Saturday, 03 May 2014 12:34

ብዙ አደራ ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል!

Written by  አልአዛር ኬ.
Rate this item
(2 votes)

ለኢህአዴግ ከዚህ በላይ እንዴት እናጨብጭብለት?

ኢትዮጵያውያን “የፈሲታ ተቆጢታ” እያልን እንደምንተርተው፣ ኢህአዴግም ሆነ መንግስት ይህን ሁሉ   አድርገንለትም ለምን አላሞገሳችሁኝም፣ ለምንስ አላጨበጨባችሁልኝም? ብሎ ጭራሹኑ እኛው ላይ ቢያፈጥና ቢወቅሰንም፣ እኛ ግን የቻልነው ብዙ ነው

በአይሁዳውያን ቅዱስ ሚሽናህ ውስጥ “በራስህ አስተያየት ጠቢብ አትሁን” የሚል ድንቅ ምክር ሰፍሯል፡፡ ይህን ድንቅ ምክር እንደሚገባ አድርጐ ልብ ያለው የሚመስለው ስመጥሩው እንግሊዛዊ ደራሲ ቻርለስ ዲከንስ በ1853 ዓ.ም “Bleak House”  በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፉ፤ “የራስ በራስ ሙገሳ ከተራ ምስክርነት ቁጥር እንኳ አይገባም” በማለት ጽፏል፡፡
ሰዎችም ሆኑ መንግስታት ይህን በመሰለው የራስ በራስ ሙገሳ አለመጠን ሲጠመዱ፣ የትህትና ልባቸው በትዕቢት ሲደነድንና ከእኔ ወዲያ ላሳር እናም ግነን በሉኝ በሚል ክፉ ደዌ መለከፋቸው አይቀሬ መሆኑን ለማረጋገጥ አብነት ፍለጋ መባዘን ከቶውንም አያስፈልገንም፡፡ እነሆ የዚህ ክፉ ደዌ አሳዛኝ ሰለባ ከሆነ በርካታ አመታትን ያስቆጠረው ኢህአዴግና ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት እዚሁ አፍንጫችን ስር ያሉ ቋሚ ምስክራችን ናቸው፡፡
ኢህአዴግ የመንግስትነት ስልጣን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ ለሀገሪቱ እድገትና ሰላም፣ ለህዝቦቿም ነፃነትና የዲሞክራሲ መብቶች መጠበቅ ዋነኛው መንገድ የእሱና የእሱ ብቻ እንደሆነ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ እኛኑ ከማስገንዘብ ቦዝኖ አያውቅም፡፡ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በዚሁ ላይ ያልተቋረጠ ግነን በሉኝ፣ አጨብጭቡልኝ ውትወታ ጨምሮበታል፡፡
ስለ ሰዎች ባህሪይ የሚያጠኑ ምሁራን፣ አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ሌሎች ሰዎችንም ሆነ መንግስታትን የሚያደንቁት ስለሚያደንቋቸው ሰዎችም ሆነ መንግስታት የተሟላ መረጃና እውቀት ሳይዙ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግም ዝነኛው አሜሪካዊ ፖለቲከኛና የጥበብ ሰው ቤንጃሚን ፍራንክሊን፤ “Poor Richards Almanack” በሚል ርዕስ በ1755 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፍ “ሙገሳ ወይም አድናቆት የቸልተኝነት ልጅ ናት” በማለት ጽፈዋል፡፡
ይህ ግን ለመንግስት ከቁጥር የሚገባና ነገሬ የሚለው ጉዳይ አይደለም፡፡ እራሱን በራሱ አሞግሶ አልጠግብ ያለው መንግስት፤ ይባስ ብሎም እኛን ተገዥዎቹን የጭብጨባና የሙገሳ ንፉግ እንደሆንበት ግልጽ ስሞታ ማሰማት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡
በቅርቡ የመንግስታቸውን የዘጠኝ ወር የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ለፓርላማው ያቀረቡት የኢህአዴግ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ ከፓርላማ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሲሰጡ፣ የሚመሩት መንግስታቸው ከአስሩ ስምንት ያመጣ ጐበዝ ተማሪ በመሆኑ ሊጨበጨብለትና ሊሞገስ እንደሚገባው ከፍ ያለ አጽንኦት በመስጠት አስገንዝበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም፤ ይህን ማስገንዘቢያቸውን ሲሰጡን በእውቀትም ይሁን ያለ እውቀት በደንብ ያልነገሩን ነገር ኢህአዴግም ሆነ መንግስታቸው ከአስሩ ስምንት ያመጣው አስሩንም ጥያቄዎች ራሱ አውጥቶ፣ ለጥያቄዎቹ የሰጠውን መልስም ራሱ አርሞ መሆኑን ነው፡፡ የእውነት እንነጋገር ከተባለ ግን በእንዲህ ያለ አሰራር ከኢህአዴግም ሆነ ከመንግስት የሚጠበቀው ስምንት ከአስር ማግኘት ሳይሆን አስር ከአስር መድፈን ነበር፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ መንግስት ላመጣው የስምንት ከአስር ውጤትም ቢሆን ተገቢውን እውቅና ሰጥተነዋል፡፡ ያለዚያማ በ2002 ዓ.