Saturday, 08 March 2014 13:45

“አዝማሪን በቅራሬ ማባበል ነው የሚባልበት ዘመን አክትሟል”

Written by  ወልደመድህን ብርሃነመስቀል
Rate this item
(1 Vote)

      “አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ በሕይወት ቢኖር ሙዚቃ የጀመረበትን 56ተኛ ዓመት ያከብር ነበር። እኔ ሙያው ላይ ከተሰማራሁ 52 ዓመታትን አስቆጥሬያለሁ፡፡ ከሊስትሮ ሥራ ጀምሬ፣ በምግብ ቤት ውስጥ ተቀጥሬ ሰርቻለሁ፡፡ በአናፂነት ሙያ ላይ የተሰማራሁበት ጊዜ ነበር፡፡ በድምፃዊነትም በትምህርት ቤት፣ በጃንሜዳ፣ በሚካኤል፣ በጊዮርጊስና በሩፋኤል አብያተ ክርስቲያናት አገልግያለሁ፡፡ አሁንም በየመድረኩ በሙያዬ በመሥራት ላይ እገኛለሁ፡፡
“እኛ በቀዳሚነት መንገድ ጠርገን ተስፋ የሚጣልበት አሁን ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ዛሬ በርካታ ድምፃዊ፣ ግጥምና ዜማ ደራሲ፣ ሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾች … አሉ፡፡ ሙያውና ባለሙያው ተከብሯል፡፡ በቀድሞ ዘመን ‘አዝማሪን በቅራሬ ማባበል ነው’ በሚል በንቀት እንታይ ነበር፡፡ ሙያውን በተመለከተ በዚህ ዘመን ከሚታዩ ጉድለቶች ውስጥ እንደ ቀድሞ ዘመን መድረክ ሞልተው የሚታዩ ትላልቅ ኦርኬስትራዎች አለመኖራቸው አንዱ ነው፡፡
“ሙያውንና ባለሙያውን ማሳደግ ዓላማ ያደረገ የሙዚቀኞች ማህበር የማቋቋም ጥረት ማድረግ ከተጀመረ ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ብዙ አፈናና ጫናም ነበረብን፡፡ ማህበር እንዲቋቋም ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ፣ ሻለቃ ጽጌ ፈለቀ … የመሳሰሉ ሰዎች ብዙ ደክመዋል፡፡ ለዚሁ ዓላማ በምድር ጦር፣ በፖሊስ ሠራዊት፣ በሀገር ፍቅር፣ በራስ ቴአትር … በነበሩ የሙዚቃ ክፍሎች የተደረገውም ድካም ቀላል የሚባል አልነበረም፡፡
“የዚያ ጅማሬና ጥረት ውጤት ሆኖ አሁን በአዲስ መልክ ተቋቁሞ መሥራት የጀመረው የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር ትልቅ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አያለሁ፡፡ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ባለሙያዎች ከየት እንደተነሳን፤ ምን መልካም ዕድልና ችግር እንደገጠመን፤ በሙያው ውስጥ እነማን እንደነበሩ፤ አሁን ቅርስ ሆነው የሚገኙት የሙዚቃ ሥራዎችን ለማቀናበር የተከፈለው ድካም ምን ይመስል እንደነበር … ለማስተዋወቅ ማህበሩ ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡ ተተኪዎችንም ለማፍራት የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ዛሬ ያስመረቃቸው ወጣቶች ያቀረቧቸው ሥራዎች ምስክር ናቸው። የተስፋ ብርሃን እየታየ ነው፡፡ ተስፋው ቀጣይ እንዲሆን እንተባበር፡፡”
የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር ከሰላም ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ባዘጋጁት “የአርባን አዲስ ፕሮጀክት የአንድ ዓመት ወርክሾፕ ስልጠና” ተከታትለው ያጠናቀቁ 30 ሰልጣኞችን ለማስመረቅ የካቲት 22 ቀን 2006 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አዳራሽ በተሰናዳው ፕሮግራም የተጋበዘው አርቲስት ማህሙድ አህመድ ነበር ከላይ የቀረበውን ንግግር ያደረገው፡፡
