Saturday, 15 February 2014 13:14

በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ስትጓዝ የኖረች የቅኔ ንግሥት

Written by  ጵሮስፎራ ዘዋሸራ
Rate this item
(3 votes)

ዝነኛዋ ባለቅኔ እመት ገላነሽ አዲስ በ1974 ዓ.ም ሠዓሊ ዘውዱ ኃይሌ
ፐርትሬታቸውን እንደሠራው
በደብረጽላሎ አማኑኤል ገዳም የሚገኘውና በመፈራረስ ላይ ያለው
የእመት በላይነሽ አዲስ መቃብር
በደብረጽላሎ ገዳም እመት ገላነሽ ካረፉ በኋላ የቅኔ ጉባኤያቸው እንዳይፈታ ቅኔ ሲያስተምሩ የነበሩት መሪጌታ አበራ ብርሃኑ


በኢትዮጵያ የቅኔና የባለቅኔ ታሪክ ሲነሣ እመይቴ ገላነሽ ሐዲስ የማይዘነጉ የቅኔ ንግሥት ሆነው በአእምሮዋችን ውስጥ ይመላለሳሉ። እኒህ የቅኔ ንግሥት ምንም እንኳን የዓይን ብርሃናቸውን አጥተው ለመኖር ቢገደዱም ዓይናማዎች ከሚያደርጉት በላይ በሕይወታቸው በዚያ በጨለማው ዘመን አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ፈጽመው አልፈዋል፡፡
እመይቴ ገላነሽ የባለቅኔዎችን ሐሳብ አስቀድሞ የማወቅ ችሎታ ስለነበራቸው፣ከአባታቸው ከቄሰ ጎበዝ ሐዲስ ኪዳን ጀምሮ የብዙ ባለቅኔዎችን ቅኔ በእሳቤ እየደረሱበት ነጥቀዋቸዋል፡፡ ከብዙ ባለቅኔዎች ጋር እንቆቅልሽ ቅኔ በመላላክ ቅኔያቱን በምርምር ፈትተዋል፡፡ በተለይ ከቦገና ግራሩ የቅኔ መምህር ከጥበቡ ካሣ ጋር ምሥጢር ያለው ቅኔ ይላላኩ እንደነበር ይታወቃል፡፡
ከእንቆቅልሽ ቅኔዎቻቸው ውስጥ
ሐወፀ ሮጌል ወወልደ ነጐድጓድ መዋቲ፡፡
ክሳድየ እኁብ እመ ትፈትሐ ለዛቲ፡፡
ይህንን ቅኔ ወልደ ነጐድጓድ ሟችን ሮጌል ጐበኘው፡፡ ይህንን ከፈታህ አንገቴን እሰጣለሁ ብሎ በጥሬው ሰው ሊፈታው ይችላል፡፡ ግን ትርጉሙ ይህ አይደለም፡፡
ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድና መቃብር (ሮጌል) እንደ ሀና ጸ የተራራቁ ናቸው ማለት ነው፡፡ ወልደ ነጐድጓድ ዮሐንስ ሞቶ ግን ወደ መቃብር ያልገባ መሆኑን እንቆቅልሹ ያስረዳል፡፡
በመጨረሻ እመይቲ ገላነሽና መምህር ጥበቡ በእንቆቅልሽ ቅኔ ሲፈታተሹና ሲመላለሱ ኖረው በመጨረሻ እመይቴ ገላነሽ ሳይፈቱት የቀረ የጥበቡ ቀጣይ ቅኔ አለ፡፡
ይኸውም “ሞቶን ሞተኪ ሞተ ፈጣሪ ገላም ገላነሽ ይህንን ፈትተሽ ፈክሪ” የሚለው ነው፡፡
የቅኔ ተማሪዎቻቸውና አስነጋሪዎቻቸው ዘራፊዎቻቸው ሲቀኙም መጨረሻውን እንዲህ ለማለት ፈልገህ ነው አይደል! ብለው የቅኔውን ምሥጢር እየደረሱበት ሲያስተካክሉ ኖረዋል፡፡ ግስን እየተነተኑና ቅኔን እየዘረፉ በቅኔ ሙያቸው ለ50 ዓመት አስተምረዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር ፈትል ሲፈትሉ፣ ስፌት ሲሰፉ ተወዳዳሪ አልነበራቸውም ይባላል፡፡ የፈተሉት ፈትልና የሰፉት ስፌት በሁለት ሺህ ዓ.ም እርሳቸውን የሚዘክር በዓል ባሕርዳር ላይ ተዘጋጅቶ በነበረበት ጊዜ ለዕይታ በቅቷል፡፡
