Saturday, 15 March 2014 13:27

የዩኒቨርስቲው የታሪክ ትምህርት ክፍል ተግዳሮቶች

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(1 Vote)

ታሪክ ትምህርት ክፍል የሚማርም ሆነ የሚሰራ ከታሪክ ጋር በተያያዘ ሊያከናውን ላቀዳቸው ተግባራት መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት አለመቻሉ፣ ተማሪዎችን ወደ ታሪክ ትምህርት ክፍል እንዳያቀኑ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሏል፡፡ ለታሪክ ፀሐፍት የሚከለከሉት መረጃዎች፤ አይጦች እንዲጫወቱበት መፈቀዱም እንደ ቅሬታ ቀርቧል፡፡

  • የመዘጋት ስጋት እያንዣበበበት 50ኛ ዓመቱን አክብሯል
  • ታሪክ እንደ ፖለቲካ መታየቱ ችግር ፈጥሯል

 የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ምሥረታ 50ኛ ዓመቱን ምክንያት በማድረግ የካቲት 21 እና 22 ቀን 2006 ዓ.ም ባሰናዳው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ 25 የጥናት ወረቀቶች የቀረቡ ሲሆን   የመጨረሻው የጥናት ፅሁፍ  የታሪክ ትምህርት ክፍሉ ባሉበት ተግዳሮቶች ዙሪያ አወያይቷል። “ይህን ያህል የታሪክ ባለሙያዎች በዚህች አገር አሉ ወይ?” በተባለበት መድረክ ማጠናቀቂያ ላይ ነበር የታሪክ ትምህርት ክፍሉ የመዘጋት አደጋ እንደተጋረጠበት የተጠቆመው፡፡
በአገሪቱ ከሚገኙት 32 ዩኒቨርስቲዎች፣ 19ኙ የታሪክ ትምህርት ክፍል አላቸው፡፡ እነዚህን የትምህርት ክፍሎች በአንድ የሚያሰባስብ ማህበር ለመመሥረት የደብረ ብርሃንና የባህር ዳር ዩኒቨርስቲዎች ነበሩ በቅድሚያ እንቅስቃሴ የጀመሩት፡፡ የማህበሩ ዓላማም  ታሪክ የራሱ የሆነ ዲስፕሊን እንዳለውና ሙያው ሳይንሳዊ መሆኑን ማሳወቅ፣ ሀሰተኛ ዘገባዎችን በምክንያታዊነት በማረጋገጥ ማሳየት፣ ታሪክ ፀሃፍትም ሆኑ ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርስቲዎች … በታሪክ ዙሪያ ሲሰሩ  መከተል ያለባቸውን  መመሪያዎች  መቅረጽ ናቸው።
ይህንን ጅማሬ በተሻለ ሁኔታ ለማስቀጠል በታሪክ ትምህርት ክፍል ያሉት ችግሮች ምንድን ናቸው? በሚለው ዙሪያ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
የአገሪቱና የሕዝቡ ታሪክ እንደሚገባው አልተፃፈም
ይህንን ታሪክ ማን ነው መፃፍ ያለበት?
ባለሙያ ባልሆኑት ብቻ ሳይሆን በታሪክ ባለሙያዎች ተጽፈው በቀረቡ መፃህፍትም መረጃን የማጣረስ፣ የማጋነንና የአንዱን ታሪክ ለሌላው የመስጠት ነገር ይታያል፡፡
ሕዝቡ ውስጥ ያለው ታሪክን የመፈለግ ስሜት የተረዱ ጋዜጦችና መፅሄቶች ለታሪክ ቦታ እየሰጡ ነው፡፡
 እንዲህም ሆኖ  ችግሩን ቀርፎ፣ ለተሻለ ለውጥና ዕድገት መሠራት ባለበት በዚህ  ሰዓት የታሪክ ትምህርት ክፍሉ በተማሪ እጦት አደጋ ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በክልል ዩኒቨርስቲዎች ሻል ያለ ነገር ቢኖርም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ወደ ታሪክ ትምህርት ክፍል የመግባት ፍላጎት ያጡበት ምክንያት ምንድነው? የሚለው ጥያቄ የቀሰቀሰው ውይይት፤ የችግሩ ምንጭ የት ነው? ከተማሪዎቹ? ከመምህራኑ?  ከቋንቋ ችግር? የ70/30 የትምህርት ፖሊሲ?… በሚሉና ከሌሎች እይታዎች አንፃር ሃሳቦችን አንሸራሽሯል፡፡
