Saturday, 15 February 2014 13:15

የአብነትን ‹‹አርሰናል›› መፅሐፍ እንደገመገምኩት…

Written by  ከመስከረም ደጀኔ
Rate this item
(1 Vote)

          በኢትዮጵያ የህትመት ታሪክ ውስጥ ቀዳሚውን ሥፍራ ይዞ የነገሰው የነፃው ፕሬስ ጉዞ፤ አስደማሚ ውጤት ለመፍጠር መቻሉ አያከራክርም፡፡ በአገራችን በተፈጠረው አንፃራዊ የዲሞክራሲ ጅማሮ የተነሳ በይፋ የተፈቀደው የነፃ ፕሬስ ህትመት፤ እንደጀማሪ ባህልነቱ ህፀፆች አልነበሩበትም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን፤ የንባብ ባህል እንዲደራጅ የነፃው ፕሬስ የተጫወተው ሚና፣ ልኬትና ወሰን አበጅቶ ከማስቀመጥ ይልቅ “ታሪካዊ ሚና” ቢባል ይሻላል፡፡
የነፃው ፕሬስ ህትመትን ማበብ ተከትሎ ወደ ሙያው ተቀላቅለው ድንቅ ስራዎችን እያበረከቱ ለህዝቡ በማስተዋወቅ፣ የንባብ ባህል እንዲደረጅ ያስቻሉ በርካታ ወጣት ጋዜጠኞችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ብዙዎቹ በአድካሚው ሙያቸው፣ ፅናትን እንደ ትርፋቸው፣ ብርታትን እንደምንዳቸው፣ ተስፋን እንደ ጡረታ ዋስትናቸው ቆጥረው ይሰራሉ። በሙያው የከበረ ስምና ዝና ለማግኘት የቻሉ ወጣቶች የመኖራቸውን ያህል፤ ስራዎቻቸውን በመፅሐፍ መልክ አዘጋጅተው በማቅረብ ጠቀም ያለ ክፍያ ለማግኘት የበቁ ጋዜጠኞችም አልጠፉም፡፡  እጅግ ብርቱ ፈተና በሰፈነበት፣ ፅናትና ቁርጠኝነት ወሳኙ ሀይል በሆነበት የነፃው ፕሬስ ዓለም ውስጥ የገጠማቸውን ሁሉ በትዕግስት ችለው፣ ሙያዊ ብቃታቸውንና ዕውቀታቸውን ለህዝባቸው ሲመግቡ ቆይተው፤  የመፅሐፍ ዓለሙን ጎራ የተቀላቀሉ የብዕሩ ዓለም ቤተኞችን ለማየት መብቃታችን እሰየው አሰኝቶናል፡፡
የመፃህፍት ህትመት ከቅርብ አመታት ወዲህ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መጥቷል፡፡ በኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ታሪክ ውስጥ አይነተኛ ቦታ የነበራቸው ጋዜጠኞች የካበተውን ዕውቀታቸውንና ልምዳቸውን ለህዝባቸው የሚያካፍሉበትን ተጨማሪ መድረክ ያመቻቸም ሆኗል፡፡ ከእነዚህ የነፃው ፕሬስ ባለሙያዎች መካከል ጋዜጠኛ አብነት ታምራት አንዱ ነው፡፡ የመፅሐፍ ንባብን እንደ ቀለብ ለሚቆጥሩ ብቻ ሳይሆን፤ እግር ኳስን እንደ መሰረታዊ ጉዳይ ለሚከታተሉ  ኢትዮጵያዊያን በአይነቱ ለየት ያለ መፅሐፍ ለህትመት አብቅቷል፡፡
መፅሐፉ