ለአንድም ቀን ቤተ ክርስቲያን ቅኔ ማኅሌት ገብተው ቅኔ ባለመቀኘታቸው ይቆጩ የነበሩት እመይቴ ገላነሽ፤ ይህንኑ ጾታዊ እኩልነት ያልነበረውን ጽልመታዊ አሠራር እንዲህ በማለት ነቅፈውታል፡፡ ቅኔው ሥላሴ ነው፡፡ (አድማሱ ጀንበሬ) ዝክረ ሊቃውንት 1963)
ለብእሲት በዊኦታ
ውስተ ቤተ ማኅሌት ጊዜ ማኅሌት
ኢኮነ ነውረ አመ ሊቃውንት ሐተቱ
ማኅሌት እስመ እምቀዲሙ ለብእሲት ውእቱ።
ካህናትሰ ኪያየ ይእዜ ለእመ ከልሁ በከንቱ፡፡
ብዙኃ ነውረ ከመ ይከብቱ፡፡
አኮኑ ገቢረ እምተገብሮቱ፡፡
ኢፈለጡ ወቤተ ነሠቱ፡፡
ትርጉም፡ በማኅሌት፣ በጭብጨባ፣ በዘፈን ጊዜ ሴት ወደ ማኅሌት ብትገባ ነውር አይደለም  ዝማሬ ዘፈን እልልታ ጭብጨባ ቀድሞውንስ ቢሆን ለሴት ነውኮ፡፡
 ብዙ ነውር የሚሰበስቡት ካህናት ግን በእኔ ላይ በከንቱ ቢጮሁብኝም  ገቢር ተገብሮ/አገባብ/የቅኔ አገባብ/ስለማያውቁ ቤቱን እያፈረሱት ነው፡፡
ይህ ቅኔ መራርነት ያለውና የሴትነትን ስሜት የሚነካ ነው፡፡ እኒህ የቅኔዋ ንግሥት ሐዋርያው ጳውሎስንም ይተቹታል፡፡ ጳውሎስ ሴቶችን አስመልክቶ ሲያስተምር “አንስትሰ ይትገልበባ ርእሶን ለእመ የሐውራ ውስተ ቤተ መቅደስ” (ሴቶች ወደ ቤተ መቅደስ ሲሔዱ ራሳቸውን ይሸፋፈኑ ብሏል) በጉባዔም እንዳያስተምሩ ከልክሏል፡፡ ይህንን የሴት ተቆጭ ሐዋርያ እመይቴ ገላነሽ በመወድስ ቅኔያቸው ለመርታት እንዲህ ይሉታል፡፡
መገስጸ አንስት ጳውሎስ በቃለ ተግሳጽ
ለእመ ይቤ ኢትምሀር ብእሲት በጉባዔ፡፡
ለዘራዔ ንባብ ጳውሎስ ኢንሬስዮ ሠራዔ፡፡
ሥርዓተ ብእሲት ባሕቲታ
በብእሲት አምጣነ ተነግረ መወድስ ትንሣኤ፡፡
ወከመ ይስብኩ መወድሰ
ገላነሽ ፈነወት አርድእተ በበክልኤ፡፡
ጳውሎስሂ ለእመ ሰምዐ ዜና ዲቦራ መጽንዔ፡፡
እምኢኮነ ለአንስት መገሥጸ ወከላኤ፡፡
ዲቦራ እምነ እስመ ወውዐት ውዋዔ፡፡
በቅኔ ወበመዝሙር በቅድመ ጉቡአን ሰብአ.ጽዋዔ፡፡  
(አድማሱ ጀንበሬ ዝክረ ሊቃውንት 1963 ገጽ 306-307)    
ትርጉም፡ ሴቶችን በመቆጣት በመገሰጽ የሚታወቀው ጳውሎስ፤ በጉባዔ ሴት አታስተምር ቢልም ንባብ የሚዘራ ጳውሎስን እንደሠራ አንቆጥረውም፡፡ መወድስ ትንሣኤ የተነገረው እኮ በሴቶች  ነውና፡፡ (ማርያም መግደላዊት ስለጌታችን  ትንሣኤ አስቀድማ ስለአበሠረች ነው)፡፡
መወድስን ይሰብኩና ያስተምሩ ዘንድ ገላነሽ ሁለት ሁለት እያደረገች ተማሪዎችን ልካለች፡፡
ጳውሎስ አጽናኙ የሆነውን የዲቦራ ዜና ቢሰማ፣ የሴቶች ተቆጭና ጩዋሂ ባልሆነም ነበር፡፡
ዲቦራ እናታችን በቅኔና በመዝሙር በተጠሩ  በተሰበሰቡ ሰዎች ፊት ጩኸትን ጮሃለችና፡፡
