Monday, 03 February 2014 13:38

“የግንኙነት ጥበብ ሥነ - ልቦናዊ ገፅታ”ን በወፍ-በረር እንዳየሁት

Written by  ነቢይ መኰንን
Rate this item
(3 votes)

           የመጽሐፉ ርዕስ ….የግንኙነት ጥበብ ሥነ - ልቦናዊ ገፅ ደራሲ…ፀሐዬ አለማ የገጽ ብዛት…..169 የዚህ መጽሐፍ ፍሬ ጉዳይ አንድ ዶክተር ኤሪክ በርንስ የተባሉ የሥነ-ልቦና ተመራማሪ፣ የቀነበቡትን አዲስ ዓይነት ትንታኔ ለኢትዮጵያውያን አንባቢዎች ጭብጡን ለማስያዝ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ንድፈ-ሀሳቡን መሬት ለማስያዝ ማለት ነው፡፡ የደራሲውን ሥራ አንብቤ ወፍራም ነው፣ ቀጭን ነው፣ ከማለቴ በፊት እኚህ ዶክተር ኤሪክ በርንስ ደሞ ማን ይሆኑ?ብዬ ከራሴ ጋር ተጠያየቅሁ፡፡ ከዚያ መጽሐፍ መገላለጥ ጀመርኩ፡፡ የሚከተለውን ማንነታቸውን ተገነዘብኩ፡፡ እስቲ ባጭሩ ለናንተም ላካፍላችሁ፡፤ ተካፍሎ አብሮ መብላት በረከት አለውና፡፡ ኤሪክ ኤሪክሰን በርንስ ይህ ሰው ጁን 15 1902 ዓ.ም. ፍራንክፈርት፣ ጀርመን ተወለደ፡፡ ‹‹በብዙዎች የሚታወቀው ነገር እናትና አባቱ እሱ ከመወለዱ በፊት መፋፋታቸው ነው!! በሚሥጥር ተይዟል የሚባለው ግን ከጋብቻ ውጪ በተፈጠረ እርግዝና ምክንያት የእናቱ ልጅ መሆኑ ነው፡፡ ወላጅ አባቱን በጭራሽ አይቶት አያውቅም። የእናቱን የመጀመሪያ ባል አያውቀውም›› ይላል የኤሪክን የመቃብር ንባብ የሚጠቅሰው፣ የ1994ቱ የኒው ዮርክ ታይምስ፡፡ አይሁዳዊው ወጣት፤ እናቱ፣ ሐኪሙን ዶክተር ሆምበርገርን፤ ከማግባቷ በፊት በእራሷ ኤሪክን ስታሳድግ ቆይታለች፡፡

ኤሪክ፣ ለረዥም ዓመታት ሆምበርገር ዕውነተኛ አባቱ (a biological father) መሆኑ ተደብቆት ነበር፡፡ በመካያው ዕውነቱን ሲያውቅ ግን፣ የራሱ ማንነት ጠፋው፡፡ ይህ የጥንት ልምዱ፤ የማንንም ሰው የማንነት አፈጣጠርን የማወቅ ጉጉቱን ክፉኛ ቀሰቀሰበት። ኤሪክሰን የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ፣ የጥበብ ስሜቱ መጠቀ፡፡ መነጠቀ፡፡ ስለሆነም በአውሮጳ የተለያዩ ስፍራዎች ተዘዋወረ፡፡ አንድ ወዳጁ በመከረው መሠረት ‹‹ሳይኮ -አናሊሲስ›› (የሥነ - አዕምሮ ትንተና እንደማለት) አጠና፡፡ ከቪየና የሥነ - አዕምሮ ትንታኔ ተቋም ሠርቲፊኬት አገኘ፡፡ የመጤ - ፍሩዳዊ አስተሳሰብ ባለቤቶች (New-Freudian Tinker) ካርል ዩንግ አልፍሬድ አድለር ኤሪክ ኤሪክሰን ካረን ሆርኒ ኤሪክ ፍሮም ከእነዚህ ጠቢባን መካከል፣ ብዙዎቹ በፍሩድ፤ “ባልበሰለ አዕምሮና በጠዋት የልጅነት ጊዜ አስተሳሰብ” ላይ ይስማማሉ፡፡ ያም ሆኖ በአንዳንዶች ነጥቦች ላይ የማይስማሙ፣ ሀሳቡን የማይጋሩ፤ ወይ በቀጥታ የሚጋጭ አስተሳሰብ ያላቸው አሉ ፡፡ በዚህ ምክነ - እሳቤ እኒህ ግለሰቦች የራሳቸው ን ልዩ ንድፈ-ሀሳብ ስለውስጠ - ስብዕና መስበክ ጀመሩ። ቀጠሉበት፡፡

