Monday, 03 February 2014 13:57

የስለት ልጇ የቅኔ መምርት፤ እማሆይ አመተ ማርያም

Written by  ኦርዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(11 votes)

         ሀዲስ አለማየሁ “ፍቅር እስከመቃብር” በተባለው ዝነኛ መጽሐፋቸው ውስጥ ከቀረጿቸው ባለ ታሪኮች (ገፀ ባህርያት) አንዱ የስለት ልጅ ነው፡፡ የስለት ልጅ የነበረው በዛብህ ድምፀ መረዋ ስለነበር በአካባቢው ወጣት ሴቶች “የሚታይ እንጂ የማይበላ ፍሬ” ለመባል በቅቷል፡፡ እንዲህ የተባለበት ምክንያት በዛብህ በልጅነቱ ከፍተኛ ህመም አድሮበት ሊሞት ሲያጣጥር ወላጆቹ በስለት ለታቦት ስለሰጡት ነው፡፡ የስለት ልጅ በመሆኑም እንደ እኩዮቹ ትዳር መስርቶ ቤተሰብ ገንብቶ መኖር ስለማይችል ነበር ወጣቶቹ ያንን ስም ያወጡለት፡፡ “ፍቅር እስከመቃብር” የተጻፈው በ1958 ዓ.ም መሆኑን አንዘንጋ፡፡ ከአሥር ዓመት በኋላ እዚያው ጐጃም ውስጥ ጥቅምት 16 ቀን 1968 ዓ.ም እናርጅ እናውጋ ወረዳ፣ ልዩ ስሙ “ኩሬ ኪዳነምህረት” በተባለ ቀበሌ ገበሬ ማህበር፣ አንዲት ህፃን ከወ/ሮ ሙኒት አድገህ እና ከአቶ አሰፋ እጅጉ ተወለደች። ህፃኗ እንደ ጓደኞቿ ለመጫወት ቀርቶ እንደ ልቧ የሚያንቀሳቅስ ጤና አልነበራትም፡፡

ብዙ በሽታዎች ይደራረቡባት የነበረ ሲሆን በተለይ እግሯ እያበጠ ለመራመድ ሁሉ ትቸገር ነበር፡፡ ወላጆቿ ከተለያዩ የጠበል ቦታዎች እየወሰዱ ቢያስጠምቋትም ህመሟ ከመሻሻል ይልቅ እያደር እየባሰባት መጣ፡፡ አባቷ መጨረሻ ላይ የዘየዱት መላ፣ ልጃቸው ከዚያ ሁሉ ህመም ተፈውሳ እንደ ጓደኞቿ ጤናማ ከሆነች “ግብር አድቃቂ (ፈጭታ)፣ ቤተክርስቲያን አገልጋይ ትሆናለች እንጂ በዓለማዊ ህይወት አትኖርም” ሲሉ ለአምላካቸው መሳል ነበር። የልጃቸው ጤናም ቀስ በቀስ እየተሻሻለ መጣ። በ1977 ዓ.ም አገራችንን ከፍተኛ የድርቅ አደጋ ባጋጠማት ወቅት በዘጠኝ ዓመቷ ማለት ነው) የህፃኗ ወላጆቿ ወደ መተከል ይዘዋት ሄዱና ፓዌ፣ ልዩ ስሙ “መንታ ውሃ” ወይም ቀጠና ሁለት መንደር 26 ውስጥ መኖር ጀመረች፡፡ አጐቷ ቄስ ደምስ አያሌው በጥንታዊው ሥርዓት መሠረት፣ ፊደልና የግዕዝ ቁጥር ሲያስተምሯት ጐን ለጐንም ዘመናዊ ትምህርቷን ቀጠለች፡፡ ዘመናዊ ትምህርቷን እዚያው ፓዌ በሚገኙ ት/ቤቶች እስከ 8ኛ ቀጠለችና 9ኛ ክፍልን ቻግኒ ተማረች፡፡ ውጤቷ በጣም ጥሩ ስለነበር፣ ወደ 10ኛ ክፍል አልፋ ለሁለተኛው ወሰነ ትምህርት የማጠቃለያ ፈተና እየተዘጋጀች ሳለ፣ አንዲት መነኩሲት በአካባቢው መጥተው ሃይማኖታዊ ትምህርት ሲሰጡ ዓለማዊ ፍላጐቷን የሚፃረር ስሜት በውስጧ ተቀሰቀሰ፡፡