እመይቴ ገላነሽ፤ሐዋርያው ጳውሎስን በዚህ ዓይነት መንገድ ሞግተውታል፡፡ ጳውሎስን የተቹት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ እማሆይ ገላነሽ የግዕዝ ቅኔ መምህርት ሆነው ለ50 ዓመታት በማስተማር ሲኖሩ በሴትነታቸው ምክንያት አንድም ቀን እንኳን በቤተክርስቲያን ውስጥ ቅኔ ተቀኝተው አያውቁም ነበር፡፡ ይቀኙ ብሎ የጋበዛቸው ካህንም አልነበረም፡፡ ለዚህም የሚሰጠው ምክንያት ከላይ እንደተገለጠው ሐዋርያው ጰውሎስ ሴት በጉባኤ ወይም በማኅበር  አታስተምር ብሎ በመናገሩ ነው።
እኒህ ዝነኛ ባለቅኔ እግዚአብሔርንም እንዲህ በማለት ይሞግቱታል፡፡
ሚበዝኁ ዘእማሆይ ገላነሽ (አድማሱ 1963 ገጽ 148)
ይእዜ አእመርኩ ከመ ኢይፈትሕ ካዕበ እግዚአብሔር ሊቀ ፈታሕት፡፡
እመ ከደኖን ጽልመተ ለእለሥጋዬ አዕይንት፡፡
እስመ ረሰየ ይርአያ አዕይንትየ ዘውስጥ ምሥጢራተ ቅኔ ክቡት፡፡
ትርጉም፡ የፈራጆች ፈራጅ እግዚአብሔር በትክክል እንደማይፈርድ ዛሬ አወቅሁ፡፡ የፊት ለፊት ዓይኖቼን አጥፍቶ ሸፍኖ በውስጥ ዓይኖቼ ግን የቅኔ ምሥጢርን እንዳይ አድርጓልና፡፡
እማሆይ ገላነሽ፤በምዕራብ ጎጃም ውስጥ በቀድሞ አጠራሩ ይልማናና ዴንሣ ወረዳ በአሁኑ አጠራር በጎንጂ ቆለላ ወረዳ በጽላሎ አማኑኤል ገዳም በ1898 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ አባታቸው ቄሰ ገበዝ ሐዲስ ኪዳን ይባላሉ፡፡ እናታቸው ደግሞ  ወ/ሮ ወርቅነሽ እንግዳ ይሰኛሉ፡፡ በስምንት ዓመታቸው በኩፍኝ በሽታ ምክንያት የዓይን ብርሃናቸውን አጥተዋል ነገር ግን ይህ የአካል ጉድለት የአእምሮአቸውን ብሩህነት ሊገታው ስለአልቻለ በልጅነታቸው ከአባታቸው ከቄሰ ገበዝ ሐዲስ ኪዳን ዘንድ ውዳሴ ማርያምን፣ ቅዳሴ ማርያምን፣ መልክዐ ኢየሱስንና መልክዐ ማርያምን፣ መዝሙረ ዳዊትን በቃላቸው አጥንተዋል፡፡ ቀጥሎ ቅኔ ከነጓዙ ከአባታቸው ዘንድ ተምረው በመምህርነት ተመርቀዋል፡፡ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜንም ተከታትለዋል፡፡
እማሆይ ገላነሽ የቅኔ መምህርት ሆነው ከተመረቁ ጊዜ ጀምሮ አባታቸው እስከ ዐረፉበት 1928 ዓ.ም ድረስ የአባታቸው ረዳት መምህርት ሆነው ሲያስተምሩ ኖረዋል፡፡ ከአባታቸው ዕረፍት በኋላም የቅኔ ጉባኤውን ተረክበው ተወልደው በአደጉበትና ተምረው ለመምህርነት በበቁበት በደብረ ጽላሎ አማኑኤል ገዳም ለ50 ዓመታት ቅኔን አስተምረዋል፡፡ ያረፉት ሐምሌ 11 ቀን በዕለተ ሐና ሲሆን ሥርዓተ ቀብራቸው የተፈጸመው ሐምሌ 12 ቀን 1978 ዓ.ም ነው፡፡ ዐጽማቸው ያረፈውም በደብረ ጸላሎ ገዳም ሲሆን በአሁኑ ሰዓት የመቃብራቸው ሁኔታ በፎቶግራፍ ላይ የሚታየውን ይመስላል፡፡
እመት ገላነሽ በደብረ ጽላሎ ቅኔ መምህራን ተዋረድ 55ኛዋ ሲሆኑ ባለትዳርም ነበሩ፡፡ ባለቤታቸው አቶ ጥሩነህ ኪዳነማርያም ፈረሰኛ ነበሩ፡፡ እመት ገላነሽ ከአቶ ጥሩነህ ሦስት ልጆችን ወልደዋል፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸው መሪጌታ አዳም ኪዳነማርያም ይባላሉ (በአያታቸው ስለሚጠሩ ነው፡፡) ሁለተኛዋ ወ/ሮ መሠረት ጥሩነህ ሲባሉ ሦስተኛ ልጃቸው እንደተወለደ ሞቶባቸዋል፡፡
