Monday, 27 January 2014 09:23

አደጋ የተጋረጠበት የአንጥረኝነት ሙያ

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(2 votes)

           ትግራይ ውስጥ በአክሱም አውራጃ ናአዲር በሚባል ወረዳ በ1950 ዓ.ም ነው የተወለዱት። የገበሬ ቤተሰብ ልጅ ቢሆኑም አባታቸው ንግድ ሥራም ይሞክሩ ነበር፡፡ የ10 ዓመት ልጅ እያሉ ከትግራይ ወደ አዲስ ዓለም መጡ፡፡ በመቀጠል ወደ ጅማ አቀኑ፡፡ ሦስተኛው ማረፊያቸው አዲስ አበባ ሆነ፡፡ በልጅነታቸው ከሥራ ጋር መተዋወቅ ሲጀምሩ ሱቅ እያፀዱ በወር 3 ብር ይከፈላቸው ነበር፡፡ በሥራው እያደጉ ሲመጡ በሳምንት 3 ብር ይከፈላቸው ጀመር። እየቆዩ ሲሄዱ በወርቅና ብር ሥራ ላይ የተሰማሩ ቤተሰቦቻቸውን በመጠጋት፣ ከ6 ዓመት ጥረት በኋላ የራሳቸውን ጠረጴዛ ይዘው መሥራት ጀመሩ፡፡ “በአገራችን ሁሉም ሰው ወርቅ ነጋዴ ነው” የሚሉት አቶ ገብረሥላሴ ኪዳኔ፤ የወርቅና ብር ሥራ ጠባቂ ስላጣ ከሚጠፉ ሙያዎች አንዱ ሆኗልም ይላሉ፡፡ ወጣትነትዎን ባሳለፉባት አዲስ አበባ ምን ልዩ ትዝታ አለዎት? መኖሪያዬ ጣሊያን ሠፈር የነበረ ቢሆንም በጽዳት ሥራ ጀምሬ ወደ ወርቅና ብር ሥራ ያደግሁት መርካቶ ውስጥ ነበር፡፡

በ1970 ዓ.ም ለወርቅ ፈርጥ እንድገዛ ተልኬ በወጣሁበት ተይዤ፤ በኢህአፓነት ተወንጅዬ ለ4 ወር ከታሰርኩ በኋላ የሚመሰክርብኝ ስላልተገኘ ተለቅቄያለሁ፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ ሠራተኞች እንዲደራጁ ሲፈቀድ፣ አሰሪያችን መደራጀታችንን በመጥላቱ፣ በሐሰት ክስ በፍርድ ቤት አስመስክሮብኝ፣ የ6 ወር እስር ቢወሰንብኝም ከ4 ወር በኋላ ተፈትቻለሁ፡፡ በዚያ ዘመን የፍርድ ቤት እስረኛ ዕድለኛ ነው ተብሎ ይታይ ነበር፡፡ ምክንያቱም ያለ ፍርድ የሚታሰሩና የሚፈቱበትን ጊዜ የማያውቁ ብዙ እስረኞች በተለያዩ ቦታዎች ነበሩ፡፡ በዘመኑ በወርቅና ብር ሥራ ላይ የተሰማሩ ስንት ማህበራት ነበሩ? የአሰሪዎች ማህበር አንዱ ነው፤ ሁለተኛው የሠራተኞች ማህበር ሲሆን ሌላኛው የሕብረት ሥራ ማህበር ነበር፡፡ ሦስተኛው ማህበር የወርቅና ብር ሥራ ሙያ ያላቸው በጋራ በመሰባሰብ የመሰረቱትና አሁን ፒያሳ ጣና ወርቅ ቤት በሆነው ሱቅ ውስጥ ተሰባስበን፤ የየራሳችንን ጠረጴዛ በመያዝ፣ በሙያው የምንተዳደር ሠራተኞች ነበርን፡፡ የዚያ ማህበር አባል የሆንኩት በሐሰት ተፈርዶብኝ፣ የእስር ጊዜዬን አጠናቅቄ ከወጣሁ በኋላ ነበር፡፡ በማህበሩ ውስጥ እስከ 1978 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ ኃላፊነቶችም አገልግያለሁ፡፡