ም በተካሄደው አራተኛው ብሔራዊ ምርጫ “99.6 በመቶ” ድምጽ በማግኘት አይመረጥም ነበር፡፡ ታዲያ ለኢህአዴግ ከዚህ የበለጠ እንዴት አድርገን እናጨብጭብለት?
ኢትዮጵያውያን “የፈሲታ ተቆጢታ” እያልን እንደምንተርተው፣ ኢህአዴግም ሆነ መንግስት ይህን ሁሉ   አድርገንለትም ለምን አላሞገሳችሁኝም፣ ለምንስ አላጨበጨባችሁልኝም? ብሎ ጭራሹኑ እኛው ላይ ቢያፈጥና ቢወቅሰንም፣ እኛ ግን የቻልነው ብዙ ነው፡፡
የኑሮ ውድነት ቀንበሩ ከብዶን ወገባችን ሲበጠስና የእለት ተዕለት ህይወታችን ገሀነም ሆኖብን ኤሎሄ ስንል “እድገቱ ያመጣው ችግር ነውና ቻሉት” ስንባል ምን አልን? “በባለ ሁለት አሀዝ ኢኮኖሚዋ እየተመነደገ ነው” በምትባለው ሀገራችን፣ በሚሊዮን ለምንቆጠር ዜጎች የቧንቧ ውሀ ማግኘት እንደቅንጦት “የፈረንጅ ውሀ” ሲቆጠርብን ምን አልን? የመልካም አስተዳደር ችግር ነው በሚል ሰበብ በየደቂቃው መብራት ሲጠፋብንና ኑሮአችንን ሲያመሰቃቅለው፣የንግድ እንቅስቃሴያችንን እያስተጋጎለ ለከፍተኛ ኪሳራ ሲዳርገን፣ ምን አልን? በኔትዎርክ መቋረጥ የተነሳ የንግድና ሌሎች  ስራዎቻችን እግር ተወርች ተቀይደው ተራ የስልክ ግንኙነት ብርቅ ሲሆንብን፣ ምን አልን? በመልካም አስተዳደር እጦት ሳቢያ  ፍትህ ሲጓደልብን፣ የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻችን ያለአግባብ ሲጣሱና ሲረገጡብን፣ ጠግበው መብላት ከናፈቃቸው ልጆቻችን ጉሮሮ ነጥቀን ለመንግስት የምንከፍለው በቢሊዮን የሚቆጠር የግብር ገንዘብ ያላ አግባብ ሲባክንና የምዝበራ ሲሳይ ሲሆን፣ ሌላም ተጨማሪ አከርካሪያችንን የሚቆርጥ ፍዳና መከራ ሲጫንብን፣ የተጫነብንን መከራ እንዲያቀልልን አምላካችንን ከመማፀን ውጭ መንግስትን ከቶ ምን አስቀየምነው?
በእውኑ ዜጎች ለመንግስታቸው ለዚያውም በወጉና በአግባቡ ላልያዛቸው --- ከዚህ የበለጠ ውለታ፣ከዚህ የበለጠ መስዋዕትነት መክፈል ይቻላቸዋልን? በመላው ዓለም ይህን መሰል ውለታና መስዋዕትነት ለመንግስታቸው መክፈል የቻሉት ኢትዮጵያዊያን ብቻ ናቸው፡፡ ኢህአዴግም ሆነ መንግስት ይህን ዋነኛ ጉዳይ በቅጡ ለመረዳት አለመቻሉ አሊያም በተአብዮ ደረቱን መንፋቱና ልቡን ማደንደኑ አለመታደል እንጂ ሌላ ምን ሊባል ይችላል፡፡
የሆኖ ሆኖ ግን የፈለጉትን ያህል ቢሸሹት የማይሸሽ፣ ቢክዱት የማይካድ አንድ እውነት አለ፡፡ ለሁሉም ጊዜ አለው፡፡ ሁሉም ደግሞ ልክና ገደብ አለው፡፡ አቻ የለሹ የኢትዮጵያውያን መከራና ፍዳን የመሸከም ትዕግስትና ጽናት እስከዝንተ ዓለም ድረስ መዝለቅ እንደማይችል ኢህአዴግም ሆነ መንግስት ያጡታል ብሎ ማሰብ እንደ  ጅላጅል ያስቆጥራል፡፡
ምንም እንኳን ይህን ሁሉ ውለታና መስዋዕትነት የከፈልንለት መንግስት፣ በሙገሳና በአድናቆት ንፉግነት ስሞታ ቢያቀርብብንም የቀጣዩን ፈተና ጥያቄዎች የምናወጣውና የምናርመው እኛ የሉአላዊ ስልጣን ባለቤቶች የምንባለው ዜጎች መሆናችንን፣ ኢህአዴግም ሆነ መንግስት በሚገባ ልብ ሊሉት ይገባል፡፡
በቅዱስ ቶራህ “ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፡፡ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል” ተብሎ እንደተፃፈ፣ እንደ መንግስትነቱ መጠን ብዙ አደራ የተሰጠው ለኢህአዴግና እርሱ ለሚመመራው መንግስት በመሆኑ ከእርሱ አብዝተን እንሻለን፡፡

Read 2933 times