መሪጌታ አዳም ጎንደር ውስጥ የዐደባባይ ተክለ ሃይማኖት የመጽሐፍ መምህር ነበሩ፡፡ እርሳቸውም ሰባት ልጆችን ወልደው በድንገት አልፈዋል። ከመሪጌታ አዳም ልጆች፣ ሰብለ ወንጌል አዳም ውጭ አገር ስትሆን ሌላዋ ሐመልማል አዳም አዲስ አበባ ውስጥ እንደምትገኝ መሪጌታ አበራ የእመት ገላነሽ የልጅ ልጅ ባለቤት አጫውተውኛል፡፡
እመት ገላነሽ ሐዲስን የምናስታውሳቸው በቅኔ ሙያቸው ቢሆንም መልካም ዘር ተክተው በማለፋቸው ጭምር እንዘክራቸዋለን፡፡ የእርሳቸው ልጅ ወ/ሮ መሠረት ጥሩነህ እውነትም መሠረት ያላቸው ናቸው፡፡ ከእርሳቸው አብራክ ሙሉነሽ፣ አስረሳሽ፣ አጀቡሽ፣ ውባለች፣ ኃይሉና በያብልብኝ ተገኝተዋል፡፡ ወ/ሮ ሙሉነሽ ደግሞ /የእመይቴ ገላነሽ የልጅ ልጅ/ መሪጌታ አበራ ብርሃኑን አግብተው ሰገነትን፣ ደጊቱን፣ የትምወርቅን፣ ዘውዲቱን፣ ቤተልሔምንና ኪዳኑን ወልደዋል። እነዚህ ሁሉም የመሪጌታ አበራ ብርሃኑ ልጆች ሲሆኑ ኪዳኑ አበራ በአሁኑ ሰዓት የእመት ገላነሽን የቅኔ ጉባኤ ተክተው፣ ቅኔን በደብረ ጽላሎ አማኑኤል በማስተማር ላይ ናቸው፡፡
ወጣቱ ኪዳኑ አበራ በቅኔ መምህርነት ማዕረግ ከመመረቃቸው በፊት የእመት ገላነሽ ጉባዔ እንዳይፈታ ሲያስተምሩ የነበሩት አባታቸው መሪጌታ አበራ ብርሃኑ ናቸው፡፡ እርሳቸው በአሁኑ ሰዓት ስለደከሙ መምህር ኪዳኑ አበራ በቅኔ ሙያ እስኪመረቁ ድረስ የጉባዔው መምህር የነበሩት የገዳመ አስቄጥስ ተክለሃይማኖት ወክርስቶስ ሠምራ የቅኔ መምህር የሆኑት ዘለዓለም ተድላ ናቸው፡፡
ቀደም ሲል የእመት ገላነሽ የቅኔ ጉባዔ የነበረው ቤተክርስቲያኑ አካባቢ በሚገኘው መኖሪያ ግቢያቸው ውስጥ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ግን የቅኔ ቤቱ የተደራጀው ራቅ ብሎ ለተማሪዎች ኑሮ የተመቸ ሆኖ ነው፡፡ ቅኔ ቤቱ ከአንድ ትልቅ ዋርካ ዛፍ አጠገብ የሚገኝ ሲሆን በአብዛኛው በሳር ቤት የተሠራ ነው፣ የቅኔ ጉባኤውም ሳር ቤት ነው፡፡
በደብረ ጽላሎ በአሁኑ ሰዓት ሦስት ቅኔ መምህራን አሉ፡፡ እነርሱም መምህር ኪዳኑ አበራ፣ ለዓለም ብርሃኑና ክቡር አደራው ናቸው። የመምህር ኪዳኑ ዘሮች እስከ ዐስር ትውልድ ደርሰዋል። (በቅኔ መምህርነት ማለት ነው) ዐሥረኛው መምህር ኪዳኑ አበራ ናቸው፡፡ እርሳቸውም ገና የ24 ዓመት ወጣት ሲሆኑ ትዳር የመሠረቱትም በቅርቡ ነው፡፡
የደብረ ጽላሎ የቅኔ ጉባዔ በእመት ገላነሽ ስም የተሰየመ ሲሆን ጽርሐ ጽዮን ይባላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ እስከ 200 የሚደርሱ የቅኔ ተማሪዎችም  ይኖሩበታል፡፡   


Read 5577 times