ምንም ሳታቅማማ ወዲያውኑ ዘመናዊ ትምህርቷን እርግፍ አድርጋ ወደ ገዳም ሄደች፡፡ ገዳም የገባችው በ17 ዓመቷ ሲሆን የገባችበት ገዳምም “ወለተ ሀና” የሚባልና እናርጅ እናውጋ ወረዳ ደብረ ወርቅ የሚገኝ ታላቅ ቦታ ነው። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው የአባቷን ቃል አክብራ የስለት ልጅነቷን ተግባራዊ ማድረግ የምትጀምረው፡፡ ከዚህ በኋላ የታላቅነቷን ምዕራፍ ትጀምራለችና እኔም “አንቺ” ሳይሆን “አንቱ” እያልሁ ጽሑፌን እቀጥላለሁ፡፡ እስካሁን የምተርክላችሁ ታሪክ ባለቤት የቅኔ መምህርት ሲሆኑ ስማቸውም “መምህርት ዓመተ ማርያም አሰፋ” ይባላል፡፡ ዓመተማርያም የ38 ዓመት ሴት ቢሆኑም በህጻንነት ዘመናቸው መንኩሰዋል፡፡ በወለተ ሀና ገዳም ቆይታቸው ቀን መነኮሳይያቱን ሲያገለግሉ እየዋሉ፣ ማታ ማታ “እማሆይ እናቴ ወለተማርያም” ከሚባሉ እናት ውዳሴ ማርያምን፣ ትምህርተ ኅቡዓትን እና ህማማተ መስቀልን ተማሩ። ከዚያ በኋላ የትምህርት አቀባበላቸውን ያዩት መምህርታቸው “ጀር ገብርኤል ሂጂና ትምህርትሽን ቀጥይ” ስላሏቸው ወደ ጀር አመሩ፡፡ ግን ከቦታው ሲደርሱ ያልታሰበ ነገር ገጠማቸው፤ ዕውቀታቸውን ያጋሩኛል ብለው የሄዱባቸው መምህር ሞቱ፡፡ በዚህ የተነሳ ወለተ ሃና ገዳም ሳሉ ከተዋወቋቸው አንዲት ወጣት ጋር ወደ ታላቁ ገዳም ዲማ ጊዮርጊስ ተጓዙ፡፡ ትምህርታቸውን በትጋት እየተከታተሉ ለተወሰነ ጊዜ መቆየት ቢችሉም በጠባያቸው ምስጉን ነበሩና የወለተ ሀና ገዳም መነኮሳይያት በብዙ ልመና መልሰው ወሰዷቸው፡፡

ገዳሙን ለሁለት ዓመት በእመ ምኔትነት (የገዳሙ ኃላፊ በመሆን) ካገለገሉ በኋላ የትምህርታቸው መቋረጥ የእግር እሳት ስለሆነባቸው፣ ደቦዛ ቅዱስ ሚካኤል ደብር ውስጥ ይገኙ ወደነበሩት መሪጌታ ሰሎሞን ዳዊት ዘንድ በመሄድ፤ መልክአ ማርያምና መልክአ ኢየሱስ ተምረው የቅኔ ትምህርት እንደጀመሩ፣ መምህራቸው ለትምህርት ወደ አዲስ አበባ በመሄዳቸው ወደ ዲማ ተመለሱ፡፡ ከወለተ ሀና ገዳም አብረዋቸው ከመጡት እማሆይ ኅርይት ጋር በመሆንም መጀመሪያ ከመሪጌታ ዲበኩሉና ከመሪጌታ ፍሬ ስብሐት ቅኔን ከነአገባቡ ተማሩ፡፡ የ20 ዓመት ወጣት እያሉም እዚያው ዲማ ጊዮርጊስ ውስጥ ሥርዓት ምንኩስና ፈፀሙ፡፡ ቀጥለውም “ዘሚካኤል” ከተባሉ የትርጓሜ መጻሕፍት ሊቅ ዘንድ የውዳሴ ማርያም፣ የቅዳሴ ማርያም እና ሐዲሳትን ትርጓሜ ተማሩ፤ ለዕውቀታቸው ማስረጃ ይሆናቸው ዘንድም የመምህራቸውን ምስክርነት (ማስረጃ) ተቀበሉ፡፡ ሆኖም ለቅኔ ያላቸው ፍቅር እጅግ ከፍተኛ ስለሆነና ችሎታቸውን ያዩ ሁሉ ስለሚገፋፏቸው በመጽሐፍ ትርጓሜ መግፋታቸውን ትተው ወደ ጨጐዴ ሀና ተጓዙ፡፡

