Saturday, 08 March 2014 13:37

ኒድልማንን እንደማስታውሰው Remembering Needleman

Written by  ደራሲ - ውዲ አለን ትርጉም - ዮሐንስ ገለታ
Rate this item
(1 Vote)

       አራት ሳምንታት ቢቆጠሩም የሳንዶር ኒድልማን ሞት ለማመን ከብዶኛል፡፡ የአስከሬን ማቃጠል ስነ-ስርዓቱ ላይ ስገኝ በወንድ ልጁ ጥያቄ መሰረት ሀባብ ይዤ ነበር፡፡ ሀሳቤ ግን እዚያ አልነበረም፡፡ በስፍራው የተገኘነው ብዙዎቻችን ለቀስተኞች የየራሳችንን ህመም ከማድመጥ በቀር ሌላ ሌላውን ሀሳብ ረስተን ነበር፡፡
ኒድልማን አስከሬኑ ስለሚቃጠልበት መንገድ እያቀደ በማሰላሰል ተጠምዶ ነበር፡፡ አንዴ እንዲያውም ያለኝን አልረሳውም፡፡ “ከመቀበር ብቃጠል ይሻለኛል፤ ቅዳሜና እሁድን ከሚስቴ ጋር ከማሳልፍም…”፡፡ በመጨረሻም እንዲያቃጥሉት ወሰነና አመዱን ለሄድልበርግ ዩኒቨርሲቲ ተናዘዘ፡፡ ኋላ ላይ ዩኒቨርሲቲው አመዱን በአራቱም አቅጣጫ ለነፋስ በትኖ፣ ጥቂት ያህል በስልቻው ውስጥ አስቀረ፡፡
የተጨማደደ ሱፉንና ግራጫ ሹራቡን እንደለበሰ ፊቴ ላይ ድቅን ይልብኛል፡፡ ብዚ ጊዜ በከባድ ሀሳቦቹ ስለሚዋጥ፣ ኮቱን ሲደርብ ከእነ ማንጠልጠያው ይለብሰው ነበር፡፡ አንድ ጊዜ የፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ የለበሰው ኮት ውስጥ ማንጠልጠያው መኖሩን ታዝቤ ብነግረው፣ ፈገግ ብሎ እንዲህ አለኝ፤ “ጥሩ ነዋ! ቲዮሪዎቼን የሚያጣጥሉ ሰዎች ቢያንስ ሰፊ ትከሻ አለው ብለው ያስቡ”፡፡
ኒድልማንን በቀላሉ መረዳት አዳጋች ነው፡፡ ጋግርቱ ከደንታቢስነት ተቆጠረበት እንጂ እሱስ ጥልቅ ሀዘኔታ የሚሰማው እሩህሩህ ሰው ነበር፡፡ አንድ ጊዜ የማዕድን ማውጫ ጉድጓድ ውስጥ የተከሰተ አስከፊ አደጋን ከተመለከተ በኋላ፣ አንድ ዋፍልስ ኬክ በልቶ ሁለተኛ መድገም አቅቶት ሁሉ ነበር፡፡ በዝምታው ምክንያት ሰዎች አይቀርቡትም፡፡ እሱ ግን “ንግግር የተበከለ የመግባቢያ መንገድ ነው” ብሎ ከፍቅረኛው ጋር እንኳ የሚግባባው በጽሑፍ ነበር፡፡
ከኮሎምቢያው ዩኒቨርሲቲ ዲን አይዘንአወር ጋር ተጋጭቶ ከስራው በተባረረ ጊዜ እኚህን የቀድሞ ጄነራል፤ የምንጣፍ መወልወያ ይዞ መንገድ ላይ ጠበቃቸውና አይዘንአወር መሸሸጊያ ፍለጋ አጠገባቸው ወደሚገኝ የአሻንጉሊት መሸጫ ሱቅ ሮጠው እስኪገቡ አባረሯቸው፡፡ (ከዚህ ቀደም እነኚህ ሁለት ሰዎች በደወል ትርጉም ቀላል ተከራክረዋል፡፡ የደወል ድምፅ የሚያመለክተው የአንድን ክፍለ ጊዜ መጠናቀቅ ይሁን የሌላ ክፍለ ጊዜን መጀመር በአደባባይ እንካ ሰላንቲያ ገጥመው ነበር፡፡)
ኒድልማን ሁሌም ቢሆን ሰላማዊ ሞትን ነበር የሚመኘው፡፡ “ልክ እንደ ወንድሜ ጆዋን፣ በመጻሕፍቶቼና በወረቀቶች መሀል…”ይላል… (የኒድልማን ወንድም የጠፋበትን መዝገበ-ቃላት ሲፈልግ ዴስክ ስር ታፍኖ ነበር የሞተው)፡፡