ችግሩን የፈጠሩት ምክንያቶች ዘርፈ-ብዙ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ ታሪክ እንደ ሳይንስ ሳይሆን እንደ ፖለቲካ መታየቱ አንዱ ችግር ነው፡፡ የዘርፉ ምሩቃን በሆኑና ባልሆኑ ታሪክ ፀሐፊዎች ተዘጋጅተው የሚቀርቡት መፃሕፍት “እኔን ይወክላል/አይወክልም” የሚል ጭቅጭቅ ሲነሳ የሚታየው በዚህ ምክንያት ነው ተብሏል። እስካሁን የተፃፈው “የሰሜንና የክርስቲያን” ታሪክ ነው የሚባለውም ፖለቲካን መሠረት ያደረገ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ በአገሪቱ የታሪክ ትምህርት ክፍል ያላቸው ዩኒቨርስቲዎችም “ካሪኩለም የመጋራት ችግር የለብንም ወይ?” የሚል ጥያቄ አንዳቸው ለሌላኛው የሚያቀርቡትም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ነው። ተማሪዎች እንዲማሩበት የቀረበላቸውን መጽሐፍ አይተው “የእኛስ ታሪክ የታለ?” ብለው የሚጠይቁት ለዚህ ነው፡፡ ለ32 ዩኒቨርስቲዎች መከፈት መነሻ የሆነው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፤ “ራሱን ከእኛ ያገለለ መስሎ ይሰማን ነበር” የሚል ወቀሳ ቀርቦበት ነበር፡፡
አንዱ ላዘጋጀው መጽሐፍ ሌላው አካል ተነስቶ ምላሹን በመጽሐፍ የሚያሳትመው የፖለቲካ ትኩሳት በወለደው ስሜት እንጂ በሳይንሳዊ ምክንያታዊነት አይደለም ተብሏል፡፡ የባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች፤ የሕዝብ ታሪክ ለመፃፍ በሚያደርጉት ጥረትም የሙያ ዲሲፕሊን የመጠበቅ ችግር እንደሚታይ ተጠቁሟል። የታሪክ ትምህርት ክፍል በተማሪ ድርቅ እንዲመታ አስተዋጽኦ ካደረጉት ነገሮች ሌላኛው የ70/30 ትምህርት ፖሊስ በተማሪዎች ላይ የፈጠረው ስጋት እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን ይሄም “ተማሪዎች ምን ባጠና ነው ሥራና ጥሩ ገንዘብ የምናገኘው?” የሚል ጥያቄ እንዲያነሱ ስላስገደዳቸው ዲፓርትመንቱን እንዳይመርጡ አድርጓቸዋል” ተብሏል፡፡
የታሪክ ትምህርት ክፍል መምህራንም ለችግሩ አስተዋጽኦ አድርጋችኋል የሚል ትችት ቀርቦባቸዋል። አንድ ተሳታፊ በሰጡት አስተያየት፤ የዛሬ 18 ዓመት ለአድዋ ድል 100ኛ ዓመት በኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር በኩል የተዘጋጀ ታሪክ ከመታተሙ በፊት የዘርፉ ባለሙያዎች እንዲያዩላቸው ጥረት ቢያደርጉም እንዳልተሳካላቸው ጠቁመዋል፡፡ በታሪክ ትምህርት ክፍል የሚማርም ሆነ የሚሰራ ከታሪክ ጋር በተያያዘ ሊያከናውን ላቀዳቸው ተግባራት መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት አለመቻሉ፣ ተማሪዎችን ወደ ታሪክ ትምህርት ክፍል እንዳያቀኑ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሏል፡፡ ለታሪክ ፀሐፍት የሚከለከሉት መረጃዎች፤ አይጦች እንዲጫወቱበት መፈቀዱም እንደ ቅሬታ ቀርቧል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ስር ያለውና ግቢ ገብርኤል አካባቢ ባለው የፀሐፊ ትዕዛዝ ወልደ መስቀል ታሪኩ ቤት ውስጥ የሚገኘውን ሰነድ ማየት ፈልገው ከ6 ወራት በላይ ቢመላለሱም የሚያስተናግዳቸው እንዳጡ አንድ ተሳታፊ ተናግረዋል። ለችግሩ በመፍትሔነት የቀረቡት ሀሳቦችም ብዙ ነበሩ። የታሪክ ትምህርት ክፍልን ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋምነት እንዴት ማሸጋገር ይቻላል? ተማሪዎች የአገርና የሕዝባቸውን ታሪክ ከታች ጀምሮ እንዲያውቁት ምን ይደረግ? ስለ ታሪክ በሕዝቡና በምሁራኑ መካከል ያለውን ልዩነት ማስታረቅ የሚቻለው እንዴት ነው? የታሪክ ባለሙያዎችስ ዕውቀትና ችሎታቸውን በምን መልኩ ያሻሽሉ? ለዚህ ተግባራዊነትስ የአጭርና የሩቅ ጊዜ እቅዶቻችን ምን ይሁኑ? የሚሉ ጥያቄዎች ተሰንዝረዋል፡፡
