Saturday, 19 April 2014 12:34

የብርሃን ልክፍት - ከርዕሱና ከአንድ ዘለላ ግጥም መታከክ

Written by  ከአብደላ እዝራ
Rate this item
(2 votes)

የዮሐንስ ሞላ አንድ ዘለላ (ፍሬ የተንጠለጠለበት) ግጥሙን ለማንበብ እንደመንደርደሪያ ከርዕሱ ልጀምር፡፡ ለግጥሞቹ ስብስብ የቋጠረው ርዕስ “የብርሃን ልክፍት” ይመስጣል፡፡ ርኩስ መንፈስ አደረበት ለማለት ፈሊጡም “ጋኔን ለከፈው” ይላል። ለወገግታ፣ ለብርሃን መታመም - ርዕሱ ብቻውን የአንድ እምቅ ግጥም ፍካሬ ነው፡፡ ፍቅረኛው ስለ አሞካሸችው ፊቱ በራ ብንል፣ በፀዳል አሸበረቀም ነው፡፡ በራ (ሲጠብቅ ሲላላ) ቦግ የማለት እልህም አለ - ተመልጠውም ቢሆን፡፡ ሀገረኛም ሲቀኝ “እንካ ብላ አለችኝ ደረቁን እንጀራ/ እሷ በነካካው በራሰው ልትበላ” ውስጠቱ የግንኙነታቸው ሥነልቦናዊ ሽክረት፣ብርሃን ተሰስቶበት አድፍጧል፡፡ ብርሃን በጐም እኩይም ነው፡፡ ገመናን ይጋርዱታል እንጂ ለብርሃን አይሸጡትም፡፡ አይነስውሩ ፈጣሪን እየገረመመ እጁን ሲዘረጋ የተቀኘው ይመዘምዛል። “ያውና እዚያ ማዶ ብርሃን ያድላሉ/ አሁን ሮጬ ብሄድ አለቀ ይላሉ”
ይህም ልክፍት ነው፡፡
አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት ብለን
ፅልመቱን ዘለልን፤
መብራት የጠገበ መሬት የመሰለን፣
የረገጥነው ብርሃን
አዘቅት ሆኖ ዋጠን፡፡
----ብሏል ከብርሃን ሀይቅ ሲደፍቀን፤ ሰዓሊና ገጣሚ አገኘሁ አዳነ- “መልቲ ብርሃን” በሚል ግጥሙ፡፡
የብርሃን ልክፍት ገጣሚያን ብቻ ሳይሆኑ ደራሲያንም ይዘምሩለታል፡፡ አዳም ረታ በ”ግራጫ ቃጭሎች” ድንቅ ልቦለዱ፣ አብይ ገፀባህሪይው መዝገቡ መጐርመስ ጀምሮ የሴት ውበት ሲያጥወለውለው በብርሃን ልክፍት ነው የተገለጠው።
“…ወሰንን የወደድኳት በብርሃን ተከባ ስላየሁዋት ነው…የንፋስ መውጫ ከተማ ከሰማይ የወረደ የኮከብ ስብርባሪ ትመስል ነበር፡፡ ደመራው ከየቤታችን በችቦ ተሸክመን ባመጣነው እሳት ይለኮስና ይቀጣጠላል። የተከመረው እንጨት ፍምና አመድ እየሆነ እንደ ቅራሪ መቅጠን ሲጀምር ሰዎች ወደየቤታቸው ይበታተናሉ። ወሰን የለሽን ያየሁዋት ይህን ጊዜ ነበር። ወደ እሳቱ ተጠግታ ተቀመጠች፡፡ ቆመው የነበሩ ሰዎች ገለል ገለል ብለው ወሬ ጀመሩ። ከሁዋላዋ የአገር ልብስ የለበሱ ሴቶች የኖራ ግድግዳ መስለው ቆመው ነበር … ከበስተኋላዋ የቆመው ከነጠላና ከጋቢ የተሰራው የሰው ግድግዳ ሲፈርስ ተአምር ተፈጠረ፡፡ ያ የኖራ አገር ባህል ልብስ ግድግዳ ሰማይ ላይ የምትፎልል ድፍን ጨረቀ ከልሎ ኖሮአል። ታድያ ጠቆር ያለው የወሰን ጭንቅላት ድፍንዋ ጨረቃ መሐል ላይ የተቀመጠ መሰለ፡፡ ወሰን በስዕል ላይ የማያትን ትንሽ ማርያም መሰለችኝ፡፡ አፌን በለጠጥኩ፡፡ ትንፋሽ አጠረኝ፡፡ የደመራውን እሳት ትቼ እሷ ላይ ዐይኖቼን እንደ መዥገር አጣበቅሁ፡፡” ገፅ 71-72
