Saturday, 08 March 2014 12:52

ተጠያቂነት የጠፋበት የቴሌኮም ስርዓት!

Written by  በኪሩቤል ሆነ
Rate this item
(1 Vote)

       አገራችን ባለፉት አመታት ካሳየቻቸው ለውጦች ዋነኛው የመሠረተ ልማት መስፋፋት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በመንገድ፣ በባቡር፣ በውሀና በሀይል አቅርቦት እንዲሁም በቴሌኮም መስኮች ሰፊ የመሰረተ ልማት መስፋፋት ተስተውሏል። ነገር ግን ልብ ብሎ ላስተዋለው ይህ መስፋፋት ሁለት ገጽታዎች ተላብሶ ይታያል። በአንድ በኩል ይህ ፈጣን የመሠረተ ልማት ግንባታ እጅግ ብዙ ኢትዮጵያውያንን በማገናኘት የሀገሪቱን የልማትና የምርታማነት ከባቢ ያሠፋ ሲሆን በተዋናዮቹም ላይ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት እድገት መፍጠር ችሏል፡፡
በአሁን ወቅት 24 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ከዛሬ አስር አመት ከነበረው አንፃር ሲታይ ይህ ቁጥር እጅግ አስገራሚ ሊባል የሚችል እድገት ማሳየቱን ይጠቁማል፡፡ ያለ ምንም ጥርጥር ይህን መሠሉ እድገት በሌሎችም መስኮች እንደሚኖር መገመት አዳጋች አይደለም፡፡ የመሠረተ ልማት እድገቱ ሌላ ገፅታ ደግሞ አለው። ይህም ከጥራት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ መቼም ጥራት የመሠረተ ልማት መስፋፋት ዋነኛ ደንቃራ መሆኑን መረዳት አያቅትም፡፡ በሁሉም የመሠረተ ልማት አይነቶች ጥራት ከፍተኛ ችግር እንደሆነ ዘልቋል፡፡ ሌሎቹን የመሠረተ ልማት አይነቶች ትቼ በስራዬና በትምህርቴ ምክንያት ስለምከታተለው የሀገሪቱ የቴሌኮም ዘርፍ፣ ከ13 ዓመታት በላይ እንዳገለገለ ባለሙያ፤ የዘርፉ የጥራት ችግር ጥልቅና ውስብስብ ምክንያቶች ያሉት እንደሆነ አስባለሁ፡፡
የማይቆራረጥ የቴሌኮም አገልግሎት ይኖር ዘንድ የማይቆራረጥ የሀይል አቅርቦት መኖር የግድ ነው፡፡ የማይቆራረጥ የሀይል አቅርቦት በሌለበትና የመጠባበቂያ ሀይል ባልተዘጋጀበት ሁኔታ ግን የቴሌኮም መስመሮችም ሆነ የማስተላለፊያ ጣቢያዎች በአግባቡ ሊሠሩ አይችሉም፡፡ ምክንያቱ ባይታወቅም የሀይል አቅርቦቱ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ መቆራረጥ ይስተጓጎላል። ይህም በምሬት ለምናስተናግደው የቴሌኮም አገልግሎት መቆራረጥ የራሱን ድርሻ መጫወቱ አልቀረም። የሀገሪቱ አቅርቦት መቆራረጡ እንዳለ ሆኖ አብዛኞቹ የቴሌኮም ማስተላለፊያ ጣቢያዎች ደግሞ ደጋፊ ወይም ምትክ የሀይል አቅርቦት መስጫ ጀኔሬተሮች የሏቸውም፡፡ ይህም ማለት የሀይል አቅርቦት በተቋረጠ ቁጥር የቴሌኮም አገልግሎትም ይቋረጣል ማለት ነው፡፡
