Saturday, 26 April 2014 12:50

የማርያኖ ቅጥር ለወጣቶች የተሰጠውን ትኩረት ያሳያል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

ከ3 ወራት በላይ የፈጀው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ቅጥር ሰሞኑን በኤሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል በፖርቱጋላዊው ማርያኖ ባሬቶ እና በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ መካከል በተፈረመው የውል ስምምነት ተቋጭቷል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ  የቅጥሩ ሂደት የዘገየው ውጤታማ  አሰልጣኝ ለመቅጠር በተከተልነው ጥንቃቄ የተሞላበት አሰራር  ነው ብለዋል፡፡ የፊታችን ሀሙስ በይፋ ስራቸውን የሚጀምሩት ዋና አሠልጣኙ ማርያኖ ባሬቶ ከማክሰኞው የፊርማ ስነስርዓት በኋላ ባለቤታቸውንና አንድ ልጃቸውን ወደ አዲስ አበባ  ይዞ ለመምጣት  ወደ አገራቸው ተጉዘዋል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ በአሰልጣኙ ቅጥር ምንም ደላላ እንዳልገባበት የገለፀ ሲሆን የፊርማም እንዳልተከፈለ አመልክቷል፡፡
በባህርያቸው ቀጥተኛ እና ግልፅ ሰው መሆናቸውን፤ ውሸት እና አሉባልታ እንደማይወዱ ለስፖርት አድማስ የተናገሩት ማርያኖ ባሬቶ፤ በሙያቸው በታታሪነት በማገልገል ስኬታማ መሆን ዋና ትኩረቴ  ነው ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሃላፊነት ለመስራት የወሰንኩት ጉልህ ለውጥ ለመፍጠር የምችልባቸው እድሎች በመመልከቴ ነው ካሉ በኋላ፤  በእግር ኳሱ ዙርያ ያሉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በወጣት እና ታዳጊ ተጨዋቾች በትኩረት ለመስራት   ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየታቸው እንዳነሳሳቸውና  ኢትዮጵያውያን የእግር ኳስ ተጨዋቾችን በፕሮፌሽናል ደረጃ  እስከ አውሮፓ ማሳደግ እንደትልቅ ሙያዊ ስኬት   የሚቆጠር መሆኑን   ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያ በገቡ በማግስታቸው አዲሱ የስራ ሃላፊነት ትልቅ ክብር መሆኑን ተገንዝቤያለሁ ያሉት ማርያኖ አዲስ አበባን ዞር ዞር ብለው በጎበኙበት ወቅት የከተማዋ ሰላማዊነት ማርኮኛል ብለው፤ የህዝቡ አቀባበል  ደስ እንዳላቸውና በተለይ እግር ኳስ የሚወደድበት አገር ለመስራት ጉጉት ተፈጥሮብኛል ብለዋል፡፡የኢትዮጵያ እግር ኳስ በማይናወፅ መሰረት ላይ ተገንብቶ በእድገት አቅጣጫ እንዲጓዝ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማድረግ እድሉን በማግኘታቸው ተደስቻለሁ ያሉት ዋና አሰልጣኙ፤ ከሁሉም የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ቅን የሆነ ድጋፍ እንደማገኝ አምናለሁ  ብለዋል፡፡  
በ2ዓመት 10 ሚሊዮን  ብር የሚስወጣው ውል
