Saturday, 26 April 2014 13:16

የሰሎሞን ዐይኖች

Written by  ኦርዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(7 votes)

ደራሲ - ሰሎሞን ሞገስ (ፋሲል)
ርዕስ - ጽሞና እና ጩኸት
የገፅ ብዛት - 70
የህትመት ዘመን - ጥር 2006 ዓ.ም
የሽፋን ዋጋ - 20 ብር
ዘውግ - ግጥም
መቅድመ ኩሉ
እውነተኛ የግጥም ደራሲ በጣር ላይ ያለች ነፍስ ይመስላል፤ ዓለም ምኑም አይደለችም፡፡ ሃብትና ንብረትም ቁቡ አይደሉም፡፡ እውነተኛ ገጣሚ ስሜቱ የሸረሪት ድር ያህል ስስ ነው፤ ሃብት ማጋበስ፣ ዝና፣ ርካሽ ተወዳጅነት፣ ስልጣን ምኑም አይደሉም፡፡ እሱ የሚኖረው የብህትውና ኑሮ ነው፤ ከሰው ጋር ቁጭ ብሎ ብቻውን ያወራል፤ ሰዎች ሲገፉ እሱ ይታሰራል፡፡ የምንዱባን ፊት ሲጠቁር እሱ እንባውን ይዘረግፋል፤ ምንዝሩ ህዝብ ሆዱን ሲቆርጠው እሱን ይሞረሙረዋል፤ ፍትህ ሲጓደል የህዝብን ዋይታ ይጮኻል፡፡ በአጠቃላይ የእውነተኛ ገጣሚ ህይወት ምስኪን ናት፤ የእሳት ራት፡፡
ለመሆኑ “እውነተኛና ሃሰተኛ ገጣሚ አለወይ” የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፤ መልሴ “አዎ!” የሚል ይሆናል፡፡ ያገሬ አርሶ አደር ጀግኖችን ሲያደንቅ:-
“ሁሉም ወንድ ነወይ ሱሪ ቢያገለድም?
አባ ስበር…ታጠቅ የእኔ ወንድም!” ይላል፡፡ እውነት ነው፤ ወንዱ ሁሉ በጾታው ወንድ ቢሆንም በግብሩ ወንድ ያልሆነ ወንድ ግን ሞልቷል፡፡ የጊዜያችን አብዛኛው ግጥምም  ወንድ እንዳልሆነው ወንድ የሚመሰል ነው፡፡ ምክንያቱም ቤት መምታት ብቻ ግጥም መግጠም አይደለማ! እዚህ ግባ የማይባል የቃላት ድሪቶ በመከመር ግጥም መጻፍ አይቻልም፡፡ ማሳተም ስለተቻለ ብቻ ገበያውን በአሰስ ገሰስ ከማጣበብ ውጭ የሚፈይደው የለም፤ አያስተምርም፤ አያዝናናም፣ አያስደምም፡፡ ይህ እርግማን ነው፤ ግጥም ትልቅ ተሰጥኦን የሚጠይቅ ረቂቅና ምጡቅ የጥበብ ዘርፍ ነው፡፡ ማንም ተነስቶ ሊጓዝበት የሚችል አውራ ጐዳና አይደለም፤ ተሰጥኦና በንባብ እንዲሁም በህይወት ልምድ መደበርን ይጠይቃል፡፡ “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” እንዲሉ ግጥም ለመጻፍ ከመድፈራችን በፊት ተሰጥኦው አለኝ ወይ? ብሎ ራስን መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ተሰጥኦ ከተፈጥሮ የሚታደሉት እንጂ በግብዝነት የሚታገሉት አይደለም፡፡
በአንፃሩ ተፈጥሮ ለግጥም ያዘጋጀቻቸው፣ ራሳቸውን በንባብ እንደገና የፈጠሩና ይህንን ድንቅ ተሰጥኦቸውን በገቢር የገለጡ (ጥቂት ቢሆኑም) ብርቱ ገጣሚዎች ስላሉን ተስፋ እንዳንቆርጥ ሆነናል፡፡ ከእነዚህ ብርቱ ገጣሚዎች አንዱም ሰሎሞን ሞገስ (ፋሰል) ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ የሰሎሞን ዐይኖች እንደ ንስር ጥልቅ ናቸው፤ እመቀ ዕመቃት ጠልቀው፣ ሰማየሰማያት መጥቀው የማየት ልዩ ኃይል አላቸውና!