ፍቅርና ብርሃን እንደ ልክፍት የደመቁበት ትዕይንት ዝርግ ግጥም አከለ፡፡ ለዚህም ነው አዳም ረታ “አንዳንድ ልጃገረዶች በብርሃን የተከበቡ ናቸው” የሚለው፡፡ ከረጅም የአያልነህ ሙላቱ ግጥም የሾለከ መንቶ፣ የዮሐንስን “የብርሃን ልክፍት” ገና ሳነብ ኮሰኮሰኝ - ሊያሸብር፡፡
አይቸግርም ወይ አይፈጥርም ወይ ጣጣ
ጨለማና ብርሃን በአንድ ላይ ከወጣ፡፡
የብርሃንም ብቻ ሳይሆን የጨለማም ልክፍት ያደፍጣል፡፡ ልክ ደበበ ሰይፉ “ፀሐይ ላያይ ተፈጥሞ” በሚለው ግጥሙ እንደተቀኘው፡፡
ምንም ዐልፎ ሒያጅ ፍቅርሽ ቢሆንበት፣ የሰንበሌጥ የሣር ባላ
ምንም ፈገግታሽ ቢጨልምበት፣ ምን እያደር ውልሽ ቢላላ
አዚምሽ እንደሆነ ወድቆበታል፣ አያልፋትም ያንቺን ኬላ፡፡
ይህን ውሉ እንደጠፋ ልቃቂት የተወሳሰበን ርዕስ ዮሐንስ ስለመረጠ፣ መጽሐፉን በጥሞና እንድናነብ ያስገድዳል፡፡ ጥያቄው ግጥሞቹ የስብስቡን ርዕስ “የብርሃን ልክፍት”ን ይመጥናሉ ወይ ነው፡፡ እያንኳኳ ከግዕዝም የተዋሳቸውን ቃላት አንድ ለእናቱን - ቴዎድሮስን - ተከታትሎ ህዝብ የተቀኘውን ስንኞች ተቀብሎ በግጥም የገራውን እንደ ባህላዊ ረቂቅ መንቶዎች (እሱ ዕንጉርጉሮ የሚለውን) ለመመጠን የፃፈውን በአንክሮ ማንበብ ይጠይቃል፡፡ ግጥሞቹ በርዕሱ ተደናግዘው አልመጠኑት ይሆናል፤ ወይም ለብርሃን ብቻ ሳይሆን የምጣድ ቂጥ ለመሰለ የተለበለበ ጥቁረት የተቀኛቸው ግጥሞች፣ የመጽሐፉን ርዕስ አደብዝዘውትስ ከሆነ? ኮስታራ ንባብ ይሻል፡፡ እዚህ የተነፈስኩት ግን ብዙ ወረቀቶች መሃል ተወሽቆ ሊዘነጋ የሚችል፣ አንባቢም በፈገግታ የሚያልፈው የቀላል ከባድ አጭር ግጥም ነው፤ ተራ ግጥም ግን አይደለም፡፡ አለወትሮው ቀለል ያሉ ቃላት ቢጠቀምም እሳቦቱ አልተሸረሸረም፡፡ “The vocabulary in this poem is very simple. It is the concepts that, perhaps, alarm some readers” አይነት፡፡ ተራ ቃላት እና ምርጊቱ የተላላጠ ትዕይንት፣ ለጠነነ ግጥም መከሰቻም ይበቃሉ፡፡ ከግጥሞቹ ስብስብ የተፈናጠረ “ፍርሃት”ን አብረን እናንብብ፡፡
            ፍርሃት
“ምነው ሁሉም ቀርቶ፤ ጫማሽን ባ‘ረገኝ
ከየደረሽበት፤ ቀድሜሽ እንደገኝ፡፡
ልልሽ አስብና፤ ለፍቅርሽ ውዳሴ
ኩነኔ፥ፀፀቱን… ትፈራለች ነፍሴ፡፡
ማን ያውቃል…? ጫማሽ ያረጀለት ምን ውስጥ እንደሚጣል?!