ታሪክ ዘርፈ ብዙ ሙያ ነው፡፡ የሳይንስ፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የወታደራዊ … እየተባለ በተለያዩ ክፍሎች ይመደባል፡፡ የታሪክ ባለሙያዎች ማህበር ቢኖርና ለእያንዳንዱ የታሪክ ክፍል ዲፓርትመንት ተቋቁሞለት ታሪኩ ቢፃፍ ተገቢና ተአማኒ ይሆናል፡፡ እንዲህ ባለመሆኑ ምክንያት አሁን እየተፃፈ የሚቀርበው ታሪክ ፖለቲካዊ ሆኗል። ፖለቲካ ውስጥ ደግሞ  በፍቅር መስራት ብዙ አይጠበቅም ተብሏል፡፡
“ሁሉም የሚቀበለው ታሪክ ማግኘት ቢያስቸግርም የሚቻልበት ዕድል ግን አለ፡፡ እስከ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ታሪክ ወደ ሰሜን ያደላ ቢሆንም በራሱ ግን ችግር አይደለም፡፡ የታሪክ ታላቅነት የተለያዩ ጉዳዮችን ይዞ ለቀጣዩ ትውልድ መልዕክት ማስተላለፍ ማስቻሉ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ታሪክን ጥንቁቅ ሆኖ ማዘጋጀትን ይጠይቃል፡፡ በመረጃ አጠቃቀምም ብልህ መሆን ያስፈልጋል። ለመፍረድ አለመፍጠንና አተረጓጎም ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግን ይጠይቃል፡፡ ታሪክ ባለቤት ሊኖረውም የግድ ይላል፡፡ መንግሥት ታሪክን በፍርሀት ነው የሚያየው፡፡” ስለዚህም መደራጀት አለብን የሚሉ ሀሳቦች ተሰንዝረዋል፡፡
“ለታሪክ ሁሉም ሰው ጆሮውን ይከፍታል። የአገር መሪዎች ችግር ሲገጥማቸው ወደ ታሪክ ትምህርት ክፍል መረጃ ፍለጋ ሮጠው የሚመጡት የታሪክን ጥቅም ስለተረዱት ነው፡፡ ታሪክን ሕዝቡ፣ መንግሥት፣ ጋዜጠኞች፣ ታሪክ ፀሐፊዎች … ለመቆጣጠር የሚፈልጉትም ለዚህ ነው፡፡ ታሪክ አፃፃፋችን ፖለቲካው ላይ ትኩረት ስለሚያደርግ ነው እንጂ ተደራሽነታችንን ብናሰፋ አሁን የተከሰተውን ችግር ለመቅረፍ እንችላለን” ያሉም አሉ፡፡
“አገሪቱና ሕዝቧ ጥንታዊ ናቸው፡፡ ታሪኩ መጠበቅ አለበት፡፡ ቀድሞ የተፃፈው ታሪክ ችግር አለበት ማለት የታሪክ ትምህርት መሰጠት የለበትም የሚያስብል አይደለም፡፡ በታሪክ ምሁራን መሐል ግን የጋራ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ ስምምነቱ ካለ ችግሩን በሂደት ማስተካከል ይቻላል፡፡ በየትም አገር ቢሆን አሁን እኛ የገጠመን መሰል ችግር ይከሰታል። እነሱ ግን ለጋራ ዓላማ አብረው በመስራት ለውጥ አምጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ፤ በ50ኛ ዓመት የታሪክ ትምህርት ክፍሉ ሲምፖዚየም ላይ በቀረበው መልኩ ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ አሁን እየተነጋገርን ያለነው በዩኒቨርስቲዎች ያሉ በ100ሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎችን እንዴት መድረስ እንዳለብን ነው” በሚል የቀረቡ ሀሳቦችም ነበሩ፡፡
የታሪክ ትምህርት ክፍል በገጠመው ችግር ዙሪያ እንዲህ ዓይነት አስተያየቶች፣ ጥያቄዎችና ምላሾች ከተንሸራሸሩ በኋላ ለችግሩ እልባት ለማበጀት ኮሚቴ አዋቅሮ መንቀሳቀሰ መፍትሔ እንደሆነ በመታመኑ በቀድሞው ኮሚቴ ውስጥ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም ተካትቶ፣ የሚደርስበትን ውሳኔ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚያሳውቅ ተገልጿል፡፡  

Read 1974 times