ሰሎሞን በገጣሚነት ብቅ ያለው “እውነትን ስቀሏት” በሚል ርዕስ በ2001 ዓ.ም ባሳተመው የግጥም ስብስቡ ነው፡፡ በ2004 ዓ.ም “ከፀሐይ በታች” በሚል ርዕስ ሁለተኛ ስብስቡን ያሳተመ ሲሆን “ጽሞናና ጩኸት” የተሰኘው የግጥም ስብስቡ ሶስተኛ ስራው ነው፡፡ ሰሎሞን “እውነትን ስቀሏት” ላይ አስደምሞን “ይበል” ብንልለትም “ከፀሐይ በታች” በተባለው ስብስቡ ላይ የተወሰኑ ግጥሞቹ ልል ነበሩ፡፡ ግን ያንን ላላ ያለበትን ጐን በአያሌው አጠንክሮና ራሱን አርሞ በ “ጽሞና እና ጩኸት” ግጥሙ ብቅ ብሏል፡፡
የጽሞና እና ጩኸት ይዘት
“በጽሞና እና ጩኸት” ስብስብ ውስጥ የተካተቱት 59 ግጥሞች ሲሆኑ በአስራ አንድ የገለጣ ዘይቤዎች የተቀመሩ ናቸው፤ ወይም ከላይ በተጠቀሰው አሃዝ የሚፈረጁ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ እነሱም  -
ትዝብት (ምፀት) 18    - ንፅፅር 3
ተፈጥሮ 7         - ፍቅር 7
ዝምዝም ወርቅ 5     - ሃገር 2
ትንቢት 3        - ምርምር 2
ፍልስፍና 9        - ተስፋ 1
ህብር 2 ናቸው፡፡
የጠቀስኋቸው ርዕሰ ጉዳዮች የቀረቡበትን ዘዴ (ቴክኒክ) ለማሳየት እንጂ የሁሉም ይዘት ያው የሃገርና የወገን ጣጣ ነው፡፡ ለማሳያነት ያህል የተወሰኑትን ልጥቀስ፤
ሰሎሞን ህሊናውን ረፍት የነሳው የአይረቤ ነገሮች መብዛት ይመስላል፤ በግጥሙ ውስጥ በብዛት የምናገኘውም ፖለቲከኞችን፣ ምሁራንን፣ መንደርተኞችንና ትውልዱንም ጭምር የታዘበበትን መንገድ ነው፡፡ ሰሎሞን ምሁራንን እንዲህ ታዝቧል፡፡
“…ወይ ፀሐይ አያስጥል፣
ወይ ዝናብ አይከልል፣
የፎቶ ላንቲካ ጌጥ ከመሆን በቀር፣
ምንድን ነው ትርጉሙ የዲግሪ ቁም ነገር?
