነው፡፡ በካፍ ድረገፅ ላይ መስራት የጀመርኩት በቅርቡ ነው።

ባለፈው ሳምንት 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ድልድል ለማውጣት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ካፍ ያዘጋጀውን ስነስርዓት የተካፈልኩትም በኢትዮጵያ ላይ ያተኮሩ ዘገባዎችን እንድሰራ ነው፡፡ በካፍኦንላይን ድረገፅ መስራት ከጀመርኩ ካለፉት ሶስት ወራት ወዲህ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዙርያ ሶስት ሰፋፊ ዘገባዎችን አቅርቢያለሁ፡፡ ባለፈው ሳምንት ደግሞ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ የምድብ ማጣርያው ድልድል በወጣበት ስነስርዓት ላይ ስለነበሩ ኢትዮጵያ ስለገጠሟት ተጋጣሚዎች የተሰማቸውን አጭር አስተያየት በመጠየቅ አጭር ሪፖርት አቅርቢያለሁ፡፡ የምድብ ማጣርያ ድልድል የማውጣት ስነስርዓቱ ካይሮ በሚገኘው የኮንፌደሬሽኑ ዋና ፅህፈት ቤት አዳራሽ ሲካሄድ ብዙም የተለየ ነገር አልነበረውም፡፡ በስነስርዓቱ ላይ ከምድብ ድልድሉ ባሻገር የቀድሞው የእግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ሳህሉ ገብረወልድ በኢትዮጵያ የካፍ አካዳሚ ዋና ዲያሬክተር ሆነው ተሹመዋል፡፡ በስነስርዓቱ ኢትዮጵያን ወክለን የተገኘነው እኔ የቀድሞው የእግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ሳህሉ እና የአሁኑ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ ናቸው።

ከዚህ ባሻገር አንድ ምድብ ድልድል ውስጥ የገባነው አገራት የማላዊ እና የአልጄርያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች ነበሩ። እኔ የተቀመጥኩበት አካባቢ ከነበሩት ጋዜጠኞች አንዷ የማሊ ዜግነት ያላት ነበረች፡፡ ጋዜጠኛዋ ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ያደረጋቸውን ጨዋታዎች መከታተሏን ገልፃ አጨዋወታቸው እንደሚያስደስታት፤ በተለይ 18 ቁጥሩን (ሽመልስ በቀለን ነው) ምርጥ ተጨዋች ነው ብላኛለች፡፡ በስነስርዓቱ ላይ የተለያዩ አገራት አሰልጣኞችን አግኝቻለሁ፡፡ በተለይ የኢትዮጵያን ድልድል እጣ ካወጡት የቀድሞው የግብፅ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሃሰን ሺሃታ ጋር ተዋውቄ መጠነኛ ውይይት አድረገናል፡፡ የስፖርት ጋዜጠኛነቱን መቼ እና እንዴት ጀመርሽው? ወደ የስፖርት ጋዜጠኝነቱ በቀጥታ የገባሁት ከ7 ዓመታት በፊት ነው፡፡ ለእግር ኳስ ስፖርት ልዩ ፍቅር ያደረብኝ ገና ከልጅነቴ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በተለይ አስተዋፅኦ የነበረው ኳስ በጣም ይወድ የነበረው አያቴ ነው፡፡ በ1998 እ.ኤ.አ ፈረንሳይ ያዘጋጀችውን 16ኛው ዓለም ዋንጫን ከአያቴ ጋር ሆነን ስንከታተል የነበረው ሁሉ ትዝ ይለኛል፡፡ ያኔ በቤታችን ቴሌቭዥን ባይኖረንም ሌሊት ሁሉ እየወጣን ኳስ በሚታይባቸው ቤቶች እየተገኘን የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን ተመልክተናል፡፡