ግልፁን እንነጋገር ከተባለ ይህ ችግር የኢትዮ ቴሌኮም ችግር ነው፡፡ እንደ ቴሌኮም አገልግሎት ሠጪ ተቋም፣ሁሌም የማስተላለፊያ ጣቢያዎቹ በቂና አስተማማኝ የሀይል አቅርቦት ማግኘታቸውን ከዛም ባለፈ ምትክ ሀይል ማቅረቡን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡ ገንዘብ ለመሠብሠብ የሚያሳየውን ፍላጎት ያህል ይህንን ሃላፊነቱንም መዘንጋት የለበትም፡፡ አንዳንድ ሃላፊዎች ሊያደርጉት እንደሚሞክሩት፣ይህንን የቴሌኮም አገልግሎት መቆራረጥ በመሠረተ ልማት አቅራቢው ላይ መለጠፍ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ እንደማለት ነው፡፡ የመሠረተ ልማት አቅራቢው ሀላፊነት መሠረተ ልማቱን ማቅረብና በአግባቡ መስራቱን መፈተሽ ብቻ ነው፡፡ ከዛ በኋላ ያለው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪው ስራ ነው የሚሆነው፡፡
ሌላው እዚህ ላይ ማንሣት የሚገባው የቴሌኮም መሠረተ ልማት ጥገና ጉዳይ ነው። መቼም ኢትዮ ቴሌኮምን የሚከታተል ሁሉ የባለሙያ እጥረት የሚያንደፋድፈው ተቋም መሆኑን ለመገንዘብ ብዙም ጊዜ አይፈጅበትም። ይህ የባለሙያ እጥረቱ ደግሞ ከለውጡ በኋላ በእጅጉ ተባብሷል፡፡ በዚህም የተነሳ የጥገና ክፍሉ ተገቢውን እለታዊ (ቀላል) እንዲሁም ወቅተዊ (መካከለኛ እና ከባድ) ጥገና ማድረግ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚገባው የቴሌኮም መሠረተ ልማቶች ከ80 በመቶ በላይ የሆነ አቅማቸውን መጠቀም ከጀመሩበት እለት ጀምሮ ጥገና የሚያሻቸው መሆኑን ነው፡፡
ለኢትዮ ቴሌኮም፣ ጣቢያዎች መሠረታዊ የአገልግሎት አከርካሪዎች መሆናቸውን የዘነጋ ይመስላል፡፡ ተቋሙ ለወጣባቸው ወጪ ባይጨነቅ እንኳን ለሚሠጡት ኢኮኖሚያዊ ጥቅም መጨነቅ ነበረበት፡፡ መቼም አለመታደል ነው፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች እየተደራረቡ መጥተው አሁን የቴሌኮም መሠረተ ልማት ጥራት ችግር ህዝብን እያማረረው ይገኛል፡፡ ለነገሩማ መማረሩ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች መቀጠሉ አይቀርም፡፡ ለምን ቢባል ደግሞ ሀላፊነት በጎደለው የቴሌ ውሳኔ ምክንያት ነው፡፡
ቴሌ የበፊቱን መሠረተ ልማት በሙሉ ነቅሎ በሌላ ለመተካት ወስኗል፡፡ አይ ተቆጪ ማጣት! በዚህ ውሳኔ ታዲያ ሚሊዮኖች የፈሠሠበት መሠረተ ልማት ተነቅሎ ይጣልና በሌላ ሚሊዮኖች በወጣበት ይተካል፡፡ እስከዛው ታዲያ እኛም በኮሙኒኬሽን እጦት እንዳክራለን፡፡
በቴሌኮም የሚታየው የጥራት ችግር ከላይ እንደተገለፀው በሁሉም መስኮች መታየቱ አልቀረም። የሚገርመው ግን የጥራት ችግሩን አስመልክቶ አሁንም ቢሆን ተገቢው አካል ሀላፊነት አለመውሰዱና አለመጠየቁ ነው፡፡
እስከ መቼ ይሆን ባለ መንገዱ በኮንትራክተር፣ ባለ መብራቱ በመስመር፣ ባለ ስልኩ በአቅራቢ እያመካኘ የሚቀጥለው? መቼ ነው ሁሉም ወገን ለስራው ሀላፊነቱን መውሰድ የሚጀምረው? ያንን ጊዜ እንናፍቃለን፡፡
(ኪሩቤል ሆነ፤በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በቴሌኮም ኢንጂነሪንግ የማስተርስ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን ላለፉት 13 ዓመታት በኢትዮጵያ የቴሌኮም ሴክተር ውስጥ በተለያየ ሀላፊነት ሠርተዋል፡፡ ለበለጠ መረጃ በኢሜል አድራሻቸው በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ይገኛሉ፡፡)   

Read 3805 times