በቅጥር ሂደቱ የመጨረሻ እጩዎች ከነበሩት አሰልጣኞች መካከል በአንደኛ ደረጃ  ታስበው ከነበሩት  ሰርቢያዊው ጎራን ስቴፋኖቪች ያልተሳካ ድርድር በኋላ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ከሌሎቹ የመጨረሻ እጩዎች ከፖርቱጋላዊያኑ ማርያኖ ባሬቶ እና ዞራን ፍሊፖቪች እንዲሁም ከስዊድናዊው ላርስ ኦሎፍ ማትሰን ግንኙነት ያደረገው ወዲያውኑ ነበር፡፡  በመጨረሻም የእግር በተለያዩ ሃሳቦች በመቀራረቡ አሰልጣኙ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ጋበዘ፡፡ ባለፈው ሰኞ እና ማክሰኞ የመጨረሻው ድርድር በማከናወን ከስምምነት ላይ  ደረሰ፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከማርያኖ ባሬቶ ጋር ባደረገው ድርድር ዋናው ትኩረት የደሞዝ እና ሌሎች ጥቅማጥቅሞችን በተመለከተ ነበር፡፡ በ2 አመት  ኮንትራት ቅጥር ለማርያኖ ባሬቶ 18 ሺ ዶላር ወርሃዊ የተጣራ ደሞዝ ለመክፈል የተስማማው  ፌደሬሽኑ የአሰልጣኙን የመኖሪያ ቤት፣ ተሽከርካሪና ነዳጅ የመሳሰሉት ጥቅማ ጥቅሞች  ይሸፈንላቸዋል፡፡ አቶ ጁነዲን ባሻ   እንደተናገሩት የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ  የዋና አሰልጣኙን ደሞዝ እና ሌሎች ወጭዎች ቢያንስ ለ3 ወራት ከካዝናው ለመክፈል ያስባል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን መንግስት፤ ስፖንሰሮች እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚሰጡትን ድጋፍ ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል፡፡ ማርያኖ ባሬቶና እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የገቡትን ውል  ለማፍረስ ከፈለጉ ከ3 ወራት በፊት ማሳወቅ አለባቸው ተብሏል፡፡ ማርያኖ ባሬቶ ከብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሃላፊነታቸው ጎን ለጎን በሚያከናውኗቸው ተግባራት ዙርያ ሰፊ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ በውሉ መሰረት ማርያኖ ባሬቶ  በኢትዮጵያ እግር ኳስ የአሰለጣጠን ስርዓት ውስጥ ለውጥ እንዲፈጥሩ ተፈልጓል፡፡ መሰረታዊ እና ዘላቂ ውጤት የሚገኝበትን አሰራር በመዘርጋት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱም ተጠይቋል፡፡ በተለይ ደግሞ በታዳጊ እና ወጣት ተጨዋቾች ላይ ያተኮሩ ስራዎችን በማከናወን በዘላቂ መሰረት ላይ ብሄራዊ ቡድኑን እንዲገነቡ መመርያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ዋና አሰልጣኙ ከላይ በተዘረዘሩት አቅጣጫዎች  ከአገሪቱ የፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች ጋር ተቀራርበው የሚሰሩ ሲሆን ከየክለቡ  አሰልጣኞች፤ አመራሮች እና  ከተጨዋቾቻቸው ጋር ወጥ በሆነ ግንኙነት እንደሚንቀሳቀሱ ፤ ልምዳቸውን በማጋራት እንደሚሰሩና ኢትዮጵያዊ ተጨዋቾች በፕሮፌሽናል  ደረጃ ስኬት እንዲኖራቸው መሰረታዊ አቅጣጫዎች እንደሚነድፉም ይጠበቃል፡፡ ዋና አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ  በብሄራዊ ቡድኑ ከኢትዮጵያዊ ረዳት አሰልጣኞች ጋር ለመስራት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውም ሲታወቅ አስፈላጊው የእውቀት እና የክህሎት ሽግግር ለመፍጠር  እንደታሰበ ተገልጿል፡፡
ለ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በማለፍ እስከ ግማሽ ፍፃሜ መድረስ ከማርያኖ ባሬቶ
እስከ 12 ሚሊዮን ብር በጀት ከፌደሬሽን