ግን ያ ሕንጻ ምሳ ሰዓት ላይ ሲፈራርስ፣ ኒድልማን ቆሞ እንደሚመለከትና የፍርስራሹ ፍንጣሪ አናቱን እንደሚቆጋው ማን አስቦ ነበር? ኩርኩሙ ታላቅ ድንጋጤ ፈጠረበትና ፊቱ ላይ ወፍራም ፈገግታ እያሳየ የህይወት ዘመኑን አገባደደ፡፡ ትንፋሹ ከመውጣቱ በፊት “አይ፤ አልፈልግም፡፤ ፔንጉይንማ በፊትም አለኝ” ብሏል፡፡
ኒድልማን በሞተበት ወቅት እንደተለመደው በርካታ ጉዳዮች ላይ እየሰራ ነበር፡፡ “መልካምና ሚዛናዊ ባህሪ የተሻለ ሞራላዊ ይዘት ያለው ብቻ ሳይሆን በስልክ ሊተገበርም ይችላል” በሚል ቲዮሪው ተመስርቶ አዲስ ዓይነት ስነ-ምግባር እየገነባ ነበር፡፡ ተጋምሶ የነበረው አዲስ የስነ-ትርጉም ምርምሩም፤ የአረፍተ ነገር መዋቅር በተፈጥሮ የሚታደል፣ ማማረር ግን በልምድ የሚገኝ መሆኑን ያረጋግጣል (ቢያንስ ሁልጊዜ ቱግ ቱግ እያለ ይሄንኑ ስለማረጋገጡ ይሞግታል)፡፡ በመጨረሻም፤ አንድ ሌላ መጽሐፍ ስለ ሆሎካስት አዘጋጅቷል፡፡ ስለ ክፋት ድርጊቶች አብዝቶ ሲጨነቅ የኖረው ኒድልማን፤ እውነተኛ ክፋት ሊደረግ የሚችለው የአድራጊው ሰው ስም “ብላኪ” ወይ ደግሞ “ፒቲ” የሚባል ከሆነ ብቻ እንደሆነ በርቱዕ አንደበቱ ይሞግት ነበር፡፡ ከብሔራዊ ሶሻሊዝም ሀሳብ ጋር የነበረው አጉል ቅብጠት በአካዳሚያዊ ክበባት ውጉዝ እንዲሆን አድርጎትም ነበር፡፡
በሂትለር ላይ ያለውን አቋም ለመንቀፍ በጣም ቀላል ነው፤ ግን ደግሞ ፍልስፍናዊ ጽሑፎቹን ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ ዘመናዊ ስነ-ህላዌን ሲነቅፍም ሰው (ምንም እንኳ የነበሩት አማራጮችቹ ውስን ቢሆኑም) ከዘላለማዊነት በፊት መኖሩን ሞግቷል፡፡ በኑሮ እና ኑሮ መካከል ልዩነቶችን ማየት ከመቻሉም በላይ አንደኛው መልካም እንደሆነ ለማወቅ ታድሎ ነበር፤ የትኛው እንደሆን ቆይቶ ለማስታወስ ቢቸግረውም፡፡ ለኒድልማን የሰው ልጅ ነፃነት ማለት የህይወትን ወለፈንድነት መረዳትን ያካትታል፡፡ “እግዜር ዝምተኛ ነው” ማለትን ያበዛ ነበር፡፡ “እንደው ግን ሰውንም ጭምር ፀጥ ማሰኘት ቢቻል ኖሮ!” ይላል።
ንጹህ ህላዌን መጎናፀፍ የሚቻለው በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ብቻ ነው፤ ያኔም ቢሆን መኪና መዋስ ያስፈልግሃል ብሎ ያስብ ነበር ኒድልማን፡፡ በእሱ አመለካከት የሰው ልጅ በተፈጥሮ ውስጥ የራሱ ሚና ኖሮት የሚንቀሳቀስ ፍጡር እንጂ፤ ከተፈጥሮ ተነጥሎ የሚታይ “ቁስ” አይደለም፡፡ እናም መጀመሪያ ምንም ያልተሰማው እንደሆነ በማስመሰል፤ ኋላ ላይ ግን ራሱን በጨረፍታ የማየት ተስፋ ሰንቆ ወደ ሌላኛው የክፍሉ ጥግ በፍጥነት ካልተንደረደረ በስተቀር የሰው ልጅ የራሱን ህልውና ሊታዘብ አይቻለውም፡፡