በስፖርት ጋዜጦች አምደኛ ሆኜ መስራት ከመጀመሬ በፊትም በተለያዩ የሬዲዮ የስፖርት ፕሮግራሞች በስልክ አስተያየቶችን በመስጠት ንቁ ተሳትፎ አደርግ ነበር በተለይ በሬዲዮ ፋና የስፖርት ዝግጅቶች ላይ ጠፍቼ አላውቅም፡፡ በጋዜጠኛነት መስራት የጀመርኩት በ1999 ዓ.ም በዩኒቲ ዩኒቨርስቲ በሚታተመው ኤቢቢአይ ዊክሊ በተባለ ጋዜጣ ከስፖርት አምድ አዘጋጆች አንዷ ሆኜ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ በ2001 ዓ.ም ላይ በሰንደቅ ጋዜጣ የሃገር ቤት የስፖርት ዘገባዎችን በተለይ በእግር ኳስ ላይ በማተኮር ሰርቻለሁ፡፡ የሃበሻ ሊግን እንዴት ጀመርሽው? የስፖርት ጋዜጠኛ ሆኜ እየሰራሁ ባንድ ወቅት የተለየ ስራ እንዴት መስራት እችላለሁ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ይሄኔ የአገር ውስጥ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን በቀጥታ ሬድዮ ስርጭት የማስተላለፍ ሃሳብ መጣልኝ፡፡ ማን አብሮኝ ቢሰራ ጥሩ ነው በሚል ሌሎች የስፖርት ጋዜጠኞችም ማማከር እና መፈለግ ጀመርኩ፡፡ አስቀድሜ ያነጋገርኳቸው መሸሻ ወልዴ እና ማርቆስ ኤልያስ ናቸው፡፡ በአገር ውስጥ የእግር ኳስ ውድድሮች ላይ ባተኮሩ ዘገባዎቻቸው በከፍተኛ ደረጃ የሚታወቁ የስፖርት ጋዜጠኞች ናቸው፡፡ ታዋቂው የስፖርት ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊም ሃሳቡን በመደገፍ አብሮን ነበር። መጀመርያ እነዚህ ጋዜጠኞች የሊግ ጨዋታዎችን በቀጥታ የሬድዮ ስርጭት የማስተላለፉ ሃሳብ ስኬታማ አይሆንም ነበር ያሉት፡፡ የአገር ውስጥ የሊግ ጨዋታን 90 ደቂቃ በሬድዮ ሲተላለፍ ማን ሊሰማው ይችላል የሚል ጥያቄ ተፈጥሮባቸው ነው፡፡ እንሞክረው ግዴለም አልኳቸው፡፡

የክለብ ጨዋታዎችን በሬድዮ በቀጥታ ለማስተላለፍ ሃሳብ ሲጠነሰስ የእኔ የጓደኞቼ እቅድ የመጀመርያውና ማንም ሞክሮት የማያውቀው ስራ ነበር። በመጨረሻም ፕሮግራሙን የሃበሻ ሊግ በሚል ሰይመነው የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎችንና ሌሎች ውድድሮችን በቀጥታ የሬድዮ ስርጭት ለማስተላለፍ እቅድ በመንደፍ በዛሚ ኤፍኤም 90.7 ለመስራት አመለከትን፡፡ ለዛሚ በቀጥታ ያመለከትነው ጣቢያው ለሃገር ውስጥ ስፖርት ቀዳሚ ትኩረት እንዳለው በመገንዘባችን ነበር፡፡ የጣቢያው ሃላፊዎች ያቀረብነው እቅድ ተቀብለው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ስራ እንድንጀምር ፈቀዱልን፡፡ ፕሮግራሙ መሰራት ከተጀመረ በኋላ ቢያንስ ለ3 ወራት ያህል ምንም ገቢ አልነበረውም፡፡ ከጊዜ በኋላ ግን የዛሚ ሃላፊዎች በስፖንሰርሺፕ ገቢ ፕሮግራሙን ማጠናከር እንዳለብን ተነገረን፡፡ እንደማስታውሰው በዛሚ ኤፍኤም 90.7 ላይ በሀበሻ ሊግ ለመጀመርያ ጊዜ በቀጥታ የሬድዮ ስርጭት ያስተላለፍነው ጨዋታ በ2003 ዓም ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት በሱፕር ካፕ በአበበ ቢቂላ ስታድዬም የተገናኙበት የዋንጫ ጨዋታ ነበር፡፡ አሰራራችን በመደበኛዋ የኖኪያ ሞባይል ቀፎ የግጥሚያውን አጠቃላይ ሂደት በመከታተል እና የተለያዩ መረጃዎችና አስተያየቶችን ጎን ለጎን በማቅረብ ማስተላለፍ ነበር፡፡ በወቅቱ ጨዋታውን ለማስተላለፍ 5 ጋዜጠኞች ተሳትፈናል፡፡ እኔ፤ ኢብራሂም ሻፊ፤ ማርቆስ ኤልያስ፤ መሸሻ ወልዴ እና ዳግም ዝናቡ ነበርን፡፡ በሱፕር ካፑ የዋንጫ ጨዋታ ስኬታማ የቀጥታ ስርጭት ካደረግን በኋላ የ2003 የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ሲጀመር በሬድዮ ለማስተላለፍ አስቀድመን ከእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ከዚያም ከክለቦች ጋር በመነጋገር በደብዳቤ ፈቃድ አግኝተን መስራት ቀጠልን፡፡ በዚያው ዓመት የተካሄደውን የሲቲ ካፕ ውድድርም ሙሉ ሽፋን በመስጠት ሰርተናል፡፡