“አንዳንድ ጊዜ በውድም ሆነ በግድ ፍቅር ይይዘኛል፡፡ ይግረምህና የሚለማመጠኝን ወንድ ብዙዉን ጊዜ አልወድም፡፡ ኮስተር ሲልብኝ ይስበኛል፡፡ ሀይለኛ ወንድ እወዳለሁ፡፡” ትላለች የበዐሉ ግርማ ፊያሜታ፡፡ ይህች በፍቅር የከነፈላት፣ በግጥም ‹ፍርሀቱን› የተናዘዘላት ሴት፣ ማቅማማቱን መለስለሱን ስታጤን እንደ ፊያሜታ ከሆነች ተናጋሪው ከልቧ ሳይዘልቅ ይባክናል፡፡
ይህን አጭር ግጥም ምናልባት ያቀጠነው ስንኞቹ በጣም በተለመዱ ቃላት መተንፈሳቸው ነው፡፡ እነዚህ የተለመዱ ቃላት በነፍስ ወከፍ አያባንኑም፤ በየቀኑ ተፍቀዋል፡፡ ሻከር ደንደን ባለ አባባል ቢታገዝ፣ ቢያብቅ የግጥሙ ስነ ልቦናዊና ህይወታዊ ንዝረቱ በበለጠ ይደመጥ ይሆናል? ላይሆንም ይችላል፤ ስንኞቹ አባብጠው ተንከርፍፈው ካነካከሱስ? ዮሐንስ ሞላ “ሰም ወርቅ መጠፋፈር፣ ቅኔ መቀኘቱ/ ዝንቱ ውእቱ ከንቱ” በማለት ከሁለት ቋንቋ እያንኳኳ መግጠም የሚችል ነው፣ በቃላት አይታማም፡፡ ደበበ ሰይፉ አንዳንዴ በተራ ቃላት ይቀኛል፡፡
ዘመዴን ስስመው
ጉንጬ ቢሻክረው
እኔንም ሻከረኝ፤
ዕድሜ መለስለሱ ማብቃቱ ታወቀኝ፡፡
ሲል የጎነጎነው ምስል፣ የተናጋሪው ስጋት ይሁን ብስለት የተወሳሰበበት ገጠመኝ ይመስጠናል፥ የዕምቅነቱን ስንጥቅ እናሰላስላለን፡፡ ጥርሳቸው በረገፈ፣ በማይናከሱ ቃላት እንኳን ውብ ግጥም በመተት ሳይሆን፣ በምናብ መታኘኩን እናጤናለን፡፡
ተናጋሪው ፍርሀቱ ምንድነው? ከራሱ ጋር የሚያወጋ (ንባበ- አዕምሮ Soliloquy) እንጂ ከሚያፈቅራት ፊት ተገፎሮ ያነበበላት አይመስልም። ፍቅሯን ማወደስ ነው የሚሰቅቀው። ያልተንዛዛ ግጥም፤ ጥንካሬው ሥነ ልቦናዊ መብሰክሰክና ያልሰመረ ፍቅር ከዉስጡ ክፋት ሲቀፈቅፍ በሹክሹክታ ማስደመጡ ነው፡፡ እሷ ልቧ ተቆልፎ ለፍቅሩ ወከክ ተርከክ አለማለቷ፤ እሱም ህይወቱን በሌላ አቅጣጫ ለመቀየስ ጉዞ ጀምሮ የፃፈላት የስንብትና የሽንፈት ግጥም ይሁን አይሁን አለማወቃችን፤ ከገለጠው የሸሸገው ማደናገዙ ነው ውበቱ፡፡ ፍቅር ታደላለች ፍትህ ይጎድላታል እንዳንል የሴቷ ድምፅ አይሰማም፡፡ ዝምታዋ ግን ትዕግስት ዓለምነህ “የዝምታ ጩኸት” የምትለው አያዎነት-Paradox አላስተረፈም፡፡
ተስፋዬን ቆርጬ ፥ ብሄድ ሳላወራው፤ …
በዝምታዬ ውስጥ ጩኸቱ ተሰማው፡፡