ጨጐዴ በአሁኑ ወቅት ልክ እንደ ዋሸራ፣ ጐንጂና ፅላሎ ታላቅ ክብር ያለው የሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው የቅኔ ጉባኤ ቤት ነው፡፡ እማሆይ አመተ ማርያም ጨጐዴ ሀና፤ ከ1994 -1998 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ቅኔን በአግባቡ ከተማሩ በኋላ በመምርነት ተመርቀው ወደ ዲማ ተመለሱ፡፡ መምህር ዘሚካኤል ጋ ፍትሐ ነገሥትን መማር ስለፈለጉም ጉባኤ ቤት ሰሩ፡፡ ግን መምህራቸው “እስካሁን የተማርሽውን አስተምሪ እንጂ ከዚህ በላይ ለሴት ምን ያረጋል” አሏቸው፡፡ በዚህም እልህ ተጋቡና የዋሸራን ቅኔ አመል ለመመርመር ቀራንዮ መድኃኔዓለም ከነበሩትና የዋሸራ ምሩቅ ወደነበሩት መምህር ተስፋ ሥላሴ ዘንድ በመሄድ፣ ውስጠ ዘቅኔና ዕርባ ቅምር ተማሩ፡፡ የቅኔ ትምህርታቸውን ከተለያዩ ሊቃውንት ጉባኤ አጠናቅቀው ለማስተማር ወደ ዲማ ቢመለሱም “ሴት ሴትን እንጂ ወንድን አታስተምርም” የሚል ሥርዓት ስላለ ሃሳባቸው ሳይሳካ ቀረ፤ ሆኖም የእማሆይን የቅኔ ችሎታ የሚያውቁ የባሕርዳር ፈለገ ገነት ጊዮርጊስ ካህናትና የገዳሙ ኃላፊዎች ለመምህርነት እንደሚፈልጓቸው ተነገራቸውና በ1999 ዓ.ም ወደዚያው አመሩ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምረውም የንባብና የቅኔ መምህርት ሆነው በመቀጠራቸው በርካታ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡ በትምህርት ዘመናቸው ልክ እንደ ወንዶቹ ሁሉ እየለመኑ በቁራሽ ኖረዋል፤ ከውሻ ጋርም ታግለዋል፤ የተማሪ ቤት ችግርን ሁሉ ተጋፍጠው ነው ከዚህ ደረጃ የደረሱት፡፡ ሆኖም ነዋሪነታቸው አዲስ አበባ የሆነ “መዓዛ ድንግል” የሚባሉ በአካል የማያውቋቸው ደግ ሴት በየወሩ 25 ብር ይልኩላቸው፤ የእነማይ ወረዳ ማህበረ ቅዱሳን ቅርንጫፍም አቅሙ የፈቀደውን ድጋፍ ያደርግላቸው እንደነበር ውለታቸውን በከፍተኛ ስሜት ያስታውሱታል፡፡ ተማሪዎቻቸው ከጐጃም፣ ከሸዋ፣ ከወለጋ፣ ከትግራይ፣ ከጐንደርና ከወሎ የመጡ ሲሆን ከዋልድባ ገዳም የመጡ መነኮሳይትንም በእማሆይ ጉባዔ አይቻለሁ፡፡