በሃበሻ ሊግ ፕሮግራም በመጀመርያ አካባቢ ብዙም ትኩረት አላገኘንም፡፡ ምናልባት ቀጣይነት ላይኖራቸው ይችላል በሚል ሳይሆን አይቀርም፡፡ ከስፖርት ቤተሰቡ የምናገኘው ምንም አይነት የሚያበረታታ አስተያየት እና ድጋፍ አልነበረም። አንዳንድ አድማጮች በአዲስ አበባ የሚደረጉ የእግር ኳስ ግጥሚያዎችን የምንሰራ ስለመሰላቸው ለፕሮግራማችን ከጅምሩ ትኩረት አልሰጡም፡፡ ነገር ግን የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎችን ማስተላለፍ ስንጀምር አዲግራት ላይ ትራንስ ኢትዮጵያ ከኢትዮጵያ ቡና ያደረጉትን ጨዋታ በማቅረባችን የስፖርት ቤተሰቡን ቀልብ መግዛት ችለናል፡፡ ከዚህ በኋላ ከክለቦችም ለፕሮግራሙ እውቅና አገኘንበት፡፡ አድማጮችም ያበረታቱን እና ድጋፋቸውን በመግለፅ እንድነሳሳ አደረጉን፡፡ በተለይ አንዳንድ አድማጮች በክልል የሚደረጉ ጨዋታዎችን ለመከታተል ፍላጎት በማሳየት እንደውም ይሄ ጨዋታ ይተላለፋል ወይ? በሚል ጥያቄ የፕሮግራሙን አስፈላጊነት ይጠቁሙን ነበር፡፡ በዚህ መሰረት በ2003 ዓ.ም የሃበሻ ሊግ በጥሩ ሁኔታ ተሰርቶ የውድድር ዘመኑ አለቀ፡፡ በ2004 ዓ.ም ፕሮግራሙ ለፕሪሚዬር ሊግ እና ሌሎች የእግር ኳስ ውድድሮች ሰፊ ሽፋን በመስጠት የብዙ አድማጮች እና ተካታዮችን ትኩረት አግኝቶ ሲሰራ አሳለፈ፡፡