ኤሪክና ሩት የተጋቡት በኦክቶበር 1942 ነበር፡፡ ሴት ልጃቸው ኤለን ከመወለዷ ከአራት ወር በፊት በ1941 በኒውዮርክ የአዕምሮ ትንተና ተቋም ውስጥ በዚሁ ሙያ ሠልጥኖ፣ ከፖል ፌደርን ጋር የሥነ- አዕምሮ ዋና ተንታኝ ሆነ፡፡ ከሥነ አዕምሮ ትንታኔ (ሳይኮ አናሊሲስ) ጋር መፋታት፡፡ የትራንዛክሽናል ትንተና መጀመር የትራንዛክሽናል ትንተና ሥርወ-አመጣጥ\ዘፍጥረት ከ1949 ጀምሮ ኤሪክ በርን ከፃፋቸው ስድስት ሐተታዎች በመጀመሪያዎቹ አምስት ጽሁፎች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ያን ጠዋት ፣ ገና የፍሩድን ትንተና በወግና በማዕርግ ለመየዝ እያኮበኮበ ሳለ ፤ ፍሩድ ስለ ውስጠ - ህሊና \ ህሊና - ገበር /Ego/ የጻፈውን ጽንሰ-ሀሳብ ይሞግተውና ያጣጥለው ነበር። በ1941 በኒውዮርክ ሳይኮ አናሊሲስ ተቋም ጥናቱን ሲጀምር፣ ከፖል ፌደርን ጋር ተገናኘ፡፡ ቀጥሎም በሳንፍራንሲስኮው የሳይኮ-አናሊሲስ ተቋም ጥናቱን ሲያኪያሂድ ኤሪክ በእርግጥም የሳይኮ አናሊሲስ ባለሙያ መሆን እንዳለበት አመነ፡፡ ያም ሆኖ ያን ማዕረግ ሊያገኘው አልቻለም፡፡ አባል ለመሆን ያስገባው ማመልከቻ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ የ1956 ማመልከቻው ቀለጠ፡፡ እንዲወድቅ የተደረገበት ምክንያትም ገና ብቁ አይደለህም የሚል ነበር፡፡ ከ3 ፣ 4 ዓመት ሥልጠናና ትንተና በኋላ እንደገና እንዲያመለክት ተነገረው፡፡

ኤሪክ ተቀባይነት ማጣቱ ብግን፣ ድብን ፣ አደረገው፡፡ ይሄ ሁኔታ እልህ ውስጥ ከተተው፡፡ ለሳይኮ - አናሊሲስ አዲስ ሀሳብ አክላለሁ የሚለውን ስሜቱንም ይብስ አነሳሳው። “ ሳይደግም አይጣላም” ማለት ይሄ ነው። ያ የመገፋት ስሜት እንነዳለ ሆኖ ኤሪክ በርን አዲስ አይነት የሥነ አዕምሮ ትንተና ራሱ በራሱ ሊያወጣ ቆርጦ ተነሳ። 1956 ገና ሳይገባደድ ሁለት የጥናት ወረቀቶች አቀረበ፡፡ በሳንፍራንሲስኮ ና ባንግሌይ ፖተር ክሊኒክ ባቀረበው ጥናት ላይ የተመሠረቱ ወረቀቶች ነበሩ፡፡ እነዚህም “ኢንቲዩሽን 5” ፣ “ዘ ኢጎ ኢሜጅ እና ኢጎ ስቴትስ ኢን ሳይኮ ቴራፒ›› የሚሉ ናቸው፡፡ በርን የፒ.ፌደርንን የኢካንና የሲልበረርን ጥናቶች እያጣቀሰ የኢጎ ስቴትስ ፅንሰ-ሀሳብና ‹‹የጎልማሳነት››፣ እና ‹‹የህጻንነት›› ህሊናን እሳቤ ከየት እንዳመጣው አብራራ፡፡ በሚቀጥለው ሀተታው፣ ‹‹ሰለሥተ- ግንዛቤ ›› ያላውን ዛሬ የምንጠቀምበትን ሦስትዮሽ አመለካከት፤ ማለትም፣ ወላጅ ፣ ጎልማሣና ሕጻን፤ የሚለውን በመግለጽና የሦስት ክቦሽ መርሀ-ግብር በመንደፍ ጽንሰ-ሐሳቡን አስተዋወቀ፡፡ ጉድፍ ወይም እክል እንዴት እንደሚታይ ገለጠ። ንደፈ-ሐሳቡንም ‹‹ስትራክቸራል አናሊሲስ›› ሲል ሰየመው። ‹‹ኤ ኒው ሳይኮቴራፔቲክ አፕሮች›› ብሎም አውደ - ስም አወጣለት፡፡ ሦስተኛው ሀተታው፣ ‹‹ትራንዛክሽናል አናሊሲስ፣ አዲስና ስኬታማ የቡድን ህክምና (መድህን)›› በሚል፤ ከጥቂት ወራት በኋላ ጻፈ፡፡ በሎስ አንጄለሱ የአሜሪካ ግሩፕ ሳይኮቴራፒ አሶሴሽን የ1957 ምዕራብ ቀጠና ስብሰባ ላይ እንዲያቀርበው ተጋብዞ ፀሐይ ያየ ሥራ ሆነለት፡፡