ምናልባት ለዚህ ለከረፈፍ አፍቃሪ ተገልጦ ቢነበብ ነው፡፡ ሆኖም ተፈቃሪዋ ግጥሙ ውስጥ ትግዘፍ እንጂ፤ ሀቁ ግን ዮሐንስ ዝምታ ውስጥ አስምጧታል፡፡ ዝምታዋ ዮፍታሔ ንጉሴ እንደተቀኘው የጥሞና ነው፡፡
ሲመቸኝ ዝም ብል፥ ዝም ያልኩ መስሎታል
ሲታሰብ ነው እንጂ ዝም ማለት የታል
ገጣሚው የመለመለው ገፀ ባህሪ ተምታቶበታል፤ ጤነኛ አይመስልም፡፡ ለፍቅር ሰክኖ የእሷን ልብ ለማስገር መረቡን ከመዘርጋት ይልቅ አቅማማ ፥ ፍቅር ደግሞ ለእልኸኛ እንጂ ለተሸነፈ ወኔ፣ ለፈሪ ክንብንቧን አታወልቅም፡፡ እንዴት ጥራጊና እድፍ እየረጋገጠ የሚያልቅ ጫማዋን ለመሆን ይመኛል? እርጥብ ከንፈሮቿን፣ ጡት መያዣዋን ልሁን ቢል እንኳን ለፍቅርም ክብር ነው፡፡ በዐሉ ግርማ በ ‹ኦሮማይ› የጋዜጠኛውን እጮኛ ሲገልጣት፤
“ውብ ከንፈሮቿን አጣብቃ በመልቀቅ … ራሷን የምትስም ትመስላለች፡፡ አንዳንዴ ሲላት
ጡቷን ወጣ አድርጋ ትስማለች እንዳለው፡፡ እዚሁ መወሸቅን አይመኝም፡፡ ባላገሩ ይደፍራል፤
እንጀራና ወጥ ይበላልኛል
እንደ ሶስት ዓመት ልጅ ጡት ያሰኘኛል፡፡
የኛው ጫማን እንደ ቋንጣ አንጠልጥሎ ድመት ይመስል ይዘላል፡፡ ጫማዋን ሳይሆን ገላዋን የተመኘ ፍቅረኛ ቢሆን ኖሮ
ልልሽ አስብና፥ ለፍቅሽ ውዳሴ፤
ኩነኔ ፀፀቱን … ትፈራለች ነፍሴ፡፡
በማለት ሸሽት ባልወረረዉ፡፡ የሥጋና የነፍስ ቅጣት፤ ጸጸት ምን አመጣዉ?
ዝነኛው T.S. Eliot ረዘም ያለ ድንቅ ግጥም አለው <The Love Song of … Prufrock> የተባለ፡፡ የሱም አፍቃሪ - ፐሩፍሮክ- ዮሐንስ ሞላ እንደሚያደፋፍረው ተናጋሪ ፈሪና ተጠራጣሪ ነው፡፡ የዘመነኛ፤  በትምህርት የረገበውን ግለሰብ መብሰክሰክን መደናገርን (በፍቅር - በሴት ጉዳይ) የሰፈፈበት ነው፡፡ ሊያስጎበኛት የሚመኘው ርካሽ የመንደር አልቤርጎና አቧራ የለበሰ ምግብ ቤት “Is it perfume from her dress/that makes me so digrees?” እያለ በስጋት ይባዝናል፤ ለሚያዉድ ሽቶ ይናገራል፡፡ “I have measured out my life with coffee spoons” ካልጠፋ የኑሮ መለኪያ ህይወቱን በቡና ማንኪያ ያሰላል፤ አተላውን ባማሰለበት፡፡ ኢልየትም ዮሐንስም የቀረፁት አፍቃሪ የተደናገረ ኢ-ጀግና -anti hero- ስለሆነ የለመድነውን ባህርይ ይፃረራል፡፡ ይህ ዮሐንስ ያናዘዘው ገራገር የመሰለ አፍቃሪ ለሱ ካልሆነች፤  ካልሰመረለት ብትገጠጣብ ደስ ይለዋል፡፡
ማን ያውቃል …. ?