በእነዚህ ጊዜያት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ብቻ ሳይሆን ለብሄራዊ ቡድን ጨዋታም ሽፋን መስጠት ጀመርናል፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ በሃበሻ ሊግ ያስተላፋችሁት የብሄራዊ ቡድን ጨዋታ የትኛው ነበር? ሌሎቹስ? በሃበሻ ሊግ ለመጀመርያ ጊዜ ያስተላለፍነው የብሄራዊ ቡድን ጨዋታ ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ዋልያዎቹ በኮቶኑ ከተማ ከቤኒን ጋር ያደረጉት ነው፡፡ ይህ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በመጀመርያው ግጥሚያ እዚህ አዲስ አበባ ላይ 0ለ0 ተለያይቶ ከሜዳ ውጭ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ለመሻገር የሚያደርገው ወሳኝ የመልስ ጨዋታ ነበር፡፡ በቤኒና ከተማ ኮቶኑ ተገኝቶ ቢያንስ የግጥሚያውን ሂደት በቀጥታ ሬድዮ ስርጭት ለኢትዮጵያውያን ስፖርት አፍቃሪዎች ማስተላለፍ አስፈላጊ ነበር፡፡ ሃሳቡን በመደገፍ የስፖንሰርሺፕ ድጋፍ የሰጠኝ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ነበር፡፡ በወቅቱ እንደማስታውሰው ሉሲዎቹም ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ታንዛኒያ ላይ ወሳኝ የመጨረሻ ጨዋታ ነበራቸው፡፡ ይሁንና የሉሲዎቹን በርካታ ጋዜጠኞች በተለያዩ ሬድዮ ጣቢያዎች የቀጥታ ስርጭት ለመስራት አስበው ስለነበር እኔ የዋልያዎቹን ጨዋታ ሽፋን ለመስጠት ጥረት አደረግኩ፡፡

የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ያቀረብኩላቸውን ሃሳብ ተቀብለው ሙሉ ድጋፍ በማድረግ ቀና ትብብር ሰጡኝ፡፡ እንግዲህ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከሜዳው ውጭ ከቤኒን ጋር ተገናኝቶ 1ለ1 በመያየት ለመጨረሻው ማጣርያ ምእራፍ ገባ፡፡ በመቀጠል ያስተላለፍነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጨዋታ ወደ 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ኦብዱርማን ላይ ከሱዳን ብሄራዊ ቡድን ጋር የነበረው የደርሶ መልስ ትንቅንቅ የመጀመርያ ጨዋታ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ ብሄራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ አልፎ ደቡብ አፍሪካ ባስተናገደችው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ሲሳተፍ በምድብ 3 ከዛምቢያ፤ ከቡርኪናፋሶ እና ከናይጄርያ በሁለት ከተሞች ያደረጋቸውን 3 ጨዋታዎች እዚያው ደቡብ አፍሪካ በመገኘት በቀጥታ የሬድዮ ስርጭት አስተላልፈናል፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ ብሄራዊ ቡድኑ በ20ኛው የዓለም ዋንጫ ማጣርያ በገለልተኛ ሜዳ በኮንጎ ብራዛቪል ያደረገውን ጨዋታ ያስተላለፍን ሲሆን የዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣርያ የመጨረሻው ጨዋታ በናይጄርያዋ ከተማ ካላባር ሲደረግም ሽፋን ሰጥተናል፡፡ በሀባሻ ሊግ በቀጥታ ሬድዮ ስርጭት የተሰሩት የእግር ኳስ ጨዋታዎች በስፖርቱ ላይ ምን አስተዋፅኦ ነበራቸው? በሬድዮ ቀጥታ ስርጭት ያስተላለፍናቸው ጨዋታዎች ለአገር ውስጥ የሊግ ውድድሮች በቂ ትኩረት እና ክትትል እንዲኖር አድርገዋል፡፡