ጋዜጠኛ አብነት፤ ‹‹አርሰናል›› የተሰኘው መፅሐፉን ያዘጋጀው የረጅም ጊዜ የጋዜጣ ዓለም ዕውቀትና ልምዱን ተጠቅሞ ነው፡፡ ስለ አርሰናል ክለብ ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች፣ መዛግብትና መፅሐፍት አሰባስቦ፤ ቅደም ተከተሉን ጠብቆ፣ እጅግ ባማረ ቋንቋ እያሰናሰለ ለንባብ አቅርቦታል። በእንግሊዝ እግር ኳስ ታሪክ ሁነኛ ስፍራ ያለውና በኢትዮጵያዊያን ስፖርት አፍቃሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት የተቀዳጀው አርሰናል የእግር ኳስ ክለብ፤ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ አሁን እስከደረሰበት ደረጃ  አሳምሮ ይተርካል - መጽሐፉ፡፡
የአርሰናል ምስረታ ከተጠነሰሰበት ውልዊች ጀምሮ አሁን እስከደረሰበት ኤምሬትስ ድረስ ያለው ታሪካዊ ጉዞ ማራኪ ቢሆንም፤ የመፅሐፉ  አዘጋጅ የዚህን ክለብ ማራኪ ታሪክ ለማስነበብ የተጠቀመበት የትረካ አፃፃፍ ያስገርማል፡፡ የክለቡን ታሪክ በአምስት ምዕራፎችና በተለያዩ ንዑስ አንቀፆች ከፋፍሎ በቅደም ተከተል በማስቀመጥ መፅሐፉን ያለእፎይታ እንድናነበው አድርጓል፡፡
በ219 ገፆች የቀረበው የክለቡ ታሪክ፤ ከታሪክ ማጣቀሻነቱ በዘለለ እንደ አንድ የስነፅሁፍ ልምድ መፍጠሪያ መፅሐፍ እንዲቆጠር ፀሐፊው የተጠቀመበት ስልት አስደናቂ ነው፡፡ ፀሐፊው በሜዳ ላይ የሚንቀሳቀሱ ተጨዋቾች ያደረጓቸውን የአንድ ወቅት እንቅስቃሴዎች ብቻ ሳይሆን፤ ያስቆጠሯቸውን ምርጥ ግቦች አስፍሮ ለአንባቢ ለማስረዳት የተጠቀመባቸው የምስል አተራረክና አገላለፅ ጥበቡ፤ የጀመርነውን ምዕራፍ ካነበብንም በኋላ የአፃፃፍ ስልቱንና ብቃቱን ለመመርመር  ተመልሰን እንድናነብ ያስገድደናል፡፡ የላቀ የንባብ ፍላጎት ያላቸው መደበኛ አንባቢዎችን ብቻ ሳይሆን፤ አማራጭ ስላልቀረበላቸው ብቻ ከንባብ ርቀው በመቀመጥ፣ የእግር ኳስ መረጃዎችን ብቻ በማነፍነፍ ተጠምደው የሚውሉ የስፖርት አፍቃሪዎችን ወደንባብ እንዲሳቡ ይጋብዛል፡፡
በተለያዩ ዘዴዎች ተበታትነው የሚታዩትንና በሳምንታዊ ጋዜጣዎች ላይ ጊዜ እየጠበቁ  ለንባብ የሚቀርቡትን የክለቡን መረጃዎች እየለቀሙ ማንበብ፣ ለክለቡ የልብ ደጋፊዎች፣ ለእግር ኳስ አፍቃሪዎችና ለንባብ ባህል አራማጆች ብዙም ፋይዳ ያለው ባለመሆኑ ለንባብ በበቃው ‹‹አርሰናል›› መፅሐፍ በአንድ መድበል ተካቶ መቅረቡ ሁነኛ መፍትሄ ነው፡፡
የመፅሐፉ ግብ
 በመግቢያው  ላይ መፅሐፉ ለኢትዮጵያዊያን ስፖርት አፍቃሪዎች የሚሰጠው ጠቀሜታ እጅግ ባጠረና በተመጠነ መልኩ ቀርቧል፡፡ ይሁንና የመፅሐፉ አጠቃላይ ጉዞ በዚሁ እንዲያከትም በማድረግ ግቡን አሳንሶ  መተመን አግባብ አይደለም ብዬ አምናለሁ፡፡ የዚህ ታላቅ ክለብ ተመክሮ ለኢትዮጵያዊያን ታላላቅ ክለቦች የሚሰጠው ፋይዳ የጎላ ነው፡፡ ክለባዊ መዋቅርና አደረጃጀቱ በጥልቀት አለመቅረቡ በመፅሐፉ ላይ የሚታይ አንድ ደካማ ጎን መሆኑ ባይካድም፤ በዝርዝር ከተቀመጡ ነጥቦች በመነሳት የመፅሐፉ ጠንካራ ጎን ሚዛን ይደፋል ብሎ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡
በመፅሐፉ ላይ ከተቀመጡት አንኳር ነጥቦች መካከል ስለክለቡ ደጋፊዎች የተቀመጠው ዝርዝር በበኩሉ፤ ጉዳዩን ወደእኛ እውነታ በማምጣት ለመዳሰስ አለመሞከሩ ቅር ያሰኛል፡፡ መፅሐፉ ታላላቅ የተባሉ የክለቡ ደጋፊዎችን በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ ልዕልት ኤልሳቤትና ልዑል ሃሪ ከንጉሳዊያን ቤተሰቦች የተጠቀሱ ሲሆን ኬቨን ኮስትነር፣ ማት ዴመንና ዴሚ ሙር ከፊልም አክተሮች፤ ሬይ ዴቪስና ጄይ ዚ ከሙዚቀኞች፤ ዳረን ቤንት፣ ሞ ፋራህ፣ ቲዬሪ ሆንሪ፣ ራፋኤል ናዳል፣ ሀሪ ሬድናፕ፣ ፍብሪጋዝ፣ ዲያጎ ማራዶናና ዴኒስ ቤርካምፕ ከስፖርተኞች እንዲሁም ፖል ካጋሜ ከፖለቲከኞች ከተዘረዘሩ በርካታ ታላላቅ ሰዎች መካከል ስማቸው ተጠቅሷል፡፡
ታላላቅ ኢትዮጵያዊያን ፖለቲከኞች፣ ባለሀብቶች፣ የስፖርት ሰዎችና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ሰፊ ድጋፍ የሚሰጡት አርሰናል፤ በኢትዮጵያዊያን በኩል ያለው ገፅታ ምን መልክ እንዳለው ለማሳየት የእነዚህ ታዋቂ ሰዎች ዝርዝር መካተት ነበረበት፡፡ ከዚህ አንፃር መፅሐፉ ክፍተት ስለሚታይበት ደራሲና ጋዜጠኛ አብነት ታምራት ይሄንን  ለመሙላት በቀጣይ ክፍል ስራው ትልቅ ጥረት ማድረግ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ፀሃፊው፣ የኢትዮጵያዊያን ታላላቅ ሰዎችን ዳራ በመተንተን፣ ከአርሰናል ክለብ ጋር ያላቸውን ቁርኝትና ለክለቡ ያላቸውን ፍቅር በጥልቀት ቢዳስስ ኖሮ፣ መፅሐፉን የበለጠ አገርኛ ቅርፅ እንዲኖረው ማድረግ ይችል ነበር፡፡
ከዚህ የአብነት የብዕር ትሩፋት በመንደርደር፣ ሌሎች ስፖርት ተኮር አገርኛም ሆነ የባህር ማዶ መፃህፍት ለንባብ እንደሚቀርቡ እምነቴ ነው። ምክንያቱም የንባብ ባህልን ማሳደግ የሚቻለው ለንባብ የሚቀርቡ አማራጮችን በማስፋት መሆኑ አያነጋግርምና፡፡
ሌሎችም ይሄ ፀሃፊ የጀመረውንና ለአንባቢው ትውልድም ሆነ ለስፖርት አፍቃሪው አማራጭ ይዞ ብቅ የማለት ይትበሃልን ገፍተውበት፣የአለማችን ምርጥ የስፖርት ጀግኖችን ታሪክ ለትውልዱ የሚያቀርቡበትን መስመር ከወዲሁ መተለም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እንደ ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሰረት ደፋርና ወርቅነሽ ኪዳኔ የመሳሰሉ ጀግና ኢትዮጵያዊ አትሌቶችን ታሪክ በመጽሐፍ አትሞ በማቅረብ፣ ትውልዱ ከእነሱ ጀግንነት የጠለቀ ትምህርትን እንዲያገኝ ማድረግ ጠቃሚ ስለሆነ፤ የመስራት አቅሙና ብቃቱ ላላቸው ፀሐፊዎች ሁሉ “አርሴናል” የማንቂያ ደወል እንደሚሆናቸው እምነቴ ነው፡፡    

Read 3570 times