ጫማሽ ያረጀለት ምን ውስጥ እንደሚጣል?!
የውበት ዕድሜዋን በጫማ ማለቅ መጥኖ አኮማተረው፡፡ ቢሆንና አፍቅራው ጊዜን አብረው መቆረጣጠም ቢጀምሩ “ውበቷ በአጭር ወቅት ይላላጣል” በማለት ዛሬ ስለአጣት ብቻ ራሱን ያታልላል፡፡ “ከመጎዳት ተርፌያለሁ” እያለ ልቦናውን ይሸነግላል፡፡
እንኳን እሷን ማግባት ራሱን መግራት ተስኖታል፡፡ ደራሲ አበራ ለማ አንድን ምስል ለብዙ ቀናት እያጤነው ለመነጋገር ሲበቃ (ከስዕሉ ጋር) ስለፍርሀት ውብ ግጥም ይቀኛል፡፡ ሲጀምረው
ያ መረቡ ልቤ ረገበ እምቢ አለ
አንድ ራሱን ማስገር አቃተው ዋለለ፡፡
እያለ የግለሰቡ ስነ ልቦናዊ ገመና ይገፈፋል፡፡ የዮሐንስ አፍቃሪ አበሻ አበሻ አልሸት አለ፤ መጋጠም፤ መላተም ሳይሆን ተኮፍሶ መፍርጠጥ ተመቸው- ኢ-ጀግና ነውና በመንደራችን ያሉትን ጥቂቶቹን ይወክላል፡፡  “ፍርሃት” በስድስት ስንኞች የተዋቀረ ግጥም፣ የተናጋሪውን የመንፈስ ረግረግነት፣ ፍዝነት ለማንፀር በተራ፣ ወዙ በተመጠጠ ቃላት ተቀመመ፡፡ ፍቅር ያልተዋጣለት ዳግም ከእሷም ሆነ ከሌላ ሄዋን ንዝረቱን ከማባባስ፣ እንደ አሸናፊ ራሱን የማሞካሸት አባዜ ግለሰብን ሲያመክነው ነው ዮሐንስ መላ የተቀኘው፡፡ የሚያሳስበው ግን አፍቃሪ፤ ለሴቷ የተጋረደ ቂም ቁርሾ ያከማቸው ባለመፈቀሩ መሆኑ ነው፡፡ አንኳር ጉዳይ ቅስስ ባሉ ቃሉት እና በጠባብ ትዕይንት ግጥም አክሎ ሲቀልጥና ሌላ ቅርጽ ሲያበጅ ተስተውሏል፡፡
የግጥሞቹ ስብስብ አብይ ርዕስ “የብርሃን ልክፍት” በየስንኞች ተዛምቷል፡፡ “ከአድማስ ባሻገር” ጨለማ ውበትን ሲያደበዝዝ ይገልጣል፡፡
“--- በስተቀኝ ካለው ግድግዳ ላይ የተሰቀለው በህብረ ቀለማት ስለቀለማት የተሰራው ስዕል ብርሃን በማጣቱ የቅኔው ውበት ጠፍቷል፡፡”
ለዚህም ነው ደበበ ሠይፉ፣ ዮሐንስ ሞላ፣ አለማየሁ ገላጋይ…ብርሃን ብርሃን የሚሉት፡፡ የሽፋኑ ስዕል የአንድ አፍሪካዊ ጣት ሲቀጣጠል፣ ጨለማ ሲገረሰስ ቢደምቅም፣ አንድ የነጭ መዳፍ - ምዕራባዊ - ክብሪት መጫሩ የአንድምታ አምባጓሮ ሊያያይዝ አቅም አለው፤ ለዛሬ ግን “ፍርሃት”ን መወልወሉ በቂ ነበር፡፡

Read 3693 times