ከዚያ በኋላ የግለሰቦችን ቤት እየተከራየሁ፣ በራሴ ሱቅ በመሥራት እስካሁን በሙያው ዘልቄያለሁ፡፡ የማህበራቱ ዕጣ ፈንታ ምን ሆነ? የሠራተኞች ማህበር ብዙ ክሶች ነበሩት፤ የሕብረት ሥራ ማህበሩም ከባንክ ዕዳ ጋር በተያያዘ ፈርሷል፡፡ የአሰሪዎች ማህበር አሁንም ያለ ይመስለኛል፡፡ በኋላ የተመሠረተው የወርቅና ብር ሠሪዎች ማህበርም አለ፡፡ በአዲስ አበባ ምን ያህል የወርቅና ብር መሸጫ መደብሮች አሉ? “ኢትዮ ዕደ ጥበብ የማዕድናት ንግድ ሥራ አክስዮን ማህበር”ን በ1998 ዓ.ም ስንመሰርት ባገኘነው መረጃ፤ በከተማው ውስጥ 300 የሚደርሱ የወርቅና ብር መስሪያና መሸጫ መደብሮች ሲኖሩ፣ በአንጥረኝነት ሙያ ላይ የተሰማሩት ሰዎች በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ የእኔ ሱቅ በሚገኝበት ገዳም ሠፈር ብቻ 50 እና 60 የሚሆኑ ባለሙያዎች በየቤታቸው የወርቅና ብር ሥራ አገልግሎት ይሰጣሉ። እንዲህ በየቤቱ የሚሰሩት በአገር አቀፍ ደረጃ ጥናት ቢደረግ፣ በ100ሺዎች የሚቆጠሩ ይሆናሉ የሚል ግምት አለኝ፡፡ ከዚህ ውስጥ ዘጠና ከመቶ የሚሆኑት የትግራይ ተወላጆች ናቸው፡፡ ወርቅና ብር አንጣሪዎች የትግራይ ሰዎች ባይሆኑ እንኳን ሙያውን ከትግራይ ሰዎች ተማርነው ማለታቸው አይቀርም፡፡