በተለይ በየክልሉ የተካሄዱ ጨዋታዎችን ስናስተላልፍ በየከተማው ተዘዋውረው ስታድዬም በመግባት መከታተል ለሚቸገሩ የስፖርት ቤተሰቦች የሚደግፏቸውን ክለቦች ወሳኝ ግጥሚያዎች ሂደት ባሉበት እንዲከታተሉ እና በትኩሱ ውጤቶችን እንዲያገኙ አስችለናል፡፡ የፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች እና የብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾችን ግለታሪኮች እና ልዩ ልዩ አስተያየቶች የቀጥታ ስርጭታችን አካል በመሆናቸውም በስፖርት ቤተሰቡ ከፍተኛ እውቅና የሚያገኙበትንም ትኩረት መፍጠራችን በጉልህ የሚታይ ስኬት ነበር፡፡ አንዳንዴ ተጨዋቾች በስልካችን እየደወሉ ይህን ጨዋታ ታስተላልፋላችሁ ብለው ይጠይቁናል፤ አዎ ካልናቸው ለቤተሰቦቻቸው እየነገሩ እንዲከታተሉ ያደርጋሉ፡፡ በዚህም ለእነሱ ምን ያህል ጥቅም እየሰጠን እንደነበር ተገንዝበናል፡፡ ከአድማጮች፤ ከክለብ ሃላፊዎች፤ ከትልልቅ የስፖርት ቤተሰቦች በፕሮግራማችን እርካታ ተሰምቷቸው ይሰጡን የነበረው የማበረታቻ ድጋፍ እና ምርቃት ከምናገኘው ገቢ ይልቅ የበለጠ ሃላፊነት ተሰምቶን እንድንሰራ ምክንያት ነበር፡፡

የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎችን በተለይ በክልል የሚደረጉትን ስናስተላልፍ አንዳንዴ በትራክ ላይ ሆነን ነው የምንሰራው፤ ይህም በየግጥሚያዎቹ ያለውን ፉክክር የሚያሟሙቅ ነበር፡፡ ተጨዋቾች የሚሰለፉባቸው ጨዋታዎች በቀጥታ የሬድዮ ስርጭት መተላለፉን ሲያውቁ እና ደጋፊዎቿቸው እየተከታተሏቸው መሆኑን ሲረዱ ብቃታቸውን በይበልጥ እንዲያሳዩ እናነሳሳቸው ነበር ማለትም ይቻላል፡፡ ስናስተላልፍ በቆየናቸው እያንዳንዱ የሊግ ጨዋታዎች አጠቃላይ ሂደቱን በቀጥታ ከማስተላለፍ ባሻገር የተጋጣሚ ክለቦችን ፕሮፋይል እና በየሳምንቱ የምንመርጣቸውን ሁለት ሁለት የክለቡ ተጨዋቾች ግለታሪክ እና አስተያየት ማቅረባችንም ለውድድሩ የተለየ ድምቀት የፈጠረ ነበር። በተለይ አዳዲስ እና ተስፋ ላላቸው ተጨዋቾች ቅድሚያ በመስጠት ስንከተል የነበረው አሰራር ተወዳጅ እንደነበር በብዙ የምስጋና አስተያየቶች አረጋግጠናል፡፡ በሌላ በኩል ውድድሮችን የሚመሩ ዳኞች ፍትሃዊ ዳኝነት በአግባቡ እንዲሰጡ የቀጥታ ስርጭታችን ተፅእኖ ነበረው፡፡ በሃበሻ ሊግ በቀጥታ የሬድዮ ስርጭት በምንሰራቸው የእግር ኳስ ጨዋታዎች ሁሉም የሊግ ተጨዋቾች በተለይ የብሄራዊ ቡድን አባላት ከፍተኛ ምስጋና አድናቆት በመስጠት በተደጋጋሚ አበረታተውናል ይም የፕሮግራሙን ተፈላጊነት ያመለክታል፡፡