ለህይወት ሂደት የሰጠው አንድ ስያሜ “አንግስት ዜይስት” ይሰኛል፤ በግርድፉ ሲተረጎም የጭንቅ ወቅት እንደማለት፡፡ በእርግጥ ድርጊቱ የሚከናወነው ጊዜ በሚለው ፅንሰ ሀሳብ ውስጥ ባይሆንም ሰው ማለት ጊዜ ውስጥ እንዲኖር የተፈረደበት ፍጡር መሆኑን ጠቁሟል፡፡ ከብዙ አሰላስሎት በኋላ ኒድልማን በምሁራዊ ምጥቀቱ ተመርቶ አለመኖሩን ተረዳ፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን ባልንጀሮቹም እንደሌሉና እውን የሆነው ብቸኛው ነገር ስድስት ሚሊዮን ብር የተበደረበት የባንክ ሰነድ ብቻ መሆኑ ተገለፀለት፡፡ ቆይቶ ብሄራዊ ሶሻሊዝምን እንደማይደግፍ በግልጽ መታወቅ ሲጀምር ከበርሊን ኮበለለ፡፡ በቅጠላ ቅጠል እየተሸሸገና ሶስት ፈጣን እርምጃዎችን ወደ ጎን ወደ ጎን ብቻ እየተራመደ ማንም ሳያውቀው ድንበሩን ተሻገረ፡፡
አውሮፓ ውስጥ በሄደበት ሁሉ ተማሪዎችና ምሁራኑ ሁሉ መልካም ስምና ዝናውን በማሰብ በማናቸውም ነገር ሊተባበሩት ይጓጉ ነበር፡፡ በስደት ሆኖ “ጊዜ፣ ትርጉም እና ዕውነታ፣ የምንነት ስልታዊ መገለጥ” የሚለውን መጽሐፉንና ከዚህ ቀለል የምትለውን “በሚሰወሩ ወቅት ሊመገቡባቸው የሚችሉ ምርጥ ምግብ ቤቶች” የምትል አዝናኝ መጽሐፉን ለማሳተም ጊዜ አግኝቷል፡፡ ቼይም ዊዝማን እና ማርቲን ባቤር ኒድልማን ወደ አሜሪካ እንዲሄድ የሚያስፈቅድለት ፒቲሽን ቢያስፈርሙለትም እንኳ በወቅቱ አሜሪካ እንደደረሰ ሊያርፍበት የፈለገው ሆቴል፣ ያልተያዘ ክፍል የሌለው ስለነበር ጉዳዩ ሳይሳካ ቀረ፡፡ ፕራግ ውስጥ ከተደበቀበት ቦታ የጀርመን ወታደሮች ሊደርሱ ጥቂት ሲቀራቸው፣ ወደ አሜሪካ ለመምጣት ወሰነ፡፡ ሆኖም ትኩረት የሚስብ አንድ ትዕይንት በአውሮፕላን ማረፊያው ተከሰተ፣ አውሮፕላኑ ከተፈቀደለት ጭነት በላይ ነበር የያዘው። በዚያው በረራ ላይ የነበረው አልበርት አንስታይን፣ ኒድልማን ጫማዎቹ ውስጥ የወሸቃቸውን የጫማ ቅርፅ ማስጠበቂያ እንጨቶች ቢያወጣቸው ኮተቱን በሙሉ መጫን እንደሚችል አብራራለት፡፡ ከዚህ በኋላ ሁለቱ በርካታ ደብዳቤዎችን ተጻጽፈዋል፡፡ በአንድ ወቅት አንስታይን እንዲህ ሲል ጽፎለታል፤ “ያንተ ሥራ እና የኔ ሥራ በጣም ይመሳሰላሉ፤ ምንም እንኳ ያንተ ሥራ ምን እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር ባልችልም”
በአሜሪካ ቆይታው በአንድ ወቅት ከህዝብ አፍ ሲጠፋ “አለመኖር በድንገት ቢያጋጥምዎት ሊያደርጓቸው የሚገቡ ጠቃሚ ክሮች” የምትል መፅሐፍ አሳተመ፡፡ በተጨማሪም Semantic Modes of Non-Essential Functioning የሚል ሌላ መጽሐፍ አሳትሞ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘ ፊልም ተሰርቶበታል።