አዘጋጆቹ በጠበቁት መጠን ብዙ ሰው ባይመጣም ሥራ፣ ሥምና ታዋቂነታቸው ከፍ ብሎ የሚታይ ታላላቅ እንግዶች ግን ነበሩ፡፡ ፕሮፌሰር አብይ ፎርድ፣  ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋ፣ አርቲስት መርዓዊ ስጦት፣ ጋሽ ተስፋዬ አበበ፣ አርቲስት ሃይማኖት ዓለሙ … የመሳሰሉ እንግዶች በተገኙበት የዕለቱ የክብር እንግዳ ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋም ንግግር አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር የሙዚቃ ዝንባሌ ያላቸው ወጣቶችን አሰልጥኖ የሙያ ሰው ለማድረግ ያሳየው ጥረት የሚደነቅ ነው ያለው ግርማ ይፍራሸዋ፤ “ይህ ጥረት የአገራችንን ሥነ ጥበብ ያሳድጋል፤ ጥበብ የሚያልቅ ስለሆነ ወጣቶች ዕውቀታቸውን በትምህርትና ስልጠና ለማሳደግ መጣር ይኖርባቸዋል፡፡ የጥበብ ጥማታችሁን ለማርካት ዕውቀት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ማህበሩ የጀመረው እንዲህ ዓይነት ተግባር ከግቡ እንዲደርስ እኔም አቅሜ የፈቀደውን ለመርዳት ፈቃደኛ ነኝ” ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር ፕሬዚዳንት አርቲስት ዳዊት ይፍሩ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር የአመሠራረት ታሪኩ ረጅም መሆኑንና በቅብብል ለዛሬ መድረሱን አመልክተው፣ የነበረባቸው የቢሮ ችግር አሁን መቀረፉን ገልፀዋል። የሙዚቃ ሙያና ባለሙያ አገርና ሕዝብን እያገለገሉ ብዙ ዘመናትን አስቆጥረዋል ያሉት አርቲስት ዳዊት ይፍሩ፤ ማህበራቸው የሙዚቀኞችን ሥራና የሕይወት ታሪክ እንዲታወቅ ከማድረግ ባሻገር ተተኪ ወጣቶች ለማፍራት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
“የማህበርና የባለሙያዎችን ታሪክ በድረ ገፃችን በማስፈር ለሕዝብ አቅርበናል፡፡ ብዙ ታላላቅ ሥራዎችን ያከናወኑ አንጋፋ ባለሙያዎች በእርጅና ምክንያት መድረክ እያጡ ነው፡፡ እነሱን ለማገዝ የነደፍነው እቅድ አለ፡፡ ወጣቶቹ ከአንጋፋዎቹ እንዲማሩ ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡ ይህንን ዓላማችንን በማገዝ ረገድ ሰላም ኢትዮጵያ ባለፉት 3 ዓመታት አብሮን እየሰራ ነው፡፡” ብለዋል፡፡
ዛሬ ያስመረቅናቸው 30 ወጣቶች በሙዚቃው ዓለም ሲሰማሩ ሙሉ የሚያደርጋቸውን የተለያየ ዕውቀት እንዲያገኙ አድርገናል ያሉት የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር ፕሬዚዳንቱ፤ ስለ ቅጂና ተዛማጅ መብቶች ምንነት፣ በሕገ ወጥ መንገድ ስለሚባዛው ካሴትና ሲዲ ስለ ስቱዲዮ ቴክኒክ፣ ስለ መሠረታዊ የኮምፒዩተር አጠቃቀም፣ ስለ ሙያ ሥነ ምግባር … ስልጠና እንደተሰጣቸው አመልክተዋል። ሰልጣኞቹም በዕለቱ የተለያዩ ታዋቂ ድምፃዋያንን ሥራዎች በማቅረብ የምረቃ ሥነ ስርዓቱን ከማድመቃቸውም ባሻገር የተማሩትንም በተግባር አሳይተዋል፡፡  

Read 2469 times