በሃበሻ ሊግ ስርጭቶች አድካሚው የስፖንሰርሺፕ ገቢ ፍለጋ እንደሆነ እገነዘባለሁ፤ ለመሆኑ በዚህ ረገድ የነበረው ልምድ ምን ይመስላል? ያው እንደነገርኩህ ፕሮግራሙ ሲጀመር ምንም አይነት የስፖንሰርሺፕ ገቢ ሆነ ድጋፍ አልነበረውም፡፡ እንደወጪ የሚቆጠረው ለስልክ የሚወጣው ወጭ ነበር፡፡ በእኔ የሚሸፈን ይህ ወጭ ለአንድ የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታ እስከ 300 ብር የሚጠይቅ ነበር፡፡ የሃበሻ ሊግ አጀማመር ስኬታማ ሆኖ ትኩረት እስኪያገኝበየሳምንቱ ቢያንስ አንድ የሊግ ጨዋታ በማስተላለፍ ያለምንም ገቢ ብዙ ሰርተናል፡፡ ሃበሻ ሊግን የጀመርኩት ፕሮግራሙን በትጋት እና በመስራት ተወዳጅነት እንዲያገኝ እና መሰረት እንዲይዝ በማሰብ በመሆኑ ከጅምሩ ገቢ አለማግኘቱ አላስጨነቀኝም፡፡ ከስልክ ወጭ ባሻገር አብረውኝ ለሚሰሩት የስፖርት ጋዜጠኞች ለትራንስፖርት እያልኩ የተወሰኑ ገንዘቦች እከፍልም ነበር፡፡ ሃበሻ ሊግ በቀጥታ የሬድዮ ስርጭቱ የስፖንሰሮችን ትኩረት መሳብ የጀመረው ፕሮግራሙን ማካሄድ ከቀጠልን ከ3 ወራት በኋላ ነበር፡፡ በእርግጥም የሚደግፉንን ስፖንሰሮች ማፈላለግ አድካሚ ስራ ነበር፡፡ የፕሮግራም ሃሳባችን አዲስ በመሆኑ ድጋፍ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው ድርጅቶች አፋጣኝ ምላሽ አልነበራቸውም፡፡ የስፖንሰርሺፕ ድጋፉ ለአገር ውስጥ የእግር ኳስ ውድድሮች ድምቀት እና ለውጥ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ለማሳመን ያለመታከት ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ በመጨረሻም ቢጂአይ ኢትዮጵያ፤ ባህር ትራንዚት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን በየሳምንቱ በተከታታይ እንድናስተላለፍ በሰጡን ድጋፍ ገቢ ማስገባት ጀመርን፡፡ ከዚያ በፊት አብዛኛውን ጊዜ ስፖንሰር ባላገኝም በወጪ እየተጎዳሁ እሰራ ነበር፡፡ እርካታ የማገኘው ለስፖርቱ እና ለሙያው ባለኝ ፍቅር ብቻ ነበር፡፡

ከዛሚ ኤፍኤም 90.7 ጋር በገባነው ውል መሰረት ከስፖንሰሮች የማገኘውን ገቢ 60 በመቶ ለጣቢያው ሰጥቼ የእኔ ድርሻ 40 በመቶ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከውጭ አገር የምድውልበትን የስልክ ወጭ እንድከፍል ይነገረኝ ነበር፡፡ ከስፖንሰርሺፕ ገቢው ከነበረው 40 በመቶ የገቢ ድረሻ የስልክ ወጭን ጨምሮ፤ የሆቴል፤ የአየር ትኬት እና ሌከሎች ወጭዎችን መሸፈን ይጠበቅብኝ ነበር። ይገርምሃል ከውጭ አገር በሬድዮ ቀጥታ ለማስተላልፈው ጨዋታ የስልክ ወጭዬ ከ2ሺህ ብር በላይ ነበር፡፡ በአጠቃላይ ግን የሃበሻ ሊግ በተጀመረ በሁለተኛው ዓመት የስፖንሰርሺፕ ገቢውም ማደግ ጀመረ፡፡ የፕሮግራሙም የስርጭት አድማስ እና ተፈላጊነት እየጨመረ በመምጣቱ በአድካሚ ሁኔታ የነበረው አጀማመር እየተቀየረ ነበር፡፡ የሃበሻ ሊግ የተቋረጠበት ምክንያት ታድያ ምንድነው? ዋናው ምክንያት ጳጉሜ 2 ቀን 2005 ዓ.ም ዋልያዎቹ ለአለም ዋንጫ ማጣሪያ ኮንጐ ብራዛቪል ላይ ከሴንትራል አፍሪካ ጋር ያደረጉትን ጨዋታ ለማስተላለፍ የ55ሺህ ብር ስፖንሰር አግኝቼ ከዛሚ ኤፍኤም 90.7 ጋር ድርሻችን ስንከፋፈል የተፈጠረው አለመግባባት ነበር፡፡ ከጣቢያው ጋር በመጀመርያ የተነጋገርነው ከላይ ከተጠቀሰው የስፖንሰርሺፕ ገቢ 23.000 ብር የትኬት ተነስቶ ከቀረው 40% እንዲሰጥ በመስማማት ወደ ብራዛቪል ተጉዤ ጨዋታውን ሠራሁ፡፡ ይሁንና ወደ አገር ቤት ስመለስ የትኬት እንዲነሳ አልተነጋገርንም ተባልኩና ከአጠቃላይ 55ሺ ብር 21ሺ ብር ብቻ እንደሚሰጡኝ ነገሩኝ፡፡ መሆን የነበረበት የትኬት 23ሺ ተነስቶ ለኔ 12ሺ ብር እንዲከፈል ነበር፡፡ ነገር ግን ቀደም ብዬ ያናገርኳቸው የፋይናንስ ሃላፊዋም ሆነ ስራ አስኪያጇ ይህንን ባለመቀበላቸው ገንዘቡ እንደማይሰጠኝ ተነገረኝ፡፡