እርጥብ ነው፤ ጭንጫ ነው መሬቱስ የአገሬ፣
ምንድን ነው እሴቱ የምሁሩ ፍሬ?” (ገፅ 33)
ገጣሚው ቅኔ የተማረ አይመስለኝም፤ ግን “ዝምዝም ወርቅ፣ ምርምር እና ህብር” በሚባሉት የቅኔ መንገዶችም ጽፎ እናገኘዋለን፤ “ኢትዮጵያዊነት“ በሚል ርዕስ ያስነበበን ግጥም “ዝምዝም ወርቅ” በምንለው የቅኔ መንገድ የጻፈ ነው፤ እንዲህ ቀርቧል፡፡
“ኢትዮጵያዊነት ዕዳዬ ኢትዮጵያዊነት ፀጋዬ፣
ኢትዮጵያዊነት ስቃዬ ኢትዮጵያዊነት ደስታዬ
ኢትዮጵያዊነት ጉድለቴ ኢትዮጵያዊነት ሙላቴ
ኢትዮጵያዊነት ሹመቴ ኢትዮጵያዊነት ቅጣቴ
ኢትዮጵያዊነት ጭነቴ ኢትዮጵያዊነት እረፍቴ
ኢትዮጵያዊነት ሕይወቴ ኢትዮጵያዊነት ስቅለቴ
ኢትዮጵያዊነት ለቅሶዬ ኢትዮጵያዊነት ተስፋዬ” (ገፅ 16)፡፡
“ህብር” በሚባለው መንገድ የተጻፉ ግጥሞችንም ከሰሎሞን ሥራዎች ውስጥ እናገኛለን፤ ህብር ሁለት ትርጉም መስጠት እንዲችል ሆኖ በአንድ ወይም በሁለት ቃላት የሚገለጥ የቅኔ መንገድ ነው፤ የሚከተሉትን ለአስረጅነት ላቅርብ
“ሙያችን ነው አሉ ልብስ አጣቢዎቹ
እኔስ የሚገርሙኝ አለቅላቂዎቹ፡፡
ለጉዞ ቢነሳ ጓዝ ጉዝጓዙን ቋጥሮ
ይዘልቀው ይሆን ወይ አሁን ስንቱን አስሮ” (ገፅ 72)  
ህብራዊ ቃላቱ ያሉት “አለቅላቂዎቹ” እና “አስሮ” ከሚሉት ላይ ነው፤ ሰሙ ልብስን የሚያለቀልቁ ሲሆን ወርቁ “አለቅላቂዎቹ” አቃጣሪዎች፣ አሳባቂዎች፣ አቶክቷኪዎች፣ ነገረ ሰሪዎች፣ ሸውከኞች ወዘተ ማለት ነው፡፡ “ስንቱን አስሮ” የሚለውም ሰሙ ስንቱን ዕቃውን ሸክፎ፣ ቋጥሮ፣ ቀርቅቦ ማለት ነው ብለን ልንተረጉመው ስንችል ወርቁ ደግሞ ስንቱን ህዝብ ወይም ሰው አስሮ፣ ከርቸሌ አስገብቶ፣ ህሊናውን ቀፍድዶ ይገፋዋል? ማለት ነው፡፡ ይህን አይነቱን የቅኔ መንገድ በተለምዶ “ሰምና ወርቅ” እያሉ በርካታ ሰዎች ሲጠሩት እንሰማለን፤ ግን ስህተት ነው፡፡ የሰምና ወርቅ መንገድ እንደዚህ አይደለም፤ ይህ “ህብር” የሚባለው መንገድ ነው፡፡
ሰሎሞን ሰባት ግጥሞችን የጻፋቸው እንደ ሩሲያ ደራስያን ከተፈጥሮ ጋር እያዛመደ ነው፤ እዚህ ቁጭ ብለን በሩሲያ የሚገኙትን የቮልጋን ወንዝና የካውካሰስን ተራራዎች አብረናቸው የኖርነውን ያህል እናውቃቸዋለን፡፡ ይህን ኃይል የሰጡን ደግሞ እነፑሽኪንና፣ ጎጎል፣ ዶስተዬብስኪ፣ ማክሲም ጎርኪና ራዲሽዮቭን የመሰሉ አንጋፋ ደራሲያን ባበረከቱልን የብዕር ትሩፋት ነው፡፡ ሰለሞን እንደዚያ ነው፤ ተፈጥሮን ያደንቃል፤ ተፈጥሮን በጥልቅ የሚመለከቱ ዐይኖች አሉት፡፡