ከኮሚኒስት ፓርቲ ጋር በነበረው ግንኙነት ምክንያት ከሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ እንዲለቅ ተጠይቆ ነበር፡፡ ዕውነተኛ ነጻነት መገኛዋ ኢኮኖሚያዊ እኩልነት የሰፈነበት ማኅበረሰብ ብቻ መሆኑን ገልፆ፣ የጉንዳኖችን አኗኗር እንደ አርአያነት ጠቅሷል፡፡ ጉንዳኖችን ለሰዓታት ያህል በቁጭታዊ ተመስጦ ካስተዋለ በኋላ “የምር ተቀናጁ እኮ ናቸው! ብቻ ሴቶቻቸው ትንሽ ከዚህ የተሻለ ውበት ቢኖራቸው እንዴት ስኬታማ በሆኑ!” ይል ነበር፡ በሚገርም ሁኔታ የሀገሪቱ ምክር ቤት ኒድልማን ፀረ-አሜሪካ ተሟጋች መሆኑን ሲበይንበት፣ የራሱን ፍልስፍና እየጠቀሰ ወደ ሥራ ባልደረቦቹ አላከከባቸው፡፡ “ፖለቲካዊ ድርጊቶች ከዕውነተኛ ህላዌ ውጭ ሊኖሩ ከመቻላቸውም በላይ የሚያስከትሉት ምንም ዓይነት የሞራል ጣጣ የለውም” ብሏል፡፡ በዚህ ጊዜ አካዳሚያዊ ማህበረሰቡ ለተወሰኑ ሳምንታት ቅጣት ውስጥ ቢቆይም ወዲያው ፕሪኒስተን የሚገኘው ፋካልቲ ዋጋውን ሊሰጠው ወሰነ፡፡ ኒድልማን በሰበቡ የነጻ ፍቅር እሳቤውን ለማስረዳት ይሄንኑ አመክንዮ ተጠቀመ፤ ሆኖም ከሞከራቸው ሁለት ተማሪዎች አንዷም አምነው አልተቀበሉትም፤ እንዲያውም የአስራ ስድስት አመቷ ታዳጊ አጋለጠችው፡፡
የኒዩክሌር ሙከራዎች እንዲቋረጡ ተግቶ ይሰራ ነበረው ኒድልማን፤ ወደ ሎስ አላሞስ በመብረር በዚያ ከሚገኙ በርካታ ተማሪዎች ጋር በማበር ከአንድ ቀድሞ ከታቀደ የኒዩክለር መሞከሪያ ሥፍራ ላለመንቀሳቀስ አድማ መቱ፡፡ ደቂቃዎች ተቆጥረው ሙከራው እንደማይቋረጥ ግልፅ ሲሆን ኒድልማን “ኦ ኦ” ሲል ተሰማና ወዲያውኑ እግሬ አውጭኝ አለ። ጋዜጦቹ ያልዘገቡት ነገር ቀኑን ሙሉ እህል የሚባል አለመቅመሱን ነበር፡፡      
በሕዝብ የሚታወቀውን ኒድልማን ማስታወስ ቀላል ነው፡፡ ብሩህ፣ ቁርጠኛ ደራሲ፡፡ እኔ ግን ግለሰቡን ኒድልማን ነው ሁሌም በደስታ የማስታውሰው። ሁሌም ምርጥ ኮፍያ የሚያደርገውን ሳንዶር ኒድልማን። አስከሬኑ ሲቃጠልም ኮፍያ አድርጎ ነበር፡፡ እንዲህ በማድረግ የመጀመሪያው ሰው ይመስለኛል፡፡ የማስታውሰው የካርቱን ፊልም አብዝቶ የሚወደውን፤ ስለ አኒሜሽን በቂ ማብራሪያ በማክስ ፕላንክ ቢሰጠውም ሚኒ ማውስን ለፍልሚያ የጋበዘውን ኒድልማን ነው፡፡
ኒድልማን በእንግድነት ቤቴ በቆየበት ወቅት፣ አንድ የሚወደው ዓይነት ቱና (የታሸገ ዓሳ) እንዳለ በመረዳቴ፣ የእንግዳ ክፍሉን ማብሰያ ቤት በዚሁ ዓይነት ቱና ሞላሁት፡፡ የቱና ፍቅሩን ለእኔ ለመግለፅ ቢያሳፍረውም አንዴ ብቻውን ሆኖ ሁሉንም ጣሳዎች ከፍቶ “ሁላችሁም ልጆቼ ናችሁ” ሲል ሰማሁት፡፡
የኒድልማንን ሰባኛ ዓመት የልደት በዓል አስታውሳለሁ፡፡ ሚስቱ ፒጃማ ነበር የገዛችለት፡፡ አዲስ መርሴዲስ እንድትገዛለት ፍንጭ ሲሰጣት ስለከረመ በግልፅ በሚታይ መልኩ ተበሳጭቶ ነበር፡፡ ብቻውን ወደ ማንበቢያ ክፍሉ ሄዶ፣ እንደ ሕፃን ልጅ መነፋረቅና መደንፋቱ እስከዛሬም ድረስ መለያው ሆኖ የሚታወስ ነው፡፡ ቆይቶ ግን በፈገግታ ተሞልቶ ወደ ግብዣው ተመለሰ፡፡ ፒጃማውንም ሁለት አጫጭር ተውኔቶች በሚመረቁበት ምሽት ለብሶ ታየ፡፡

Read 2781 times