የትግራይ ባለሙያዎች የዕውቀት መነሻ ምንድነው? በአፈ ታሪክ እየተነገረ እንደመጣው ከሆነ፣ ከንጉስ ሰለሞንና ንግስት ሳባ የሚወለደው ቀዳማዊ ምኒልክ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ፣ ሁሉም እስራኤላዊ የበኩር ልጁንና ከየሙያው ዘርፍ አንዳንድ ሰው እንዲሰጠው ሲወሰን፣ አብረው ከመጡት መሐል አንጥረኞችም ስለነበሩበት፣ ያ ታሪክ መነሻ ሆኖ ነው ትግራይ የወርቅና የብር ሥራ ባለሙያዎች መፍለቂያ የሆነችው፡፡ ወርቅ እንዴትና ከየት ተገዝቶ ነው በተለያየ መልኩ ተሰርቶ በየወርቅ መደብሩ የሚሸጠው? እስከ 2001 ዓ.ም ድረስ በአገራችን የከበሩ ማዕድናት ግብይት እንዴት መከናወን እንዳለበት የሚመራ ሕግ ስላልነበረ፣ የወርቅ ዋነኛው ምንጭ ሕብረተሰቡ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በእኛ አገር ነጋዴው፣ የቤት እመቤቶች፣ ሹፌሮች፣ ባለሆቴሎች፣ የቡና ቤት ሴቶች…ሁሉም ሕጋዊ ፈቃድ የሌለው የወርቅ ግብይት እርስ በእርሱ እያከናወነ ለዘመናት ዘልቋል። ብሔራዊ ባንክ ወርቅ መግዛትና መሸጥ የጀመረው በቅርቡ ነው፡፡ የዓለም የወርቅ ዋጋ በመገናኛ ብዙኃን መነገር የጀመረው አሁን ነው፡፡ የ”ኢትዮ ዕደ ጥበብ ማዕድናት ንግድ ሥራ አክስዮን ማህበር” መመሥረት መንግሥት ሕግ እንዲያወጣና በዘርፉ ያለውም ክፍተት እንዲደፈን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ማህበሩ በዚህ ዘርፍ ያደረገው አስተዋጽኦ ምን ነበር? ማህበሩን መሥርተን በ1999 ዓ.ም ተግባራዊ እንቅስቃሴ ስንጀምር ከብሔራዊ ባንክ፣ ከጉምሩክ ባለስልጣን፣ ከንግድና ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ተቀራርበን መነጋገር ጀመርን፡፡ “ወርቅ በሕጋዊ መንገድ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ለምን አይገባም?” የሚለውን ጥያቄ ያቀረብነው በዚያ አጋጣሚ ነው። ብሔራዊ ባንክም ወርቅ እንዲሸጥልን ጥያቄ አቀረብን፡፡ ከዚህም ባሻገር ከፊታችን የሚመጣ የሚሌኒየም በዓል ስለነበር፣ በሕጋዊ መንገድ የምንገዛውን ወርቅ ወደ ዱባይና ጣሊያን ወስደን የተለያዩ ጌጣ ጌጦችን አሰርተን፣ ወደ አገር ውስጥ በማስመጣት ለሚሌኒየም በዓሉ ለሽያጭ እናቅርብ ብለንም ጠየቅን፡፡ “ጥያቄያችሁን በምን ሕግ እናስተናግደው?” የሚለው ምላሽ፤ ችግሩን ለመቅረፍ ተጨማሪ ጥረት ማድረግ እንዳለብን አመለከተን፡፡ ለሚመለከታቸው የባለስልጣንና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ደብዳቤዎች መፃፋችንን ገፋንበት፡፡ በግንባር እየተገኘንም ለማስረዳትና ለማሳመን ጥረት አደረገን፡፡ እንዲህም ሆኖ አንዱ አካል ከገደብ ጋር የፈቀደልንን ሌላው አካል ሙሉ ለሙሉ እንደከለከለን ስናስተውል፣ ዋናው ችግር የሕግ አለመኖር ስለሆነ፤ በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩና በአንጥረኝነት ሙያ የተሰማሩትን ስብሰባ ጠርተን፣ ከመንግሥት ጋር የምንወያይበትን መድረክ አመቻቸን፡፡ በውጤቱም “የከበሩ ማዕድናት ግብይት አዋጅ” በ2001 ዓ.ም ለመውጣት ቻለ፡፡ ይህ ሕግ ባለመኖሩ ምክንያት ለሚሌኒየም በዓል ያሰብነውን ታላቅ ስራ ተግባራዊ ሳናደርግ ቀረን፡፡

ለሥራው የማህበራችን አባላት 3 ማሊዮን ብር አዋጥተው ነበር፡፡ ማህበሩ የተቋቋመበት ዓላማዎች ምን ነበሩ? የከበሩ ማዕድናት የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ማስቆም፣ ሙያውን ማስፋፋት፣ ሕጋዊ ከለላና ጥበቃ እንዲኖረው ማድረግ፣ ማምረቻ ፋብሪካ መክፈት፣ ለሥራው የሚያገለግሉ ማሽኖችን ማስመጣት፣ ሙያው ትውልዶች እንዲቀባበሉት ትምህርት ቤትና ማሰልጠኛ መክፈት…በሚሉ ዓላማዎች ነው የተቋቋመው፡፡ እስካሁን ከዓላማዎቹ የተወሰኑትን አሳክቷል፡፡ 777 ሜትር ካሬ መሬትና ቤት ፒያሳ ላይ ገዝቷል፡፡ ለሥራው የሚሆኑ ማሽኖች ባለቤትም ሆኗል፡፡ በዱባይ የወርቅ ፋብሪካ የነበራቸው አንድ ኢትዮጵያዊና ሕንዳዊያን በዘርፉ ለመስራት ማሽኖቻቸውን ጭምር ነቅለው ይዘው ቢመጡም እኛን አላሰራ ያለን የሕግ አለመኖር እነሱንም ለፈተና ዳረጋቸው፡፡ በዚህ ምክንያት ማሽኑን ሸጡልን፡፡ ዝርዝር ታሪኩ ብዙና ሰፊ ቢሆንም በሂደት የእኛ ማህበር አባል ሆኑ፡፡ በዚህም ምክንያት የማህበራችን መጠርያ ሥም “አዲስ የወርቅና ብር ጌጣጌጥ ፋብሪካ ኃ.የተ.የግ.ማህበር” ተባለ፡፡ በኋላ ሕንዳዊያኑ አንዳንድ ችግር ፈጥረው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ስናመራው፣ የማሽናቸውን ዋጋ ጠይቀው፣ ተከፍሏቸው ወደ አገራቸው ሄዱ፡፡ እስከዚህ ጊዜ ድረስ እኔ የማህበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ነበርኩ፡፡ ሙያውን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የማቋቋም እቅዳችሁ ምን ደረሰ? የሕንዶቹን ከመግዛታችን በፊት የወርቅና ብር መስሪያ ማሽኖችን ከውጭ ለማስመጣት ጥናት አሰርተን ነበር፡፡ የምናስመጣውን ማሽን ለማስተከል ያቀድነውም በትግራይ ክልል ነበር።