‹‹በአሜሪካን ጆርናል ኦፍ ሳይኮቴራፒ›› በ1958 ታተመና ‹‹ትራንዛክሽናል አናሊሲስ›› የተባለው የኤሪክ በርንን አዲሱን መፍትሔ-ተኮር፤ የትንተና መላ፣ ዘላቂ የሥነ-አዕምሮ-መድሕን ጥበብ ሆነ። ከፒ. ኤ. ሲ(ወ-ጎ-ህ) ወላጅ፣ ጎልማሳ፣ ህጻን) ዘይቤው ጽንሰ-ሀሳቡ መዋቅራዊ ትንተና እና ኢጎ(የህሊና - ገበር) (የህሊና ገበና ማለትም ያስኬዳል) ሁኔታ፤ እንደገና በማፀህየቱ፤ የ1957ቱ ጥናት አዳዲስ ገፅታዎች ፤ የሥነጽሁፍ ገድሎችና ጨዋታዎች ቁጥር እንዲጨምር አደረገ፡፡ አበለፀገ። ‹‹ጌምስ ፒፕል ፕሌይ›› ዓለም አቀፍ የሽያጭ ምርጥ መጽሐፍ ነው፡፡ ደራሲው ኤሪክ በርንስ ነው፡፡ ድንቅ፣ አስገራሚና የሰው ልጆች በየጊዜው እየደጋገሙ የሚጫወቷቸውን ቴያትራዊና ስነ አዕምሮአዊ ሁኔታዎች የሚያሳይና የሚተነትን ነው። መልካሙ ዶክተር፤ መረጃ ጠላፊዎች የዛሬ 10000 ዓመትም ሊደርሱበት የማይችል ታሪክ ጽፏል›› ይላል፤ ኩርት ቮኔጉት ጁኒየር፣ በ1965ዓ.ም እትም፤ የላይፍ መጽሔት፡፡ ዘ ቺካጎ ትሪቡንም ‹‹በየእልፍኙ፣ በየአደባባዩ፣ በየመኝታቤቱ፣ በየምክር መስጫ ክፍሉ የሚከሰቱ የእሙናዊው ዓለም ሰቆቃዎች ናቸው›› ይለዋል፡፡ ኤሪክ ብዙ የስነ አዕምሮ መጻሕፍትን ጽፏል፡፡ በዋና የጽንሰ-ሀሳቡ ቁልፍ ግን፤ አቶ ፀሐዬ አለማ ‹‹የግንኙነት ጥበብ ሥነ-ልቦናዊ ገጽታ›› በሚል ርዕስ የተረጎመው ነው፡፡ የመጽሀፉን መሠረታዊ ይዘት በወፍ - በረር ስናየው የሚከተለውን ይመስላል፡፡ (ይቀጥላል)

Read 4420 times