እኔም ቢያንስ የትኬቱ እንዲሰጠኝ ጥረት አድርጌ ነበር፡፡ ነገር ግን ያ ሳይሆን የ23ሺ ብር ደረሰኝ በሬዲዮ ጣቢያው አሰርቼ 21ሺ ብር ብቻ ሰጡኝ፡፡ አጠቃላይ 14ሺ ብር አጣሁ ማለት ነው በማላውቀው ምክንያትም ከስራ እንደታገድኩ የተነገረኝም ከዚህ በኋላ ነበር፡፡ ቢያንስ ገንዘቡን ባይሰጡኝ የሃበሻ ሊግ ፕሮግራምን በጣቢያው ለመቀጠል ከዚህ በኋላ በርካታ ጥረቶችን አድርጊያለሁ፡፡ ግን እስካሁን ምክንያቱን ባለማውቀው ሁኔታ ምላሽ ሊሰጠኝ አልቻለም፡፡ እኔም በዚህ ምክንያት ሞራሌ ተነክቶና አዝኜ ከምወደው ስራ ከፕሮግራሜ ከሃበሻ ሊግ ርቄ አገኛለሁ፡፡ ዛሬም ቢሆን የዛሚ ሃላፊዎች ምን ያህል እንደተጐዳሁ ተረድተው በተለይ ገንዘቤን እንደሚመልሱልኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ምክንያቱም ከማንም በበለጠ ድካሜን ይረዱታል ብዬ ስለማስብ ነው፡፡ እስቲ ለመሰነባበቻ ያህል በኮሜንታተርነት ከነበሩሽ ገጠመኞች አንዳንዶቹን አጫውችን በኮሜንታተርነት ስሰራ ብዙ አስገራሚ እና አስቂኝ ገጠመኞች አሉ፡፡ አንዴ በክልል ጨዋታ እያስተላለፍን ነው፡፡ ጨዋታውን ለማስተላለፍ ትራክ ላይ የነበረው መሸሻ ወልዴ የግጥሚያውን ሂደት እየተከታተለ ሲያወራ ቆይቶ ‹አሉላ ግርማ› ብሎ ይጣራል፡፡ ይሄኔ ለእጅ ውርወራ ላይ መስመር ላይ የነበረው አሉላ፤ ማነው የጠራኝ ብሎ በመዞር ‹ወዬ› በማለት ሳቅ በሳቅ ያደረገን አጋጣሚም ትዝ ይለኛል፡፡