ዋና አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ2015 እኤአ ለሚደረገው የሞሮኮው 30ኛው አፍሪካ ዋንጫ ማለፋቸው ይጠበቃል ያሉት የእግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ ሲሆኑ፤ በአፍሪካ ዋንጫው ገብቶ መሳተፍ ብቻ ሳይሆን ከምድብ ፉክክር ባሻገር ለግማሽ ፍፃሜ በመድረስ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ ከ10 ወራት በኋላ ሞሮኮ ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ የሚያልፉ 15 ቡድኖችን ለመለየት ለሚካሄደው ማጣርያ የምድብ ድልድሉ ነገ በካይሮ ከተማ ይወጣል፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ለምድብ ድልድሉ  በቀጥታ የደረሱትን 21 አገራት እና  በቅድመ ማጣርያ ካለፉት አገራት ጋር በመቀላቀል ከእጣ አወጣጡ በፊት በአራት ማሰሮዎች በመመደብ  አሳውቋል፡፡ ከ31 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ያለቅድመ ማጣርያ ለምድብ ማጣርያ ውድድር  የበቃችው ኢትዮጵያ በማሰሮ 3  ከቤኒን፣ ከአንጎላ፣ ከኒጀር፣ ከዚምባቡዌ፣ ከሞዛምቢክ፣ ከማላዊ፣ ከብሩንዲ፣ ከላይቤርያ እና ከሱዳን ጋር ትሆናለች፡፡ በማሰሮ 1 የሚገኙት ናይጄርያ፣ ቡርኪናፋሶ፣  ኮትዲቯር፣  ቶጎ፣  ማሊ፣  ደቡብ አፍሪካ፣  ኬፕቨርዴ ፣  ዲሪ ኮንጎ፣  ዛምቢያ፣  ቱኒዚያ እና ጋና ፤በማሰሮ ሁለት ግብፅ፣  ሊቢያ፣  አልጄርያ፣  ሴኔጋል፣  ካሜሮን ፣ ጊኒ፣  ሴራልዮን፣  ጋቦን፣  ኡጋንዳ ፣ ኮንጎ ኪንሻ እና ማዕከላዊ አፍሪካ፤ እንዲሁም በማሰሮ 4 ቅድመ ማጣርያ ያደረጉት አገሮች ተመድበዋል፡፡ ለ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ  የሚደረገው  ምድብ ማጣርያ  ከ5 ወራት በኋላ ሲጀመር የምድብ ማጣርያው  28 ብሄራዊ ቡድኖች በሰባት ምድቦች ተደልድለው በሁለት ወራት ውስጥ እያንዳንዳቸው 6 የደርሶ መልስ ጨዋታዎች በማድረግ የማለፍ እድላቸውን ይወስናሉ፡፡ በማጣርያው ሂደት ከሰባቱ ምድቦች አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ የሚያገኙት 14 ቡድኖች በቀጥታ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፋቸውን ሲያረጋግጡ፤ ከሁሉም ምድቦች በምርጥ ሶስተኛነት የሚያልፈው 15ኛው ቡድን ይሆናል፡፡ ሞሮኮ በአስተናጋጅነቷ 16ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ቡድን ሆና በቀጥታ ታልፋለች፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ2015 እኤአ ለሚደረገው አፍሪካ ዋንጫ ለመብቃት ቢያንስ እስከ 12 ሚሊዮን ብር በጀት እንደሚያስፈልገው ለመገመት ተችሏል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ለብሄራዊ ቡድኑ ይህን በጀት ለሟሟላት ከቴሌቭዥን ስርጭት መብት፤ ከስታድዬም ትኬት ሽያጭ፤ ከተለያዩ የስፖርት ቁሳቁሶች ሽያጭ እና ከስፖንሰርሺፕ ድጋፎች ከሚያገኛቸው ገቢዎች ባሻገር  ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፎችን ከመንግስት እና ከሌሎቹ የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ማግኘት ይጠበቅበታል፡፡
ለታዳጊ እና ወጣት ተጨዋቾችና ውድድራቸው አበረታች  ትኩረት በፌደሬሽን
በአውሮፓ ደረጃ ልምድ የመቅሰም ፕሮጀክት በማርያኖ ባሬቶ