ይህንን ያሰብነው በሁለት ምክንያት ነው፡፡ አንደኛው ምክንያት የሙያው መነሻ ስፍራ በመሆኑ ነው። ሁለተኛው ምክንያት ፋብሪካውን እዚያ ከፍተን ትምህርትና ስልጠና ለመስጠት መንቀሳቀስ ብንጀምር፣ ለማሰልጠንም ለመሰልጠንም ፍላጐት ያላቸው ብዙ ሰዎችን እናገኛለን በሚል ነበር፡፡ ይህንን ተሞክሮ ያገኘነው ደግሞ ጣሊያንን በጐበኘንበት ጊዜ ነው፡፡ በጣሊያንም ለአንጥረኝነት ሙያ መነሻ የሆነች ከተማ አለች፡፡ በዚህ ምክንያት ከተማዋን ላይ ሙያውን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት አላቸው፡፡ የጣሊያኗን ከተማና ትግራይን እህትማማች ከተሞች የማድረግ እቅድ ሁሉ ነበረን፡፡ ሃሳባችንን ተግባራዊ ማድረግ ችለን ቢሆን ኖሮ በጥፋት ላይ ያለ አንድ ሙያን እንታደግ ነበር፡፡ ሙያው እየጠፋ ስለመሆኑ ማስረጃችሁ ምንድን ነው? የአክሱም፣ የጐንደር…የሚል መለያ ያላቸው መስቀሎች፣ የአንገትና የጆሮ ጌጦች ነበሩ፡፡ እነዚህ ሥራዎች በአገር ውስጥ ጥበቃ የሚያደርግላቸው ባለመኖሩ፣ ዲዛይናቸው ወደ ውጭ እየሄደ በአርቴፊሻል ጌጣ ጌጥ ጭምር ተሰርተው እየመጡ ገበያውን አጥለቅልቀውታል፡፡ ይህ ደግሞ ሙያው እየጠፋ መሆኑን ያመለክታል፡፡ የሹራብ ሥራም እንዲህ ቀስ በቀስ ነው እየጠፋ ያለው፡፡ ዛሬ በጣት የሚቆጠሩ ሹራብ ሰሪዎች፤ ለትምህርት ቤቶች የሚሆኑ ሹራቦችን እየሰሩ ሲሆን ገበያውን የተቆጣጠረው ግን የቻይና ምርት ሆኗል። ለሹራብ አምራቾች ማህበር በተሰጠው የኮልፌ የንግድ ቦታ ሹራብ አምራቾችን ማግኘት እያስቸገረ ነው፡፡ የወርቅና ብር ሥራም ሕጋዊ ከለላና ጥበቃ ስላልተደረገለት፣ በመጥፋት ሂደት ላይ ነው ያለው፡፡ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ውስጥ እንኳን አልተካተተም። አንጥረኝነት ሙያ በመጥፋት አደጋ ላይ ስለመሆኑ ከዚህ በላይ ምን ማስረጃ ያስፈልጋል?

Read 4127 times