“በፕላኔቶች ላይ እረማመዳለሁ፣
በጥልቁ ባህር ላይ ቆሜ እደንሳለሁ፣
ከአበባ፣ ከነፋስ፣ ከወፍ አወራለሁ፤
ሲያሻኝ በህዋው ላይ ቤቴን እሰራለሁ፤
ጨረቃዋ ላይ ነው ተኝቼ እምዝናና፣
ምንድነህ ብትሉኝ ገጣሚ ነኝና!” (ገፅ 37) ይለናል ሰለሞን የገጣሚን ምጥቀት፣ የገጣሚን ልዩ ኃይልና ምሉዕ ሰብዕና ሲነግረን፡፡ ለእውነተኛ ገጣሚ የሚሳነው ነገር የለም፤ በጥልቅ ባህር ላይ ደንሳል፡፡ ግን ጥልቁ ባህር እውነተኛ ባለው ነው? ባህር ላይስ ቤት መስራት ይቻላል? በጨረቃ ላይ እሚተኛ ምን አይነት አስማተኛ ቢሆን ነው? መጠየቅ መመራመር አለብን፡፡ አለዚያ ግልብ አንባቢዎች እንሆናለን፡፡  
ገጣሚው ነቢይ ነው፤ ካለፈ፣ ከሄደ በኋላም ታሪክ እንደሚሠራ፣ በመቃብሩ፣ በደሙ፣ በአጥንቱ ላይ ሁሉ ገና እንደሚጽፍ በእርግጠኝነት ነግሮናል፤ እንዲህ እያለ፡-
“… ብዕር ቢጠፋብን
ቀለም ቢደርቅብን
ብራና ቢቸግር ቢያልቅ ወረቀታችን፣
እንጽፋለን ገና በየግንባራችን፡፡
የጋፍነውን ምሬት፣ ያማጥነውን ሲቃ፣
ወረቀት ቢቸግር፣ ብራና ባይበቃ፤
የሆንነውን መሆን፣ ያየነውን ስቃይ፣
እንጽፋለን ገና በየመንገዱ ላይ፡፡
የጅቦቹን ዝርፊ፣ የመድሎውን አቅም፣
የዘር ማጥራቱንም፣ የኑሮውን ሸክም፣
በአጥንታችን ብዕር ከትበነው ለዓለም፣
እንጽፋለን ገና በደማችን ቀለም፡፡
ታሪክ እንዳይስተው የኖርነውን ስቃይ፣
እንጽፋለን ገና መቃብራችን ላይ፡፡” (ገጽ 13) ድንቅ ግጥም ነው፡፡ ህዝባዊ ደራሲያን ከሞቱ በኋላም በሞቱለት ህዝብ ህሊና ውስጥ መቼም ህያዋን ናቸው፡፡ አሌክሳንደር ፑሽኪን “ሀውልት” በሚል ርዕስ እንደ ጻፈው ማለት ነው፡፡
“ለሚመጣው ትውልድ ከበስተኋላዬ
ሃውልት አቁሜያለሁ ለመታሰቢያዬ” እንዳለው፡፡ የደራሲ ሐውልት ስራው ነው፤ መቸም የማይፈርስ፤ በውሃ ሙላት የማይበሰብስ፡፡ የሰለሞን “እንጽፋለን ገና” እንደዚያ ዓይነት ኃይለ ቃል አለው፤ መልእክቱ ግዙፍ ነው፤ ህሊናን ይረብሻል፤ ራስ ምታት ሆኖ አምባገነኖችን ያተራምሳል፤ ይህ የሚሆነው ግን ህሊና ያላቸው ከሆኑ ብቻ ነው፡፡
ያም ሆኖ ሰሎሞን ሰሞኑን የፈራበት አንድ ጉዳይ ገጥሞታል፤ ሰዎችን ለማስደሰት ሲል አህያ፣ ውሻ፣ ፈረስ፣ ወዘተ ሆኖ በማገልገሉ “በግ ሁን” ብለውታል፤ ይህንን ከሁሉም በላይ ፈርቷል፡፡
ለምን? ግጥሙን እንመልት
“አህያ ሁን አለኝ አህያ ሆንሁለት፣
አሰሱን ገሰሱን እንድሸከምለት