ሌላው ደግሞ የብሄራዊ ቡድን ጨዋታ ለመጀመርያ ጊዜ ለማስተላለፍ እና ከአገር ውጭ ለመጀመርያ ጊዜ የተጓዝኩበት ጨዋታ ላይ የገጠመኝ ነው፡፡ በቤኔኑ ኮቶኑ ስታድዬም ኢትዮጵያ እና ቤኒን ያደረጉት ወሳኝ ፍልሚያ ላይ ማለት ነው፡፡ በዚያ ጨዋታ ወቅት ስታድዬም ልንገባ በነበረበት ሰዓት ዝናብ በመዝነቡ ከአንድ የብሄራዊ ቡድን ተጨዋች የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጃኬት ተውሼ በመልበስ ጨዋታውን በቀጥታ ወደ የማስተላልፍበት የስታድዬሙ ክፍል ገባሁ፡፡ ጨዋታውን የማስተላልፈው በቤኒን እና በሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋዜጠኞች መካከል ሆኜ ነበር፡፡ ጨዋታው ከመጀሩ በፊት በስታድዬሙ አካባቢ የነበረው ዝናባማ የአየር ሁኔታ በድንገት ተቀይሮ ከባድ ሙቀት ተፈጠረ፡፡ ኢትዮጵያም 1ለ0 እየተመራች ነበር፡፡ የብሄራዊ ቡድኑ አጣብቂኝ ሁኔታ እና አስጨናቂው ወበቅ አጨናነቀኝ። የለበስኩትን የብሄራዊ ቡድን ጃኬት በማውለቅ ወገቤ ላይ አስርኩና ጨዋታውን ማሰራጨቴን ቀጠልኩ፡፡ በዙርያ የነበሩት አፍሪካውያን ጋዜጠኞች ጃኬቴን በጣም ወደውታል መሰለኝ አስር ጊዜ እየጎነታተሉ ካለሰጠሽኝ እያሉ አስቸገሩኝ፡፡ በወቅቱ በስታድዬሙ የነበረው ሙቀት እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ጨዋታውን የማስተላልፈው በደመነፍስ ነበር ለማለት ይቻላል። ጭራሽኑ ከሙቀቱ በተያያዘ ለተወሰኑ ደቂቃዎች በቀጥታ መስመር ላይ ብሆንም ስልኩን ይዤ በዝምታ ተውጬም ነበር። በዙርያ የነበሩት ጋዜጠኞች ጃኬቱን እንድሰጣቸው መለመኑን ትተው ከላዬ ላይ ልብሱን ጎትተው ለማውለቅ ሲሞከሩ ተቆጣኋቸው፡፡ “ኧረ እባክህ እረፍ“ ስል በአማርኛ ተናገርኩ። ይህ ቁጣዬ በቀጥታ የሬድዮ ስርጭት ይከታተለኝ ለነበረው ስፖርት አፍቃሪ መተላለፉ አስደንግጦኝ ነበር፡፡ ሌላው ገጠመኜ ግን አስከፊ ነበር፡፡

ወደ 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ኦብዱርማን ላይ ከሱዳን ብሄራዊ ቡድን ጋር የተደረገው ጨዋታ ላይ ነበር፡፡ የሚገርምህ ይህን ጨዋታ ሳስተላልፍ የነበረው በተለይ ነውጠኛ የሱዳን ደጋፊዎች በነበሩበት የስታድዬም ክፍል ነበር፡፡ በዛ ላይ ኢትዮጵያ የሚለውን ቲሸርት ለብሼያለሁ። በዙርያ የነበሩት የሱዳን ደጋፊዎች የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጎል ማግባት ሲጀምር ይተናኮሉኝ ያዙ፡፡ አንዳንዶቹ አይናቸው ያጉረጠርጣሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ በቁጣ እየተወራጩ ሊተናኮሉኝ ይሞክራሉ፡፡ እኔ ግን ትንሽ ብሸበርም ለአድማጮች በነበረኝ ክብር ሁኔታውን በመቋቋም ማስተላለፌን ቀጥያለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ትንኮሳቸው እየባሰ መጣና አንዳንዶቹ ደጋፊዎች የሲጋራ ጭሳቸውን ፊቴ ላይ ያቦኑብኝ ጀመር፡፡ ይህ ሁኔታ ግን ከስራዬ አላሰናከለኝም፡፡ ከጨዋታው መልስ ግን ከቦነነብኝ የሲጋራ ጭስ ብዛት ታምሜ ለሶስት ቀናት በከባድ የራስ ምታት አልጋ ላይ ማሳለፌን አስታውሳለሁ፡፡

Read 5625 times Last modified on Saturday, 17 May 2014 11:41