ብሄራዊ ቡድን ብቻውን መቆም የለበትም ያሉት የእግር ኳስ  ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ፤ ዋና አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ከክለቦች፤ ከሀ-17 እና ሀ-20 ብሄራዊ ቡድኖች ጋር ተቀናጅተው እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡ ባለፉት 2 ዓመታት በዋናው ብሄራዊ ቡድን ከተፈጠረው መነቃቃት በኋላ ስልጣኑን ከያዘ መንፈቅ  እንኳን ያልሆነው የእግር ኳስ ፈደሬሽን ዘላቂ እድገት ለማስመዝገብ በታዳጊ እና ወጣት ተጨዋቾች ላይ መሥራት፣  እነሱንም ለፕሮፌሽናል ደረጃ ማብቃት እና ተተኪ ማድረግ ያስፈልጋል በሚል አቅጣጫ በመስራት ጉልህ እርምጃዎችን እንደወሰደ ይታወቃል፡፡ በዚህ መሰረትም ከ20 ዓመት በታች እና ከ17 ዓመት በታች ዕድሜ ያላቸው ብሔራዊ ቡድኖች በብሄራዊ ፌደሬሽኑ የተዋቀሩ ሲሆን በክለቦች ከ17 ዓመት በታች ውድድር በተቃና ሂደት ላይ ነው፡፡
በታዳጊ እና ወጣት ብሄራዊ ቡድኖች ኢትዮጵያውያን ሙያተኞች እንዲሰሩም ተደርጓል፡፡ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በአሠልጣኝ ወንድማገኝ ከበደ በመሰልጠን ላይ የሚገኝ ሲሆን ወደ አፍሪካ ወጣቶች እግር ኳስ ዋንጫ እያደረገ ያለውን ማጣርያ ጨዋታ ወደ ሲሸልስ አምርቶ 2ለ0 አሸንፎ መልካም አጀማመር አሳይቷል፡፡  
ሰሞኑን ደግሞ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ   ከ17 ዓመት በታች ላለው ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን የዋና አሠልጣኝ ቅጥር ማድረጉን አስታውቋል፡፡ ለሃላፊነቱ የተመረጡት የቀድሞው የፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ዳይሬክተር  ኢንስትራክተር ዮሐንስ ሳሕሌ ናቸው፡፡  ማርያኖ ባሬቶ በተለይ በወጣቶች ላይ በመስራት እግር ኳሱ ለእድገት በሚያመች መሰረት ላይ እንዲቀመጥ እና እንዲሻሻል ፍላጎት አላቸው፡፡  የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በዋና አሰልጣኝነት ከመምራት ጎን ለጎን የታዳጊ እና ወጣት ቡድኖችን በመከታተል፤ በየጊዜው የሚመረጡ ወጣቶችን ወደ አውሮፓ ትልልቅ ክለቦች የሚወስዳቸውን አቅጣጫዎች እንደሚዘረጉ ቃል የገቡት ዋና አሰልጣኙ ፤  ከፖርቱጋሉ ስፖርቲንግ ሊዝበን ፕሬዝዳንት ጋር በስልክ ተነጋግረው የክለቡ አካዳሚ ለኢትዮጵያን እግር ኳስ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ  መሆናቸውን ገልፀውልኛል ብለዋል፡፡ በዚህ እቅዳቸው መሰረት የተመረጡ የኢትዮጵያ ወጣት ተጨዋቾችን ወደ ስፖርቲንግ ሊዝበን አካዳሚ በየጊዜው በመላክ 1 ወር እና ከዚያም በላይ ካምፕ ገብተው ስልጠና እንዲያገኙ እና ልምድ እንዲቀስሙ ለማድረግ እሞክራለሁ ይላሉ፡፡ በዓለም እግር ኳስ ከሚታወቁ ምርጥ የእግር ኳስ አካዳሚዎች አንዱ ከሆነው የፖርቱጋሉ ክለብ ስፖርቲንግ ሊዝበን አካዳሚ መውጣታቸውን ማርያኖ ባሬቶ  በማስታወስ አካዳሚው ታላላቆቹን የፖርቱጋል ተጨዋቾች እነ ልዊስ ፊጎ፤ ሲሞን ሳብሮሳ፤ ሊውስ ናኒ እና ክርስትያኖ ሮናልዶን ያፈራ ነው ፡፡ በአሰልጣኝነት በሰራሁባቸው አገራት ለወጣት ተጨዋቾች የፕሮፌሽናል እድገት አስተዋፅኦ የነበራቸውን ስራዎች በትኩረት አከናውኛለሁ ያሉት ማርያኖ ባሬቶ፤ በጋና ቆይታቸው ወቅት በአሁኑ ወቅት አለም አቀፍ እውቅና ያላቸውን እነ ማይክል ኤሲዬን፤ አሳሞሃ ጊያን እና ሱሊ ሙንታሪን ወደ ዋናው ቡድን በመቀላቀል ስኬታማ ማድረጋቸውንም ገልፀዋል፡፡ በሌላ በኩል በቆይታቸው ኢትዮጵያዊ እግር ኳስ አሰልጣኞች የሙያ ደረጃቸውን የሚያሻሽሉበትን ሁኔታ ፈጥረው ፤ በተለያዩ የአውሮፓ ክለቦች ተወስደው ወቅታዊ የስልጠና እውቀት እንዲቀስሙና የልምድ ልውውጥ እንዲያገኙ እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡
ማርያኖ ባሬቶ በአፍሪካ ባላቸው ልምድ ተማምነዋል፤ ስለጋና ታሪካቸውም ይናገራሉ
የ57 ዓመቱ ማርያኖ ባሬቶ በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የፕሮፌሽናል አሰልጣኝነት ፍቃድ አላቸው፡፡ እግር ኳስ በከፍተኛ  ደረጃ ተወዳጅ በሆነባቸው ፖርቱጋል፤ ራሽያ እና ጋና ላለፉት 10 ዓመታት በቆዩበት በስራ ዘመናቸው በብሄራዊ ቡድንና በክለብ ደረጃ በዋና እና በረዳት አሰልጣኝነት ከፍተኛ ልምድ አካብተዋል፡፡ የአካል ብቃት ኤክስፐርት ሆነውም አገልገለዋል፡፡  
ዋና አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ በአፍሪካ ባላቸው ልምድ ከፍተኛ መተማመን እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በወጣትነታቸው በሞዛምቢክ ለ7 ዓመታት  መኖራቸውን እየገለፁ ፤ የጋና ብሄራዊ ቡድኑን በማሰልጠን  በኦሎምፒክ መድረክ የነበራቸውን ተሳትፎ እና ከዚያም ቡድኑን በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ እንዲያልፍ ማድረጋቸውን እንዲሁም  በአንጎላም ክለብ በመስራት በቂ ልምድ እንዳላቸው ጠቃቅሰው  በስፖርቱ ዙርያ  ብዙ ጓደኞቻቸው አፍሪካውያን በመሆናቸው  የአፍሪካን እግር ኳስ ጠንቅቀዉ እንደሚያዉቁ ይናገራሉ፡፡
ማሪያኖ ባሬቶ  የጋናን ብሔራዊ ቡድን በመምራት ያሳለፉትን የ9 ወራት ቆይታቸውን ስኬታማነት እና አወዛጋቢነትም በተመለከተ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ከ10 አመት በፊት የጋናን ኦሎምፒክ ብሄራዊ ቡድን በተረከቡበት ወቅት በማጣርያ ውድድር ዛምቢያ፤ ደቡብ አፍሪካ እና  አልጄርያን አሸንፈው በግሪክ አቴንስ ተዘጋጅቶ ለነበረው ኦሎምፒክ ማለፋቸውን ሲያስታውሱ ከኮሎምቢያ ጋር 2 እኩል እንዲሁም ፓራጓይን 2ለ1 በመርታት ከምድባቸው ቢያልፉም ያኔ በጁቬንትስ ይጫወት የነበረው ስቴፈን አፒያህ  በአምበልነት የሚመራው ቡድናቸው በጥሎ ማለፍ በጃፓን 1ለ0 ተሸንፈ ብለዋል፡፡
 ከኦሎምፒክ በኋላ ደግሞ የጋናን ብሔራዊ ቡድን በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በ2006 እኤአ ጀርመን ላዘጋጀችው ለዓለም ዋንጫ አብቅተዋል፡፡ በአጠቃላይ ማርያኖ ባሬቶ በጋና ቆይታቸው በማጣርያ፤ በዋና ውድድሮች እና በአቋም መፈተሻ 33 ያህል ጨዋታዎችን አድርገው ሽንፈት ያጋጠማቸው በአንድ ጨዋታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይሁንና ከጋና ብሄራዊ ቡድን ጋር ለሁለት ዓመታት የተፈራረሙትን ኮንትራት ስራዬን ለማከናወን የጋና እግር ኳስ ፌደሬሽን በቂ ትብብር አላደረገልኝም የሚል ምክንያት አቅርበው  በገዛ ፈቃዳቸው ለቅቀዋል፡፡ ይህን ተከትሎ የጋና እግር ኳስ ፌደሬሽን  ማርያኖ ባሬቶን ከስራቸው ስለመልቀቃቸው አስፋላጊውን ማስጠንቀቂያ ከ3 ወራት በፊት አላሳወቁኝም በሚል ለዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር  ፊፋ ክስ አቅርቦ 85 ሺ ዶላር የገንዘብ ቅጣት  በአንድ ወር እንዲከፍሉ ተወስኖባቸዋል፡፡ ከጋና ጋር የነበረኝ ቆይታ ሲቋረጥ የተላለፈብኝን ቅጣት ከኪሴ ከፍዬ ነበር ያሉት ማርያኖ፤ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር በሚኖረኝ ቆይታ   የማይመች አሠራር ካለ ለቅቆ የመሄድ መብቴ የተጠበቀ ነው ብለዋል፡፡

Read 1664 times