ውሻዬም ሁን ብሎኝ ሆንሁኝ ላስደስትው፣
ጭራ እየቆላሁኝ እንዳጨዋውተው፤
ፈረሴም ሁን ብሎ ፈረሱ አደረገኝ፤
በየዳገቱ ነው ወስዶ እሚጋልበኝ፡፡
እንጃ ግን ሰሞኑን “በግ ነህ” ተብያለሁ፣
ሊያርዳኝ ነው መሰለኝ አሁን ፈርቻለሁ” (ገፅ 35)
ሰሎሞንን ያሰጋው ፈረስ፣ አህያ ወይም ውሻ መሆን አይደለም፤ በግ መሆን ነው፡፡ በግ መሆን አንገትን ለቢላዋ ይዳርጋል፤ በመሆኑም እምብዛም የዋህነት እንደማይጠቅም ነግሮናል፡፡
አርሶ አደሩ ሲያቅራራ “እምብዛ ዝምታ ለበግም አልበጃት፣
አምሳ ሆና ቆማ አንድ ነብር ፈጃት” እንደሚለው መሆኑ ነው፡፡
በአጠቃላይ የሰለሞን ሞገስ ግጥሞች እንዴ ተነብበው የሚጣሉ አይደሉም፤ ልክ እንደ ቅኔ ሊመረመሩ፤ ለመሰጠሩ ይገባል፤ በመረመርናቸው በመሰጠርናቸው ቁጥር “አጀብ!” የሚሰኙ ፍሬ ሃሳቦችን፣ ምርምሮችንና አዳዲስ ሃሳቦችን እናገኛለን፡፡ እኛ የምናየው ፊትለፊታችን ያለውን ነው፤ የሰሎሞን ዓይኖች ግን ከግድግዳው ጀርባ ያለውን ሁሉ አጥርተው ያስተውላሉ፤ ሰሎሞን ድንቅ ገጣሚ ነው፡፡ ለመሆኑ ቅኔ ቢማር ኖሮ በዚህ ተሰጥኦው ላይ ምን ዓይነት ገጣሚ ይወጣው ነበር ይሆን? ብየም አስቤያለሁ፡፡  በመጨረሻም ከሰሎሞን “ጽሞና እና ጩኸት” ላይ ያየኋቸውን ድክመቶች ጠቅሼ ጽሑፌን ልቋጭ፤ ጽሞና እና ጩኸት የተጻፈው በአማርኛ ነው፡፡ ማንኛውም የጽሁፍ ቋንቋ የራሱ ህግና ሥርዓት አሉት፡፡ ከህግና ስርዓቱ መሃል የቃላት አጠቃቀምና ስርአተ ነጥቦች ቀዳሚዎች ናቸው፡፡ የመጽሀፉ ታላቁ ድክመት የሥርአተ ነጥብ አለመኖር ነው፡፡ አብዛኞቹ ግጥሞ የሥርአተ ነጥቦች ቀዳሚዎች ናቸው፡፡ የመጽሐፉ ታላቁ ድክመት የሥርዓተ ነጥብ አለመኖር ነው፡፡ አብዛኞቹ ግጥሞች የስርዓተ ነጥብ ድህነት አለባቸው፡፡ በጣም አልፎ አልፎም ቢሆን ፀያፍ ብዜቶችን ለምሳሌ “መልዓክቶች” አይነት አይቻለሁ፤ ይህ ለመጽሐፉ ተነባቢነት መሰናክል ሊሆን ይችላልና ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ገፅ 48 ላይ የቀረበውና ቤት ሰበር ግጥምን የተመለከተው ጉዳዩም ስህተት ነው፤ ቤት ሰበር ግጥም የተጀመረው በግዕዙ ቅኔ “ፍልስ” ተብሎ የሚታወቅ እንጂ ሰሎሞን የጀመረው አዲስ ነገር አይደለም፡፡ በርካታ ግጥሞችን ርዕስ አልቦ ማድረግም ጥቅሙ አልታየኝም፡፡ በተረፈ ባለ ንስር አይኑ ሰሎሞንን በርታ አለማለት ንፍገት ይመስለኛል፡፡      

Read 3826 times