መምህርት እመተማርያም በሙያቸው ምን ያህል እውቅና እንዳላቸው ከአንዳንድ ተማሪዎቻቸው አስተያየት ጠይቄ ነበር፡፡ “እማሆይ አፀደ ማርያም ይባላሉ፤ የመጡት ከግሸን ደብረ ከርቤ ነው፡፡ “ቅኔ ለመማር ጐንደር ውስጥ ከሚገኙት መሪጌታ ጥበቡ ጋ ስሄድ “ባህርዳር ያሉት የቅኔ መምህርት ይሻሏችኋል” አሉኝና መጣሁ፤ በእርግጥም ተገቢ ሰው ሆነው አገኘኋቸው፡፡” ብለውኛል፡፡ “ወንድ የተማረውን መማር አለብኝ ብዬ አክሱም ውስጥ ወደሚገኙት መምህርት ሕይወት ጋ ስሄድ ወንድ መምህር ዘንድ ወሰዱኝ፤ መምህሩ ግን ወንድ ነው እንጂ ሴት አላስተምርም ብለው አሰናበቱኝ፡፡ ከዚያ ዋልድባ ሄድሁ፤ እዚያም ትምህርት የለም። ስለዚህ ወደ እማሆይ አመተማርያም መጣሁ” የሚሉት ደግሞ እማሆይ እህተ ማርያም የተባሉ መነኩሲት ናቸው፡፡ ለ10 ዓመት ፍቅርተ ክርስቶስ ገዳም (ወሎ)፣ ለሰባት ዓመታት ዋልድባ ገዳም መኖራቸውን እና መሠረታቸው ወለጋ መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ “እማሆይ ወለተ ሚካኤል የተባሉ እናት ናቸው፡፡ “ዋልድባ ውስጥ የሴት አስተማሪዎች ስለሌሉ ወደዚህ መጣሁ፡፡ እዚህ ተረጋግቼ እየተማርሁ ነው፤ ዘመናዊ ትምህርት ነቀምት ውስጥ እስከ 9ኛ ተምሬያለሁ፤ ግን ግዕዝን መማር አለብኝ ብዬ ነው ከዋልድባ የመጣሁት”ብለውኛል፡፡ “አዲስ አበባ ውስጥ እማር ነበር፤ 10ኛ ክፍልን ተፈትኜ ውጤቴን ሳላይ ነው ወደ ገዳም የሄድሁት” የሚሉት እማሆይ ወለተመስቀልም፤ “ለሃይማኖት ዕውቀት ሁሉ ዋናው ቁልፍ ቅኔ ነው፤ በዚህ ምክንያት ነው ቅኔ ለመማር የመጣሁት” ሲሉ አጫውተውኛል።

በአጠቃላይ ከቤትና ከምግብ በቀር ሌላ ችግር እንዳላጋጠማቸው ሁሉም ተማሪዎች ነግረውኛል፡፡ ድሮ የቅኔ ሊቃውንት ወ/ሮ ሐይመት እና እመይቴ ገላነሽ ብቻ ነበሩ፡፡ ዛሬ ግን በጐጃም፤ መምህርት አመተማርያምና መምህርት ኅርይት፤ በትግራይ (አክሱም) መምህርት መብራትና መምህርት ሕይወት የሚባሉ ሊቃውንት መኖራቸው ሲረጋገጥ አዲስ አበባ ውስጥም ሁለት መምህራት እንዳሉ ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ አንድ ያስተዋልሁት ችግር አለ፤ ሴቶች ምንም ያህል በዕውቀታቸው የመጠቁ ቢሆኑም ቤተክርስቲያን ውስጥ ቅኔ ሊነጥቁ ይችሉ ይሆናል እንጂ አይዘርፉም፤ ወይም እጣነ ሞገር አይቀኙም፡፡ ግን ደግሞ ሴቶች እንዳይቀኙ ወይም ቤተክርስቲያን ውስጥ ቅኔ እንዳይዘርፉ የሚከለክል ሕግ የለም፡፡ ታዲያ ለምን ይሆን ሴቶች ዕድሉን መነፈጋቸው? እንኳንስ ንፅህና ያላቸው መነኮሳይያት ብዙ የሚወራባቸው ደባትር ይቀኙ የለም እንዴ? “ሴት ሴትን ታስተምር እንጂ ወንድን አታስተምር?” የሚለው አባባልም የሲኖዶስም ሆነ የፍትሐ ነገሥት ድጋፍ የለውም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስኮ “ወንድ፣ ሴት” ሳይል ሁሉንም እኩል ነው ያስተማረ፡፡ ሴቶች በአደባባይ ሲያስተምሩ ሲያዩም በርካታ ተከታዮችን (በተለይ ሴቶችን) ያፈራሉ እንጂ ጉዳቱ ምን ላይ እንደሆነ በፍፁም ግልጽ አይደለም፡፡ ዛሬኮ በየክብረ በዓሉ ሴት የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ከበሮ አዝለው አምላካቸውን እያመሰገኑ ናቸው፡፡ ታዲያ ለምን ሴት ሊቃውንቱ ቤተክርስቲያን ውስጥ አምላካቸውን በቅኔ አያመሰግኑም? ለምንስ የተማሩትን ሃይማኖታዊ ትምህርት (በተለይ ትርጓሜ መጻሕፍትን) ዓውደ ምሕረት ላይ አያስተምሩም? ቅድስት ቤተክርስቲያን ልታስብበት ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡

Read 7575 times